ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ።
ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
ድንገቴው እግር
በስራ አጋጣሚ ወደ አንድ ተቋም አመራሁ። ይህ ተቋም የአእምሮ እድገት ውስንነት(ኦቲዝም) ያለባቸው ወገኖች መገኛ ነው። በዕለቱ እግሬ ወደ ብሄራዊ ማህበሩ እየረገጠ ነበር። ገና ወደ ውስጥ ከመዝለቄ ሰዎችን ለማየት የናፈቁ አይኖች ከአይኖቼ ሲጋጩ አስተዋልኩ።
የልጆቹ ዓይኖች ሰው እንደራባቸው ያሳብቃሉ ። ከመግቢያ በሩ ጥቂት አለፍ እንዳልኩ አንድ በፍጥነት ሲሮጥ የቆየ ልጅ በድንገት ደርሶ ተጋጨኝ። ለጊዜው ብደነግጥም አንዳች ቃል አልተነፈስኩም። ቀልጠፍ ብዬ ከመሬት የወደቀውን የእጅ ስልኬን ላነሳ ጎንበስ ከማለቴ በእጅጉ ከደነገጠው ልጅ ጋር ዳግም ተፋጠጥኩኝ። በፊቱ ጭንቀትና መደናገር ይነበባል። በጣም ደንግጦ ነበርና ደጋግሞ ይቅርታ ‹‹ይቅርታ›› ይለኝ ያዘ ።
ልጁ በእዚህ ብቻ የበቃው አይመስልም። በአይኖቹ ይቅርታውን መቀበሌን ለማረጋገጥ ይመስላል በትኩረት ማተረ ። አላስደነገጥኩትም ‹‹ችግር የለውም ያጋጥማል›› ብዬው ወደ ፊት ተራመድኩ። ካሰብኩት ክፍል ስደርስ በርካታ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ምንጣፍ ፤ ሸማ እና ሌሎችንም የእጅ ስራዎች ሲከውኑ አስተዋልኩ። በሁኔታቸው መገርም መደነቄ አልቀረም።
ልጆቹ ስራቸውን የሚሰሩት በከፍተኛ ትኩረት ነው። ሁሉም በሚባል መልኩ በአይኖቻቸው ሰላም ብለውኝ ወደ ስራቸው አቀረቀሩ። ቆሜ የሚሰሩትን ሁሉ ማየት ጀመርኩ። ይህኔ ቅድም በድንገት የተጋጨሁት ልጅ ወደ እኔ ተመልሶ መጥቶ ነበር። ወዲያው ማንን እንደፈለኩ በተለየ አክብሮትና ትህትና ጠየቀኝ።
የፈለኩትን ሰው ማንነት ተናግሬ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ። አመጣጤ የማህበሩን ስራ አስኪያጅ ለማግኘት ነበር። ወይዘሮ የሸዋጌጥ ክብረት ትባላለች። መምጣቴን እንዳየች በአክብሮት ተቀብላ አስተናገደችኝ። ውይይታችንን ከመጀመራችን በፊት እርስ በእርስ በመተዋወቅ ጥቂት አወራን። ቀለል አለኝ።
ወይዘሮ ሸዋጌጥ ክብረት በፍቅር የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ስራ አስኪያጅ በመሆን ታገለግላለች። ማህበሩን በ1987 ዓም 80 የሚሆኑ የአእምሮ እድገት ውስነት ባለባቸው ልጆች ወላጆች የተቋቋመ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከ 15 ሺ በላይ አባላት አሉት ።
የማህበሩ ዋነኛ አላማ ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በተጓዳኝም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል። ልጆቹ በልጅነታቸው የህመም ደረጃቸው ከተለየ በአካባቢው ወደሚገኙ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ ይደረጋል።
በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው ማንኛውም አይነት ጥቃት እንዳያገኛቸው ይሰጋሉ ። በተያያዘም ከሰዎች መገለል እንዳይደርስባቸው ልጆቻቸውን ይደብቃሉ። በልጆቻቸው የሚያፍሩና የሚሸማቀቁም አይታጡም። ይህ አይነቱ አጋጣሚም ልጆቻቸውን ለ20 እና 30 አመታትን በቤት ውስጥ አስረውና ደብቀው እንዲያቆዩዋቸው ምክንያት ይፈጥራል ።
የወላጆች ነገር
