ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መገኛ ናት። እነዚህ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በርካታ ሀገር በቀል ባህሎች፣ እውቀቶች እና ስርዓቶች ያላቸው እንደመሆናቸው ሀገሪቱም አያሌ ባህሎች፣ እውቀቶችና ስርአቶች ይገኙበታል።
እያንዳንዱን ብሄረሰብ ብንመለከትም እንዲሁ በርካታ ባህሎች፣ ስርአቶችና ሀገር በቀል እውቀቶች አሉት። የሀዲያ ብሄር ቱባ ባህል፣ ስርአትና ሀገር በቀል እውቀት ካላቸው ብሄረሰቦች አንዱ ነው። ከብሄረሰቡ ባህላዊ ስርዓቶች መካከል “ዎገና’’ የተሰኘው ባህል ይጠቀሳል። ዎገና የሀዲያ ብሄረሰብ ከብት የማስቆጠር ስርዓት ነው። በዛሬው ሀገርኛ አምዳችንም የዎገና ስርዓት ምንነትን፣ የስርዓቱን አፈጻጸም እንዲሁም ፋይዳውን እንዳስሳለን።
አቶ ካሳሁን አባይነህ በአማርኛ ቋንቋ ስነጽሁፍና ፎክሎር የትምህርት መርሃ ግብር ሁለተኛ ዲግሪ ለማግኘት “ባህላዊ የከብቶች ቆጠራ (ዎገና) ስርዓት ክዋኔ በሀዲያ ብሄር” በሚል ርዕስ በሰሩት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደጠቀሰው፤ “ዎገና” ማለት አንድ ከብት አርቢ ከብቶቹ ከመቶ በላይ ወይም ከሺህ በላይ ሲሆኑለት ድግስ በመደገስ ሰዎች አውቀውለት ከሀብቱ ጋር በተያያዘ የክብር ማዕረግ ስያሜ የሚያገኝበትና የሚረጋገጥበት ስርዓት ነው።
በዎገና ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሃፍ በመጻፍ ላይ የሚገኙት አንትሮፖሎጂስት ተፈራ ጋቦሬ እንደሚሉት ደግሞ፤ “ዎገና” “ዎኦ” እና “ገና” የሚሉ ሁለት የሀዲይሳ ቃላት ተጣምረው የፈጠሩት ቃል ሲሆን፤ “ዎኦ” ውሃ ሲሆን “ገና” መርጨት የሚል ትርጉም አለው።
ስለዚህ ዎገና ማለት ከብቶች ላይ ውሃ፣ ማር እና ወተት በጥብጦ በእርጥብ ሳር እየነከሩ የመርጨት ስነ ስርዓት ነው። ዎገና ስርዓት በሁለት ይከፈላል፤ የከብት ብዛት ከአንድ መቶ በላይ ሲደርስ የሚፈጸመው ስርዓት “ጢቤ ዎገና” ሲባል፤ ከሺህ በላይ ሲደርስ የሚፈጸመው ደግሞ “ኩማ ዎገና” ይሰኛል። ከ100 በላይ ያስቆጠረው አርቢ “ጢባሞ” ሲባል፤ ከአንድ ሺህ በላይ ያስቆጠረው አርቢ ደግሞ “ኩማሞ” ተብሎ ይጠራል።
አንድ ከብት አርቢ ዎገና ስርዓት ለመድረስ ከ20 እስከ 40 ዓመት እንደሚፈጅበት የሚናገሩት አቶ ተፈራ ጋቦሬ፤ የዎገና ስርዓትን ለመፈጸም ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ይገልጻሉ። የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ አንድ ከብት አርቢ ያረባቸው ከብቶች ቁጥር ከ100 በላይ መድረስ አለበት። ይሁንና የከብቶቹ ቁጥር ከመቶ ስለተሻገረ ብቻ “የዎገና’’ ስርዓትን ማዘጋጀት አይችልም። የከብቶቹ ቁጥር መቶ እና ከዚያ በላይ መድረሱን በሚያረጋግጡት በ“መሃራኖ” መረጋገጥ አለበት።
“መሃራኖ” ማለት ከዚህ ቀደም ከ100 በላይ ከብት ያስቆጠሩ ከብት አርቢዎች ማህበር ነው። እንደ አቶ ተፈራ ማብራሪያ በሀዲያ ዞን ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ800 በላይ የሚሆኑ መሃራኖ በህይወት አሉ። እነዚህ “መሃራኖ” በሶስት ማህበር ተደራጅተው ይገኛሉ።
እንደ አቶ ተፈራ ማብራሪያ ፤ ከዚህ ቀደም ስርዓቱን ያስፈጸሙት መሃራኖ የአርቢው ከብት ለዎገና ስርዓት ደርሷል ወይ የሚለውን የማጣራት ስራ ይሰራሉ። የማጣራት ስራውን በግልጽ እና በስውር ያከናውናሉ። ከብቶቹን ገዝቶ ነው ወይስ ራሱ አርብቶ ነው፤ ምንጩ ከየት ነው? የሚለውን የማጣራት ስራ ይሰራሉ። ራሱ አርብቶ መቶ እና ከዚያ በላይ ያደረሰ ካልሆነ ስርዓቱ አይፈጸምለትም።
አጣሪዎቹ የከብቶቹን ቁጥርና የአረባብ ሂደቱን ካጣሩ በኋላ የዎገና ስርዓት ለማካሄድ መሟላት ያለባቸው ሌሎች ነገሮችንም ያጣራሉ። ከሚያጣሯቸው ነገሮች መካከል ከከብቶች እርባታ ጎን ለጎን በእርሻ ስራው ያለው እንቅስቃሴና የጓሮ አያያዝ፣ የሚኖርበት ቤትና የቤቱ ግቢ ሁኔታ፣ በደጁ ላይ ጥላ የተከለ መሆን አለመሆኑ፣ በምግብ ራሱን የቻለ መሆኑ፣ እሱ እና ባለቤቱ ለጉዞ የሚጠቀሙባቸው በቅሎና ፈረስ እንዳለውና እንደሌለው ያረገጋግጣሉ።
የማጣራት ስራው እላይ በተጠቀሱት ብቻ አያበቃም። እጩ መሃራንቾና ቤተሰቡ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለው መስተጋብርም ይጣራል። እጩ መሃራንቾ እና ባለቤቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብር፣ በማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ፣ ሀቀኝነታቸው፣ አስታራቂነታቸው፣ የተቸገረን የመርዳት ሁኔታቸው፣ ወዘተ ምን እንደሚመስል የአካባቢውን ማህበረሰብ በመጠየቅ ያጣራሉ።፡ እነዚህን ነገሮች ከተረጋገጡ በኋላ አርቢው የዎገና ስርዓት ለማዘጋጀት ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ የዎገና ስርዓት እንዲያዘጋጅ ይሁንታ ይሰጠዋል።
በደጋ አካባቢ የግጦሽ መሬት እጥረት ያለ ሲሆን አርቢዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ከብቶቻቸውን ይዘው የሚያሳልፉት በዞኑ ውስጥ እና በአጉራባች ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች ነው። የወገና ስርዓት ለመፈጸም ይሁንታ ሲያገኙ ለከብቶቹ በረት በማዘጋጀት ከቆላማ አካባቢዎች ወደ ደጋ እንደሚያመጡ አቶ ተፈራ አብራርተዋል። ከብቶቹ ከቆላ አካባቢ ወደ ደጋ ከተመለሰ በኋላ ድግሱ ይጀመራል። ከሳምንት በኋላ ስርዓቱ ይፈጸማል።
እንደ አንትሮፖሎጂስት ተፈራ ገለጻ፤ በወግና ስርዓቱ ላይ በቅርብ እና በሩቅ የሚገኙ የሁሉም ቤተሰቦች ይሳተፋሉ። ስርዓቱ ላይ የሚሳተፉ፣ ስርዓቱን የሚፈጽሙትና ቤተዘመዶች በዋዜማው ይመጣሉ። ቤተዘመዶች እና ተጋባዝ እንግዶች በቡድን በቡድን እየሆኑ ሲመጡ የደስታ መግለጫ የሚሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘው ይመጣሉ። ያልተኮላሸ በሬ፣ ማር፣ ቅቤ፣ወጪታ ይዘው እየጨፈሩ እና ጡሩንባ እየነፉ ወደ ስፍራው የሚሄዱት።
ሁሉም በቡድን በቡድን ይዘው የመጡትን በሬ ለሰውዬው ካስረከቡ በኋላ ይመርቃሉ። ከዚያም በሬውን በማረድ የተወሰነውን ብልት እጩ መሃራንቾ ቤት በማስገባት የተቀረውን ደግሞ ወደተዘጋጀላቸው ድንኳን ይዘው ይሄዳሉ። የመጣው ቡድን ራሱን እያስተናገደ ይበላል፤ይጠጣል። ሌሊቱን የተለያዩ ጭፈራዎች ይደረጋሉ። ከዚህ ቀደም ከብቶቻቸውን ያስቆጠሩ መሃራኖ በእለቱ ከሌሎች ሰዎች ጋር አይገናኙም። ለብቻቸው አንድ ቤት ውስጥ ነው የሚሆኑት።
የወገና ስርዓቱ የሚካሄደው ንጋት ላይ ነው። ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ቤተዘመዶች እየጨፈሩ ከብቶችን እየነዱ ወደ ወንዝ እንደሚሄዱ የጠቆሙት አንትሮፖሊጂስት ተፈራ፤ ወንዙ ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጥ መሆኑን በቅድሚያ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ከብቶቹ ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት ሰውም ሆነ የሌሎች ሰዎች እንስሳት እንዲያቋርጧቸው አይፈቀድም። የዎገና ስርዓት ሳይካሄድ ወንዙን ሌላ ሰው ወይም የሌላ ሰው እንስሳ ከተሸገረ የሰውዬው ሀብት ላይ ጥላ ያጠላበታል ተብሎ ይታሰባል። ወንዙን ቀድሞ የተሻገረ ሰው ሀብቱን ይዞ ይሄዳል ተብሎ ይታሰባል። የዚያን ሌሊት ከተቻለ አውሬዎች እንኳ ወንዙን እንዳይሻገሩ ቤተሰቡ መከላከል ይኖርበታል ይላሉ።
አንትሮፖሎጂስት ተፈራ እንዳሚናገሩት፤ ዋናው የወገና ስርዓት በሚካሄድበት ዕለት ንጋት ላይ የቤቱ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ አንድ ጥጃ ተሸክሞ ከከብቶች በረት ይወጣል። ጥጃውን ይዞ ሲወጣ ከብቶች ተከትለውት ከበረት ይወጣሉ። ጥጃውን የያዘው ልጅም ወደ ወንዙ ይሄዳል። እጩ መሃራንቾ እና ሚስቱም ወደ ወንዝ ይሄዳሉ። ወደ ወንዙ ሲሄዱ ዘመድ አዝማድ ከቧቸው ይጨፍራል ይሸልላል፣ ያቅራራል። ከብቶቹ ወደ ወንዙ ገብተው ወንዙን ሲሻገሩ ባል እና ሚስቱ ውሃ ውስጥ ቆመው ውሃ፣ ማር እና ቅቤ የተቀላቀለበት ፈሳሽ ከብቶች ላይ ይረጫሉ። ስርዓቱ ሲከወን እልልታውና ድራንቻ ይቀጥላል።
ወንዝ ላይ የሚካሄደው የዎገና ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ልክ ወደ ወንዙ ሲኬድ እንደተደረገው ሁሉ ባልና ሚስቱን አጅቦ ጭፈራ፣ ሽለላ እና ቀረርቶ ይደረጋል። ከወንዝ ወደ ቤት ሲመለሱ “መሃር እዮና” የሚል እና “ሸምበለለዮኒሄ” የሚሉ ባህላዊ ጭፈራዎች ይጨፈራሉ። “መሃር እዮና” ማለት ሹምት ይስማማህ፤ ወይም ሹመት ያዳብር የሚል ትርጉም ሲኖረው፤ “ሸምበለለዮኒሄ” ማለት ደግሞ ሁሉ ሞልቶ፣ ሁሉ ተትረፍርፎ ማለት ነው።
ስርዓቱ ከወንዝ መልስ ቤት ውስጥም ይቀጥላል። ከወንዝ መልስ ባልና ሚስቱ እቤት መሶሶ ስር እንዲቀመጡ ይደረጋል። አባዎራውና ባለቤቱ መሰሶ ስር ከተቀመጡ በኋላ ከዚህ ቀደም ክብት ያስቆጠሩ መሃራኖ እና አበጋዙዋ ወደ ቤቱ ይገባሉ። መሃራኖ እና አበጋዙዋ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ አንድ ወይፈን ይቀርብላቸዋል። ከሰውዬው ጎሳ የተመረጡ ሽማግሌ በወይፈኑ ጀርባ ላይ ለምለም እርጥብ ሳር በማድረግ ይመርቃሉ። ምርቃቱ ከተካሄደ በኋላ ወይፈኑ ይታረዳል። ከታረደ በኋላ ነፍሱ ሳትወጣ የወይፈኑ “ሀንጩፋ” (የመራቢያ አካል) ተቆርጦ ይወጣል።
አቶ ተፈራ እንዳሉት፤ ከወይፈኑ ስጋ ክትፎ ተዘጋጅቶ፣ ቅቤ በብዛት እየተጨመረበት አበጋዞች እና መሃራኖ ይበላሉ። ማር እና ብርዝ ይቀርብላቸዋል። አስቆጣሪዎቹ ባልና ሚስቱም ይስተናገዳሉ። በልተው ጠጥተው ከጠገቡ በኋላ ስርዓቱን ይፈጽማሉ።
ስርዓቱን የሚፈጽሙት በፊት ማዕረጉን የተቀበሉ አበጋዙዋና መሃራኖ ናቸው። እነዚህ መሃራኖ ስርዓቱን ለመፈጸም ከታረደው ወይፈን “ደልቾ” (ሻኛ)፣ “ኤድራሳ” (ፍሪምባ)፣ “ሚዳዶ” (ጎድን)፣ “ሀንጩፋ” (የዘር መተላለፊያ) ይቀርብላቸዋል። እነዚህን ወደ አስቆጣሪው እና ባለቤቱ ይዘው ይቀርቡና በቅድሚያ ለአስቆጣሪው ደልቾ በጥርስ ያስነክሱና በቢላ ይቆርጣሉ። በመቀጠል ኤድራሳ በመቀጠል ደግሞ ሚዳዶ ያስነክሱና በቢላ ይቆርጣሉ። ከዚያ በመቀጠል ለሚስቱም በተመሳሳይ በጥርሷ በማስነከስ ይቆርጣሉ። በማስከተልም ሀንጩፋውን በአስቆጣሪው ቀኝ እጅ ላይ ያስገባሉ። የሚስቱ ደረት ላይ ደግሞ ከወይፈኑ ሆድ እቃ የተወሰደ ሞራ ይለጥፋሉ። በመጨረሻም ስርዓቱን ያስፈጸሙት መሃራኖ እና አበጋዞች አስቆጣሪውን መሃራንች ጢባሞ ወይም አበጋዝ ጢባሞ ብለው ይሰይሙታል። ሚስቱን ደግሞ “ጊፍቴ” ይሏታል።
የስርዓቱ ፈጻሚዎች ስርዓቱን ሲያከናወኑ መሃር እዮና እና ሻዕሞና እያሉ ሲሆን፤ “መሃር እዮና” ማለት ሹመት ያዳብር እንደማለት ነው፤ “ሻዕሞና” ማለት ደግሞ ይቅናህ ክብር አይለይህ ማለት ነው። መሃራኖ እና አበጋዞች ስርዓቱን ከፈጸሙ በኋላ ተጠርተው የመጡ ቤተዘመዶችም ልክ እንደ መሃራኖ ሁሉ እንደ አመጣጣቸው በቡድን በቡድን በመሆን ስርዓቱን ይፈጽማሉ። ይዘው የመጡት ማር፣ ቅቤ እንዲሁም በዋዜማ ይዘው መጥተው ያረዱት በሬ ሻኛ፣ ፍርምባ እና ጎድን ይዘው በመምጣት መሃር እዮና እና ሸምበለለዮኒሄ እየጨፈሩ ስርዓቱን ይፈጽማሉ።
ይህም የሚደረገው መሃራኖ እና አበጋዙዋ ለአዲሱ አስቆጣሪው የሰጡትን ሹመት ማጽደቃቸውን ማረጋገጫ ነው። የወገና ስርዓት ተፈጽሞለት እውቅና ያገኘ ሰው በብሄሩ ይከበራል። ስብሰባዎችን በምርቃት ይከፍታል። አቶ ካሳሁን አባይነህ ሁለተኛ ዲግሪ ለማግኘት “ባህላዊ የከብቶች ቆጠራ (ዎገና) ስርዓት ክዋኔ በሀዲያ ብሄር” በሚል ርዕስ በሰራው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደጠቀሰው፤ በመጨረሻም “ወበጣ” አስቆጣሪውን እና ሚስቱን ገላ የማጠብ ስርዓት ይፈጸማል። ገላ የማጠቡን ስራ የሚሰሩት ቅርብ ቤተሰብ ናቸው። የወበጣ ስርዓት የሚፈጸመው አስቆጣሪው ወገና ስርዓት ለመፈጸም መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስርዓቱ እስከተፈጸመበት ባሉ ጊዜያት ካጋጠሙ ችግሮች ለማንጻት ነው።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሀገር በቀል እውቀት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ እያሱ ጥላሁን እንደሚሉት፤ የዎገና ስርዓት ሰው ጠንክሮ ከሰራ ከምንም ተነስቶ ባለመቶ ከብት መሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ዎገና ሀብት እንዴት ማፍራት እንደሚቻል ያሳያል። ከብት ከሚያስቆጥሩት ኢንተርፕሪነርሽፕን መማር ይቻላል። በሀዲያ አከባቢ ያላቸውን አነስተኛ መሬት ተጥቅመው እጥረት አለብኝ ብለው ሳይቀመጡ ሀብት ማፍራት መቻላቸው ጥንካሬያቸውን ያመለክታል።
ከብት አርቢዎች በሀዲያ ዞን ውስጥ ባለው የመሬት ጥበት ምክንያት ወደ አጎራባች ዞኖች በመሄድ ከብቶቻቸውን እንደሚያረቡ የሚጠቅሱት አቶ ኢያሱ፤ በተለይም ጊቤ ወንዝን ተሸግረው ወደ ጅማ፣ ወደ ዳውሮ በመሄድ ከብቶቻቸውን እንደሚያረቡ ይናገራሉ። አንዳንዶች ከብቶቻቸውን ይዘው እስከ ጋምቤላ እንደሚሄዱ በመጠቆም በተለይም ሰፊ መሬት እና ውሃ ወዳለባቸው አጎራባች አካባቢዎች በመሄድ በሰላማዊ መንገድ የተፈጥሮ ሀብትን በመጋራት ከብቶችን የሚያረቡበት እውቀት የሚደነቅ ነው ይላሉ። የተፈጥሮ ሀብትን ብቻ ሳይሆን ከብቶቹን እና ከከብቶቹ የሚገኘውን ተዋጽኦ ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር የሚጋሩበት መንገድ የሚበረታታ መሆኑንም በመጥቀስ፣ እነዚህ ከብት አርቢዎች ከአካባቢው አልፎ ለመሃል ሀገር ሰንጋዎችንም እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ ከብት አርቢዎቹ ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለከብት አርቢዎቹ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰት በሽታ ምክንያት ከብቶች ይሞታሉ። ባለ መቶ የነበሩ ሰዎች በአንዴ ባዶ እጃቸውን የሚቀሩበት ሁኔታ ያጋጥማል፤ መድሃኒት አይቀርብላቸውም። በመሆኑም መንግስት ለእነዚህ ከብት አርቢዎች ትኩረት መስጠት አለበት፤ መድሃኒቶችን ማቅረብ አለበት። አብዛኞቹ አርቢዎች ባሉባቸው የጊቤ በረሃ አካባቢዎች የመድሃኒት ማዕከላት ሊገነቡም ይገባል።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሮቹን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኢያሱ፣ የአከባቢውን ከብቶች ዝርያ በዘመናዊ ዝርያዎች ለመተካት እና አርቢዎቹ ብዙ ሳይንከራተቱ ምርትና ምርታማነታቸውን ከፍ ማድረግ እንዲችሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ዩኒቨርሲቲው የከብት እርባታ ማዕከል በማዘጋጀት የወተት እና ስጋ መጠናቸው ከፍ ያሉ ዝርያዎችን ለማበራከት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ተናግረው፣ ዩኒቨርሲቲው የኮርማ አገልግሎት በመስጠት የተሻሻለ ዝርያ ለማሰራጨት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2015