በበዓላት ሰሞን በመገናኛ ብዙኃን ከምንሰማቸው ወሬዎች መካከል ‹‹… ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል … ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸው ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል …›› የሚሉት አገላለፆች ይገኙበታል።ከቀናት በኋላ የሚከበሩትን የትንሳኤ (ፋሲካ) እና የኢድ-አልፈጥር በዓላትን ምክንያት በማድረግ እነዚህን ጥሪዎች/ምክሮች መስማታችን አይቀርም።
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያኑ የዐቢይ ፆምን፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ደግሞ የረመዳን ፆምን በተመሳሳይ ወቅት ፆመዋል። ታዲያ እነዚህ ዐበይት የፆም ጊዜያት በአማኞች ዘንድ ልዩ ስፍራና ክብር የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ተግባራት ናቸው።አማኞች የሥጋ ምቾታቸውን ቀንሰው ስለትናንት፣ ስለዛሬና ነገ በፆም፣ በፀሎትና በስግደት ፈጣሪያቸውን በሚማጸኑባቸውና በሃይማኖቶቹ አስተምህሮዎች የሚታዘዙ ሌሎች ተግባራትንም በሚፈፅሙባቸው በእነዚህ የፆም ወራት፤ ሕዝቡ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እንዲሁም ለሀገር ሰላምና እድገት የሚጠቅሙ መልካም ተግባራትን በማከናወን ማሳለፍ እንደሚገባው ቀደም ብለው አሳስበዋል።
እርግጥ ነው፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ይሁን ሙስሊሙ በዓላትን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንዳይዘነጉ መንገር ተገቢና አስፈላጊ ምክር ነው። መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው።መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ካለው የተለየ ይሆን ነበር።
ታዲያ እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ነጥብ የማኅበረሰቡ የመረዳዳት ባህል ከበዓላት ሰሞን መሻገር እንዳለበት ማስታወስና ይህ እንዲሳካ ለሚስችሉ ተግባራት ትኩረት መስጠት ሊሆን ይገባል።በበዓላት ወቀት ሕዝቡ መረዳዳት እንዳለበት ከማስታወስ በተጨማሪ ከበዓላት ውጭ ባለው ጊዜም የመረዳዳት ተግባሩን አጠንክሮ መቀጠል እንዳለበት ማስገንዘብም ተገቢ ይሆናል። ይህ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው የመረዳዳት ባህል በበዓላት ሰሞን ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ለማድረግ የመረዳዳት ባሕልን ከአንድ ሰሞን ኹነት የተሻገረ ተግባር አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ‹‹ያለንን ማካፈል የባሕላችን አንድ አካል ሆኖ የዘለቀ ዕሴት ነው። እጦት ለገጠማቸው ማካፈል አሥር እጥፍ መልሶ የሚያስሸልም ተግባር ነው። ከበዓል ሰሞን ባሻገር በቀጣይነት የመስጠት ተግባራችንን ማስፋት በእኩልነት ተደራሽ የሆነ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ከሚያስችሉ ግብዓቶች አንዱ ነው። በተለያየ የኑሮ ደረጃ የምንገኝ ሁሉ ማዕድ ማጋራትን እንዲያሰፉ አበረታታለሁ›› የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር። አዎ፣ የመረዳዳት ባሕልን ከአንድ ሰሞን ድርጊት አሻግሮ ዘላቂ ለማድረግ ‹‹ያለንን የማካፈል›› መርሕን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል።ያለንን በማካፈል መርሕ የምናምን ከሆነ የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ የበዓላትን ሰሞን መጠበቅ አያስፈልገንም።ያለውን በማካፈል መርሕ የሚያምን ሰው መተጋገዝ ጊዜና ቦታ የማይገድበው በጎ ተግባር እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
ዛሬ በሌሎች የተረዳና የተደገፈ ነገ ሌሎችን መርዳቱና መደገፉ አይቀርም፤ዛሬ ያለውን ያካፈለ ሰው በእርሱ ማካፈል የሌሎች ችግር እንዲቃለል ከማድረጉ በተጨማሪ ሌሎችም ያላቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ትምህርት ይሰጣል።ያለንን የማካፈል መርሕ እንዲህ ዓይነት አካሄዶችን በመገንባት መረዳዳትን ዘላቂ ለማድረግ ያስችላል።
የመረዳዳት ባሕል ትርጉም የሚኖረውም ውስን ጊዜያት እየተጠበቁ በሚከናወኑ የመተጋገዝ ሥራዎች ሳይሆን፣ ቀጣይ በሆኑ የመደጋገፍ ተግባራት ነው።ዘላቂ የሆነና ያለንን በማካፈል መርሕ ላይ የተመሠረተ የመረዳዳት ተግባር ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን ያጎለብታል፤መተማመንንና መከባበርን ያዳብራል፤በጋራ ለማደግ ጠንካራ መሠረት ይሆናል።እነዚህ እሴቶች ለሀገር ሰላም ትልቅ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ።በአጠቃላይ ዘላቂ የሆነ የመረዳዳት ባሕልና ተግባር በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ሀገር እንዲኖር ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በበርካታ ችግሮች ውስጥ ይገኛሉ።የሰላም እጦት ያስከተላቸው ምስቅልቅሎች፣ የዋጋ ንረት፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎች ችግሮች የመረዳዳትን አስፈላጊነት በእጅጉ ከፍ ያደርጉታል።የዋጋ ንረት አልቀመስ ባለባቸው የዘወትር ቀናትስ ያለው የመረዳዳት ባሕላችን እንዴት ነው? ‹‹እኔ በልቼ፣ ወገኔ ፆም ማደር የለበትም›› ብለን እየተረዳዳን ነው? እንደሚታወቀው ወቅታዊው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡን የመኖር አቅም በእጅጉ እየፈተነው ነው።የዋጋ ንረት በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም።የዋጋ ንረቱ እንኳን ቅናሽ ማሳየት ይቅርና ባለበት መቀጠልም አልቻለም።አሁን ያለው የዋጋ ንረት ከእስካሁኑ ሁሉ የከፋ እንደሆነ እየታየ ነው፤ፈጣን የማስተካከያ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ነገም ከዛሬውም የባሰ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።አልፎ አልፎም ቢሆን በመገናኛ ብዙኃን የሚደመጡ የነዋሪዎች አስተያየቶችና አቤቱታዎች በምሬቶች የተሞሉ አሳዛኝና አሳሳቢ ቅሬታዎች ናቸው።ስለሆነም የኑሮ ውድነቱ የሚፈጥረውን ጫና ለመቋቋም ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን በማጠናከር መልካም እሴቶችን ለክፉ ጊዜ ማለፊያነት መጠቀም ይገባል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ የመረዳዳት ባህል ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አስፈላጊ ነው።‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› በሚባለው ብሂል ከተግባባን ሰው የሌለበት ኑሮ ደግሞ ከሀገር እንደሚያጎድል እንስማማለን።ስለሆነም ገንዘብ ያለው ሲበላና ሲጠጣ፤ ገንዘብ የሌለው ደግሞ እየተራበና እየተጠማ እንደሆነ ማስታወስ አለበት።ብዙ ወገኖቹ እየተቸገሩ ብቻውን በልቶ ብቻውን እየኖረ ያለ ሰው ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› ብሎ ቢናገር ንግግሩ ከቀልድና ሹፈት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነውን የመረዳዳት ባሕል ከበዓል ሰሞን ቀናት በማሻገርና ዘላቂ በማድረግ የመረዳዳት ባሕላችን ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ያስፈልጋል።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም