
ዘመናዊነት ካመጣቸው ችግሮች አንዱ ተፈላጊው መረጃ ሁሉ በስልካችን በኩል መምጣቱ እና ስልካችንን ለእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለማኅበራዊ ሚዲያ፣ ለጌሞች እና ለመሳሰሉት ተጨማሪ ተግባራት ለረጅም ሰዓታት መጠቀም የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሞባይል ስልክ መጠቀም ከጀመርን ከሁለት አስርተ ዓመታት እንኳን የበለጠ አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን በተለይ በከተሜው አካባቢ ያለ ስልክ እስትንፋስ የሌለ እስከመምሰል ደርሷል፡፡
ዋናው ጥያቄ የሞባይል ስልኮችን መጠቀም ሳይሆን አጠቃቀሙ ላይ ያለው ግንዛቤ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የብዙዎቻችን አጠቃቀም በሳይንስ ያልተደገፈና በዘፈቀደ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ አስገራሚው ነገር ግን አጠቃቀማችን ቴክኖሎጂው በተለይም በጤና ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር በቀላል ሳይንስ ማስቀረት እየቻልን ቸልተኛ መሆናችን ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል በመኝታ ሰዓት ሞባይል ስልኮችን መጠቀም ከስክሪኑ የሚወጣው ጨረር አዕምሮን እንዲጨናነቅና እንዲነቃ ስለሚያደርገው ለእንቅልፍ እጦት ይዳርጋል። ከዚህ አንጻርም ከመኝታ ከአንድ ሰዓት በፊት ከእጅ ስልክ ጋር ብንለያይ ሳይንስ ይመከራል። እኛ ጋር ግን ይህ ተቃራኒ ነው፡፡ እንዲያውም እንቅልፍ እንቢ ሲለን በቀጥታ ስልክ መነካካት ነው የሚቀናን፡፡
ይህ የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ችግር ከኛም አልፎ መዘዙ ለሕፃናት መትረፉን ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በየቤቱ ሕፃናት ለረዥም ጊዜ የሞባይል ስልክ ሲጠቀሙ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህን እንደ ችግር የምንቆጥረውም አይደለም፡፡ በእርግጥ መቼና በየትኛው ዕድሜ ለልጆች ስልክ ይሰጥ የሚለው ‘የሚሊዮን ዶላር’ ጥያቄ ነው። አንዱ ወገን ልጆች ዘመናቸውን መምሰል ነው ያለባቸው፣ መረጃ የሚቃርሙት በስልክ ነው፣ ስለዚህ መነካካት እስከቻሉ ድረስ ይጠቀሙ፤ ይበርብሩ ይላል። ሌላኛው ‘የለም፤ የለም፤ አደጋው ይከፋል፣ መርገምቱ ይሰፋል’ ይላል። ክርክሩን ለጊዜው ወደ ጎን ትተነው ከጤና አኳያ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በቀላል ሳይንስ ማስቀረት እየቻልን ቸልተኛ የሆንባቸውን ጥቂት ነገሮች በጥናቶች አስደግፈን እንታዘብ፡፡
ጥናቶች እንዳሳዩት የሞባይል ስልክን አዘውትረው የሚጠቀሙ ሕፃናት እስከ 3% የሚደርስ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ተጨማሪ ለአጭር ዕይታ (short sidededness) ሕመም የመጋለጥ ዕድል አላቸው። ከእይታቸውም ባለፈ የእንቅልፍ መዛባት፣ የመደበት፣ የራስ ምታት፣ የአንገት ሕመም እና ከፍ ሲልም እንደ ኦቲዝም ባሉ የዕድገት እክሎች የመጠቃት ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል።
ሌላው ለረጅም ሰዓት ስልክ እየነካኩ መቆየት ከሚያመጣቸው ችግሮች ውስጥ ምስሉ ላይ በሚታየው መልኩ አንገትን ጎንበስ አድርጎ ዘለግ ላለ ጊዜ ከመቆየት ጋር የተያያዙ የአንገት ዲስኮች ማበጥ፣ የአንገት ጡንቻዎች አቅም መዛነፍ እና ለረጅም ጊዜ ጫና የሚበዛበት የፊተኛው የአንገት ክፍል ላይ ያሉ የአጥንት ጠርዞች በጫና ምክንያት ያለዕድሜ መበላት (degeneration) ይጨምራል። ይህም ኑሮን ለሚያውክ የአንገት ሕመም እና ለአላስፈላጊ ቀዶ ሕክምና ይዳርጋል። ይህ በሳይንስ የተደገፈ የሞባይል ስልክ መዘዝ መፍትሔው ቀላል ቢሆንም ብዙዎች ከቁብ አንቆጥረውም፡፡
