በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን እየገጠሟት ላሉ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የዘመኑ ወደር የለሽ ሳይንስ ነው፤ ባዮ-ቴክኖሎጂ። በተለይ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከምግብ አቅርቦት፣ ፋብሪካ ምርት፣ ከጤና (ክትባትና ሌሎች መድሃኒቶች ማምረት)፣ ከአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሃብትን ተንትኖ ከማወቅና ለእነዚህ እንደግብዓት ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት ያለ መስክ ነው።
እንዲሁም ባዮ-ቴክኖሎጂ አካባቢን በንጽህና ለመያዝና የተራቆቱ ሥርዓተ-ምህዳሮችን መልሶ ለማቋቋም፣ የኢንዱስትሪና የግብርና ተረፈ ምርቶችን መልሶ በመጠቀም ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግና ከባቢያዊ ብክለትን ከማስወገድም ባሻገር ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዚህም ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የተያያዘችው ጉዞ የሰመረና ውጤታማ እንዲሆን በርካታ የባዮ-ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራዎችን በማመንጨት ወደ ኅብረተሰቡ ለአገልግሎት የማሸጋገር ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በዚህ የሳይንስ ዘርፍ ላይ እንደአገር ምርምሮችን እያደረገ የሚገኝው የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው። ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ የጨቅላ እድሜ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ ዘመናዊና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ አንዳንድ የምርምር ሥራዎቹን ከሼልፍ ላይ በማውረድ የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወደ ሚያግዝበት ደረጃ በመሸጋገር ላይ ይገኛሉ።
እንዲሁም ተቋሙ ባደረገው የምርምር ሥራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ ምርቶችን በቤተ ሙከራ ደረጃ ማምረት መቻሉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
እርሳቸውም ተቋሙ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ምርምሮችን እንደገለጹት፤ የቆዳ ኢንዱስትሪ ሴክተር ላይ የተበላሸ ቆዳና የቆዳ ተረፈ ምርት እሴት ተጨምሮበት መልሶ ጥቅም ላይ መዋል እየቻለ ምንም ጥቅም ሳይሰጥ በቀጥታ ይጣላል። እንዲሁም ቆዳ በየቦታው ሲጣልም ይስተዋላል። ሆኖም ከቆዳ ተረፈ ምርትና ከተበላሸ ቆዳ ጀላቲን/gelatine (ለተለያዩ ምርቶችና መድሃኒቶች ማጣበቂያነትና ማሸጊያነት የሚውል ፕላስቲክ) በቤተ ሙከራ ደረጃ ማምረት ተችሏል።
ነገር ግን በአገር ውስጥ ምርት መተካት እየተቻለ ጀላቲን አሁን ድረስ ከውጭ ይገባል። ስለዚህ በቤተ ሙከራ ደረጃ ጀላቲን ማምረት ተችሏል። በቀጣይ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት ፋርማስቲካል ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ጀላቲን የማምረት ሥራ እንደሚሠራ ይናገራሉ።
ሌላኛው የእንጨት ፋብሪካዎች ቺፑድ ወይም ኮፒስታቶ ለመስራት ሙሉ ለሙሉ እንደግብዓት የሚጠቀሙት እንጨት ነው። ነገር ግን ከደን መመናመን፣ ከሚጠይቀው የኃይል አቅርቦት፣ ወጪና የሰው ኃይል አንጻር ቺፑድን ሙሉ ለሙሉ ከእንጨት ከማምረት ይልቅ በከፊል በየሜዳው የሚወድቀውን የቡና ገለባ ወይም ግልፋፊ መጠቀም አይቻልም ወይ? የሚል ምርምር መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
50 በመቶ የቡና ገለባ ወይም ግልፋፊ እና 50 በመቶ ደግሞ እንጨትን በመጠቀም ቺፑድ የማምረት ምርምር ተከናውኗል። በዚህ መልኩ የተሠራው ቺፑድ ጥንካሬውና ጥራቱ ተፈትሾ ሙሉ ለሙሉ ከእንጨት ከተሠራው ጋር ተመሳሳይ ነው። ምንም ልዩነት የለውም። የምርምር ውጤቱ የደን መመንጠርን 50 በመቶ የሚቀንስ እንዲሁም የፋብሪካዎችን የኃይል አቅርቦት፣ ወጪና የሰው ኃይል ፍላጎት በከፊል በመቀነስ ምርትና ምርታማነታቸውን የሚያሳድግና በኢኮኖሚ ትርፋማ የሚያደርጋቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
ከዚህ ባሻገር ኢንስቲትዩቱ ውጤታማ ያደርገኛል ብሎ እየሠራው ያለው የምርምር ሥራ የማይክሮ አልጌ ፕሮጀክት ነው። በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሚገኙ አብያታ፣ ሻላና ጪቶ ሀይቆች ውስጥ ከፍተኛ የማይክሮ አልጌ ሀብት አለ። ይህ አልጌ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፕሮቲን መጠኑና ለሰው ልጅ በሚያስፈልጉ የምግብ ይዘቶች መጠን በእጅጉ የዳበረ እምቅ የሆነ አልጌ ነው። ይህን አልጌ ከሀይቆቹ በመውሰድ በቤተ ሙከራ ደረጃ ለምግብነት መዋል የሚችል ንጹህ አልጌ ማምረት ተችሏል።
ቀሪው ሥራ በቤተ ሙከራ የተመረተውን ለምግብነት የሚውለውን ንጹህ አልጌ እዛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ለማምረት የአልጌ ማምረቻ ገንዳ ወይም ጉድጓድ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ስለዚህ ከቤተ ሙከራ ወጥቶ በጉድጓድ ለምግብነት የሚውል ንጹህ አልጌ ማምረት ከተቻለ በኋላ ዘርፉ ለኢንቨስትመንት ክፍት ይደረጋል።
ይህም የረብጣ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚስብ ፕሮጀክት ነው። እንደአገርም ለወደፊት ትልቅ የኤክስፖርት አቅም የሚፈጥር ነው። እንዲሁም በአአገሪቱ ከሚስተዋለው የመቀንጨር ችግር አንጻር ማይክሮ አልጌን እንደቅመም ከምግቦች ጋር ጨምሮ ለልጆችና ለነፍሰጡር እናቶች በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በአጠቃላይ ከብረት ፋብሪካ የሚወጣ ተረፈ ምርትን ወደ ቀለም ፋብሪካ ግብዓትነት መቀየር፣ ሽንብራን ለጾም ማኪያቶነትና ለህጻናት ምግብ ማዋል፣ ከድንች ተረፈ ምርት ባዮ ፕላስቲክ እና ከእምቦጭ ወረቀት ማምረት ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ ምርቶችን በቤተ ሙከራ ደረጃ ማምረት ተችሏል። በመሆኑም አምራች ኢንዱስትሪዎች የኢንስቲትዩቱን የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር ቢቀይሩ ውጤታማና ትርፋማ እንደሚሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ከፍተኛ የምርምር ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት የፈሰሰባቸውን እነዚህ የምርምር ውጤቶችን አምራች ኢንዱስትሪዎች ወስደው ወደ ምርትና አገልግሎት ሲቀይሯቸው አይስተዋልም። ይህም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከማሳጣቱ ባሻገር በዘርፉ ለሚደረጉ ምርምሮች ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ሳትጠቀምበት እንድትቀር የሚያደርግ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ እነዚህን የምርምር ሥራዎች ወደ ህብረተሰቡ ደርሰው ለአገልግሎት እንዲበቁ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የማሸጋገር ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ይኖርበታል።
በተጨማሪም መንግሥት አዋጭ የሆኑ የባዮ ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራዎችን አምራች ኢንዱስትሪዎች ወስደው ለአገርና ህዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት በሚያመጣ መንገድ ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲቀይሩ አስገዳጅ ሕግ ወይም መመሪያ ሊያወጣ ይገባል።
እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እንዚህን የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራዎችን ከሸልፍ ላይ በማውረድ ከላብራቶሪ ምርትነት ባለፈ በስፋት ህብረተሰቡ ወደ ሚገለገልበት ምርትና አገልግሎት ቢቀይሩ ውጤታማና ትርፋማ ይሆናሉ። ከራሳቸው አልፈውም ለአገር ምርትና ምርታማነት እድገት የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ።
በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ባለሀብቱ እንጀራ ጋግሮና ወጥ ሰርቶ ከመሸጥ እንዲሁም ስሚንቶ አብኩቶ ህንጻ ገንብቶ ከማከራየት የመሳሰሉ ኋላቀርና አዋጭ ካልሆነ የቢዝነስ ዓለም ተላቆ ወደ ዘመኑ አዋጭ የባዮ-ኢኮኖሚ ሥርዓት መግባት ይኖርበታል። በዚህም በትንሽ ካፒታል እራስንም አገርንም በሚቀይሩ የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በመሰማራት በአጭር ጊዜ የሚሊየነሮችን ጎራ መቀላቀል ይቻላል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም