በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል መጣሁ መጣሁ እያለ ነው፡፡ በዓሉ በመጪው እሁድ የሚከበር መሆኑን ተከትሎ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ለማክበር ዝግጅቶችን እያደረጉ ናቸው፡፡ ለእዚህም ሁሉም እንደየአቅሙ ለግብይት መውጣት ጀምሯል፡፡
እኛም ለበዓሉ ድምቀት አንዱና ዋናው ጉዳይ የሆነውን የግብይት ሂደት በመቃኘት የሸማቹና ነጋዴውን እንቅስቃሴ፣ ለመረዳት በቅድሚያ በአዲስ አበባው ሾላ ገበያ ተገኝተናል፡፡ አቶ ሙሉጌታ አሰፋን በዚሁ ገበያ አገኘናቸው፡፡ ገበያ እንዴት ነው ስንል የጠየቅናቸው አቶ ሙሉጌታ ‹‹ሕዝቡ የኑሮ ውድነቱ ከትዕግስቱ በላይ ሆኗል›› ሲሉ መለሱልን፡፡ ኑሮ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የከበዳቸው አሁን መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 50 ብር፣ ድንች 30 ብር፣ ቲማቲም 35 ብር ካሮት 30 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑንና ዋጋው በጣም ውድ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ እኛም በገበያው ላይ የታዘብነው ይህንኑ ነው፡፡
አቶ ሙሉጌታ ጡረተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ የኑሮ ውድነቱ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። መንግሥት ጡረተኞችን ቢያስብና ገበያውን ማረጋጋት ቢችል መልካም መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም በእንዲህ አይነቱ የበዓል ወቅት ገበያን ማረጋጋት ከመንግሥት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረው ነጋዴው አቶ ከበደ ናደው እህል በረንዳ ሄደው የሚፈልጉትን ያህል እህል ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። የዋጋ ንረቱን ያስከተለው የአቅርቦት እጥረት እንደሆነም ጠቅሰው፣ እጥረቱም የተከሰተው በየኬላው ባለው ችግር ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እህል ከየአካባቢው እየገባ አይደለም የሚሉት አቶ ከበደ፣ እህል በነጻነት ከየአቅጣጫው እንደበፊቱ መግባት ቢችል የሚታየውን የእህል አቅርቦት እጥረት ማቃለል ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
እህልን ጨምሮ ማንኛውም የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ በተለይም በበዓል ወቅት ተፈላጊና አስፈላጊ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ከበደ፤ አሁን ገበያው ላይ የሚታየው የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም መሆኑን ይገምታሉ፡፡ ቀን በቀን በሚለዋወጥ ዋጋ ሸማቹ ብቻ ሳይሆን ነጋዴውም ጭምር እንደተቸገረም ነው የገለጹት፡፡ በዕለቱ ያለውን ዋጋ በመግለጽም ዛሬ ያለው ዋጋ ነገ ባለበት አይቆይም ይላሉ፡፡ ዋጋው ተለዋዋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአንዳንድ ምርቶችን የእለቱን ዋጋ አስመልክተው ነጋዴው እንዳሉት፤ አንድ ኪሎ የገንፎ እህል እንዲሁም በሶ 80 ብር፣ ስንዴ ለንፍሮ የሚሆነው በኪሎ 90 ብር፣ ለዳቦ የሚሆነው ደግሞ 65 ብር፣ ባቄላ የተከካ በኪሎ 80 ብር፣ አንድ ኪሎ ምስር 160 ብር፣ ድፍን ምስር 130 ብር፣ የአጃ ቅንጬ ከ90 እስከ 100 ብር፣ ጥቁር ገብስ ከ55 እስከ 60 ብር፣ ዱቄት ከ80 እስከ 85 ብር ነው፡፡
ነጋዴው አያይዘውም የክርስትና እምነት ተከታዮች ከሰሞኑ የሚያከብሩት የፋሲካ በዓልና የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንድ ሳምንት ልዩነት የሚያከብሩት የረመዳን ጾም ፍቺ የሸቀጦች ፍላጎትን በእጥፍ እንዲጨምር እንደሚያደርገው ጠቅሰው፣ መንግሥት ገበያ የማረጋገት ሥራውን ከወዲሁ ቢሠራ መልካም ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለመጪዎቹ ሁለት በዓላት አስፈላጊና አይቀሬ ከሆኑ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች መካከል ዘይት አንዱ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የሚመረት ጸሐይ ንጹሕ የኑግ ዘይትና ከውጭ አገር የሚገባውን የሱፍ ዘይት በሾላ ገበያ ስትሸጥ ያገኘናት ወጣት የማታ ብርሃኑ በበኩሏ የዋጋ ንረቱ የንግድ ሥራውን ቀዝቃዛ እንዲሆን አድርጎታል ትላለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ የአገር ውስጥ የኑግ ዘይት አምስት ሊትር 1200 ብር የሚሸጥ ሲሆን ከውጭ የሚገባው ደግሞ በ900 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ያም ቢሆን የሚገዛው ሰው በቁጥር ነው፡፡ እንደቀደመው ጊዜ ሰዎች ለበዓል የሚያደርጉትን አይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም የምትለው ወጣት የማታ፣ የዋጋ ንረቱ ለነጋዴውም ትልቅ ፈተና እንደሆነበት ታብራራለች፡፡
ነጋዴዎች ከአንድ ጀሪካን ዘይት አምስትና አስር ብር ብቻ ለማትረፍ እየሸጡ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ ዘይት ዋጋው እጅግ ከመወደዱ የተነሳ ነጋዴውም አምጥቶ ለመሸጥ ተቸግሯል ስትልም ነው ያመለከተችው። ከዚህ ቀደም 20 እና 30 ካርቶን የሚመጣበት ዋጋ ዛሬ አራትና ሶስት ካርቶን ብቻ እንደሚያመጣ ተናግራለች።
ከሌሎች የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች በተጨማሪ የፋሲካ በዓልን የሚያደምቀው ዶሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዶሮ ገበያውንም ቃኘነው፡፡ ዶሮ በሾላ ገበያ ለአይን ሞልቶ እንደማይታይ፣በስፋት እየገባ እንዳልሆነ አስተያየት ከሰጡን ሸማቾችና ነጋዴዎች መረዳት ችለናል፡፡
በዶሮ ንግድ የተሠማራው አቶ ፍጹም ዘውዱ ወደ ገበያ እየገባ ያለው ዶሮ የፈረንጅ ነው ይላል፡፡ የፈረንጁ ዶሮም ቢሆን ዋጋው እንደ ፊቱ አይደለም ሲል ገልጾ፣ እሱም ውድ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም በጅምላ ሂሳብ ከሁለት መቶ ብር የበለጠ ዋጋ የማያወጣው የፈረንጅ ዶሮ አሁን ከ350 እስከ 400 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አሁን ያለው ዋጋም ለበዓሉ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ በየሰዓቱ ሊጨምር ይችላል ሲል ስጋቱን ተናግሯል፡፡
‹‹የዋጋው መወደድ ለሸማቹም ሆነ ለነጋዴው ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ነጋዴውም በስፋት አምጥቶ መሸጥ አያስችለውም፡፡ ሸማቹም እንደልቡ መግዛት አይችልም›› በማለት ለችግሩ ምክንያት ያላቸውን ጉዳዮች ጠቅሷል፡፡ በተለይ የሀበሻ ዶሮ በስፋት የሚመጣው ከአማራ ክልል ጎጃም አካባቢ እንደሆነ በመጥቀስ አሁን ላይ ከዚያ አካባቢ ምርቱ እየገባ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህ አስተያየቶች በመነሳት በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን እየፈተነ ባለው የኑሮ ውድነት ላይ የበዓል ገበያው ተደርቦ ዋጋውን ይበልጥ እንዳያንረው በማድረግ በኩል ገበያ በማረጋጋት እየሠሩ ካሉ ተቋማት አንዱ ለሆነው የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ጥያቄዎችን አቀረብን። መጪዎቹን ሁለት ታላላቅ በዓላት አስመልክቶ ገበያ በማረጋጋት ላይ ኮሚሽኑ ምን ዝግጅት አድርጓል ስንል የጠየቅናቸው የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ታምሩ በሰጡት ምላሽ፤ ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በዓላቱን መሠረት በማድረግ ገበያ ለማረጋጋት የተለያዩ ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ጫልቱ ገለጻ፤ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ቀዳሚ ኃላፊነቱ ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ነው፤ ኮሚሽኑ በተለይም ገበያን በማረጋጋት ረገድ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
የሀገሪቱ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቁጥራቸው ውስን መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረው፣ አብዛኛው የንግድ ሥራ በንግዱ ማኅበረሰብ መያዙን ነው የገለጹት፡፡ አስር በመቶ ያህል ድርሻ ያለው ኅብረት ሥራ የሀገሪቱን ገበያ በማረጋጋት ረገድ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት ማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችል በከተማዋ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ምርቶቹ ለገበያ የቀረቡትም ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ ሲሆን፤ ይህም እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ይዘልቃል፡፡
ኮሚሽኑ ገበያን በማረጋጋት ልምድ እንዳለው የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ በአሁኑ ወቅት የክልል ከተሞችን ሳይጨምር አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 97 በሚደርሱ ቦታዎች ላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶቻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ አስችሏል ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ደረጃ 138 ሸማች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሰማርተዋል። በኦሮሚያ ዳር ዳር በተመሳሳይ 15 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሠማርተዋል፡፡ በጀሞ የገበያ ማዕከልም እንዲሁ 15 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተለያዩ ምርቶችን ይዘው ወደ ገበያ ወጥተዋል። ማኅበረሰቡ ከትናንት ጀምሮ በየአካባቢው ወጥቶ ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችል ወይዘሮ ጫልቱ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ገበያን ማረጋጋት ዋና ተግባሩ ነው፤ ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ ተቋምም እንደመሆኑ በትክክል ገበያውን ማረጋጋት እንደሚችል ጠቅሰው፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም የበቆሎና የስንዴ ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች ቀርበዋል፡፡ የስንዴ ዱቄት በኪሎ 47 ብር ሲሸጥ የበቆሎ ዱቄት ደግሞ በኪሎ 36 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ጤፍ ከ5500 እስከ 6000 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡
በገበያው አትክልትና ፍራፍሬ መቅረቡን የገለጹት ወይዘሮ ጫልቱ፤ ሽንኩርት ከ25 እስከ 28 ብር በኪሎ እየተሸጠ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ዶሮና በግን ጨምሮ የእንስሳት ተዋፅዖ የሆኑ እንደ እንቁላልና ቅቤ ያሉትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች መቅረባቸውን ጠቁመው፣ ሕዝቡ በየአካባቢው ወጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችል ነው ያስረዱት፡፡
ሁለቱን በዓላት ታሳቢ በማድረግ በቂ ምርት ወደ ገበያ ወጥቷል፡፡ ምርቶቹ በስፋት ከኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ከደቡብ አካባቢ እየገቡ ይገኛሉ ያሉት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጠቁመዋል። አንዳንዶች ሆን ብለው ከፖለቲካ ጋር በማገናኘት ሰው ሠራሽ እጥረት እንዲፈጠር እየሠሩ እንደሆነም አስገንዝበው፣ ይህንን ችግር ለመፍታትም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለማስተካከል እየሠራ መሆኑንና ችግሩ በሂደት እንደሚፈታ አስረድተዋል፡፡
ለበዓላት ያስፈልጋሉ የተባሉ ምርቶች በሙሉ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት በአስሩም ክፍለ ከተሞች በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ጫልቱ፤ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ይቀርብ የነበረው የእሁድ ገበያም ከሰኞ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት እንዲቆይ መደረጉም ገበያን ለሚረጋጋት ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ የኢዜአ ዘገባ ለትንሳኤና ኢድ በዓላት የፍጆታ ምርቶች በሁሉም አካባቢ በቂ አቅርቦት መኖሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም አስታውቋል፡፡ ከበዓላቱ አከባበር ጋር ተያይዞ በምርት አቅርቦት ዙሪያ የተደረገውን ዝግጅት በማስመልከት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፤ በተከታታይ ሳምንታት በሚከበሩት የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት የግብርና ምርቶችና የሸቀጦች አቅርቦት በስፋት መኖሩን አስታውቀዋል። በመሆኑም ላለፉት 20 ቀናት በክልሎች ከሚገኙ የንግድ ቢሮዎች አካላት ጋር በመነጋገር የምርት አቅርቦት በስፋት እንዲኖር መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ኅብረተሰቡ በተረጋጋ መልኩ መሸመት እንደሚችል አስታውቀዋል።
በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ በመግባት የተለያዩ ሕገ- ወጥ ተግባራት ላይ የሚገኙ አካላት ካሉ በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ኡመድ፤ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ተዋፅዖና ሸቀጦች ጭምር በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ሳያካትት ሌሎች 30 በሚጠጉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የሚያቀርቡ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና ምርቶችን፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ዱቄትና ሌሎችም ምርቶችን ለሸማቾች ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የእርድ እንስሳትን ጭምር ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበዓላት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የሚደረገውን የዋጋ ጫና ለመቀነስ ምርቶችን በብዛት ወደ ከተማ በማስገባት ላይ እንገኛለን ሲሉ መግለጻቸውን መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ጠቁመዋል።
በከተማችን የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ለበዓሉ ዶሮ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እንድንፈጥር ረድቶናል ያሉት ከንቲባዋ፣ እነዚህ ጥረቶቻችንን በቀጣይ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል። የገቡት ምርቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ሁሉም አካል ተባብሮ እንዲሠራ ለማሳሰብ እወዳለሁ ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2015