ለምሳሌ ሳይንስ እንደመፍትሔ ከሚያስቀምጣቸው ነጥቦች መካከል በአጠቃላይ ሞባይል የምንጠቀምበትን ሰዓት በየመሐሉ እረፍት ያለበት እና ያልተራዘመ እንዲሆን ማስቻል አንዱ ነው፡፡ ግን ስንቶቻችን ይህን ተገንዝበን ተግባራዊ እናደርጋለን የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡
ሕፃናት ለአይናቸው በሚኖረው ቅርበት ምክንያት ከነአካቴው በሞባይል ስልክ ጌም ባይጫወቱ ይመከራል። የግድ መጠቀም ካለባቸውም ትንሽ የጥንቃቄ ርምጃ ብንወስድ ከትልቅ ችግር ልንታደጋቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል የብርሃኑን መጠን መቀነስ፣ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ጨረሩን ጫና ለመቅረፍ የኔትወርክ ግንኙነት (“ኮኔክሽን”) የሌለው ስልክ/ታብሌት መስጠት አልያም “ኤር ፕሌን ሞድ” ላይ ማድረግ አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል። በፕሮግራም እንዲጠቀሙ ማድረግ እና ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ እንዲጠቀሙ በፍፁም ባለመፍቀድ ባሕሪውን እንዲያዳብሩት ማድረግም ከባድ አይደለም።
ማንኛውም ዕድሜ ላይ ያለን ሰዎች የሥራችን ባሕሪ ለረጅም ሰዓታት ስልክ መነካካት የሚያስገድደን ከሆነ ቢያንስ ምስሉ ላይ የሚታየውን “የቴክስት ፖዚሽን” የሚል ስያሜ የወጣለትን አይነት አንገትን ጎንበስ በማድረግ ለተራዘመ ሰዓት መነካካት ወይም “ቴክስት መፃፍ/ ቻት ማድረግ” የሚያመጣውን ችግር በመገንዘብ ከአንገታችን ቀና ብለን ለመጠቀም መሞከር ፣ በየመሐሉም እንቅስቃሴ ማድረጊያ ዕረፍት መውሰድ ያስፈልጋል። ግን ለነዚህ ቀላል መፍትሔዎች ስንቶች ግንዛቤው ኖሯቸው ተግባራዊ ያደርጉታል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡
የሞባይል ስልክ ጉዳይ ሲነሳ በዚህ ዘመን የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በጎና መጥፎ ገፅታ በጥቂቱም ቢሆን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ስልክ በመነካካት ረጅም ሰዓት እንድንወስድ ከሚያደርጉት ዋነኛ ምክንያቶች ግንባር ቀደሞቹ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ ለዛሬው ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በተለይም ልጆች በየትኛው ዕድሜ ላይ ምን ይሰማቸዋል በሚል በተደረገ አንድ ሰፊ ዓለም አቀፍ ጥናት ያስቀመጠውን እንመልከት፡፡
ጥናቱ 17ሺ የሚሆኑ አዳጊዎች እና ወጣቶች (ዕድሜያቸው ከ10 – 21 የሆኑ) ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በውጤቱም ሴቶች ከ11 – 13 ወንዶች ደግሞ ከ14 – 15 ዓመት ያሉት በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም በጀመሩ በዓመቱ ከፍተኛ እርካታ የማጣት ስሜት ተስተውሎባቸዋል። የሚገርመው ደግሞ ስልክና ማኅበራዊ ሚዲያ ባልተጠቀሙት ላይ የእርካታና እፎይታ ስሜት መታየቱ ነው።
በአሥራዎቹ የሚገኙ አዳጊዎች ሁልጊዜም ቢሆን ሌላው ስለነርሱ ምን እንደሚያስብ ያስጨንቃቸዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ ሰዎች በግላጭ ፍቅርና ጥላቻቸውን የሚረጩበት መድረክ ነው። አዳጊዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ ውስጥ የሚወድቁትም ለዚሁ ነው። እርካታ ጥሏቸው ይበናል። ለምን ቢባል ሁሌም የሆነ የሚበልጣቸው እኩያቸው በማኅበራዊ ሚዲያ አለ። ያ ደግሞ ደስታቸውን ይቀማቸዋል። ይህ ደግሞ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብም ይዞ የሚመጣው መዘዝ ከባድ ነውና እናስብበት፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2015