ጤናአዳም
በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ጤና አዳም ለሆድ ሕመም፣ ለተቅማጥ፣ ለጆሮ፣ ለልብ ሕመም፣ ለኪንታሮት፣ ለኢንፍልዌንዛና ከአንጀት መታወክ ጋር ለተያያዙ ህመሞች አገልግሎት ላይ ይውላል። የደረቀው ፍሬ ከተፈጨ በኋላ ተፈልቶ በመጠጣት ለተቅማጥ ሕክምና ሲውል፣ ቅጠሉ ከተንተከተከ በኋላ በውኃ ተደርጎ ለሕፃናት ሆድ ሕመም ይሰጣል። ተክሉ ተፈጭቶ ሲልም ደግሞ ለኪንታሮት በሽታ ይወሰዳል፡፡
በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ከተክሉ ተዘፍዝፎ የሚገኘው ፈሳሽ ለጉንፋን፣ ለጆሮ ሕመምና ለአንጀት መታወክ ይወሰዳል፡፡ የጤናዳም ሽታ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ጊንጦችን ለማራቅ ይጠቀሙታል፡፡ በአልጀሪያ ሰዎች ተክሉ ከተዘፈዘፈ በኋላ የሚገኘውን ፈሳሽ በጠብታ መልክ በአፍንጫ ይወስዳሉ። በመሆኑም ጤናአዳም እንደ ቀንድ አውጣና ሦስት አፅቄ ያሉ ነፍሳትን የማራቅ አቅም ስላለው በጓሯችን ቢኖር ተመራጭ ነው፤ እንዲሁም ለቁንጫም መድኃኒት ነው፡፡ የጤናአዳም የጤና ጥቅሞች ጤናአዳም በጡንቻ ላይ የሚያጋጥም ሕመምን፣ ውጥረትንና በወር አበባ ወቅት የሚያጋጥም ሕመምን የማርገብ ብቃት አለው።
መጠቀም ያለብን ግን የእፅዋት ባለሙያን በማማከር መሆን ይኖርበታል፡፡ በሻይ መልክ መጠቀም ለሽንት ቧንቧ፣ ለአንጀትና በአጠቃላይ ለደንደኔ ኢንፌክሽን መድኃኒት መሆን ይችላል። ጤናአዳም ለምግብ መመረዝ በተለይ ደግሞ ሳልሞኔላ የተባለውን ባክቴሪያና ሌሎችአደገኛ ተህዋስያን ሊከላከለን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ጤናአዳም የፀረ ባክቴሪያ ባሕሪ አለው። ይህ እጽ ነርቮችን የማረጋጋት ኃይል ማለትም የአራጌነት(sedative) ባሕሪ እንዳለው ጥናቶች የሳያሉ። በመሆኑም የእንቅልፍ ማጣት ችግር ሲያጋጥመን ብንጠቀመው ሊያረጋጋን ይችላል፡፡
ጤናዳም በአንዳንድ መርዛማ እንስሳት(ለምሳሌ በእባብ) ከተነደፍን ማርከሻ ይሆናል። ይኸውም የተነደፍነው የነርቭ ስርዓት ላይ እክል በሚፈጥሩ የመርዝ ዓይነቶች ከሆነ ነው፡፡ ጤናዳም በአንጓ ላይ የሚያጋጥም ብግነትን ሰከን የማድረግ ኃይል ስላለው ችግሩ ያለበት ሰው አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ በሻይ መልክ ቢጠጣ እፎይታን ሊያገኝ ይችላል፡፡ የጤናዳም ዘይት በዘመናዊው ዓለም ለሳሙናዎችና ለኮስሞቲክስ ምርቶች ለጥሩ መዓዛነት ጥቅም ላይ ይውላል። ይህ ዘይት መጠኑ ሲበዛ የመርዛማነት ባሕሪ ስላለው በቀጥታ በቆዳ ላይ በጥቅም ላይ መዋል የለበትም።
ነገር ግን ተመጥኖ ለቆዳ የተለያዩ ጥቅሞች እንዳስገኘ ጥናቶች ያሳያሉ። ይኸውም የፀረ-ፈንገስ ባህሪ ስላለውና ቆዳን የማጥራት አቅምም አለው፡፡ የጤናዳም የጎንዮሽ ጉዳት ከጤናዳም የሚወጣው ዘይት በሰውነት ላይ በቀጥታ ከተጠቀምን ሰውነት ውኃ ሊቋጥር እንዲሁም ሊቀላ ይችላል። በከፍተኛ መጠን ከተጠቀምነው ደግሞ የሰውነት መመረዝ ሊያስከትል ይችላል። በተለይ ደግሞ ፅንስ ያላቸው ሴቶች በከፍተኛ መጠን ከተጠቀሙት ፅንሳቸውን ሊያስወርድ ይችላል። እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የጨጓራ ሕመም ያስከትላል፡፡ ይህ በመሆኑ በዘመናዊው ዓለም የጤናአዳም የሕክምና አገልግሎቱ የተገደበ እየሆነ መጥቷል፡፡ ምንጭ፡- ሰርቫይቫል ኢንፎ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011