እጽዋትን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያጠቁና ሥጋት ከሆኑ ተባዮች የበረሃ አምበጣ አንዱ ነው። ይህ ተባይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትል መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ እኤአ ከ2019 እስከ 2022 የበረሃ አንበጣ በአገሪቱ መከሰቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህን ተባይ በቁጥጥር ስር ለማዋልም ከፍተኛ ርብርብ ጠይቆም ነበር። መንግሥት ተባዩን ለመቆጣጠር የሚያስችል መዳህኒት በአውሮፕላን ለመርጨት ከሌሎች አገሮች የአውሮፕላን ድጋፍ ለመጠየቅ ተገዶ እንደነበርም ይታወሳል። በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውን የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ክስተቱ የግብርና ሥራ ወቅቶችን ተከትሎ እንደሚመጣም ያስረዳሉ።
ለግብርና ሥራ ወቅቱን የጠበቀ ማዳበሪያ፣ ፀረአረም እና ሌሎችም የግብአት አቅርቦቶች ወሳኝ እንደሆኑ ሁሉ ሰብልን የሚያጠቁ ተባዮችን ቀድሞ የትንበያ ሥራዎችን በመሥራት መከላከልና መቆጣጠር ከወሳኝ የግብርና ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። ግብርና ሚኒስቴርም በግብርና ሥራ በእቅድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ይሄው ሲሆን፣ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉትን ሥራዎች ቀድሞ ይሰራል። ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ በግብረኃይል ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ያከናውናል።
በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ትምህርት መወሰዱም ይገለጻል። ከክስተቱ በኋላ ግብርና ሚኒስቴር በአገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ክስተቱ ሲያጋጥም ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችለውን ሥራ ሠርቷል። ከእነዚህም መካከል ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ አደረጃጀት መፍጠር፣ ለቁጥጥር ሥራውም በአውሮፕላንና በድሮን የታገዘ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ግብአት ማሟላት፣ ባለሙያዎችን ዝግጁ ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው።
እኛም ካለፈው ክስተት የተገኘ ተሞክሮ፣ ቀድሞ ለመከላከልና ችግር ሲያጋጥም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ስላለው አደረጃጀትና የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲሁም እንደ አገር ያለው የመከላከል አቅም አደረጃጀትና በዚህ ወቅት ስላለው ተባይ ወይንም ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ከግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ንጉሤ ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አቶ በላይነህ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተከተሰውን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠር በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ወይንም ሪሶርስ ሞብላይዜሽን ማድረግ አስፈልጎ እንደነበር አስታውሰዋል። ለመከላከሉ ሥራ የሚውል የኬሚካል ርጭት የሚያካሂዱ እስከ 13 የሚደርሱ አውሮፕላኖችን በማሰማራት፣ ከዚህ በተጨማሪም ድሮን በመጠቀም፣ በመኪና እና በእግር ጉዞ የታገዘ ሰፊ ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል። የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በተደረገው የርብርብ ሥራም እንደ አገር ሊደርስ ይችል የነበረውን የጉዳት መጠን መቀነስ ተችሏል ይላሉ።
ይሁንና በግለሰብ ወይንም በቤተሰብ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል ሰብላቸው የጠፋባቸው አርሶ አደሮች አንደነበሩ አይዘነጋም። ለተጎዱ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ፣ ለአርብቶ አደሮች ደግሞ የእንስሳት መኖ በማቅረብ መንግሥት ደርሶላቸዋል። እንዲህ ያለው ምላሽ የተሰጠው በግብርና ሚኒስቴር ሥር በተቋቋመው የበረሃ አንበጣ ምላሽ ፕሮጀክት አማካኝነት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ በተጨማሪ አንበጣን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአሰሳ ሥራ ይሰራል። በሥልጠና የአቅም ግንባታ ሥራም የሚከናወነው በዚሁ ፕሮጀክት ነው።
እንደ አቶ በላይነህ ገለጻ፤ የአንበጣ ክስተቱ አሁን ላይ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም እንዲፈጠር አስችሏል። መንግሥት አምስት አውሮፕላኖችን ገዝቶ በማቅረቡ በኪራይ ይከናወን የነበረውን የአውሮፕላን ርጭት በማስቀረት ወጭን መቀነስ ተችሏል። በተጨማሪም ለአሰሳ ሥራ የሚያገልግሉ ድሮኖች ተገዝተው ቀርበዋል። በአሁኑ ጊዜም ሁለት ድሮኖች በሥራ ላይ ሲሆኑ፣ በግዥ ሂደት ላይም የሚገኙ አሉ። እነዚህ አቅምን ለማጠናከር አግዘዋል።
የአውሮፕላኖቹ ዋና ተግባር እጽዋትን የሚያጠቁ ተባዮችን ለመከላከል የርጭት ሥራ ማከናወን ቢሆንም፣ የተባይ ጫና በማይኖርበት ወቅት አውሮፕላኖቹ የዘር ብዜት ለሚያከናውኑ የርጭት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉ። እርሳቸው የሚመሩት ክፍልም ከበረሃ አንበጣ ክስተቱ በኋላ በተሻለ አደረጃጀት መረጃን ከማሰባሰብ ጀምሮ የመከላከልና የመቆጣጠሩን ሥራ አጠናክሯል።
በዚሁ መሠረት ተባይን የመከላከሉ ሥራ በሁለት መንገድ ይከናወናል። አንደኛው መደበኛ ተባይን መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ተዛማች የሚባለውን የተባይ አይነት ነው። ሁለቱም የየራሳቸው ባህሪ አላቸው፤ በመሆኑም የመከላከሉና የክትትሉ ሥራም በተለያየ መንገድ ይከናወናል። መደበኛ ተባይ በአብዛኛው ከአርሶ አደሩ ቁጥጥር በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ አነስተኛ በመሆኑ አርሶ አደሩ እንዲቆጣጠረው ይደረጋል።
ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ፣ ግብርና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። ተዛማች ተባይን ግን ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥር የሚያደርገው ግብርና ሚኒስቴር ነው። ለርጭት የሚውሉ ኬሚካሎችን በማሟላት፣ ባለሙያዎችንም በማሰማራት ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ የመከላከሉን ሥራ ይሰራል።
በተዛማች ውስጥ የሚካተቱት አንበጣ፣ ግሪሳ ወፍና ተምች ናቸው። ተምች መደበኛና መጤ በመባል ይከፈላል። እነዚህ ተዛማች ተባዮች ድንበር ሳይገድባቸው ከአገር አገር ስለሚዘዋወሩ የመከላከሉ ሥራም ዓለም አቀፍ ትብብር ይፈልጋል። ለዚህ የተባይ ክስተትም መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ያግዛል። በተለያየ ዘዴ የሚከናወነው የተዛማች ተባይን የመከላከሉ ሥራ በአንድ አገር ውስጥ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ በላይነህ፤ የመከላከሉ ስራ የብዙ አገሮች ሥራ ነው ይላሉ።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ መረጃ የመለዋወጡ ሥራ ከብዙ አገራት ጋር ይከናወናል። በዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) አማካኝነት ጣሊያን ሮም ውስጥ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል አደረጃጀት ተመቻችቷል። ሥራው በቅንጅት መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ መረጃም በጋራ ያስፈልጋል። በተለይም ድንበር ዘለል ተባይ ሲያጋጥም መረጃው በቀላሉ ለሁሉም በአንዴ ስለሚዳረስ ቀድሞ ለመከላከል የጎላ ድርሻ አለው።
በዚህ የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ከሌሎች አገሮች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም ቢከሰት ሌሎች አገሮች እንዲደርሳቸው ይደረጋል። ‹‹አንበጣን በተመለከተ ሴንተር ሪጅን ወይንም መካከለኛው ዞን፣ ኢስተርን ሪጅን፣ዌስተርን ሪጅን በሚል በዓለም ይከፈላል። ኢትዮጵያ ሴንተር ሪጅን ውስጥ ትገኛለች። በዚህ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ የአንበጣ ክስተት መረጃ በዓለም ምግብ ድርጅት ወይም ፋኦ አማካኝነት ከጣሊያን ሮም ይደርሳቸዋል።
ለአብነትም መረጃው ከህንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከኢራንና ከሌሎች ለሁሉም ይደርሳል ማለት ነው›› ያሉት አቶ በላይነህ፣ አንበጣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ድንበር ዘሎ ለመሄድ ጊዜ የማይወስድበት እንደሆነ ይጠቁማሉ። መረጃው ቀድሞ ከደረሰ የመከላከሉንና የመቆጣጠሩን ሥራ ያቀለዋል ወይንም ጉዳት ሳይደረስ ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል። ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ጥረት ካልተደረገ አንበጣ መብረር ደረጃ ላይ ከደረሰ የመቆጣጠሩን ሥራ ፈታኝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
የአንበጣ መራቢያ ቦታዎች እጅግ ሰፊና ለማዳረስም አስቸጋሪ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ በላይነህ፤ በአገር ውስጥ አንበጣ መከሰቱን ለማረጋገጥ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ የተውጣጡ ወጣቶችን በስካውት በማደራጀት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመሥጠት አሰሳ እንዲያካሂዱ እንደሚደረግና እስካውቶቹ የሚሰጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ ባለሙያዎች እንደሚሰማሩ አስረድተዋል።
ሌላው እጽዋትን የሚጎዳ ተምች ወይንም የእሳት እራት የሚባለው ተባይ እንደሆነም አቶ በላይነህ ጠቅሰዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ተባይ የሚጓዘው በሌሊት ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትል በመፈልፈል ነው በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሰው። መጀመሪያም በሣር ላይ ይታያል። የተለያዩ ደረጃዎችን አልፎ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ ጥቃት ያደርሳል።
ይህን ተባይ የመቆጣጠሪያው ዘዴ ከሴቷ ተምች ጠረን በመውሰድ ነው። ወንዱ ተምች ጠረኑን ተከትሎ ሲመጣ በማጥመድ። ይህ ዘዴም በአካባቢው ላይ ያለውን የተምች መጠን ለማወቅ ያስችላል። ተምቹ ወደ እሳት እራት ሲቀየር ትል ይፈለፍላል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትል በመፈልፈል ነው በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሰው። ተምች በአገር ውስጥ ሊፈለፈል ይችላል፤ ከተለያየ አገርም ወደ አገር ውስጥ ይገባል። የንፋስ አቅጣጫን ተከትሎ የሚመጣና በመዛመት ጉዳት የሚያስከትል ተባይ ነው።
ተምች በሰብል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የበረሃ አንበጣ ከሚያደርሰው ጋር ሲነጻፀር አነስተኛ ነው። ይህ በመሆኑም የአካባቢ ማህበረሰብን በማደራጀት ነው የመከላከሉ ሥራ የሚሰራው ለማህበረሰቡ ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ ተፍጥሯል። ተምቹ ተፈልፍሎ ሲገኝ ሳይዛመት ባለበት ቦታ እንዲጠፋ የማድረግ ሥራ ይሰራል።
ሌላው በተዛማች የሚመደበው ተባይ ግሪሳ ወፍ ሲሆን፣ ወፉ በቡድን ወይንም በማስ ነው የሚጓዘው ወይንም የሚንቀሳቀሰው። ከኢትዮጵያ ውጭ የሚመጣም ነው። ይህ ግሪሳ ወፍ በስፋት ጥቃት እያደረሰ ያለው በበጋ ስንዴ ልማት ላይ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በበጋ ስንዴ ልማት ወቅት ሌሎች እጽዋቶች በስፋት ባለመኖራቸው ነው። አንድ ወፍ በቀን ከ17 ግራም በላይ የመብላት አቅም አለው። ግሪሳው ለመመገብ በሚያደርገው ሙከራ የሚረግፍም ስለሚኖር ብክነቱ ከፍተኛ ነው። ወፎቹ በመንጋ ሲንቀሳቀሱ ደግሞ የሚያደርሱት ጉዳትም ከፍተኛ ነው።
ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚደረግ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ግሪሳ ወፍ ችግር አልነበረም። ችግሩ የበጋ ሥንዴ ልማቱን ተከትሎ የመጣ ነው። የወፍ መንጋውን መቆጣጠር ባይቻል ምርት ለማግኘት አዳጋች ይሆን ነበር። ግሪሳ ወፍን የመከላከሉ ሥራም በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ያስፈልጋል። ወፎቹ በባህሪያቸው አንድ ቦታ የሚሰበሰቡ በመሆናቸው በማደሪያ ቦታቸው ላይ ርጭን በማከናወን ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ይደረጋል።
ለስንዴ ልማቱ ሌላው ጉዳት ዋግ ነው፤ ይህንንም ኬሚካል ርጭት በማካሄድ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይነህ፤ ዋግን የመከላከሉ ሥራ ከተዛማች ተባዮች ለየት የሚያደርገው በአርሶ አደር አቅም መፍታት ስለሚቻል መሆኑን ተናግረዋል። ለእዚህም ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የሙያ እገዛ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
አቶ በላይነህ ከመደበኛ ተባይ ጋር በተያያዘ ሌላው የጠቀሱት ስንዴው ከዘረዘረ በኋላ ጥቃት የሚያደርስ የስንዴ ፈንገስ የሚባለውን ነው። ይህ ተባይ ምርት ከተመረተ በኋላ ለገበያ ለማቅረብ ተጽእኖ በማሳደር ይታወቃል። ገለባው ለከብቶች መኖ ሲቀርብም መርዛማነት ያለው እንደሆነም ጠቁመዋል። የዚህ ፈንገስ ክስተት በዚህኛው የበጋ መሥኖ ልማት ላይ የከፋ ነገር ባያስከትልም የኬሚካል ርጭት መከናወኑን አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የስንዴ ዋግ በተለያየ ስያሜ ይታወቃል። ከአረም ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ተባዮችን ለመከላከል የአረም ማጥፊያ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ይገኛል፤ አርሶ አደሩ ይህን የመከላከሉን ሥራ ግብርና ሚኒስቴር በሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍ እየተጋዘ ይፈጸማል።
እጽዋትን ስለሚያጠቁ ተባዮች አቶ በላይነህ ያነሱልን ዋና ዋናዎቹን ነው እንጂ ተባዩቹ በርካቶች ናቸው። ለርጭት የሚውል ኬሚካል በበቂ ሁኔታ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄም የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) ድጋፍ እንደሚያደርግም በመግለጽ ምላሻቸውን ገልጸዋል። የተባይ ክስተቱ እጅግ በስፋት በሚስተዋልበት አካባቢ በአውሮፕላን፣ አነስተኛ በሆነበት አካባቢ በመኪና እና በሰው ጉልበት ለመከላከል የሚያስችል አቅም መኖሩን ጠቅሰው፣ በገበሬው አቅም የሚከናወኑትን ግብአቱንም ጭምር በራሱ እንደሚችል ጠቁመዋል። ግብአቶቹም በአገር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ በላይነህ ማብራሪያ፤ የዝናብ ወቅት የተባይ መከሰቻ ወቅት በመሆኑ፣ በቂ ምላሽ ለመሥጠት ተገቢው ዝግጅት ተደርጓል። የተባይ ቅኝት ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎች በመስክ ላይ ሆነው መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ እየሰሩ በመሆናቸው እስካሁን ባለው ከአቅም በላይ የሆነ የተባይ ችግር አላጋጠመም። ከክልሎች እንዲሁም ከዓለም ምግብ ድርጅት ጋር በቅንጅት እየተሰራ በመሆኑ ችግሩ ከአቅም በላይ እንዳይሆን ጥረት እየተደረገ ነው። ተባይን የመከላከሉ ሥራ በመኸር፣ በበጋ መሥኖና በበልግም በተከታታይ በተቀናጀ አሰራር እየተከናወነ ይገኛል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም