‹‹ለምንኖርባት ዓለም ኪራይ መክፈል አለብን›› በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ ለተጎዱ፤ ግራ ለገባቸው ፣ ጭልም ድንግዝግዝ ላለባቸው የብርታት፤ የጥንካሬ የተስፋ ምሳሌ ተደርጋ ትጠቀሳለች፤ የዛሬዋ የባለውለታ አምዳችን ባለታሪክ፡፡
በተለይም ደግሞ በባሎቻቸው ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ህይወት በመታደግና ለተቸገሩ ፈጥኖ በመድረስ ዝናዋ ከኢትዮጵያ ጣሊያን ብሎም አሜሪካ ድረስ የናኘ ብርቱ ኢትዮጵያዊ ሴት ናት፡፡ በአሜሪካ ምድር መንገድ የወደቁ ኢትዮጵያውያንን በመሰብሰብና የችግራቸውን ጊዜ እንዲሻገሩ በማድረጓም ‹‹የክፉ ቀን ደጀን›› የሚል ስያሜ አግኝታለች፡፡ ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ፡፡
ትውልዷም ሆነ እድገቷ ጎጃም፣ ደብረማርቆስ ነው። ለእናቷ የመጨረሻ ልጅ የሆነች ይህች ሴት ወላጅ አባቷን ግን ጨርሶ እንዳማታውቃቸው ትናገራለች። ትምህርት ያልቀመሱ እናቷ ከሻይ ቤት ጀምረው ባሳደጉት ሆቴላቸው ገቢ ነው አባትም እናትም ሆነው እሷንም ሆነ ወንድም እህቶቿን ለብቻቸው ማሳደጋቸውን ትገልፃለች፡፡
የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የሆነው ይሄው የሆቴል ንግድ ታዲያ የኋላ ኋላ ወላጅ እናቷን እንዳሳጣት ዶክተር መንበረ ትናገራለች። ልጆቻቸውን ለወግ ማዕረግ ለማብቃት እድሜያቸውን ሁሉ ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩት እኚሁ እናት በአንዲት በተረገመች የስቅለት ምሽት አንድ ሻምበል ከሌላ ደንበኛ ጋር በተፈጠረ አምባጓሮ የተተኮሰች ጥይት ሰለባ ህይወታቸውን አጡ። ከሁሉ የሚያስከፋው ይሄ ሁሉ አሳዛኝ ትእይንት ሲከናወን የአስር አመቷ ህፃን መንበረ በአይኗ በብረቱ የተመለከተች መሆኑ ነው። ይህ ሰቅጣጭ ግድያ ታዲያ መቼም ለልጅ አይደለም ለአዋቂም ቢሆን ይህ ምንያህል ከባድ እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም። እናም የባለታሪካችን ሌላኛውን የህይወት ምዕራፍ አሀዱ ብላ የጀመረችውም ያኔ ነበር፡፡ ከእናቷ ሞት በኋላ እንደማንኛውም ወላጆቹን እንዳጣ ህፃን ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ብዙ ችግሮችን ለመጋፈጥ ተገደደች፡፡
እንግዳችን ወ/ሮ መንበረ የእናቷን ህልፈት ተከትሎ እሷን የማሳደጉና መንከባከቡ በታላቅ እህቷ እጅ ላይ አረፈ፡፡ እናም በደብረማርቆስ ንጉስ ተክለሀይማኖት ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታተለች። በቀጣይም በወቅቱ አዲስ አበባ ኗሪ የነበረው ወንድሟ ዘንድ ተጠግታ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቀቀች።
ከፍተኛ የሆነ የጥበብ ፍቅር ስለነበራትም የቲያትሩን ዓለም ለመቀላቀል ሻተች፤ ሆኖም ታላቅ ወንድሟ ‹‹አንቺ የፋንታዬ ተገኝ ልጅ ነሽ፤ አዝማሪ ተብለሽ እንድታድጊ አልፈልግም›› የሚል መከላከያ በማቅረብ ጫና አሳደረባት፡፡ ይሁንና የወንድሟን ሃሳብ ‹‹አሻፈረኝ›› ብላ ወደምትወደው ሙያ ዘው ብላ ገባች፤ ለዚህም መንደርደሪያ ይሆናት ዘንድ በብዙ ልፋትና ድካም የትወና ሙያ ማሰልጠኛ ውስጥ ትምህርት ጀመረች። እናም ራስ ቲያትር፤ ሀገር ፍቅር፤ ብሔራዊ ቲያትር ቤቶች መድረክ ላይ በመሳተፍ ተዋናይ የመሆን ህልሟን እውን ማድረግ ቻለች።
የፍቅር ህይወቷም በዚህ ወቅት ነበር የተጠነሰሰው፤ የመድረክና የሙያ አጋሯ ከሆነው ሰው ጋር ተወዳጀች፤ ይሁንና የፍቅር ግንኙነታቸው እንደመጀመሪያው በአድናቆት፤ በሙገሳ አልዘለቀም፡፡ ይልቁኑም ዕለት ዕለት በአካላዊም ሆነ በስነ-ልቦናዊ ጥቃት የታጀበ ሆነ። የፍቅር አጋሯ የነበረው ነፃ የትምህርት እድል ወደ ጣሊያን ተጓዘ፡፡ ወጣቷ ተዋናይም የፍቅር አጋርዋ ያለበትን አጉል ባህሪ ‹‹እተዋለሁ›› ያለውን ቃል በማመን እና ሙያውንም ለማሳደግ ስትል ተከተለችው፡፡
ጣሊያን ሀገር ግን የጠበቀችው የትወና ሙያ ስኬት ሳይሆን አስቸጋሪ የትዳር ህይወት ሆነ። ትዳር የተቀደሰ ግንኙነት፤ ቤተሰብም የተከበረ ነው በሚል ለትዳሯ ቅድሚያ ለመስጠት ወስና የህይወትን መራራ ጎን ተጋፈጠች፡፡ ይሁንና ትዳር እንዳሰበችው የምታርፈበት ከመሆን ይልቅ የእሳት ወላፈን ሆኖ መልሶ ይለበልባት ጀመር፡፡
በተለይም የትዳር አጋሯ ምሎ ፤ተገዝቶ የነበረውን ክፉ ባህሪውን ሊተው ባለመቻሉ የጣሊያን ቆይታዋ ከፊቱ የባሰ ከባድ አደረገባት፡፡ የሰላም ቀናቶቿም ብዙ ቀናት መዝለቅ ባለመቻላቸው ኑሮዋን እንድትጠላ አደረጋት፡፡ ሀገር ቤት ሳለ ያደርግ እንደነበረው ዘወትር በውሃ ቀጠነ ሰበብ እየደበደበና እያስለቀሰ፤ ከፊትና ከኋላ በሲጋራ እያቃጠለ፤ ብሎም ወሲባዊ ጥቃቶችን ያደርስባት ቀጠለ፡፡ ይህም ስቃይ ውስጥ ከተታት፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ አብረን በሰላም እንድንኖር የምትፈልጊ ከሆነ ለእኔ ያለሽን ፍቅር ለማረጋገጥ ስትይ የፊት ሁለት ጥርሶችሽን በገዛ እጆችሽ አውልቀሽ ጠብቂኝ›› የሚል ለአዕምሮ የሚከብድ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
የዛሬዋ ባለታሪካችን ዶክተር መንበረ ይህ ቃል የማንቂያ ደውል ነው የሆነላት፡፡ ለሀገሩ ባይተዋር መጠጊያ አልባ መሆንዋ ሳያግዳት ‹‹ጨርቄን ማቄን›› ሳትል ለመውለድ ስድስት ቀናት ብቻ እየቀራት ብን ብላ ቤቱን ለቃለት ወጣች፡፡ እናም በሰው ሀገር ማረፊያዋ ቤተክርስቲያን ደጅ ሆነ፡፡ ሁሉ ሆድ የሚያባባውን ልቅሶዋን የተመለከቱት አባት ቀርበው አነጋገሯት፤ ችግሯንም ተረድተው በማዘር ትሬዛ በተከፈተ የሴቶች መጠለያ ውስጥ እንድትገባ አደረጉ፡፡ ከስድስት ቀናት በኋላም ከበርካታ የመንገድ ተዳዳሪዎች፤ የአዕምሮ ህመምተኞች መካከል ልጇን በሰላም ተገላገለች፡፡ ይሁንና የአራስ ወግ የማየት ለእሷ የቅንጦት ቅንጦት ነበር፡፡
ከወለደችበት ዕለት ጀምሮ ከዚህ ለመኖር አስቸጋሪ ከሆነው ሥፍራ ልጇን ማስወጣት የእለት ተእለት ሃሳቧ ነበር፡፡ ለሁለት ወራት ያህል በመጠለያው ከቆዩ በኋላ በአካልም በመንፈስም ታድሳ ነበርና ልጇንም ሆነ ራሷን ማቋቋም አላቃታትም። ልጇም ነፍስ እስኪያውቅ ድረስ በጣሊያን የሰው ቤት ሰራተኛነት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየሰራች ክርስቲያን የተባለ ወንድ ልጇን ለማሳደግና ለማስተማር በቃች።
ክርስቲያን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስ የጣሊያንን ምድር ለቃ ወደ አሜሪካ ተጓዘች። አሜሪካ ከነልጇ ከገባች በኋላም የጣሊያንኛ ቋንቋ ችሎታዋን በመጠቀም አንድ የጣሊያን ሬስቶራንት ውስጥ እንግዳ ተቀባይነት ተቀጥራ እስከ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅነት ደረሰች፡፡ ይሁንና ትሰራበት የነበረው ሆቴል በኪሳራ ምክንያት ለሽያጭ ሲቀርብ ግራ ተጋብታ ተቀምጣ ሳለ ለዓመታት ጠንካራ ሰራተኝነቷን ያስተዋለው አንድ ጣሊያናዊ ደንበኛቸው “ገንዘብ ላበድርሽና ሰርተሽ ክፈይኝ” የሚል ጥያቄ አቀረበላት፡፡ መንበረም ይህንን ከፈጣሪ የተላከ መልካም እድል ያለአንዳች ማወላወል ነበር የተቀበለችው፡፡ ጠንክራ በመሥራት ከጣሊያኑ ሰው ያገኘችውን ብድርም በጣም በአጭር ጊዜ መመለስ ቻለች። አሁን ላይ ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ የሳሉቴ ቪታ ሬስቶራንት ባለቤት ከመሆንም ባለፈ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል በመፍጠርም በሀገሩ መንግስት እውቅና ተችራለች፡፡
የብርቱዋ መንበረ ሌላኛው የህይወት ገፅታዋ ደግሞ እንደእሷ በአስቸጋሪ ሕይወት ምክንያት ለስደት የተዳረጉ፣ ሀገር እስከ መርዳት የደረሰ ከፍታዋ ነበር። የትናንትና ህይወቷና ቁስሏ ለዛሬ ብርታት ሆኗት ዛሬ ለሌሎች የምትተርፍ ሆናለች፡፡ ብሎም ከእናቷ የወረሰችውን ጥንካሬና ለሁሉ ደራሽነት በማስቀጠል የብዙዎቹን ህይወት ለመታደግ ችላለች፡፡
ህይወት በብዙ መልኩ የፈተነቻት ወ/ሮ መንበረ በመከራዎች ውስጥ እንድታሸንፍ የረዷትን ሰዎች በማሰብ አሁን ለዓለም መልሳ እየሰጠች ትገኛለች። በምትኖርበት አሜሪካ አቅመ ደካማ ሴቶችን፣ ቤት አልባዎችን፤ ደጋፊ የሌላቸውን ህፃናትንና አረጋውያንን ታግዛለች፤ ትረዳለች፤ በየወሩም ሆቴሏን ለምገባ ታውላለች፡፡
በተለይም በየዓመቱ አሜሪካውያኑ የሚያከብሩትን የምስጋና ቀን ምክንያት በማድረግ እስከ አንድ ሺ የሚሆኑ ችግረኞችን በሬስቶራንቷ ትጋብዛለች፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች ቀን ቤት አልባ ሴቶችን ሰብስባ ቀኑን በደስታ እንዲያሳልፉ ታደርጋለች፡፡ በተጨማሪም በአካባቢዋ ያሉ ወጣቶች በማገዝ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ተግባር ፈፅማለች፡፡
ከዚህም ባሻገርም ተወልዳ ባደገችበት በደብረማርቆስ ከተማ በእናቷ ፋንታዬ ስም የተሰየመ የሴቶች መጠለያ በመመስረት ከ80 የሚልቁ ወላጅ አልባ የሆኑ፤ የትምህርት እድልን ላላገኙ፤ አካል ጉዳተኞች የሆኑ ልጃገረዶች ከፍተኛ የትምህርት እድልን እንዲያገኙ በማድረግ እያበቃች ትገኛለች። በተጨማሪም ለደብረማርቆስ ለህፃናት ማሳደጊያ የሚሆን የሶስት ሚሊዮን ብር ቤት ገዝታ አስረክባለች። እንዲሁም ከአመታት በፊት በባሏ አሲድ የተደፋባትን አንዲት ሴት አሜሪካ በመውሰድ በማሳከም ህይወቷን ለማትረፍ ባደረገች ጥረት አለም አቀፍ እውቅና አግኝታለች።
በዚህ ብቻ ግን አልተወሰነችም፤ ብዙ አመታት ያሳለፈችበት ጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ህዝቧ ሲረግፉባት ዝም ብላ ማየት ስለተሳናት 27ሺ ዶላር በመርዳት መልሳ አለምን አስደምማለች። በቅርቡ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቿ የ50 ሺ ዶላር ድጋፍ በማድረግ የብዙ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ መሳብ ችላለች፡፡
ዶክተር መንበረ አክሊሉ በእነዚህና ዘር ቀለም ሳትመርጥ ባደረገቻቸው በሌሎች በጎ ምግባሮቿ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘች ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በአሜሪካ ባደረገችው ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት እውቅና፣ ምስጋና፣ ሽልማቶች ተሰጥቷታል፡፡
ኦክላንድ ሆሊኔልስ ዩኒቨርሲቲ እና ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም በከፍተኛ ደረጃ በክብር የሚታወቅ ጃፈርሰን አዋርድ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ እንዲሁም በ2014 ዓ.ም ከካሊፎርኒያው ሆሊኔምስ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ የተሰጣት ሲሆን፤ የወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዊሊያም ሄንስ የዶክተር መንበርን ታሪክ “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” በሚል ሰዎች የበኩላቸውን ጥረት ካደረጉ የማይፈታ ችግር እንደሌለ ጥሩ ማሳያ እንደሆነች አድርገው አቅርበው ነበር፡፡
የሀገር ቤቱ የአድዋ የባህልና የታሪክ ህብረት የዶክተር መንበረን መልካምና በጎ ምግባሯን፤ ሰፊ ልቧን ፤ እናትነቷን ፤ ለጋስነት እና ደግነቷን በመመልከት በሰባተኛው ዙር የአርአያ ሰው ሽልማት መታሰቢያ አድርጎ በመምረጥ ሸልሟታል፡፡
እኛም መገፋቷንም ሆነ በህይወቷ ያጋጠሟትን ክፉ ነገሮች ወደ መልካም በመቀየር ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ የቻለችው፤ ከተወለደችበት ቀዬ ጀምሮ ስደተኝነቷን ሳይንቁ እስከተቀበሏት ኃያላን ሀገራት የደጎች አብነት አድርገናታል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2015