ወይዘሮ የሸዋ ጌጥ ወላጆች ስለልጆቻቸው ያላቸው ግንዛቤ የተለያየ ስለመሆኑ ይናገራሉ። አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው የደረሰው የጤና ችግር በርግማን እና በፈጣሪ ቁጣ እንደሆነ ያምናሉ። እሳቸው እንደሚሉት የማህበሩ ዋንኛ አላማ ወላጆች በልጆቻቸው ሀፍረትና ሀዘን እንዳይሰማቸው ማድረግ ላይ ያተኩራል ። ሁሌም ወላጆች ከጠነከሩ፣ ከበረቱ የልጆቻውን እና የራሳቸውን መብት ማስጠበቅ ይችላሉ።
ቀልጣፋው ኪሩቤል
በግቢው ኪሩቤል የሚባል የራስ መብት ተሟጋች ክፍል ኃላፊ በስራ ላይ ይገኛል። ኪሩቤል የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ይታይበታል። እንዲያም ሆኖ ከሌሎች ሰራተኞች እኩል ስራዎችን በጥንቃቄና በአግባቡ ይከውናል። ሁሌም ቢሆን ኪሩቤል በራሱ አቅዶ የሚሰራ ትጉህ ሰራተኛ ነው። በእጁ ያለውን ስራ ሳይጠናቀቅ ፈጽሞ ለመሄድ አይነሳም ።
እንደውም አንዳንዴ የምሳ ሰአቱን እና ወደቤት የመሄጃ ጊዜውን ሳይቀር መስዋእት ያደርጋል። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከሌላው ሰው በተሻለ ሀቀኞች ናቸው። ስራዎችን ሲከውኑ በአትኩሮት ነው። የሚሰማቸውን ስሜት ፊት ለፊት ይናገራሉ። የማህበራዊ ህይወት ተሳትፏቸው ደግሞ ከሌሎች ለየት ይላል።
ማህበሩ ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ጥሩ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም አሁንም የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ላይ መስራት እንደሚኖርበት ወይዘሮ ሸዋጌጥ ያምናሉ፡ ። ማህበረሰባችን አሁንም ድረስ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች እንደማይችሉ አድርጎ ያስባል። ሁሌም የሰዎች ጥገኛ እንደሆኑ የሚኖሩ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። እውነታው ግን ይህ አይደለም። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ሰርቶ መግባት በራሳቸው ገቢ የመኖር አቅም እና ችሎታዎች አሏቸው።
ወይዘሮ ሸዋጌጥ በግቢው ስለሚገኝ አንድ ወጣት ያወጉኝ ይዘዋል። ወጣቱ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበት ልጅ ነው። ልጅ ይባል እንጂ በደሞዝ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ መሆኑን ሰምቻለሁ። እኔም ብሆን አስቀድሜ አውቄ ዋለሁ ። ኪሩቤል ይባላል። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበት ወጣት ነው ።
ኪሩቤል በባህሪው እጅግ ምስጉንና ተግባቢ ነው። ከስራ ገበታው በፍጹም አይቀርም አያረፍድም። ምናልባት ችግር እንኳን ካጋጠመው ደውሎ ይናገራል፣ አጥብቆ ይቅርታ ይጠይቃል። ምሳ ሰአት ነው ብሎ የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ አይወጣም። አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት ይተጋል። ያቃተውን ደግሞ ከሌሎች እርዳታ ጠይቆ ለፍጻሜ ያበቃዋል ።
ከወይዘሮዋ የሰማሁት እውነት እያስደነቀኝ ስለኪሩቤል ቀሪ ታሪኮችን ማድመጥ ይዣለሁ። ኪሩቤል ውይይቶች ሲኖሩ መድረኮችን ይመራል። የመክፈቻ ንግግርም ያደርጋል። የምሰማውን ነገር ማመን አልቻልኩም። ልጁን ለማየት እንደምፈልግ ተናገርኩ አፍታ አልቆየም ። ከኪሩቤል ጋር ተገናኘን።
እኔና እሱ
ስሙን ኪሩቢል አንተነህ ሲል ዳግም አስተዋወቀኝ እድሜው 23 አመት ነው። የአእምሮ እድገት ውስንነት አለበት። የሚኖረው ከወላጅ እናቱ ጋር መሆኑን አወጋኝ ። እናቱ ልጃቸውን በተለየ ፍቅር እና በእንክብካቤ ነው ያሳደጉት። ሁሌም ቢሆን በእሱ መኖር ደስተኛ ናቸው። ኪሩቤል ስለራሱ እንዲህ አለኝ።
‹‹ ሰዎች በአይን አይተው ብቻ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንዳለብኝ አያውቁም። ምናልባት እኔ ወይም የሚያውቀኝ ሰው ካልነገራቸው ። የአእምሮ እድገት ውስንነት ከመስራት ፣ ከመማር፣ በስራ ውጤታማ ከመሆን እንደማያግድ እኔ አንዱ ማሳያ ነኝ ›› ኪሩቤልን በፍቅር የአይምሮ እድገት ውስንነት ተቋም ውስጥ ያለውን የስራ ድርሻ እንዲነግረኝ ጠየቅሁት። ኪሩቢል አሁን በፍቅር የአእምሮ ውስንነት ማህበር የራስ መብት ተሟጋች ኃላፊ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ስራውን በእጅጉ ይወዳል፣ ያከብራል ።
የእሱ የምንግዜም ተግባር የአይምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች የፈለጉበት ደረጃ እንደሚደርሱ ማነቃቃት፣ ስራዎችን እንዴት መስራት እንዳለባቸው ማሳየት ፣ የልጆቹ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ያለባቸውን የአይምሮ እድገት ውስንነት እንዲቀበሉ ማድረግ ላይ ያተኩራል። ኪሩቤል በመስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን በሶሻል ሚዲያ ጭምር በመታገዝ በጎ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ይታወቃል።
ኪሩቤል የአይምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ወላጆች ምን እንደሚጠበቅባቸው ጠንቅቆ ያውቃል። ወላጆች እንደሱ ቤተሰብ በልጆቻቸው ላይ ያለውን የአይምሮ እድገት ውስንነት መቀበል ከቻሉ እና በአግባቡ ከተንከባከቧቸው ልጆቹ የሚፈልጉት ቦታ መድረስ እንደሚችሉ በቂ ግንዛቤን አዳብሯል።
ወላጆች ብዙ ጊዜ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ሲኖሯቸው የልጆቻቸውን ችግር መቀበል አይፈልጉም። ወደ ተለያዩ የዕምነት ስፍራዎች በመውሰድ ልጆቹ እንዲድኑላቸው የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ ። የአእምሮ እድገት ውስንነት የሚድን ችግር ሳይሆን በእንክብካቤ እና በድጋፍ ለውጥ የሚመጣበት ነው።
ኪሩቤል ይህን እውነታ ለማወቅ አስረጂ አስፈልጎት አያውቅም። በቻለው አቅም ሁሉ የራሱን ጥረት አድርጎ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይጥራል። እሱ ሁሌም ቢሆን ስለ ወላጅ እናቱ መልካምነት ምስክር ከመሆን ታቅቦ አያውቅም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እናቱን ከልብ ያመሰግናል። ‹‹ወላጅ እናቴ ያለብኝን ችግር ተቀብላ ድጋፍ ላገኝበት ወደምችለው ተቋም ወስዳኛለች ለዚህም ዛሬ እዚህ ላይ ልደርስ ችያለው››ይላል ወጣት ኪሩቤል ስለ እናቱ ሲናገር።
ወይዘሮ የሸዋጌጥ እንደሚሉት አዲስአበባ ላይ ከ 22 በላይ አካቶ ትምህርት የሚሰጥባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች አሉ። በነዚህ ትምህርት ቤቶችም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በእኩል ይማራሉ ። እንደ ወይዘሮዋ አስተያየት በቤተሰብ መሀል ልጆች ሲያድጉ የራስን ጥረትና ክትትል ማድረግ ያሻል ። አንዳንድ ሰዎች ለእንዲህ አይነት ልጆች ዝቅተኛ አመለካከት አላቸው። ይህ በመሆኑም ማንኛውንም ሥራ አምነው ለመስጠት አመኔታው የላቸውም ።
እንደወይዘሮዋ ሀሳብ ግን ይህ አይነቱ ያልተገባ አመለካከት ማንንም አይጠቅምም። ኪሩቤል በተቋሙ ሰራተኛ ሆኖ ሲቀጠር በማንነቱ ሳይሆን ባለው ችሎታና ዕውቀት ተመዝኖ ነው። ወይዘሮ የሸዋጌጥ ለወላጆች ይበጃል የሚሉትን መልዕክት እነሆ ይላሉ።
ሁሌም ቢሆን ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያልተለመዱ ለውጦችን ሲያስተውሉ መጠራጠር ይገባቸዋል ። ለምሳሌ ልጆቹ ቶሎ አፍ ካልፈቱ ፤ አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ካደረጉ ፣ እንደ እኩዮቻቸው መራመድ ባለባቸው እድሜ መሄድ ካልጀመሩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የልጆቹን የጤና ሁኔታ ማጣራት ይኖርባቸዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ። ወላጆች የልጆቻቸውን ችግር ካወቁ በኋላ ልጆቹን ሊመጥኑ ወደሚችሉ ተቋማት በመውሰድ በትምህርትና በስነልቦና እገዛ እንዲያገኙ መጣር አለባቸው። ይህ አይነቱ ክትትልና ሙከራ ካለም እንደ ወጣት ኪሩቤል ጥሩ የሚባል ደረጃ ለማድረስ የሚያግዳቸው አይኖርም ።
የፍቅር ገበታን በእኩል
ፍቅር የአእምሮ ውስንነት ማህበር እንደቃሉ ሆኖ ሁሉንም ተማሪዎች በፍቅር አቅፎ ይዟል ። ተማሪዎቹ በእኩል የመማራቸው ሂደት ነገ ለሚደርሱበት ዓለም የተሻለ ዕውቀትና መልካም አስተሳብን ይዘው እንዲቀጥሉ ያግዛል።
በዓለማችን በርካታ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በቀለም ትምህርት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ። በፈጠራ ስራዎቻቸው እውቅናና ታዋቂነትን ያተረፉም አሉ። ጥቂት የማይባሉት ትምህርታቸውን እሰከ ዲግሪ ደረጃ አሳድገዋል ። በትዳር ዓለም ከሀያ አመታት በላይ የቆዩ ጥንዶችም በአርአያነት ይጠቀሳሉ።
ወይዘሮ የሸዋጌጥ እንደሚሉትም በተቋሙ መጀመሪያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች የቀለም ትምህርት እንዲማሩ ይሞከራል። ሙከራው የታሰበውን ያህል ውጤት ካላስገኘ ግን ልጆች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በቂ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ይህ በመደረጉም ዛሬ በርካቶቹ እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ ተግባራት ተሰማርተው ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ተቋሙ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓመመልዕክት ለሌሎች
እንደኪሩቤል መሰል ወጣቶች ባማንነታቸው መገለልና አድሎ ካልተደረገባቸው ነገን በተስፋ ይሻገራሉ። ችሎታና ዕወቀታቸውን ሚያከብርላቸው ካገኙም ለበርካቶች አርአያና ምሳሌ ሆነው አገርን ይገነባሉ። ፍቅር አይምሮ ዕድገት ውስንነት ማህበር ሁሉንም ተማሪዎች በአንድ አሳበስቦ ፍቅር መመገቡ ነገ ለአይን የሚያጠግብ፣ ለአይምሮ የሚያረካ ተግባር መነሻ ይሆናል።
አዎ! የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ፍቅርን ከተቸሩ ራሳቸውን፣ ወገናቸውን፣ ብሎም አገርንና ዓለምን ይለውጣሉ። ዛሬ የምንተውላቸው በጎ አሻራም ለነገ ማንነታቸው ደማቅ ማህተም ሆኖ ታሪካቸውን ይቀይራል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም