በሀገሪቱ የኑሮ ወድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ወድነት አሁን ላይ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አልቻለም። የአፍሪካ ዴቨለፕመንት ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በፈረንጆቹ 2021 ከነበረው 6 ነጥብ 1 ዕድገት ዝቅ ብሎ በ2022 ወደ 5 ነጥብ 6 ወርዷል ። የኑሮ ግሽበቱ ደግሞ በ2021 ወደ 26 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ብሏል ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኑሮ ወድነት ተከሠተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው የመግዛት አቅም መዳከም ነው። ከዚህ አንጻር በአገሪቱ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት፣ የምንዛሬ እጥረት፣ የትምህርት ቤት ክፍያዎች ማሻቀብና ሌሎችም ማኅበረሰቡን እየተፈታተኑ ከሚገኙት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
መንግሥት ከወዲሁ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ ቢሆንም የሸቀጦች ዋጋ ህዝቡ በሚጠብቀው መልኩ ሊወርድ አልቻለም። የአገራችን ገበያ የመጨመር እንጂ የመቀነስ ባህሪ እያሳየ አይደለም። የሸቀጦች ዋጋ መሽቶ በነጋ ቁጥር ጨምሮ ያድራል እንጂ ቀንሶ ሲያድር አይታይም ።
በየጊዜው በሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ደግሞ መዘዙ እንደ ቱባ ክር የሚመዘዝ በመሆኑ ብዙ ችግሮችን ይወልዳል። የግለሰቦችን የመግዛት አቅምን ከማዳከም አልፎ የተቋማትን አቅም እየፈተነ ይገኛል። ይህ እየሆነ ባለበት፤ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የፋሲካ በዓል ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።
በዓሉን ደግሞ ከቤተሰብ እስከ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ማክበር የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ እንደመሆኑ ዘመድ አዝማድ በዓሉን በጋራ የሚያከብረው ለቀኑ የሚሆኑ አልባሳትን ፣ ምግብ እና መጠጦች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አዘጋጅቶ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ ሁሉም እንደ አቅሙ በተለያየ መልኩ ቀደም ብሎ ይዘጋጃል። የበዓል ሸመታ ያደርጋል። በዚህም የተነሳ የበዓል ገበያው ይጦፋል። ይህ በራሱ ለበዓሉ አንድ ደማቅ ድባብ የሚፈጥር መሆኑ አይካድም።
ይሁን እንጂ በዓላት በደረሱ ቁጥር የሚደረጉ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪዎች ፤ በአገራችን አሁን ካለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ የሸማቾች ዋነኛ ሥጋት ከሆኑም ሰነባብተዋል። የበዓል ገበያን ከሚረብሹ ሀይሎች መካከል ደግሞ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የደላላ ጣልቃ ገብነት ነው።
በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በደላሎችና በተባባሪዎቻቸው የሚሠራጨው የዶሮ፣ የበግ፣ የፍየልና የዕርድ የበሬ ዋጋ የበዓሉን ድባብ ከመረበሹም በላይ፣ ሸማቾችና ነጋዴዎች ተሳስበው ግብይት እንዳይፈጽሙ ያግዳቸዋል። ይህን ተከትሎ የበዓል ገበያው ከወትሮው የተለየ መሆኑ ደግሞ ሌላ ተደራቢ ችግር ሆኗል ።
የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የፋሲካ በዓል ገበያውን አነሳን እንጂ ዋነኛው ጉዳያችን እሱ አይደለም። የበዓል ገበያውን ምክንያት ያደረጉት የዋጋ ጭማሪዎች ከበዓል በኋላስ ? የሚለው ነው። ምክንያቱም በአገራችን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ማየት የሚገባ አይሆንም።
ከበዓል በፊት 13 ብር የነበረው የአንድ እንቁላል ዋጋ በበዓል ገበያው ወደ 16 ብር ያድጋል ። በበዓል ግርግር የጨመረው የእንቁላል ዋጋ በአንድ ጊዜ ሦስት ብር እንደጨመረ አልያም ከዚያም በላይ በሆነ ጭማሪ በአዘቦትም ይቀጥላል ። ታዲያ መውጣት እንጂ መውረድ በማያውቀው የአገራችን የገበያ ሁኔታ ፤ የበዓላት መምጣት ከደስታ በላይ ሰቀቀንን እየፈጠሩ ይገኛል ።
መንግሥት የአቅርቦት ሰንሰለቱ በደላሎች ጣልቃ ገብነት ሳይታወክ ግብይት እንዲከናወን የቁጥጥር ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት ከችግሩ መገንገን፤ ሌሎችም ወቅታዊ ፖለቲካ ጉዳዮች አንጻር ብዙም ውጤታማ ነው ለማለት አይቻልም። በርግጥ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ሊኖር የሚችለው የመንግሥት፣ የአምራቹ ፣ የሸማቾችና የነጋዴው መስተጋብር አግባብ ሲኖር ነው። ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲችል ፤ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ሲላበስ ነው።
የንግዱ ማኅበረሰብ ከፍ ካለ ራስ ወዳድነት ሊወጣ፤ ስለ ሸማቹ ህብረተሰብ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል። ኃላፊነት የተሞላበት ሀገራዊ የግብይት ስርአት እንዲኖረው የራሱን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል። የበዓል ሰሞን ገበያ በርካታ ሸማቾች የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚዘዋወርበት በመሆኑ፣ ነጋዴዎች ከብዛት የተሻለ ትርፍ ስለሚያገኙ አላስፈላጊ ከሆነ የዋጋ ጭማሪ መታቀብ ይጠበቅባቸዋል። ማህበረሰቡም የጊዜውን ሁኔታ እና አቅሙን በሚመጥን መንገድ በአቅሙ ሸምቶ በዓሉን በደስታና በአንድነት ማክበር ይኖርበታል ።
መንግስትም ቢሆን በበዓል ገበያው የምርት እጥረት እንዳይከሰት እና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪዎች እንዳይኖሩ የተለዩ አማራጮችን ማቅረብ ይጠበቅበታል። ለአብነትም የበዓል ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በገበያዎች እና በዓሉን ታሳቢ በማድረግ በተከፈቱ ባዛሮች እንዲቀርቡ ማበረታታት ይኖርበታል። አሁን እንደተጀመረው ተፈላጊ ምርቶችን ከዩኒየኖች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከአርሶ አደሩ ጋር በመነጋገርና በስፋት ለሸማቹ ህብረተሰብ የሚቀርቡበትን አሰራር አጠናክሮ መቀጠል የግድ ይላል።
ከዚህ በተጨማሪ የበዓል ገበያውን ለማረጋጋት ከሚወሰዱ እርምጃዎች በተጓዳኝ በአገሪቱ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር ገበያን በዘላቂነት ማረጋጋት የሚያስችሉ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ዘላቂ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ያስፈልጋል። ምርትን በመሰወር የገበያ እጥረት በመፍጠር ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ አካላት ላይ የማያዳግሙ እርምጃዎችን በመውሰድ እነዚህ አይነት ያልተገቡ ልምምዶች መቋጫ እንዲያገኙ ማድረግም ያስፈልጋል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም