ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን ኤባ ይባላሉ:: ተወልደው ያደጉት ወልቂጤ ቢሞራ የምትባል መንደር ውስጥ ነው። በአገራቸው ባህል መሰረት ቁርአንን የቀራ ሼህ በአካባቢው ካለ የአካባቢውን ልጆች ጠዋት ከማለዳ እስከ ከብቶች ማሰማሪያ ሰዓት ድረስ ያስቀራሉ። የአካባቢውን ልጆች ሰብስበው ቁርኣን ያስቀሩ የነበሩት ደግሞ አባታቸው ሸህ አማን ኤባ ናቸው። ሸህ ሱልጣን ከአባታቸው እግር ስር ቁርኣን ቀርተው ነበር ያደጉት።
በእስልምና ሀይማኖት ትምህርት ልጆች ቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀምጠው ከተማሩ ሙሉ ትኩረታቸውን ለሀይማኖት ትምህርቱ አይሰጡም ተብሎ ስለሚታሰብ ከወልቂጤ ተነስተው ወደ ስልጤ፤ ሀላባና ወደ ጅማ በመሄድ ይማሩ ነበር። ሼህ ሱልጣንም በተለያዩ አጎራባች ወረዳዎች በመሄድ ከታወቁ ሼሆች እግር ስር ቀርተዋል።
በመቀጠል ወሎ ክፍለ አገር በ1977 ዓ.ም ለአራት አመታት ቀርተው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በወቅቱ የነበረው አስተዳደር የሶሻሊዝም ርእዮተ ዓለም ተከታይ ስለ ነበር ሀይማኖታቸውም በነፃነት ማራመድ ሲሳናቸው ወደ ሱዳን ያቀናሉ። በሱዳን ሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሳውዲ አረቢያ ባገኙት ነፃ የትምህርት እድል አማካኝነት ይጓዛሉ። በዛም በአረብኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ድግሪ፤ በእስልምና ሀይማኖት ትምህርት ሁለተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።
ሼሁ በሳውዲ አረቢያ ለአስራ አምስት ዓመታት ቆይታቸው በሳውዲ በሚገኙ ከተሞች ማለትም በመዲና ለሶስት ዓመታት፤ በዋና ከተማው ሪያድ አምስት ዓመት፤ መካ ሁለት ዓመት፤ በጅዳ ደግሞ ለአምስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በአገራቸው ኢትዮጵያ የስርኣት ለውጥ በመምጣቱ ወደ አገራቸው መመላለስ ጀመሩ።
ጠቅልለው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ሲወስኑ አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከፍተው በድህነት ውስጥ ላሉ ሰዎች እርዳታ የሚያደርግ፤ መስጊዶችን የሚሰራ፤ ቁርኣንም በተገቢው መልኩ ለሁሉም እንዲዳረስ የማድረግ ስራን የሚከውን ድርጅት ለማቋቋም አሰቡ። ለዚህ መነሻ የሆናቸው ደግሞ በሳውዲ አረቢያ በነበራቸው ግንኙነት የገንዘብ ድጋፎችን በማሰባሰብ ለወገን ጠቃሚ የሆኑ ተግባሮችን ሲያከናውኑ መቆታቸው ነው።
አሁን ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን ኤባ የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የረመዷን ፆምንና የኢድ በዓልን በተመለከተ ከእኚህ ታላቅ አባት ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፤ ረመዷን ማለት ምን ማለት ነው ከሚል ጥያቄ እንነሳ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ “ረመዷን” ማለት . . . በቁርአን ላይ እንደተገለጸው፥ ከአላህ ዘንድ የወራት ቁጥር 12 ናቸው። እነሱም፦ ሙሀረም፣ ሰፈር፣ ረቢዕ አልአወል፣ ረቢዕ አልሳኒ፣ ጅማድ አልኡላ፣ ጅማድ አልአኺራ፣ ረጀብ፣ ሻዕባን፣ ረመዷን፣ ሸዋል፣ ዙል ቀኢዳ እና ዙል ሂጃ ናቸው። ከላይ በቀረበው አገላለጽ መሰረት፥ “ረመዷን” ማለት ከ12ቱ ወራት የዘጠነኛው ሥያሜ ነው።
ረመዷን ከሌሎች ወራት የሚለይበት በርካታ ምክንያት እንዳሉት ይገለጻል። ከሌሎች ወራት ከሚለይባቸው ምክንያቶች አንዱ “ቁርአን የወረደበት ወር መሆኑ ነው። በተጨማሪም ረመዷን የሠደቃ፣ የራህመት፣ የጀነት በር የሚከፈትበት፣ የጀሃነም በር የሚዘጋበት፣ በጎ ሥራዎች ሲሠሩ ከአላህ ዘንድ እጥፍ ክፍያ (አጅር) የሚያስገኝ በመሆኑ ከሌሎች ወራት ይለያል።
እንዲሁም ረመዳን “ለይለቱል ቀድር” የተሰኘች የ1ሺህ ወራት የአምልኮ ምንዳ ልታስገኝ የምትችል አንዲት ሌሊት የምትገኝበት ወር በመሆኑ ልዩ ነው። ወሩም የበረከት ማግኛ ወር በመሆኑ ሙስሊሞች እንዲጾሙ ይጠበቃል ።
የረመዷን ወር በርካታ ትሩፋት አሉት። ቁርአን በብዛት የሚቀራበት፣ “ቀልቦች” ወደ ፈጣሪያቸው ቀጥ የሚሉበት፣ ርኅራሔ የሚበዛበት፣ ሠደቃ የሚሠደቅበት፣ የቸርነት፣ የልገሣ፣ የደግነት፣ የተካፍሎ መብላት እና የመረዳዳት ወር መሆኑ ከትሩፋቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የረመዷን ወር በሦት አሥር ቀናት የሚከፈል ሲሆን፥ ከሦስቱ አሥሮች የመጨረሻው አሥር (“አሸረ አልአዋኺር”) ይሰኛል። በአጠቃላይ “ረመዷን” የ “ኢባዳ”(በጾምና በጸሎት ወደፈጣሪ መመለሻ) ወር ቢሆንም የሦስተኛው አሥር ቀናት የተለዩ በጾም በጸሎት ማሳለፊያ ጊዜ (የ”ኢባዳ” ሌሊቶች) ናቸው።
የረመዷን የመጨረሻው ሣምንት ሌሊቶች ከሌሎች ሣምንታት ምክንያቶቹ መካከል፥ ነብዩ መሐመድ (ሰለሏህ ዓለይሂ ወሰለም) ያደርጉት እንደነበረው ሥራ ትቶ፣ እራስን አቅቦ ለ”ኢባዳ” ማስቀመጥ ቀኑንም ሌሊቱን በመስጂድ ማሳለፍ (“ኢህቲካፍ” መግባት) አንዱ ነው። በመሆኑም ወደ መስጂድ ለ “ኢህቲካፍ” የገባ ምዕመን ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ካላጋጠመው በስተቀር ከመስጂድ መውጣት የማይቻልበት ሣምንት መሆኑንም ነው የሚጠቅሱት።
ሌላኛው ምክንያት በእነዚህ ሌሊቶች፥ የተራዊህ እና የተሃጁድ ሶላት ይሠገዳል፣ ሌሊቶቹ ያለዕንቅልፍ ቁርአን በመቅራት እንዲያልፉ ይደረጋል፣ መሻይኾች፣ ዑለማዎችና የመስጂድ አሰጋጆች በተለያየ የሶላት ወቅት ላይ (በዙህር፣ ዓስር፣ መግሪብ፣ ኢሻ)፣ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በሥነ ምግባር፣ በአምልኮ እንዲሁም በእምነቱ ዙሪያ (በዓቂዳ ጉዳይ ላይ) ምክር ይሰጣሉ ።
ሙስሊሞች “ረመዷን” ን ለቀጣዮቹ 11 ወራት የባሕርይ፣ የሥነ ምግባር፣ የአምልኮ የጥንካሬ እና የብቃት አቅም የሚያጎለብቱበት ልዩ ወር ነው። የመጨረሻው ሣምንት ሌሊቶችንም በንቃት በኢባዳ ነው የሚያሳለፉት። የመጨረሻ ሣምንት የጾም ወቅት በኢትዮጵያ በበርካታ መስጂዶች የተሃጁድ (የሌሊት) ሶላት ይሰገዳል። በተጨማሪም ረጅም ሩኩዕ፣ ረጅም ስጁድ፣ረጂም ቂያም ያካተተ ሶላት ይሠገዳል።
በአጠቃላይ ይህ ሁሉ ለኢባዳ የሚደረገውን መስዋዕትነት በአላህ እንደመገዛት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለማሰልጠን ጭምር ነው። ከ1 ሺህ ወራት ኢባዳ የላቀ ምንዳ ያላት አንድ ሌሊት (ለይለቱል ቀድር) ከቅዱሱ የረመዷን ወር የመጨረሻ ሣምንት ውስጥ ‹‹ለይለቱል ቀድር›› የምትባል በረከቷ የበዛ ሌሊት አለች። ይችኑ ሌሊት ‹‹ኸይሩን ሚን አልፊሸህር›› ብሏታል ቁርአን።
1 ሺህ ወር አላህን ከማምለክ በእዚች ሌሊት ላይ ጠንክሮ ማምለክ የ1 ሺህ ወራትን (83 ዓመት ከ3 ወራት በላይ) ኢባዳን ወይም አምልኮን ትተካለች። ሙስሊሞች ይችን በረከተ ብዙ ሌሊት በኢባዳ ለማሳለፍ በንቃት ሁልጊዜም ይጠባበቃሉ።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አሥሩንም ሌሊቶች እንቅልፍ ያለባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ቀስቅሰው የጋራ ኢባዳ እና የጋራ አምልኮ (በጀመዓ መጸለይ) በማድረግ ሳይተኙ ያሳልፉ ነበር እኛም እሳቸውን የምንከተል በመሆናችን ‹‹በአላህ መልዕክተኛ መልካም አርአያ አላቸው፤ እሳቸው የሚሉትን ሥሩ›› ስለተባልን ኢባዳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።
ሌሊቱ በዱዓ፣ በጸሎት፣ እንዲያልፍ አላህ ይቅር እንዲል ሙስሊሞች የሚማፀኑበት ሌሊት መሆኑም ተመላክቷል። ረመዷን ሠደቃ የሚሰጥበት፣ አቅመደካሞች የሚረዱበት፣ የመተጋገዝ ወር እና ለማፍጠሪያ ማዕድ ማጋሪያ ጊዜም ነው።
አዲስ ዘመን፤ በብዙዎች ዘንድ ተናፋቂ የነበረው የረመዳን ጾም ተጠናቋል። ለመሆኑ ጾሙ እንዴት አለፈ ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን ፤ ፆም ሲታሰብ ረሃቡ ድካምን ጥሙን ብዙ ሰው ያስባል። እኛ ግን ፆምን ስናስብ ባላለቀ እያልን ነው የምንፆመው። ምክንያቱም ፈጣሪ ያዘዘውን ትእዛዝ የምንፈፅምበት በመሆኑ ነው። ፆም ጤና ለሌለው ሰው ጤናን የሚሰጥ፤ ከዚህም በላይ ምንም የሌላቸው ሰዎችን ከድህነቱም ከችግሩም የሚላቀቁበት፤ የሚረዱበት ጊዜ ነው። ፆም ላለውም ለሌለውም በበረከት የሚኖርበት፤ ፆም መልካምን ነገር ይዞ የሚመጣበት በመሆኑ ደስታ ነው በፆም ጊዜ የሚሰማን።
የዘንድሮ ፆም በአገራችን በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ብዙዎች በተቸገሩበት ወቀት ላይ ነው የመጣው። በዚህም ምክንያት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተቻለውን እየረዳ፤ ህዝበ ሙስሊሙም ከጎረቤቱ ጋር ተካፍሎ እንዲበላ በማስተማር፤ የመስጊድ ኡለማዎችና ኢማሞችን ደግሞ ወደ ፈጣሪ ጥሪ የሚያደርጉ አካላት እርዳታ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አድርገናል። በዚህም ከብዙ አካላት እርዳታ ተሰብስቦ ለብዙሃኑ ተዳርሷል።
በዚህ በፆም ወቅትም በቦረና ለተከሰተው ከፍተኛ ድርቅና ረሃብ የተጎዱ ሰዎች ድጋፍ የሚውል ከየመስጊዱ የተሰባሰበ እስከ 20 ሚሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ ተገኝቶ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ሆኗል። አሁን በፆሙ ጊዜ ወደ ደብረ ብርሃን አካባቢ በመጠለያ ላሉት የሚደርስ እርዳታም በማሰባሰበ ላይ እንገኛለን። በዘንድሮው ፆም አገራችን ምንም እንኳን ችግር ላይ ብትሆንም እርስ በእርስ እየተረዳዳን በጥሩ ሁኔታ አሳልፈናል።
አንድ ሙስሊም ካለው ሃብት ላይ 2ነጥብ 5 በመቶውን ለችግረኛ ወገኖች የሚሰጥበት ስርዓት አለ፤ ይህም ዘካ ይባላል። ይህ ፆምም ለተለያዩ አካላት ማለትም ለጎረቤት፤ ለቅርብ ዘመድ፤ ለሩቅ ዘመድ፤ ምንም ለሌለው ምስኪን፤ የተወሰነ አቅም ኖሮት ለማይበቃው፤ ወላጅ ላጡ ህፃናት ዘካ ይሰጣል። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ሰደቃ የሚባል አለ። ይህ ግዴታ ሳይሆን ራሱ ምእመኑ ከፈጣሪ ዘንድ ምንዳ እንዲያገኝ ብሎ የሚያደርገው የስጦታ ነው። እንዲህ አይነት ነገሮች በሙስሊሙ ዘንድ በጣም በስፋት የሚሰራበት ጉዳይ ነው።
በተከናወነው የጎዳና ኢፍጣርም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ይዘው ወጥተው አብረው ያፈጠሩበት፤ ያጡ ወገኖችን ለመደገፍና እርስ በእርስ የመደጋገፍ ፍላጎታቸውን ለማሳየት በነቂስ በመውጣት አብረው መአድ ቆርሰዋል። በኪሳቸው የያዙትን ደግሞ ለተቸገሩት በማለት አውጥተዋል። በዚህ መልኩ ነው እንግዲ ፆሙ ያለፈው ።
አዲስ ዘመን፤ ሀጂ በእርስዎ ቤት የነበረው የረመዷን ጾም ሁኔታ ምን ይመስላል ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ እኔ በቤቴ ከሁለት ሚስቶች ስምንት ልጆች አሉኝ። እቤት ግን ያፈጠርኩት አራት ቀናት ብቻ ነው። እዚህ የህዝብ መሪ ስለሆንኩኝ የህዝብ ኃላፊነት ስላለብኝ ሰዎች በየቦታው ስለሚጠሩኝ ወደየጥሪው እየሄድኩኝ ነው የማሳልፈው። ልጆቼም ቤተሰቦቼም ይሄንን ስለሚያውቁ ቅር አይላቸውም።
አዲስ ዘመን፤ የኢድ በዓል የመጠያየቅና የመረዳዳት በዓል ነው ? በአጠቃላይ የኢድ በዓል ለሙስሊሞች ምንድን ነው ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ በዓመት ወስጥ ሙስሊሞች የሚያከብራቸው ሁለት ታላላቅ በዓላት አሉ አንዱ፤ ፆም ተፁሞ የፆም ፍቺ እለት የሚከበረው ኢድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፤ በሀጂ ጊዜ የሚከበር የአረፋ ኢድ የሚባል አለ። የአረፋ በዓል በሶስተኛው ወር በአስረኛው ቀን የሚፈፀም ኢድ ነው። ይሄኛው ኢድ የእስልምና ሀይማኖት ምሶሶ የሆነውን ረመዷን ፆም ጨርሰን ያለውም የሌለውም፤ ሴቱም ወንዱም፤ ትልቁም ትንሹም ይሄን ፆም ፈፅሞ፤ ፈጣሪ ያዘዘውን ትእዛዝ ተቀበሎ ወደ ፈጣሪው ቀርቦ ከፈጣሪው ምህረትን ተቀብሎ ንፁህ ሆኖ የሚወጣበት ወር ነው። ኢድ ማለት ደስታ ማለት ነው። ሀይማኖቱን ከፍ አድርጎ የሚያሳይበት ነው። ለዚህም ነው ሰፋ ባለ ቦታ የሚሰግደው።
አንድ ሰው ጀስሙ ላይ ወይም አካሉ ላይ ቆሻሻ ከነበረና ታጥቦ ሲነሳ የሚሰማው የመፅዳት ስሜት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፆሙ በኋላ ያገኘዋል። በመንፃት ደስታ ይገኝበታል። ኢድ ለሙስሊሙ ደስታን የሚያጎናፅፍ ትልቅ በኣል ነው።
አዲስ ዘመን -በኢድ ወቅት የሚከወኑ ተግባራት ምንድን ናቸው?
ሼህ ሱልጣን ሃጂ አማን – በኢድ ወቅት የሚከወኑ ዋናዋና ተግባራት አሉ። የመጀመርያው ኢድ ከመሰገዱ በፊት ምንም ለሌላቸው ወገኖች የሚሰጥ ምጽዋት አለ። ዘካተል ፊጥር ይባላል። ዘካተል ፊጥር ድሆች ኢድን እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲውሉ የሚሰጥ መጠነኛ ስጦታ ነው። ለአንድ ሰው አራት እፍኝ ስንዴ፤ ዱቄት፤ ጤፍ ወይም ይህንን ወደ ገንዘብ በመለወጥ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ከዚህ በኋላ ሁሉም ሙስሊም በአንድነት ለመስገድ ሰፋ ባለ ቦታ ይሰባሰብና (እዚህ አዲስ አበባ ስታዲዮም እንደሚደረገው) የኢድ ሶላቱን በጀምዓ (በጋራ) ይሰግዳል። ከዚያ ሲመለስ ከቤተሰቦቹና ከጎረቤቶቹ ጋር በጋራ በደስታ ያሳልፋል። እዚህ ላይ ግን ከምስኪን ወገኖች ጋር ተካፍሎ መብላትና መጠጣት የእምነቱ አንዱ ግዴታ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዴት ይመለከቱታል?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ ነው። ይህ ጉዳይም በታሪክ ተመዘግቦ የተቀመጠ የዓለም ህዝብ በሙሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው። ድሮ እስልምና ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መካ ላይ ተልከው ስለእምነት ሲያውጁ የአካባቢው ሰዎች አንቀበልም ብለው ሙስሊሞችን መዳረሻ ያሳጧቸው ጊዜ፤ መሸሻ መሸሸጊያ በአጡበት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮቻቸውን አዘዟቸው። ነብዩ መሃመድ በፈጣሪ ምሪት ስለሚመሩ በዛ መሰረት ወደ ሀበሻ ሂዱ እዛ አገር ትልቅ መንግስት ወይም መሊክ አለ ያ መሊክ ማንም ሸሽቶ የሚመጣ ካለ የሚቀበል፤ በግፍ አሳልፎ የማይሰጥ፤ በፍትሃዊነት የሚመራ መንግስት ስለሆነ ይቀበላችኋል ብለው ተከታዮቻቸውን ወደ ሀበሻ ላኩ።
እነሱም መልእክቱን ተቀብለው ወደ አገራችን መጡ። በመጡ ጊዜም ልክ እንደተባለው ንጉስ ነጃሺ ተቀብሎ በተገቢው አስተናገዳቸው። ቁረሾች እነዛን ሰዎች መልሱልን የኛ ናቸው ቢሉም ንጉሱ አልመልስም በማለት መጠለያ ሆነዋል። በዛን ጊዜ እስልምና የነገሰበት አገር መዲና ላይ እንኳን የእስልምና ትምህርት ሙሉ ለሙሉ አልተዳረሰም ነበር። ይህ አኩሪ ታሪካችን በኢስላም አገሮች ላይ የሀበሻ ታሪክ ተብሎ እንደትምህርት ይሰጣል። ይህ ታሪክ በዓለም የገነነ ነው።
ሶሃባዎች (የነቢያችን ወዳጆች) ሁለት ጊዜ ነው ወደ ሀበሻ የመጡት። የመጀመሪያዎቹ 15 የነበሩ ሲሆን በቀጣየም ከ70 በላይ መጡ። እስካሁን ድረስ ትግራይ ላይ ያለው አልነጃሺ በወቅቱ የሞቱ ሳህባዎች አፅም በክብር ተቀምጦ ይገኛል። የነብያችን ልጅም መጥታ የነበረ መሆኑ ታሪክ ይናገራል።
ነብዩ መሃመድ (ሰ.ዐ.ወ) እናታቸው አሚና የሞተችው በህጻንነታቸው ነው። ኢትዮጵያዊቷ እሙይ አይመን ነብዩን በሞግዚትነት የማሳደግ ኃላፊነት ወስዳ ነብዩን በማሳደግ ኃላፊነቷን ተወጥታለች። የመጀመሪያውን አዛን (ጥሪ) ያደረገውም ቢላልም ሀበሻ ነው። ቢላልን ቁረሾች ያላደረጉት ነገር አልነበርም። እሱ ግን አንድ ፈጣሪ እያለ ነው የሞተው። እናም አገራችን ለእስልምና ያበረከተችው ታሪክ ተቆጥሮ የማያልቅ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ የአይሁድ፤ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖቶችን ተቀብላ ያስተናገደችና ለዘመናትም በመከባበር ላይ እንዲኖሩ ያደረገች አገር ናት። በዚህ ረገድ እርስዎ ምን ይላሉ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ አገሪቱ ውስጥ አይሁዶች ነበሩ፤ አሁንም አሉ ይበላል፤ ክርስትናም ቀድሞ የነበረ ሲሆን እስልምና ደግሞ ከ አንድ ሺ አራት መቶ አርባ አራት አመተ ሂጀራ በፊት ነበረ የመጣው። እንግዲህ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ሀይማኖቶች አብረው ኖረዋል። መንግስታት ሲቀያየሩ ከፍና ዝቅ የሚሉ ነገሮች ይኑሩ እንጂ ህዝብ እንደ ህዝብ ግን በአብሮነት ተቻችሎ ተከባብሮ አብሮ መአድ ቆርሰው አብረው ኖረዋል። አሁን ግን በአገራችን ሀይማኖቶች እኩል መብት አግኝተዋል ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም በጋራ በመሆን የሀይማኖቶች ጉባኤ ላይ አብረን እየሰራን ነው። አሁን ያለው መሪ ሀይማኖቶችን እያከበረ ያለ መሪ ነው።
እንደ አዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ እንደ አዲስ አበባ ነዋሪ ኦርቶዶክስ ሰብሳቢ ሙስሊሙ ደግሞ ፀሃፊ ሆኖ ከሁሉም ሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቋቁመን ለህዝቡ መተላለፍ ያለበትን ነገር ተወያይተን ተመካክረን እንደሃይማኖት አባት እናስተላልፋለን። ህዝቡ የእስልምና ሀይማኖት በዓል ሲመጣ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በአብሮነት ተከባብሮ ተደጋግፎ መአድ የሚቆርስበት ሁኔታ ነው ያለወ። አገራችን በዚህ ረገድ ምሳሌ የምትሆን አገር ናት። ህዝቡ ውስጥ ያለው መከባበርና መቻቻል በየትኛውም አገር የሚታይ አይደለም። ህዝቡ ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ ማስቀጠል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፤ የቀደሙ የአገር እሴቶችን አስከብሮ ከማስቀጠል አንፃር ከህዝበ ሙስሊሙ ምን ይጠበቃል?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ እኛ ለህዝበ ሙስሊሙ እያስተላለፍን ያለው መልእክት ሁላችንም የግል ሀይማኖት ቢኖረንም አገራችን ግን አንድ ናት፤ ይህችን አገር ደግሞ ሰላሟን መጠበቅ፤ ልማቷን ማስቀጠል፤ ከዚህ በፊት ይዘነው የመጣነውን የአብሮነት ባህል ማስቀጠል ይኖርብናል የሚል ነው።
ከበፊቱ የበለጠ መቻቻል ከሚለው እሳቤ ወጥተን መደጋገፍና መተባበር መፈቃቀር ህዝቡ መገለጫው እንዲሆን መሰራት ይኖርብናል። የነበረንን እሴት አሳድገን እጅ ለእጅ ተያይዘን ማደግ ይኖርብናል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፤ ሰላም የሁሉም ሀይማኖቶች አስተመህሮ ነውና በሰላም ችግሮችን ከመፍታት ረገድ አማኞችም ሆኑ የሀይማኖቱ መሪዎችም ምን ማድረግ አለባቸው?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ ሁሉም ሃይማኖቶች፤ ሰላምን ፍቅርን አብሮነትን ይሰብካሉ። ያንን አስተምህሮ ደግሞ ወደ ህዝቡ የሚያስተላልፉት የተማሩ የበቁ አባቶች ናቸው። እነዚህ አባቶች በመመሪያ ውስጥ ያለውን ነው ህዝቡ ጋር የሚያደርሱት።
እርግጥ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የፖለቲካ አካላት ሰላምን የማይፈልጉ፤ ጥላቻን የሚዘሩ ከሌላ በኩል አልሳካ ሲላቸው ኃይማኖት ውስጥ በመግባት ጥላቻን የመዝራት ሁኔታዎች ይታይባቸዋል። እኛ ግን እንደ ሀይማኖት አባት ሀይማኖት የግል ነው ፖለቲካ አይግባ በማለት ህዝቡን ንፁህ የሆነ መንፈሳዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ ይኖርብናል። የሀይማኖት አባት እንደ ስሙ የሀይማኖት አባትነቱን ተረድቶ ከፖለቲካና ከሌሎች አላማዎች ማስፈፀሚያ ከመሆን ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።
ህዝቡም ባለችው አንድ አገር እምነቱን በተገቢው መልኩ ለማስፈፀም የአገር ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ በአብሮነት መስራት ይጠበቅበታል። ለመኖርም፤ በነፃነት ሀይማኖቱን ለማምለክም ቅድሚያ አገር መኖር ይኖርባታል።
አዲስ ዘመን፤ አሁን አሁን ይህንን የቆየ የመከባበር ባህል ለመበረዝ የሚሞክሩ አልጠፉም። ለእነዚህ ሰዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ እኛ የምናስተላልፈው መልእክት ሀይማኖታዊ ነው። የፖለቲካ ችግራችሁን ሌሎች ጥያቄዎቻችሁን ወደ ሀይማኖታችን አታምጡብን እያልን ነው መልእክት የምናስተላልፈው። ፀሎት አድርገን አደብ እንዲሰጣቸው ዱኣ ነው የምናደርገው።
እኛ በእድሜያችን ብዙ መንግስታትን አይተናል። ብዙ የፖለቲካ አስተሳሰብ የነበራቸውን መንግስታትን ተመለክተናል። ሁሉም በጊዜ ሂደት አልፏል። የማያልፈው ህዝብ ነው፤ የማይጠፋው አገር ነው፤ የማይጠፋው ሀይማኖት ነው ይሄንን ህዝቡ ጠንቀቆ ማወቅ ይገባዋል፤ ሁሉንም ነገር በሰከነ አእምሮ መመልከት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፤ አዲሱ መጅሊስ ከተቋቋም በኋላ ህዝበ ሙስሊሙ ለአገሩ ልማትና ሰላም ዘብ እንዲቆም የተሰሩ ስራዎች ካሉ ቢያብራሩልን?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ አዲሱ መጅሊስ በአዲስ መልኩ በአዋጅ ተቋቁሟል። ይህ በአዋጅ መቋቋሙ ለእኛ በጣም ትልቅ ነገር ነው። የአዲስ አበባ መጅሊስ እንደተቋቋመው ሁሉ በየክልሉ መጅሊስ ተቋቁሟል። እኛም እንደ አዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ወደ ክፍለ ከተማም በከተማዋ ወደ ሚገኙ አንድ መቶ ሀያ አራት ወረዳዎች አውርደን አቋቁመናል። የመስጊድም ኮሚቴ ተቋቁሞ ሀይማኖቱ በተቋማዊ ስርኣት ልምድና እውቀት ባላቸው ሰዎች እየተመራ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ከጎናችን ቆሞ ትክክለኛ የተቋም ቁመና እንዲኖረው ስላደረገው እጅግ በጣም ደስተኞች ነው። ከመንግስታችን ጋር ቆመንም የሰላሙም የልማቱም ዘብ ለመቆም ተዘጋጅተን በተገቢው ስርኣት እየተመራን ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፤ በመጨረሻ ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልእክት ካለ?
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ ለህዝበ ሙስሊሙ ፆማችንን ጨርሰን ኢድ አልፈጥር ላይ ደርሰናል፤ ረመዷን ውስጥ ተጋግዘን ተባብረን እብረን መአድ እንደ ቆረስን ሁሉ ኢድ ደስታ ነውና በኢድም ወቅት ሆነ ከኢድ በኋላ ባሉት ቀናት የመረዳዳት ባህላችን መቀጠል ይገባዋል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች ችግር ውስጥ ወድቀው ስለሚገኙ በተቻለ መጠን ካለን ላይ እያካፈልን ችግራቸውን እንድንካፈላቸው አደራ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፤ ውድ ጊዜዎን ሰውተው ሀሳቦትን ስላካፈሉን እናመሰግናለን።
ሼህ ሱልጣን ሀጂ አማን፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015