የአገራችን ብሎም የመዲናዋ አዲስ አበባ ሴቶች ከሚያጋጥማቸው ችግሮች አንዱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው። ይሁንና ይህን ኢኮኖሚያዊ ችግር በትዕግስት ተቋቁመው በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ሴት የባሏን እጅ ጠባቂ የሚያደርገውን የተሳሳተውን የማህበረሰቡን አመለካከት መለወጥ የቻሉ በርካታ እንስቶች አሉ። በይቻላል መንፈስ ተነስተው ችለው ያሳዩንን በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንጻሩ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ደግሞ ሴተኛ አዳሪነትን ጨምሮ በአስቸጋሪ ስራዎች ላይ ጭምር በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ሲጥሩ ይታያል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት በአዲስ አበባ ከ15ሺህ በላይ በሴተኛ አዳሪነት እንደተሰማሩ ጠቁሟል። ከነዚህ ዓመታት ወዲህ የተደረጉ ጥናቶችን ማግኘት ባንችልም፣ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ሰው ሰራሽ (ጦርነት) እና ተፈጥሯዊ ችግሮችን (ኮቪድ እና ድርቅ) ተከትሎ በተፈጠሩ ምስቅልቅሎች ምክንያት አሀዙ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡
ለሴተኛ አዳሪነት እና ሴቶችን የሚያጋጥሟቸውን ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ነበር፡፡ ከነዚህ ጥረቶች መካከል በዚህ ተግባር ላይ ለተሰማሩ ሴቶች የስራ መጀመሪያ ብድር፣ የመስሪያ ቦታ፣ ስልጠናና የመሳሰሉትን በማመቻቸት ቋሚ የኢኮኖሚ አቅም እንዲያዳብሩ ማድረግ አንዱ መንገድ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በከተማዋ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የሴተኛ አዳሪነት ህይወትን ለማስቀረትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት አላስቻለም፡፡ ችግሩን ለመፍታት ያልተቻለበት ዋነኛው ምክንያት የተከናወኑ ተግባሮች ችግሩን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ባለመሆናቸው ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አሁንም ቀጥሏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳና ላይ የወጡ ሴቶችን ካሉበት ችግር ለማላቀቅ የሚያግዝ ማዕከል ግንባታም በቅርቡ ተጀምሯል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ማእከል በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና የሚያገኙበት ነው፡፡
ኢንጂነር ዙሪያወርቅ ወዳጆ በአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ግንባታ ተወካይ ናቸው፡፡ ኢንጂነር ዙሪያወርቅ እንደሚናገሩት፤ በማዕከሉ የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ይሰጣል፤ የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠናው ተጠቃሚ የሚሆኑት ደግሞ በዋናነት ከጎዳና የሚነሱ ሴቶች ናቸው፡፡ በራሳቸው የመማር አቅም የሌላቸው፣ ሙያ ነክ ስልጠናዎችን መውሰድ እየፈለጉ ስልጠና መውሰድ ያልቻሉ ሴቶችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ስልጠና እንዲያገኙ የሚደረግበት ይሆናል፡፡
በአንድ ጊዜ 2000 ሴቶችን የሚያሰልጥንና የክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ሲሆን፣ በዓመት ደግሞ እስከ 10ሺህ ሴቶች የተለያዩ ሙያ ነክ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ የሚያደርግ ትልቅ ማዕከል ነው፡፡ የማዕከሉ ስልጠና ሴቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚያገኙትን ክህሎት በመጠቀም ራሳቸውን እና አገራችውን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ያስችላል።
ማዕከሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፤ የጎዳና ሴቶችን ከችግር ከማላቀቅ ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድ የላቀ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ የጎዳና ላይ ሴቶችን አንስቶ የክህሎት ባለቤት እና አምራች እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ የከተማዋን ገጽታም በመሰረታዊነት ይቀይራል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የማዕከሉን ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የአገሪቷን ወይም የከተማዋን ሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ብቻውን ይፈታል ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን በዋናነት በአዲስ አበባ ለተለያዩ ችግሮች ከተጋለጡ ሴቶች መካከል የተወሰኑት በማዕከሉ የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ወስደው የተወሰነ ድጋፍ ቢደረግላቸውና ለስራ ስምሪት የሚሆን ድጋፍ ቢሰጣቸው ለሌሎች ምሳሌ ይሆናሉ፡፡
በአዲስ አበባ የሚመጣው ለውጥ ለክልል ከተሞችም መነቃቃትን የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ከንቲባዋ ጠቅሰው፣ በመገንባት ላይ ያለው ማዕከል ሴቶች ችግር ሲያጋጥማቸው እና ህይወት ስትጨልምባቸው መግቢያ ቤታቸው እና ማረፊያቸው፣ የጠወለገ ተስፋቸው የሚለመልምበት ስፍራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ቀጣይ ህይወታቸው እንዲቀየር እና ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲሸጋገሩ ታስቦ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
‹‹አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መልካም ቤት እንደመሆኗ፤ በአዲስ አበባ ጎዳና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለሴተኛ አዳሪነት እና ለሌሎች ማህበራዊ ችግሮች በተጋለጡ ላይ ሊፈረድባቸው ሳይሆን ሊደረስላቸው ይገባል›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ለነዚህ ወገኖች የሚደረስላቸው አንዱ መንገድ የተሃድሶ እና የክህሎት ስልጠናዎችን በማቅረብ እንዲሁም እንዲህ አይነት የተሃድሶ እና ስልጠና ማዕከላትን በማስፋፋት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ማዕከላትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ማዕከላቱ የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው የሚገባ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ሌሎች ማዕከላት ላይ ሲያጋጥሙ የነበሩ ማዕከላትን ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ የማዋል ሁኔታዎች እንዳይኖሩ የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
እንደ ኢንጂነር ዙሪያወርቅ ማብራሪያ፤ ለማእከሉ ግንባታ ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በጀት ተይዞለታል፤ በ50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይም ያርፋል፤ በውስጡ እያንዳንዳቸው 640 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፉ 12 ህንጻዎችንም ያካትታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ህንጻዎች ጂ+1 (G+1) ናቸው፡፡ ስድስት ህንጻዎች እንደ መኝታ ቤት /ዶርም/ የሚያገለግሉ ሲሆኑ፣ አንድ ህንጻ ደግሞ ለአስተዳደር አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ከ2000 በላይ ሴቶች ለማሰልጠን የሚያስችል ሲሆን፣ በዓመት እስከ 10ሺህ ሴቶች የተሃድሶ እና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ያስችላል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ ግንባታውን በ13 ወራት ወይም በ395 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ለማጠናቀቅ እቅድ እንደተያዘለት ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በማዕከሉ ውስጥ ከሚገነቡ ህንጻዎች ባሻገር ሙሉ 50 ሺህ ካሬው ላይ የተለያዩ የማስዋቢያ ስራዎች የሚሰሩበት ሲሆን፣ ማሰልጠኛ ክፍሎችን የሚያገናኙ የአስፋልት መንገዶችም እንደሚኖሩት ጠቁመዋል። ማዕከሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም ይኖሩታል፡፡ የራሱ የሆነ የካሜራ ሲስተም፣ የዳታ ማዕከልን ጨምሮ ዘመናዊ ማዕከላት ማሟላት ያለባቸውን መሰረተ ልማቶች ያሟላ እንደሚሆንም ኢንጂነሩ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ተወካዩ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ የዲዛይን እና የግንባታ ስራዎች በአንድ ወቅት ጎን ለጎን እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ የመኝታ ቤቶቹ ህንጻ /የማደሪያ ዶርሙ/ ከመሬት በታች የሚሰሩ አብዛኛዎቹ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ስልጠና የሚሰጥባቸው ህንጻዎች የዲዛይን ስራዎች እየተሰሩ ነው። የዲዛይን ስራዎቹ እንደተጠናቀቁ የቁፋሮ ስራዎች ይጀመራሉ፡፡
ባለፈው ሰሞን በተከታታይ የጣለው ዝናብ ለቁፋሮ ስራ አመቺ አለመሆኑን ተከትሎ የግንባታ ስራው የተወሰነ መጓተት እንደተፈጠረበት የጠቀሱት ኢንጂነር ዙሪያወርቅ፤ እንዲያም ሆኖ ግን ዝናቡ ሲቆም የቁፋሮ ስራዎች መሰረታቸውንም ገልጸዋል፤ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በሜጋ ፕሮጀክቶች የማእከሉ መገንባት አገራዊ ጠቃሜታ ከፍ ያለ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የአካባቢው አስተዳደር አካላት በተለይም ክፍለ ከተማው እና ወረዳው ለፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥተው ትብብር እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ትብብር እና ቅንጅት ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ እንደ ሌሎቹ ፕሮጀክቶች ሁሉ በሲሚንቶ ችግር እየተፈተነ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂነር ዙሪያወርቅ፤ ችግሩን ለመፍታት በተቻለ መጠን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት። ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር ደብዳቤ በመጻጻፍ ሲሚንቶ እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ኢንጂነር ቴዎድሮስ ተበጀ የሳይት መሃንዲስ አማካሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ብሎክ ኤ (A) ወይም የዶርም ህንጻ የቁፋሮ ስራ ተጠናቋል፣ ብሎክ ቢ (B) እና ብሎክ ሲ (C) ላይ ደግሞ የመሰረት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። ብሎክ ዲ (D) እና ብሎክ ኢ (E) ላይም በተመሳሳይ የመሰረት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ማዕከሉ ክሊኒክ ይኖረዋል፤ የክሊኒኩም የመሰረት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የክህሎት ማሰልጠኛ ህንጻዎች አካባቢን ለግንባታ የማዘጋጀት እና የማጽዳት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡
እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ ከታየው መጠነኛ መጓተት ውጪ ፕሮጀክቱ ጥሩ እንቅስቃሴ እየታየበት መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር ቴዎድሮስ፤ በተጀመረው መልካም እንቅስቃሴ ማስቀጠል ከተቻለ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ በርካታ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ከዚህ በፊት ጎዳና ላይ የነበሩ 260 ወጣቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ የቀን ሰራተኞች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ ከጎዳና ህይወት ከመላቀቅ ባሻገር በዘላቂነት የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል አንዱ አቶ አበበ ነጋሽ ናቸው፤ በማዕከሉ ግንባታ በጉልበት ሰራተኛነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ አበበ በአፋር ክልል በግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ድርጅቱን ሲመሩ የነበሩ ግለሰብ አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውን ተከትሎ ድርጅቱ መፍረሱን ይናገራሉ፡፡ ይህን ተከትሎም የአንድ ዓመት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ። በመጨረሻም የጎዳናን ህይወት ውስጥ መግባታቸውን ይገልጻሉ፡፡
አቶ አበበ ለአንድ ዓመት በአስቸጋሪ ሁኔታ ኖረዋል፤ በ2014 ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመንገድ ጽዳት ስልጠና መውሰዳቸውን የሚናገሩት አቶ አበበ፣ ወዲያው ግን ስራ አላገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ዓመት ያለ ስራ ካሳለፉ በሁዋላ የማዕከሉ ግንባታ ሲጀመር በቀን ሰራተኝነት ተቀጥረው መስራት እንደጀመሩ ያብራራሉ፡፡ ከሁለት ዓመት አስቸጋሪ ጊዜ በኋላ ወደ ስራ በመመለሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚያነሱት አቶ አበበ፣ በማዕከሉ ውስጥ የተለያዩ ሙያዎችን ለመልመድ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡
አቶ መስፍን ዘበርጋ በማዕከሉ ግንባታ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥረው በመስራት ላይ የሚገኙ ሌላኛው የሥራ እድል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አሁን ማዕከሉ እየተገነባ ባለበት ቦታ ሌላ ማዕከል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚያ ማእከልም ለሁለት ዓመት ገደማ ያለ ምንም ስራ ቆይተዋል፡፡
በመንገድ ጽዳት ስራ ላይ ትሰማራላችሁ ተብሎ ስልጠና ተሰጥቷቸው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ መስፍን፣ እሳቸውም በጽዳት ስራ ላይ ሳይሰማሩ ቆይተዋል። በመጨረሻም በማዕከሉ ግንባታ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥረው እንዲሰሩ እድል እንደተፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡
በመንገድ ጽዳት ስራ ለመሰማራት ፍላጎቱ እንደነበራቸው የሚገልጹት አቶ መስፍን፤ ይህ ፍላጎታቸው ግን ሊሳካ እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ስራው ሲሰማሩ ደስተኛ እንዳልነበሩም ያልነበሩት አቶ መስፍን፣ በሂደት ግን ስራውን እየወደዱት መጥተዋል። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሙያዎችን ለመልመድ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ አናፂ የመሆን ፍላጎታቸው እየጨመረ በመምጣቱ የአናጺነት ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015