በኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) አማካኝነት የሚካሄደው የሰራተኞች ስፖርት መድረክ በአንጋፋነቱ ይታወቃል። በኢትዮጵያ በርካታ የሰራተኛ ማህበራት እንደመኖራቸው ግን ከቁጥራቸው አኳያ ወደ ስፖርቱ መድረክ ብቅ የሚሉት ጥቂት ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ተቋማት ወይም አሰሪዎች አቅም እያላቸው ለስፖርት ካላቸው ዝቅተኛ ግንዛቤ ጋር እንደሚያያዝ የሚናገሩ በርካታ ናቸው።
ያም ሆኖ በሰራተኛው መካከል በሚካሄዱ የተለያዩ ስፖርታዊ መድረኮች ሰራተኛው መብቱን ተጠቅሞ ተሳታፊ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ተቋማት፣ አሰሪዎችና አመራሮች የሰራተኛው ስፖርት መድረኮች ዛሬም ድረስ በድምቀት እንዲቀጥሉ ማድረግ ችለዋል። በዚህ ረገድ ለሌሎች አርአያ ከሚሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ተጠቃሽ ነው።
መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአዋጅ የተቋቋመው 2002 ላይ ሲሆን በሰራተኛው ስፖርት መሳተፍ የጀመረው ከ2004 ጀምሮ ነው። እስካሁንም ካለምንም እንከን በሰራተኛው ስፖርት የተለያዩ መድረኮች በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሚሊተሪውንም ሲቪል ሰራተኛውንም ያቀፈ ተቋም ቢሆንም በሰራተኛው ስፖርት የሚሳተፈውም በሲቪል ሰራተኞቹ ብቻ ነው። የሰራተኛው ስፖርት በኮቪድ-19 ምክንያት ለሶስት ዓመታት ተቋርጦ ዘንድሮ በበጋ ወራት ውድድሮች ሲመለስም በእግር ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በዳርት ውድድሮች በሁለቱም ፆታ እየተሳተፈ ይገኛል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የሰራተኞች ስፖርት ቡድን መሪና የኢሰማኮ ሰራተኞች ስፖርት የስነስርአትና ውድድር ኮሚቴ አባል አቶ ተሰማ አለሙ፣ መከላከያ ኮንስትራክሽን ለሰራተኛው ስፖርት የሚሰጠው ትልቅ ቦታ ለሌሎችም ተቋማት ትምህርት እንደሚሆን ይናገራሉ። ተቋሙ በሰራተኛው ስፖርት መድረክ ጥሩ እንቅስቃሴና ተሳትፎ አለው የሚሉት አቶ ተሰማ፣ የተቋሙ አመራሮች ሰራተኛውን በየልምምድና ውድድር ቦታ ዘወትር እየተገኙ በሁሉም አስፈላጊ ነገር ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።
በዚህም ሰራተኛው በመቻል ሜዳ ልምምድ እንዲሰራ ከማድረግ አንስቶ ትራንስፖርትና ትጥቅ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። ለስፖርቱ መልካም አመለካከት ያለው አመራር በመኖሩም ሰራተኛው ነፃ ሆኖ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ይህም ተቋሙን በሰራተኛው ስፖርት በውጤት ረገድ በተለይ በእግርና እጅ ኳስ በስኬት ጎዳና ላይ እንዲገኝ አስችሎታል።
“አንዳንድ ተቋማት ላይ ይሄ ነገር የለም፣ ልምምድ ሳይሰሩ ወደ ውድድር የሚመጡም አሉ” ያሉት አቶ ተሰማ፣ በኢትዮጵያ እንዳሉት ተቋማትና ድርጅቶች ብዛት በሰራተኛው ስፖርት የሚሳተፉት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የራሳቸውን ጥቅም እንጂ ሰራተኛው በስፖርት ተሳተፎ አልተሳተፈ ግድ የማይሰጣቸው የድርጅት አመራሮች መኖራቸው አንዱ ምክንያት መሆኑ ይጠቅሳሉ። አቅም እያላቸው ሰራተኛውን ወደ ስፖርት ሜዳ የመላክ ፍላጎት የሌላቸው ከትንንሽ እስከ ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ ተቋማትና ድርጅቶች እንዳሉም ያክላሉ። ነገር ግን ሰራተኛውን በስፖርቱ ማሳተፍ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አያደርግም ባይናቸው።
“ተቋማት ሰራተኛውን ወደ ስፖርት በላኩ ቁጥር ጤንነቱን ይጠብቃሉ፣ አእምሮውን ያሰፋሉ፣ ጥሩ አምራች ዜጋ ይፈጥራሉ እንጂ አይጎዱም፣ ከእኛ መማር የሚገባቸው ብዙ ድርጅቶች አሉ፣ ለምሳሌ ትጥቅ ለመግዛት ብዙ ገንዘብ አወጣለሁ ብሎ የሚያስብ አለ፣ ይሄ ግን ስህተት ነው፣ ጥቅሙ የበለጠ ነው። ባላቸው አቅም በውስን ስፖርቶችም ቢሆን ቢሳተፉ መልካም ነውና ከእኛ ተሞክሮ ቢወስዱ” ሲሉም አቶ ተሰማ ምክረሃሳብ አቅርበዋል።
መከላከያ ኮንስትራክሽን በዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድር በወንዶች እግር ኳስ 24፣ በመረብ ኳስ 12፣ በዳርት 4፣ በጠረጴዛ ኳስ 4፣ በሴቶች ቮሊቦል 12 ሰራተኞች እያሳተፈ ይገኛል። ተቋሙ ትልቅ ስም አለው፣ በየቦታው ሰፋፊ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችም አሉት፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚሰሩት በነዚህ ሰራተኞች ነው፣ በሰራተኛው ስፖርት መሳተፋቸውም ንቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለው የሚያምኑት ቡድን መሪው፣ ሰራተኛው የረፍት ቀኑን በስፖርት ስለሚያሳልፍ የስራ ቀኑ ንቁና ስኬታማ ሆኖ ይቆያል ይላሉ።
ይህም ጤንነቱን በመጠበቅና ራሱን ከአልባሌ ነገሮች ለመቆጠብ ረድቶታል። ተቋሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች በሚሳተፉበት መድረክ በመወዳደሩም ራሱን ለማስተዋወቅ አግዞታል። በዚህም ጥሩ ስም ሊያተርፍ ችሏል። ድርጅቱ ለነዚህ ስፖርተኞች በየዓመቱ ሽልማት በማዘጋጀት እንደየተሳትፏቸውና እንደየአቅማቸው ሳይሸልም የቀረበት ጊዜ እንደሌለም ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ተሰማ አስተያየት፣ የሰራተኛው ስፖርት በኮቪድ ምክንያት ለሶስት ዓመት ተቋርጦ ዘንድሮ በበጋ ወራት ውድድሮች ሲመለስ ሰራተኛው በናፍቆትና በተነቃቃ መንገድ ነው ወደ ውድድር የተመለስነው። የተወሰኑ ድርጅቶች መሳተፍ ባይችሉም አብዛኞቹ ወደ ውድድር ተመልሰዋል። በቀጣይም አሁን ካለው የተሻለ ተሳትፎ እንደሚኖር እርግጠኛ ናቸው። ስለዚህ ኮቪድ እንዳሳደረው ተፅእኖ ስፖርቱ ከዓመታት በኋላ ሲመለስ አልተቀዛቀዘም ማለት ይቻላል።
መከላከያ ኮንስትራክሽን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልሎች ከሚገኙ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ጋር ቢያንስ በዓመት አንዴ የራሱን ውድድር የሰራተኛውን ቀን አስመልክቶ ያካሂዳል። ከፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ ይህ ባህል ለጊዜው መቀጠል ባይችልም በአገር አቀፍ ውድድሮች ክረምት ላይ በወንጂ ስቴድየም ከሌሎች ተቋማት ጋር በስፋት እንገናኛለን የሚል ተስፋ አላቸው። ከመላ አገሪቱ የሚመጡ ሰራተኞች ለሁለት ሳምንት በሚቆየው በዚህ መድረክ ቤተሰባዊ ስሜት መፍጠር ተችሏል የሚሉት አቶ ተሰማ የሰራተኛው የውድድር መድረክ አላማም ይሄው ነው በማለት አስተያየታቸውን ቋ ጭ ተ ዋ ል ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም