አዲስ አበባ በ1888 ዓ.ም የተቆረቆረች የ127 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ብትሆንም በታሪኳ እንደ አለፉት አምስት አመታት የልማት ተቋዳሽ አልሆነችም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከባሕር ጠለል በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን በ1999 ዓ.ም በተደረገው የህዝብ ቆጠራ ወደ 2,739,551 በላይ ሕዝብ ይኖርባታል ቢባልም ዛሬ ላይ የከተማዋ ሕዝብ 5 ሚሊየን ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ይሁንና እስከ አለፉት አምስት አመታት ድረስ ዕድሜዋንም ሆነ ሕዝቧን የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶችም ሆነ መናፈሻዎች አልነበሯትም ማለት ይችላል። ለውጡ ከባተ ወዲህ ግን የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ፤ ነዋሪዎቿንም የሚመጥኑ ግዙፍ ወይም ሜጋ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል። እየተገነቡም ይገኛሉ። መተንፈሻ አጥታት በአየር ዕጥረት ትቃትት የነበረች ከተማ መተንፈስ ጀምራለች።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ዋና ዋና ወንዞች የሚገኙ ሲሆን፤ እነሱም ቡልቡላ፣ ቀበና፣ ሶርአምባ፣ ለኩ፣ ባንች፣ ይቀጡና ጎርደሜ ናቸው። እነዚህ ወንዞች 65 ገባር ወንዞች አሏቸው። በአጠቃላይ እነዚህ ወንዞች 607 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሲሆን፣ ከ2,000 ሔክታር በላይ መሬት በዙሪያቸው ይገኛል። የአዲስ አበባ ወንዞች በሙሉ በትንሹና በትልቁ አቃቂ ወንዞች ተጠቃለው በመጨረሻ ሙሉ በሙሉ አባ ሳሙኤል ሐይቅ ይገባሉ። እነዚህ ወንዞች ከመኖሪያ ቤት፣ ከሆስፒታሎችና ከኢንዱስትሪዎች በሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎች የተበከሉ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ ሕይወት አልባ ሆነዋል።
የትኞቹም ዓይነት ነፍሳት በወንዞቹ ውስጥ መኖር የማይችሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ በተለይ የኢንዱስትሪ ብክለቱ የጎላ ድርሻ ያለው በመሆኑ ወንዞቹ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መዋል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጥናታዊ ጽሑፎች ያስረዳሉ። ከለውጡ ወዲህ ግን በእነዚህ ወንዞች እንደገና ህይወት መዝራት እንዲችሉ እየተሰራ ነው። ባለፉት 5 ዓመታት በጥራትም ይሁን በፍጥነት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
1. የአንድነት ፓርክ
የአንድነት ፓርክ ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2018 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተጀመረ እና ጥቅምት 10/2011 በይፋ ተመርቆ ለህዝብ ክፍት ሆኗል። ፓርኩ በታላቁ ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና ባህላዊ ቦታዎችን ያቀፈ ነው። የአንድነት ፓርክ የሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግስት በ1887 የተመሰረተ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሳይቆጠሩ ቤተ መንግሥቱ የሰባት ኢትዮጵያውያን መሪዎች የመኖሪያና የሥራ ቦታ ሆኖ አገልግሏል። ቤተ መንግሥቱ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን የነበሩ እልፍ አእላፍ ታሪካዊ ሕንፃዎችና እፅዋትን ይዟል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የአንድነት ፓርኪንግ ፕሮጀክት በ9,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ አምፊቲያትር፣ ባህላዊ ሬስቶራንቶች ፣ ሱቆች እና ሌሎች መስህቦችን ያካተተ ነው። የፓርኪንግ ህንጻው ለብሄራዊ ቤተ መንግስት፣ ለሳይንስ ሙዚየም፣ ለወዳጅነት ስኩዌር ምዕራፍ 2 እና እና ለሌሎችም የልማት መዳረሻዎች ከመስቀል አደባባይ እስከ አብርሆት ግራንድ ቤተመጻሕፍት የጎብኚዎች ቀለበት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
2. የወዳጅነት ፓርክ
የወዳጅነት ፓርክ የባህል ማዕከላትን፣ የስነ ጥበብ ጋለሪ እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቦታዎችን ያካተተ 58 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእንጦጦ-አቃቂ ሪቨርሳይድ ውበት ፕሮጀክት አካል ነው። የእግር ኳስ እና የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችን ጨምሮ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመዝናኛ መገልገያዎችን እና የመጫወቻ ሜዳዎችን ያካተተ ነው።
3. የእንጦጦ ፓርክ
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሃሳበ አመንጪነተ የተጀመረው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ግንባታ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ የተጠናቀቀ ነው። የእንጦጦ ፓርክ፤ በ5 የግንባታ ሳይቶች ላይ በርካታ መዝናኛዎችን ያካተተ ነው። ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘልቀው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ከ2 መቶ ዓመታት በላይ የቆዩ ታሪካዊ ቅርሶችን ያካተተ ከኢትዮጵያ ግዙፉ የአርት ጋለሪ የሚገኝበት ነው።
በ5 ሳይቶች ተከፋፍሎ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ፤ በውስጡ የፈረስ መጋለቢያ ሜዳ እስከነ ፈረሶች ጋጥ፣ ባህላዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና በቀድሞ ነገስታት የግብር አዳራሽ አምሳል የተሰሩ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ዘመናዊ ካፊቴሪያዎች እንዲሁም ለጥንዶችና በቡድን ለሚዝናኑ የተዘጋጁ መናፈሻዎች፣ የህዋ መመልከቻ ማማና፣ የብስክሌት መጓጓዣና ሌሎችንም ይዟል።
4. የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት፦
የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት በአዲስ አበባ መሀል ፒያሳ ላይ እየተካሄደ ነው። የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን የአባቶቻቸውን ድል አክብረው ለትውልድ የሚተላለፉበት የጥንካሬ፣ የጀግንነት እና የነጻነት ማሳያ ነው። ፕሮጀከቱ በ4.6 ቢሊዮን ብር ግንባታው እየተሳለጠ ነው።
5. የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት
ይህ ፕሮጀክት በመደበኛነት ከሚሰጠው አገልግሎቶች ጎን ለጎን በአሁኑ ጊዜ ከ 1380 በላይ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ የማቆም አቅም አለው። የከተማው ሜጋ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ፕሮጀክቱን በመግቢያው ላይ በተቀመጠው ጊዜ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀሱ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ብቁ ለመሆን ችሏል። ፕሮጀክቱ ኃይማኖታዊ፣ መዝናኛና ሌሎች ህዝባዊ ዝግጅቶችን ለማክበር ማእከላዊ ቦታ ሆኖ ከማገልገል ተጨማሪ በከተማዋ የሚታየውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጥረትን ለመፍታት ያስችላል። ፕሮጀከቱ በ2.5 ቢሊዮን ብር የተከናወነ ነው።
6. የአብርኆት ሁለገብ ቤተ መፃህፍት ፕሮጀክት፤
በከተማ አስተዳደሩ እየተካሄዱ ካሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የህዝብ ቤተመፃህፍት ፕሮጀክት በፍጥነት ተገንብተው ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ።”አብርኆት”በሚል ተመርቆ የተከፈተው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከ1 ቢሊየን 115,977,250 ብር በላይ ወጭ ሆኖበታል። ይህ ፕሮጀክት የከተማው ወጣቶች ቤተመፃህፍትን ከማግኘት ጋር የተያያዙ ችግሮችን እና በጤንነታቸው እና በአእምሯዊ ፋኩልቲ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያላቸውን ተግባራትን የሚቀርፍ ነው። በ1.8 ሄክታር መሬት ላይ የተዘረጋው ይህ ቤተመፃህፍት 35000 ተጠቃሚዎችን ለ113 አውቶሞቢሎች የመኪና ማቆሚያ ቦታ የሚያስተናግድ ሲሆን ዘመናዊ የአይሲቲ ፋሲሊቲዎችንም ያካተተ ነው።
7. የሳይንስና የስነ ጥበብ ሙዚየም
በአይነቱ አዲስና ልዩ የሆነው የሳይንስና የስነ ጥበብ ሙዚየም ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልህቀት የሚመጥን ሆኖ የተገነባ ሲሆን ለኢትዮጵያም የቴክኖሎጂ እድገት ትልቅ መሰረት የሚጥል ሙዚየም እንደሆነም ታምኖበታል። ሙዚየሙ በ7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በኪነ-ህንጻ ንድፍ ውስጥ ያካተተው ክብ ቅርጽም በማያቋርጥ እድገት ውስጥ ያለን እድገትና የሰው ልጆችን ጥበብ የሚያመለክት ነው ተብሏል። ትልቁ ህንጻ ከ15ሺህ ሜትር ካሬ በሚበልጥ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አጠቃላይ ስፋቱ 132 ሜትር ያህል ነው።
8. የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እድሳት ፕሮጀክት
የከተማ አስተዳደሩ በ57 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዘጋጃ ቤቱን ዋና መስሪያ ቤት ለማደስ በአጠቃላይ 2.2 ቢሊዮን ብር ፈሰስ አድርጓል። የእድሳት ስራው የመሬት አቀማመጥ፣ ቢሮዎችን እና ባለ 850 መቀመጫዎች ያሉት የቲያትር አዳራሽ ማደስ እንዲሁም በማዘጋጃ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የልጆች መጫወቻ ስፍራን የመሳሰሉ አዳዲስ መገልገያዎችን በማካተት 50,000 ስኩየር ሜትር አካባቢን ያካተተ ነው።
8. በአዲስ አበባ የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች፡-
ከቁስቋም እስከ እንጦጦ 4.3 ኪሜ ርዝመትና 16 ሜትር ስፋት፣ ከእግረኛ መንገድ ጋር ሽሮ ሜዳ እስከ ቁስቋም 2.6 ኪሜ ርዝመት እና 30 ሜትር ስፋት ፤ ከወሎ ሰፈር እስከ ዑራኤል1.4 ኪሜ ርዝመትና 35 ሜትር ስፋት፤ ላ ጋሬ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አደባባይ 1.56 ኪሜ ርዝመት እና 13 ሜትር ስፋት፤ ከገርጂ ሮባ እስከ መብራት ሃይል – 973ሜ ርዝመትና 30ሜ፤ ከወይራ እስከ ቤቴል 1.4 ኪሜ ርዝመት እና 20 ሜትር ስፋት፤ ሲኤምሲ ሚካኤል በላይ ማለፍ – 680ሜ ርዝመት እና 30ሜ፤ ከራስ ደስታ እስከ ቀጨኔ 2.5 ኪሜ ርዝመት እና 20 ሜትር ስፋት፤ ከኃይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ 4.5 ኪ ሜ ርዝመትና 120 ሜትር ስፋት ያለው የብስክሌት ትራክ፣ የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ቦታ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ያለው ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሁላችንም በአእምሮአችን ጓዳ ያለውን ሀሳብ፣ በጓሮአችንና በደጃችን፣ በማህበረሰባችን፣ በከተማችን ከፍ ሲልም በአገራችን ያለውን እምቅ ሀብት አይናችን ከፍተን ማየት ባለመቻላችን እንደ አገርም ሆነ ሕዝብ መክሊታችንን ሳናገኝ በምድረ በዳና በበርሀ ስንባዝን መኖራችንን ያመለክታሉ።
በአንጻሩ በደጃችን፣ በጓሮአችንና በአካባቢያችን የፈሰሰውን ጸጋ መመልከት ብንችል ምን ያህል ልንበለፅግና ልንለማ እንደምንችል ያሳያሉ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር በ” ሸገርን ማስዋብ”ፕሮጀክት ማለትም በአንድነት ፓርክ፣ በኢዮበልዩ ቤተመንግስት፣ በእንጦጦ መዝናኛ ፓርክና በአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ልማት በአጭር ጊዜ አይናችንን ከፍተው በደጃችንና በጓሮአችን የተትረፈረፈውን ሲሳይ አሳይተውናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዙሪያ ገባችን እንቁ እንደሆነ በይቻላል መንፈስ፤ “ ትልቅ እናልማለን በትንሽ እንጀምራለን፤ በተግባር ሰርተን እናሳያለን፤ ከብልፅግና የሚያቆመን ኃይል የለም። ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ታላቅነቷ እንመልሳለን፤ ወዘተረፈ “ ባሉት መሰረት ግርዶሹን ገፈው፣ መጋረጃውን ቀደው፣ ሀሳብ አፍልቀው ፣ ሀብት አፈላልገው፣ የአካባቢ ግብዓት፣ የአገር ቤት ባለሙያ ከያለበት ጠርተው፣ አቀናጅተው እየመሩ፤ ለዛውም በደባ ፖለቲካ አገር እየታመሰች፣ ጽንፍና ጽንፍ በረገጠ ዘውጌያዊነት አገር እየተላጋች፤ ሌት ተቀን፣ ከቀኝ ከግራ ቀውስ ጎናቸውን ቀስፎ ይዟቸው እያለ፣ የጦርነት ነጋሪት አንድ ጊዜ ከሰሜን ሌላ ጊዜ ከምዕራብ እየተጎሰመ በነበረበት፤ እንደ አገር ጥሩ ዜና ብርቅ በሆነበት፣ ተስፋ በመነመነበት በአድናቆት እጅን በአፍ የሚያስጭን፣ አይናችንን ማመን እስኪቸግረን ታምር አሳይተውናል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ከክሽፈት በመታደግ፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ በኩታ ገጠም ግብርናና በበጋ ስንዴ ልማት፤ ወዘተረፈ ተስፋችንን አለምልመውታል። ትክክለኛ አመራር ካለና ከተሰራ ብልፅግና ላም አለኝ በሰማይ ሳይሆን የሚደረስበት፣ የሚዳሰስ፣ የሚቀመስና የሚጨበጥ መሆኑን አይናችንን ከፍተው አስመልክተውናል። ታሪካችን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንና ዜጋችን ወደ አልማዝ እንደሚቀየር አሳይተውናል።
እንጦጦና የአዲስ አበባ ወንዞች ለዘመናት ነበሩ። የኢዮበልዩ ቤተ መንግስትም ሆነ በስሩ ያሉ ቅርሶች ለዓመታት ነበሩ። የአገር ሲሳይና ጸጋ መሆናቸውን ግን እስከዛሬ ያሳየን ማንም አልነበረም። እንጦጦ እናቶች ጀርባቸውን የሚልጥና ትክሻቸውን የሚያጎብጥ እንጨት የሚለቅሙበት ጫካ ነበር። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ምስጋና ይግባቸውና ዛሬ እንጦጦ የጎብኝዎች መዳረሻ እና ህሊና ዘና የሚልበት አድርገውታል።
ከዚህ በላይ ማለም፣ ማቀድና መተግበር እንደሚቻል በተግባርና በምሳሌ ሌት ተቀን ሰርተው አሳይተውናል። ለእኔ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ከፕሮጀክትም በላይ የብልፅግና ራዕይ የተገለጠበት፤ የብልፅግና ፍኖተ ካርታ የተነደፈበት፤ ቃል የእምነት እንጂ የአባት እዳ ካለመሆኑ በላይ ስጋ ለብሶ ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት አሻራ ነው። አገራችን ሰላምና ፍቅር ብትሆን፤ ዜጎቿ አንድ መሆን ብንችል፤ የሴራ ፖለቲካ ባይኖር፤ ጥላቻና መጠራጠር፤ ምቀኝነትና መጠላለፍ፤ ሌብነትና ስግብግብነት፤ ወዘተረፈ ቢወገድ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር እንዴት ያለ ተአምር ሊያሳዩን እንደሚችል የተረጋገጠ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
ከሁሉም በላይ የልቦና የአስተዳደር ውቅራችን በአዲስ የበየነ ክስተት ነው። ዘጋቢ ፊልሙ ለሕዝብ ከመለቀቁ አንድ ቀን በፊት የማየት እድሉን ያገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የአደባባይ ምሁርና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ሲሣይ መንግስቴ ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በእርግጥም ለዚች አገር አስደናቂ የሆነ ራዕይና ብሩህ ተስፋ ያላቸው መሪ መሆናቸውን በተግባር አሳይተውና። ራዕይ ካለና የይቻላል መንፈስ ከተያዘ ታዕምር መስራት እንደሚቻል የሚያሳይ አስደናቂ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምጣት እንደሚቻል መመልከታችንን መመስከር ተገቢ ነው ይላሉ። ዶ/ር ሲሳይ በማከልም በትብብር ከተሰራም ተስፋ ሰጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታል ብለዋል።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
ቁምላቸው አበበ በአማራ ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፤ በደቡብ መገናኛ ብዙኀን፤ በጋዜጠኝነትና በታሪክ ባለሙያነት ያገለገሉ ሲሆን፤ የደቡብ ኤፍ ኤምን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም አቋቁመዋል። በፌዴራል ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በአለ በጅምላ በኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። ከአአዩ በቋንቋና ታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን፤ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ተስተጓጉሏል። ጥልቅ ሀሳብ ያዘሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ፁሑፎችን በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ ጋዜጦች በማውጣት ይታወቃሉ።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም