ግለሰቡ ይህን ግዙፍ ተቋም ከመክሰስ ወደኋላ አላሉም። በችሎት ፊት፤ በፍርድ ዓደባባይ አቅርበውት እውነተኛ ፍርድ በመሻት እስከመጨረሻው በህግ ለመፋለም ወስነው ተነስተዋል። ሥመ ገናናው ድርጅትም ስሜ አይጎድፍም፤ የግለሰቡንም ድርጊት በዋዛ አላልፍም ሲል የህግ ክፍሉን ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ በመያዝና ይጠቅሙኛል ያላቸውን ሰነዶች በመሰነድ በችሎት ፊት ቀርቦ ለማሸነፍ ቆርጦ ተነስቷል።
71507 ለዚህ የክስ መዝገብ ለብቻው የሰነድ መለያ ቁጥር በሚል ተሰጥቶታል። ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ እልክ አስጨራሽ ክርክሮች ተደርገውበታል፤ ዳሩ ግን ይህ ነው የሚባል መቋጫ አላገኘም። ክርክሩ በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መግባባት ባለመደረሱ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የተላለፈ ጉዳይ ሆነ። የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ከሥር ፍርድ ቤት የተላለፈለትን ጉዳይ በአንክሮ ተመለከተው፤ ግራ ቀኙን አመዛዘነ። በመጨረሻም የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ላይ በመመርኮዝ ብሎም ተገቢነት አላቸው ያላቸውን ህግና አንቀፆችን በማጣቀስ በተጨማሪም የተጠሪ እና አመልካችን መረጃዎችን በማመሳከር የራሱን ውሳኔ አሳለፈ።
ዳሩ ግን ጉዳዩ በዚህ አላበቃም። ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ። የዚህን ፋይል የመጨረሻ የሰበር ውሳኔ ለመስማት ደግሞ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም የመጨረሻው ቀን ሆኖ ተቆርጦለታል። አምስት ዳኞችም ከመንበሩ ላይ ተቀምጠዋል። ታዳሚዎችም ከችሎቱ ውስጥ ተገኝተዋል። በዕለቱ የተሰየሙ ዳኞችም ግራ ቀኙን የመረመሩትን ለመበየን በሰዓቱ የተገኙ ሲሆን በአመልካች እና በተጠሪ መካካል ያለውም ውዝግብ መቋጫውን ያገኛል-መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም።
አመልካች ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን የተቋሙ ነገረ ፈጅ አቶ በአካል ቀርበዋል። ተጠሪም አቶ ሰይፈ ተፊሪ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ በሌሉበት የሚታይ ሆኖ መዝገቡ ተመርምሮ ለመጨረሻ ፍርድ ከመንበሩ ላይ ተገኝቷል፤ ውሳኔም ተሰጥቶበታል።
ጉዳዩ ምን ነበር?
በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት በሚገዛው ግንኙነት ውስጥ ሰራተኛው ስራውን ከመልቀቁ በፊት የወሰደውን ብድር ሳይመልስ ስራውን በገዛ ፈቃድ ሲለቅ አሰሪው ለሰራተኛው ሊከፈለው ከሚገባው የፔሮቪደንት ፈንድ ገንዘብ ቀንሶ ለማስቀረት የሚችልበትን የህግ አግባብ የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውን ገልፀው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።
ተጠሪ ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ከዘረዘራቸው የክፍያ ዓይነቶች አንዱ የፔሮቪደንት ፈንድ ሲሆን አመልካች ለዚሁ ለተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ በሰጠው መከላከያ መልስ ተጠሪ የፔሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ መሆኑን ሳይክዱ ለተጠሪ ብር 9,000 /ዘጠኝ ሺህ/ መስጠቱን፣ ቀሪውን በተመለከተ ግን አመልካች ለተጠሪ ብድር አበድሮት እንደነበረና ብድሩን ሙሉ በሙሉ ባለመክፈሉ በመካከላቸው ባለው ስምምነት መሰረት ያስቀረው መሆኑን ጠቅሶ ሊከፈለው አይገባም በማለት ተከራክሯል።
የሥር ፍርድ ቤት ምን አለ?
የስር ፍርድ ቤትም በዚህ ረገድ የቀረበውን የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ተጠሪ ብር 9,000 መውሰዳቸውንና ከአመልካች በብድር የወሰዱት ገንዘብ መኖሩን ያለመካዳቸው ተረጋግጧል በማለት አመልካች ከተጠሪ ለዕዳ መክፈያነት ያስቀረውን የፔሮቪደንት ፈንድ ቀሪ ለመክፈል ሊገደድ አይገባም በማለት ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ ተጠሪ ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የፔሮቪደንት ፈንድ ከደመወዝ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካላቸው ክፍያዎች አንዱ መሆኑን ገልፆና ያለተጠሪ ስምምነት ደግሞ አሰሪ የሆነው አመልካች ለዕዳ መክፈያነት የፔሮቪደንት ፈንድ ቆርጦ ለማስቀረት የማይችል ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 59/1/ ስር የተመለከተ መሆኑን በዋቢነት ጠቅሶ አመልካች ቀሪ የፔሮቪደንት ፈንድ ክፍያ ብር 11,000.00 /አስራ አንድ ሺህ ብር/ ለተጠሪ ይክፈላቸው በማለት የስር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የሰጠውን የውሳኔ ክፍል ሽሮታል ሲል ይደመድማል። ታዲያ ይህ ጉዳይ በዚህ ብቻ ሊያበቃ አልቻለም፤ ወደ ሌላ የክስና የውሳኔ ምዕራፍ ተሸጋገረ።
ሰበር የደረሰው መዝገብ
የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ በድርጅቱ ህብረት ስምምነትና በብድር ፖሊሲ መሰረት የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ ስራውን በገዛ ፈቃዳቸው ከመልቀቃቸውም በላይ ብድሩ መኖሩንና ሥምምነት መኖሩንም ሳይክዱ አመልካች ከፔሮቪደንት ፈንዴ ቆርጦ እዳውን ማስቀረት አይችሉም ተብሎ መወሰኑ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 59 ድንጋጌን ይዘት፣ የግራ ቀኙን ክርክርና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በድርጅቱ የብድር ፖሊሲ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በአግባቡ ባላገናዘበ መልኩ ነው በማለት ውሳኔው እንዲሻር ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። በዚህ ሂደት ግን ብዙ ክርክሮች ተደረጉ። ለውሳኔም ሰጪውም አካል ከቀድሞ መረጃዎች ጋር በማጣመር የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በርካታ ሰነዶችም አብረው ተያይዘዋል።
አቤቱታው ተመርምሮም ተጠሪ ከስራ ስንብቱ በፊት የነበረበትን እዳ ከፔሮቪደንት ፈንድ ላይ ሊቆረጥ/ሊቀነስ/ አይገባውም በማለት በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ተደረገ።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የአመልካችን የሰበር አቤቱታ ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። በዚህ ምርመራም ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችም ግልጽ እየሆኑ መጡ።
በዚህ ሁሉ የክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ነገር ቢኖር፤ ተጠሪ ከአመልካች ጋር የመሰረቱትን የሥራ ውል ግንኙነት ያቋረጡት በገዛ ፈቃዳቸው መሆኑን፣ የሥራ ውል ከመቋረጡ በፊት ደግሞ በሠራተኝነታቸው ከአሰሪው በተሰጣቸው መብት መሰረት ብድር ወስደው ብድሩን እንደተጠቀሙና ዕዳውን ሙሉ በሙሉ ሳይከፍሉ የስራ ስንብት ጥያቄን ያቀረቡ መሆኑን ነው። በተጨማሪም ብድሩ ያለባቸው መሆኑንም ደግሞ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተደረገው ክርክር ያመኑ መሆኑ ተረጋጋጠ። እንዲሁም የብድሩ መሰረትም በአሰሪው ድርጅት ውስጥ ያለው የሕብረት ሥምምነት እና የብድር ፖሊሲ መሆኑ አከራካሪ ያለመሆኑን ነው። ከፍ ሲል እንደተገለፀው የአሁኑ ተጠሪ ዕዳ የለብኝም በሚል ያቀረበው ክርክር የለም ተብሎ በስር ፍርድ ቤት የታለፈ ስለሆነ አመልካች ዕዳው የተጠሪ መሆን ያለመሆኑን ሌላ ክስ እንዲመሰረት የሚጠበቅበት ህጋዊ ምክንያት የለም።
የአዋጁ አንቀጽ 59/1/ በህብረት ስምምነት በተወሰነው መሠረት ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ መቀነስ እንደሚቻል የሚያስረዱ ሲሆን የፔሮቪደንት ፈንድ ከደመወዝ ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያለው የክፍያ ዓይነት ነው ቢባል እንኳ ተጠሪ ዕዳ ያለባቸው ስለመሆኑ በክርክሩ ሂደት ባልተካሄደት ሁኔታ ሌላ ግልፅ ሥምምነት የሚያስፈልግበት ህጋዊ ምክንያት የለም። በመሆኑም ተጠሪ ከአመልካች ድርጅት የወሰዱትን የብድር ገንዘብ ሳይመልሱ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን በለቀቁበትና ዕዳው መኖሩንም በሥራ ክርክር ችሎት ባመኑበት ሁኔታ እዳውን ከፔሮቪደንት ፈንድ ቆርጦ ለማስቀረት ሌላ ግልጽ የሆነ ስምምነት ያስፈልግ ነበር ተብሎ በፌደራል ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮችን ከድንጋጌው መንፈስ እና ይዘት ጋር ያላገናዘበ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ሆኖ አግኝተናል ሲል ህጋዊ ትንታኔዎችን ይሰጣል።
በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ የአሁኑ ተጠሪ የወሰደውን የብድር ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሳይመልሱ ስራውን በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁበትና እዳውም የሚመለከታቸው መሆኑን በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍድር ቤት በተደረገው ክርክር ባላመኑት ሁኔታ ከፔሮቪደንት ፈንድ እዳውን ቀንሶ ለማስቀረት ግልፅ ስምምነት የለም ተብሎ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መወሰኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 59/1/ ስር የተመለከተውን የድንጋጌውን መንፈስ ከአመልካች ድርጅት የህብረት ስምምነት እና የብድር ፖሊሲ ጋር ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ውሣኔው መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል ሲል ማብራሪያ እና አባሪ መረጃዎችን በማጣቀስ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል- ሰብር ሰሚ ችሎት።
ውሳኔ
1. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ መለያ ቁጥር 107857 በ06/11/2003 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፌደራል ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
2. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ መለያ ቁጥር 57350 በ19/08/2003 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ በፌደራል ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 348/1/ መሰረት ፀንቷል።
3. አመልካች ከተጠሪው ፔሮቪደንት ፈንድ በዕዳው ምክንያት ቀንሶ የወሰደውን ገንዘብ ሊመለስ አይገባም ሲል በየነ። በዚህ ፍርድ ቤት የተካሄደው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪያቸውን በየራሳቸው ይቻሉ በማለትም መዝገቡ ተዘግቷል፣ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ሲል የመጨረሻውን የሰበር ውሳኔ አሳለፈ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015