ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመቱ መሪ እቅድ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ብላ ከያዘቻቸው አምስት ዘርፎች መካከል ማእድን አንዱ ነው። ይህ ወሳኝ ዘርፍ ለልማቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እንዲሁም ለልማቱ የሚያስፈልጉ እንደ ውጭ ምንዛሬ ያሉትን ሀብቶች ለማግኘት በእርግጥም ወሳኝ ነው።
በሌሎች ሀገሮችም ቢሆን ይህ ዘርፍ ወሳኝ ነው። ከዘርፉ የበለጠ ለመጠቀም ያደጉት ሀገሮች ሆኑ በሀገራቸው ያለውን ማእድን ከማልማት ጎን ለጎን የሌሎች ሀገሮችን ማእድን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ዕርብርብ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ የሀገራቸውን የማእድን ሀብት አስቀምጠው የሌሎች ሀገሮችን ማዕድን ሲቀራመቱ ነው የሚታዩት።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሀገሮችን የጥሬ እቃ ፍላጎት ከሚያሟሉ ግብአቶች ማዕድን በሁለተኛ ደረጃ ይይዛል። ዛሬ በስፋት የሚከናወነው የመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዲሁም ለግንባታው ከሚውሉ ዋና ዋና ግብአቶች ሲሚንቶና ብረት ይጠቀሳሉ፤ ለትራንስፖርቱ ዘርፍና ለሀይል አማራጭነት ደግሞ ነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝና የድንጋይ ከሰል ይፈለጋሉ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነት ሲታሰብ የአፈር ማዳበሪያ፣ ለእዚህ አገልግሎት የሚውሉ ፖታሽ፣ ፎስፌትን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ግብዓቶች፣ ወዘተ ከተፈጥሮ ሃብት የሚገኙ ናቸው።ይህ እንግዲህ ጥሬ አቃ ብቻን የተመለከተ ነው። በዚህ ላይ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉ እንደ ወርቅ፣ ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮች፣ወዘተ የሚገኙት ከምድር ውስጥ ነው።
እነዚህን ማእድናት ገዝቶ መጠቀም በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ፈተና ነው፤ ለማልማት ቴክኖሎጂ፣ የሰለጠነ የሰው ሀይል፤ ፋይናንስ፣ የመንግስት ቁርጠኛነት፣ አደረጃጀት ወሳኞቹ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን ሀገሮች የአቅማቸውን ያህል ማአድናቱን ለማስጠናትና ለማልማት ጥረት ያደርጋሉ።
ወደ ዝርዝር ስንመጣ ደግሞ ለማዕድን ልማት ወሳኝ ከሆኑት መካከል በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣በቴክኖሎጂ የተደራጀና የማዕድን ምርመራዎችና ትንታኔዎች የሚሰጥበት ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ አንዱ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ከምድር ተቆፍሮ የሚወጣው ማዕድን በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች፣ መጠናቸውና ጥራታቸው በቤተ ሙከራ (ላቦራቶሪ) በፍተሻ መለየትና መተንተን ይኖርበታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ካላለፈ በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ጥሬ ማዕድንና የማዕድን ውጤት ለማቅረብ እንደሚያስቸግር፣ በተመራጭነትና በተዓማኒነት ግብይቱ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ባለሙያዎቹ ያስገነዝባሉ።
ሥነ ምድር የተመለከቱ ጥናታዊ ምርምሮችና መረጃዎችን የመሰብሰብና የመተንተን ስራ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን ይኖርበታል። በዚህ መልኩ የተደራጀ ቤተ ሙከራ ማቋቋም ብቻውን በቂ እንዳልሆነም እንዲሁ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ። በላቦራቶሪ ውስጥ ያለፈ የማዕድን ፍተሻ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚኖረው የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ISO accreditation) ሊኖረው እንደገባም ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ ከምድር በረከት አንዱ የሆነው የማእድን ሀብቷ በኢኮኖሚው ውስጥ ላቅ ያለ ድርሻ እንዲኖረው ዘርፉ እንዲነቃቃ በአዲስ አደረጃጀት(ሪፎረም) መጠነሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ለማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚው ወሳኝ ለሆነው በቤተ-ሙከራ ውስጥ ለሚከናወነው የማዕድን ምርመራና ትንተና ስራ ትኩረት ሰጥታ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነችም ነው። በዚህ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረትም ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የተቋቋመውን የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ዘመኑ ከሚጠይቀው አደረጃጀት ጋር እንዲራመድ በማድረግ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የጂኦሳይንስ ቤተ-ሙከራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢጃራ ተስፋዬ ስለቤተ ሙከራው የእስካሁን እንቅስቃሴና በዘመናዊ አደረጃጀት የተሻለ ሥራ ለመሥራት እየተደረገ ስላለው ጥረት ሲገልጹ፣ በቅድሚያ በቤተ-ሙከራ ክፍሉ የሚከናወነው በመሬት ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን መመርመርና መረጃዎችን ማመንጨት ነው ይላሉ።
ቤተ ሙከራው ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉ በውስጡ የተለያዩ አደረጃጀቶች ወይንም ክፍሎች አሉት። ክፍሎቹም የፊዚካልና ሚኖሮሎጂ፣ ጂኦኬሚካል፣ የሳይንቲፊክ መሳሪያዎች ጥገና ክፍሎች ናቸው። ከነዚህ ውስጥም የጂኦኬሚካል ክፍል የድንጋይ ወይንም የአፈር (rock or soil) እና ተመሳሳይ የሆኑ ናሙናዎችን ይመረምራል። የሚከናወነው የምርመራ ሥራም ማዕድኑ በውስጡ የያዘውን ንጥረ ነገር ለመለየት ያስችላል።
ቢዘህ ክፍል በተጨማሪ የወርቅ ማዕድን ምርመራ ሥራ የሚከናወን ሲሆን፣ የወርቅ ጥራትና ካራት በምርመራ ይለበታል። ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ውክልና የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወርቅ ማዕድን አምራቾች የሚረከበው ወርቅ በቤተ ሙከራ ፍተሻ ያለፈ መሆን ይኖርበታል።
የወርቅ ማዕድን ልማት በሚከናወንባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የጥራት ምርመራን ተደራሽ ለማድረግ የምርመራ ላቦራቶሪ ማቋቋም ተችሏል። እነዚህ በየአካባቢው ተቋቁመው የምርመራ አገልግሎት የሚሰጡት ፍቃድ ካላቸው ባህላዊ የወርቅ አልሚዎች የሚቀርበውን የወርቅ ማዕድን ነው። ቤተ ሙከራውን ማደራጀቱንና ባለሙያዎችንም የማሟላቱ ሥራ የተከናወነው በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ነው። በየአካባቢው የሚከናወነው የወርቅ ምርመራ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ወርቁ ወደ ማዕከል መጥቶ ግዥው ይፈጸማል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚቀርበውን የወርቅ ግዥ የሚፈጽመው በዚህ ሂደት ነው። የወርቅ ማዕድን ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ላይ ምርመራ እንዲከናወንባቸው የተለዩት 13 ናቸው፤ ዋና ዋና ከሚባሉትም ኦሮሚያ ክልል ጉጂ፣ ሻኪሶ፤ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ፣ ግልገል በለስ፣ ሲዳማ ክልል ሀዋሳ፣ ጋምቤላ ክልል ዲማ ይጠቀሳሉ። ከተለዩት 9ኙ በሥራ ላይ ናቸው። በትግራይ ክልል ሽሬ በአፋር ክልል ደግሞ ኮነባ በተባሉት አካባቢዎች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ሥራው ለጊዜው ተቋርጧል።
በቤተ-ሙከራው ስለሚደረግ የምርመራ ዘዴ አቶ ኢጃራ ለአብነት በወሰዱት አንድ ክፍል ተመስርተው ሲያስረዱ እንደገለፁት፤ ምርመራው ፊዚካልና ዲስትራክቲቭ ይባላል። ዲስትራክቭ የሚባለው የምርመራ ዘዴ የምርመራው ውጤት ከታወቀ በኃላ ለግብዓትነት ጥቅም ላይ የዋለው ናሙና መልሶ አይገኝም። ‹‹ነን ዲስትራክቲቭ›› የሚባለው የምርመራ ዘዴ ደግሞ ምርመራው ከተካሄደ በኃላ ናሙናው ይኖራል። አብዛኛው ምርመራ ከተካሄደ በኋላ መጠኑ ቢለያይም ናሙናው የሚገኝ በዚህ ዘዴ ነው። የሳይንቲፊክ መሳሪያ ጥገና ክፍሉም ለምርመራ ክፍሉ እጅግ አጋዥ ነው።
የምድር ሀብቶች ወርቅና የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ብቻ አይደሉም። እንደ ብረት፤ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ በመሳሰሉት ላይ በምን ሁኔታ ምርመራ እንደሚካሄድ አቶ ኢጃራ ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፣ በነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ላይም በተመሳሳይ ምርመራ የሚካሄድበት እድል ቢኖርም ለጊዜው በነዳጅ ላይ እየተሰራ አይደለም ሱሉ መለሱልን። ከነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ውጭ ባለው ላይ ምርመራ እንደሚከናወንና በአብዛኛው ደግሞ ከድንጋይ አለት፣ ከአፈር ጋር በተያያዙት ማዕድን ነክ በሆኑት ላይ ምርመራው እንደሚከናወን አስረድተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የማዕድን ምርመራ ሥራ በመሰክም የተደገፈ ነው። ኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ግን አሁን እያከናወነ ባለው ተግባር ምርመራውን የሚያከናውነው የሚመጣለትን ናሙና በመመርመር ነው። በዚህም ተልእኮውን እየተወጣ ይገኛል። የመስክ የምርመራ ዘዴ ለምን እንደማይካሄድ ሲገልጹም አንዱ ክፍተት የማዕድን ልማቱ በሚከናወንበት ስፍራ ተገኝቶ ምርመራ ማከናወን አለመቻል እንደሆነ ነግረውናል። ይህን ማድረግ ያልተቻለው የአቅም ውስኑነት በመኖሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የቤተ-ሙከራ ቁሳቁስ በግዥ ከውጭ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። በዘርፉም የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ከመሳሪያው ጋር ለመተዋወቅም ስልጠናው በውጭ ሰዎች መሰጠት ይኖርበታል። ለቤተ-ሙከራ የሚሆን ህንጻ ግንባታን ለማከናወንም ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል። የማዕድን ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች በቁሳቁስ የተደራጀ ቤተ-ሙከራ ለማቋቋም ከፍተኛ በጀት ያስፈልጋል። አሁን ባለው አሰራር ከወርቅ ማዕድን ውጭ ያሉት ናሙናዎችን በማስመጣት ነው የምርመራ ሥራው የሚከናወነው ሲሉ ያብራራሉ።
“የቤተ ሙከራ ስራውን ተደራሽነትን ለማስፋት አቅም የሚጠይቅ ቢሆንም በዚሁ መቀጠሉ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት የሚያስገኝ ባለመሆኑ የግዴታ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ኢጃራ፤ በቀጣይ የመስክ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደታሰበበትና የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል።
የማዕድን ዘርፉ በሀገር የምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ሚና እንዲኖረው በሚደረገው ጥረት አሁን ባለው አሰራር የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት አቅሙ በምን ደረጃ ላይ ነው? የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ ኢጃራ፣ ‹‹በዚህ ወቅት የማዕድን ምርመራ ፍላጎት ጨምሯል። ይህም ተደራሽነትን ማስፋትን ይጠይቃል” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል። አገልግሎቱም ቢሆን በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ መሰጠት ያለበት መሆኑ የግድ እንደሆነም ጠቅሰው፤ አሁን በተሻለ አደረጃጀት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
ኢንስቲትዩቱ ለራሱ ተቋም ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በማዕድን ልማት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ አገልግሎት እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት። በህገወጥነት በሚያዙ ማእድናት ላይ የምርመራ ትእዛዝ ሲቀርብለትም መርምሮ መረጃውን እንደሚሰጥ ነው አቶ ኢጃራ ያስረዱት። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር ሲፈልጉም ኢንስቲትዩቱ ክፍት እንደሆነና ከዩኒቨርሲቲ ለተግባር ልምምድ የሚላኩትንም ተቀብሎ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የቤተ-ሙከራው መኖር ወሳኝ ከሆነ በምን አቅም ነው መገንባት ያለበት የሚል ጥያቄም አቅርበንላቸው በሰጡት ምላሽ፤ ላቦራቶሪው በዘመናዊ ቁሳቁስና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጀት ወይንም ማሳደግ ግዴታ መሆኑን እስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የላቦራቶሪው የምርመራ ውጤት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ISO accreditation) ሊኖረው ይገባል ይላሉ። እስከ አሁን ባለው አሰራር የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ባለመኖሩ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ አንዳንድ ደንበኞችም የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ወዳላቸው ሀገሮች እንደሚሄዱም አመልክተዋል። አሁን ግን ክፍተቱን ለመሙላት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ከአቅም ማጎልበቻ ዘዴዎች አንዱ በዘርፉ ተሞክሮ ካላቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር መሥራት ነው። በዚህ ትብብር ሀገር ውስጥም ወደ ውጭ ሀገር በመሄድም ተሞክሮ ለመቅሰም ጥረት ይደረጋል። በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ስለመኖራቸው አቶ ኢጃራን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ ፣ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እንቅስቃሴ ሲኖር፣የሥራ መሣሪያ ድጋፍ እንደሚደረግ ፣በቅርቡም በማዕድን ሚኒስቴር አማካኝነት ከአንድ የካናዳ ፕሮጀክት ለላቦራቶሪ ሥራ የሚያግዝ የመሣሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል። በድጋፍ ከተገኙት መሣሪያዎች አብዛኛዎቹ ለከበሩ ማዕድናት ምርመራ የሚውሉ እንደሆኑም አመልክተዋል። እንዲህ አይነት ድጋፎች አልፎ አልፎ እንደሚገኙም ነው የጠቀሱት።
የጂኦሳይንስ ቤተ-ሙከራ በአፍሪካ ደረጃ በጥሩ አደረጃጀት የሚጠቀስ እንደነበርም አቶ ኢጃራ አስታውሰው፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ስም መጓዝ ባለመቻሉ ነው በዚህ ወቅት ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ያልቻለው ይላሉ። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ለዘርፉ ይሰጥ የነበረው ትኩረት አነስተኛ መሆን አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጸሉ። በዚህ የተነሳም የተሻለ የደመወዝ ክፍያና ጥቅማጥቅ ፍለጋ የባለሙያዎች ፍልሰት መኖሩ ለመዳከሙ አንዱ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ወቅቱን የሚጠይቅ ለምርመራ ሥራ የሚያግዝ መሳሪያ ግዥ አለመኖርም ሌላው ክፍተት እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
“በአሁኑ ጊዜ በጂኦሳይንስ ቤተ-ሙከራ ውስጥ በአብዛኛው የሚያስፈልጉት ባለሙያዎች ኬሚስትና ጂኦሎጂስት ናቸው” የሚሉት አቶ ኢጂራ፣ በዚህ ዘርፍ የተመረቁ ባለሙያዎች ቅጥር እንደሚፈጸምም ነው የገለጹት። አዳዲስ ሙሩቃን ሲቀጠሩ ከሙያው ጋር እንዲተዋወቁና የተሻለ አፈጻጸም እንዲያሳዩ ተጨማሪ ስልጠና ለመስጠት አንድ ክፍል መደራጀቱንም ነግረውናል።
አቶ ኢጃራ እንደሚሉት፤ ጂኦሳይንስ ቤተ-ሙከራ መኖሩ ለማእድን ልማቱ መቀላጠፍ ወሳኝና አስፈላጊ ቢሆንም፣ በተሻለ አደረጃጀት ላይ መገኘት ይኖርበታል። ይህንንም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመፍታት በተለይም ዩኒቨርስቲዎች በሁለተኛ ዲግሪ ባለሙያዎችን እንዲያፈሩ ስምምነት ላይ በመደረሱ ወደ ትግበራ ተገብቷል። የውጭ ስልጠናም ጎን ለጎን እንዲመቻች ጥረት እየተደረገ ነው።
ቤተ-ሙከራው በተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ አሁን ካለበት በተሻለ የህንፃ ግንባታ እንዲከናወን በእቅድ መያዙንም ጠቅሰው፣ በረጅም ጊዜ አነዚህን እቅዶች በማሳካት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደታሰበ ጠቁመዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2015