አንዳንዴ የነገሮችን መደጋገም ጆሯችን ይለምድና ልባችን ይደነድናል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ድንጋጤ ይሉት ስሜት ከውስጣችን ይርቃል። ሁኔታው እንደሁልጊዜው በጆሯችን አልፎ በስሱ ነክቶን ሲያልፍ ሳናስበው ከነገሮች እንስማማለን። ይህኔ መቼም ቢሆን ዜናው አልያም መረጃው ብርቃችን አይሆንም።
ወደጆቼ! እንዲህ ለማለት መድፈሬ ያለምክንያት አይደለም። በየጊዜው ከሚገጥሙኝ እውነታዎች ተነስቼ እንጂ። ለዚህ አባባሌ በቀላሉ ከአንድ ምሳሌ ላገናኛችሁ። የሆነ ቦታ አረፍ ብላችሁ ጨዋታ ይዛችኋል እንበል። ያላችሁበት ስፍራ መሀል ከተማ ከመንገድ ዳር ሊሆን ይችላል።
እናንተ እየሳቃችሁ፣ እያወራችሁ ጨዋታ ቀጥላችኋል። ድንገት ግን የሞቀ ጨዋታችሁን የሚነጥቅ ሀይለኛ ድምጽ ወደጆሯችሁ ይደርሳል። ድምጹ ጆሮን ብቻ ሳይሆን ቀልብን ጭምር የሚገፍ ነው። ሁላችሁም ድምጹ ወደመጣበት አቅጣጫ ፊታችሁ ይዞራል። ወዲያው ዓይናችሁ ፈጥኖ ከምክንያቱ ያደርሳችኋል። አካባቢውን ያናወጠው ሀይለኛ ድምጽ ተከታትለው ከሚሄዱ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪኖች የሚወጣ ጡሩንባ ነው።
መኪኖቹን ተከትለው አምቡላንሶች ይከንፋሉ። ለአምቡላንሶቹ ቦታ ለመልቀቅ የሚራወጡ መኪኖች መድረሻ አጥተዋል። እግረኞች ቆም ብለው ሁኔታውን ይቃኛሉ። ይህን ሁሉ ዓይናችሁ በወጉ ያስተውላል። ልባችሁ ግን ፈፅሞ አልደነገጠም። እናንተ በሁኔታው ደንታ እንዳልሰጣችሁ ግልጽ ነው። በዓይናችሁ ነገሩን በዋዛ ሸኝታችሁ ፊታችሁን ወደ ጨዋታው መልሳችኋል። የሚገርመው ነገር ከተሰማው ድምጽ በስተጀርባ ከባድ አደጋ መከሰቱ ነው።
ምንአልባትም በዚያች ቅጽበት እርዳታን የሚሹ ከእሳት የገቡ ነፍሶች ጭንቅ ውስጥ ናቸው። ይህን እውነት እናንተም አሳምራችሁ ታውቃላችሁ። ያም ሆኖ አንዳችሁም ደንታ አልሰጣችሁም። ለአሳሳቢው ጉዳይ የሰከንድ ጥሞና ሳትቸሩት ወደ ጉዳያችሁ ገብታችኋል።
እንደኔ እንዲህ መሆኑ ለእኔና ለእናንተ ብርቅ አይደለም። ይህ አይነቱን አጋጣሚ ጨምሮ ሌሎች አሳሳቢ የሚባሉ እውነቶችን ጆሯችን መላመዱ ግዴለሽነትን አዋርሶናል። በየጊዜው፣ ምንአልባትም በየቀኑ ገጠመኙ መከሰቱ ልብን ያደነድናል። እንደ ልማድ ሆኖም ከእኛነት ጋር ዝምድናን ይፈጥራል።
የእሳት አደጋውን ምልክትና ጆሮ ገቡን ሀያል ድምጽ ከልብ እናጢነው ከተባለ ድንገቴው ጉዳይ እንደሰው ሊያስጨንቅ፣ ሊያስደነግጠን በተገባ ነበር። ግን ይህ ሊሆን አልቻም። ስለምን ካልን ደግሞ ሚስጥሩ ከነገሮች መላመድ ጋር ይያያዛል።
ይህን ምሳሌ እንደመነሻ ልጥቀስ እንጂ በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ጭምር በየዕለቱ ችግሩን በግልጽ እናየዋለን። እነዚህን ሁነቶች በየቀኑ ጆሯችን መልመዱ ደግሞ ከባዱን እውነት አቅልለን እንድንቀበል፣ አሳሳቢውን ጉዳይም የተለመደ እንዲመስልብን አድርጎናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደልምድ የተቆጠረው የህጻናት መጥፋትና የንብረት ዘረፋ አብሮን የኖረ ያህል ከህይወታችን መቆራኘቱን ልብ ይሏል። ይህ እጅግ አሳሳቢ የሚባል እውነት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በ‹‹አፋልጉኝ›› ጥሪ ተማጽኖው ያስተጋባል። ተጎጂዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለተመልካች ቀርበው በዕንባ እየታጠቡ ‹‹እርዱን፣ ድረሱልን›› ይላሉ። ለሁኔታው ግን አንዳንዴ ትኩረት ያላቸው የሉም ማለት አይደለም።
በአብዛኛው ይህ አይነቱን እውነት ደጋግሞ የሚያውቅ ዓይምሯችን ግን በታሰበው ልክ አይደነግጥም። አሁንም ሚስጥሩን እንመርምረው ከተባለ ለዚህ አይነቱ ስሜት ምክንያቱ ከሁኔታዎች የመላመድ እውነት ላይ ያደርሰናል።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የህክምና እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ፎቶግራፍ የለጠፉ መኪኖች በየቦታው ማየትን ለምደናል። ሁሉም ናቸው ባይባልም መኪኖቹ በአብዛኛው ለኩላሊትና ካንሰር ተጠቂ ህሙማን ገንዘብ የሚያሰባስቡ ናቸው። በተለይ አሁን ላይ በመንገዳችን የአፍታ ልዩነት ታማሚዎቹን ጭምር በአካል ማየት ልምዳችን ሆኗል።
ነገሮች በዚህ መልኩ ይበራከቱ እንጂ በውስጣችን የሚያድረው አዘኔታ የችግሩን ያህል አይደለም። እንደውም አንዳንዴ የተለመደውን ‹‹ደራሽ ለወገኔ››ን ዜማ እንደቀልድ አብረን እያዜምን ልናልፍ እንችላለን። ይህን ማድረጉ አያስከፋም። አሁንም ግን ለችግሩ ትኩረት ለመስጠት ሁኔታውን የመላመዳችን ሀቅ ዋናውን ጉዳይ ያለመፍትሄ እንድንረሳው ምክንያት ሆኗል። በተለይ የዚህ ዜማና የእርዳታ ሚኒባሶቹ መጣመር የዝምድና ያህል ቀርበውን በእኛነታችን ላይ ባዕድነትን አውጀዋል።
አሁን ያለንበት ዘመን ችግርና መከራ፣ ስደትና ሞት፣ ሽብርና ጦርነት የማያጣው ፈታኝ ጊዜ ሆኗል። ይህ ጫፍ ደግሞ እኛን ጨምሮ ከመላው የዓለም ጥግ የሚያደርሰን እውነታ ነው። አንዳንዴ በእነዚህ አጋጣሚዎች መሀል የምንሰማው ክፉ ዜና አንገት ያስደፋል፤ ለመኖር፣ መተንፈስ፣ ነገን ለማሰብ ጭምር ስጋት ይሆናል።
በየዕለቱ በነዚህ ችግሮች መሀል የሚከፈለው የህይወት ዋጋ ደግሞ ያለማጋነን ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ ታሪክን የሚለውጥ ነው። እንደውም አንዳንዴ በማንኛውም ምክንያት በከፍተኛ አሀዝ የሚገለጸውን የሰው ልጆች ሞት ሰምቶ ማመኑ ይከብዳል። የሚሆነው ሁሉ ልቦለድና ተረት ቢመስልም ድርጊቱ ግን በዕውን እየተፈጸመ መሆኑን ልቦና ያውቃል።
አሁን ላይ ግን ችግሩ ምንም ይሁን፣ ቁጥሩ የትም ይድረስ በጉዳዩ መጨነቅ የተውን በርክተናል። አንዳንዶቻችን በመንገዳችን የአስከሬን መኪና ሲያልፍ የምንደነግጠውን ያህል እንኳን የበርካቶች ሞትና ጉዳት ስሜት አይሰጠንም። መደንገጡ ቀርቶ ጆሮ ሰጥቶ ማድመጡ ሁሉ ያስጠላናል።
የአንዳንዱ ደግሞ ይብሳል። ለእሱ ዜናው፣ አልያም ምርጡ ጉዳይ ሙዚቃና ስፖርት ብቻ ነው። ይህ አይነቱ አሳዛኝ ወሬ ፍፁም አይመቸውም። መረጃው የደረሰው በቴሌቪዢን ከሆነ ፈጥኖ ሪሞት ለማንሳት አይዘገይም። በሬዲዮ ከሆነም ጣቢያ ለመቀየር የሚቀድመው የለም።
አሁን አሁን በየቀኑ ለጆሮ የሚደርሱ ተመሳሳይ መረጃዎች ለሰሚው ብርቅ ያለመሆናቸው ጉዳይ በእጅጉ ተለምዷል። እንዲህ መሆኑም በብዙዎቻችን ውስጠት ስሜት አልባነትን እየፈጠረ ነው። ልብ አላልነው ይሆናል እንጂ ይህ አይነቱ ምልክት በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚታይ አይደለም። መጠኑ ቢለያይም በእያንዳንዳችን ማንነት ውስጥ መንጸባረቅ ጀምሯል።
ሌሎችም ሆኑ እኛ ለምን ተብለን ብንጠየቅ ደግሞ ምላሻችን ተመሳሳይ ይሆን ይመስለኛል። ለምንስማቸው ከባድ ጉዳዮች ሁሉ ውስጣችን በከባድ ስሜት ያለመያዙ ሚስጥር ጆሯችን ለመረጃው ለማዳ የመሆኑ ጉዳይ ነው። የዚህ አይነቱ ልምምድና ድግግሞሽም ህይወትን እንደዋዛ እንድናየው፣ ሞትና ችግርን እንድናቀለው፣ ብርቅ የሚባሉ አጋጣሚዎች ብርቅ እንዳይሆኑብን ሰበብ ሆኗል። ጆሯችን በልቶ ሲጠግብ ልቦናችን የዘነጋውን ታላቅ ጉዳይ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም