የኢኮኖሚው ደጀንነቱን ማረጋገጡን የቀጠለው ቡና

የቡና መገኛ በመሆኗ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በቡና ምርቷም በእጅጉ ከሚታወቁ ሀገራት ተርታም ትሰለፋለች። ቡና በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥም ጉልህ ስፍራ እንዳለው ይታወቃል። በርካታ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም የሚሳተፉበት ዘርፍ ከመሆኑ በተጨማሪ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከሚጠቀሱት የግብርና ምርቶች መካከልም ግንባር ቀደም በመሆንም ይታወቃል።

ሀገሪቱ በቡና የመታወቋን ያህል ተጠቃሚ ሆናለች ወይ ተብሎ ሲጠየቅ ግን መልሱ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አይደለችም የሚል ይሆናል። ለዚህም ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የግብይት ሰንሰለቱ የተንዛዛ ሆኖ መኖሩ አንዱና ዋነኛው የዘርፉ ችግር በመሆን ሲጠቀስ ቆይቷል፤ ግብይቱ በደላላ የተተበተበ ሆኖ ኖሯል። መሰረታዊ የጥራት ችግርም እንዲሁ ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት ነበር። በዚህ የተነሳም ለውጭ ገበያ ይቀርብ ከነበረው ቡና አብዛኛው ኮሜርሻል ቡና የነበረ ሲሆን፣ የስፔሻሊቲ ቡና አቅርቦት መጠን ያነሰ ነበር። ቡናውን ለዘመናት ለውጭ ገበያ ያቀርቡ የነበሩት የተወሰኑ ነጋዴዎች ብቻ እንደነበሩና ይህም የዘርፉ አንዱ ችግር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

እነዚህንና መሰል የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የቡናና ሻይ ባለስልጣን የሪፎርም ሥራ ሰርቷል። ይህን ተከትሎም ባለፉት አምስት ዓመታት በቡና ላይ በብዙ መልኩ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በተለይም በቡና ግብይትና ጥራት ችግር ላይ ይስተዋሉ የነበሩና ስር የሰደዱ ችግሮችን በወሳኝ መልኩ መፍታት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

እነዚህ የሪፎርም ሥራዎች የተንዛዛውን የቡና ግብይት ሰንሰለት ማሳጠር ተችሏል፤ ቡና ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሥራ ለዘመናት በተወሰኑ ላኪዎች ቁጥጥር ስር የነበረበትን ሁኔታ በመቀየር አርሶ አደሩን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ላኪ መሆን የሚችሉበት አሰራር ተፈጥሯል። በተለይ የቡና የቀጥታ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ መሆን በዘርፉ ለተገኘው ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይገለጻል።

የቡና ጥራትን በማረጋገጥ በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚያስችለውን የስፔሻሊቲ ቡና መጠን የመጨመር ሥራ ተሰርቷል። በዚህም ከኮሜርሻል ቡና ብልጫ ያለው ስፔሻሊቲ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል። ባለሥልጣኑ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት፣ ጥራቱን በማስጠበቅና ያረጁ የቡና ተክሎችን በመጎንደል፣ አዳዲስ የቡና ችግኞችን በመትከል በቡና ልማት ላይም በትኩረት ሰርቷል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ‹‹ቡናችን ለብልጽግናችን በሚል›› መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው መድረክ በብሔራዊ ሳይንስ ሙዚየም በቅርቡ ባካሄደው መድረክ ላይም በዘርፉ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተጠቅሷል። የዚህ መድረክ ዋነኛ ዓላማ ለቡናው ዘርፍ ለደረሰበት ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ ጀግና አርሶ አደሮች፣ ላኪዎች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቷል።

እውቅና ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከልም ቡናቸውን በከፍተኛ ጥራት ያመረቱ፣ ቡናቸውን አምርተው በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የቻሉ በመጠን ከፍተኛ የሆነ የቡና ምርት ወደ ውጭ የላኩ፣ በከፍተኛ ዋጋ ቡናቸውን ለውጭ ገበያ መሸጥ የቻሉ እንዲሁም በሌሎችም የተለያዩ ዘርፎች ውጤት ያስመዘገቡ አካላት ይገኙበታል። እነዚህ የቡና ቤተሰቦችም በየደረጃው ተሸለመዋል።

በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ ባለፉት አምስት ዓመታዊ የቡና ምርት መጠንን ከነበረበት 500 ሺህ ቶን በእጥፍ ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከቀደሙት ዓመታት ከፍተኛ ብልጫ ያለው ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ለቡና ምርትና ጥራት መጨመር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አመልክተው፣ በተለይ በቡና ችግኝ ተከላና ጉንደላ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን አስታውቀዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቡና ምርት መጠንን ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረበት 500 ሺህ ቶን ወደ አንድ ሚሊዮን ቶን ማሳደግ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከገቢ አንጻርም እንዲሁ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን አስታውቀዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ይህን አሃዝ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የዓለም ከፍተኛ ቡና አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን እውን ለማድረግ ከመንግሥት በተጨማሪ ላኪዎች የቡና ምርት ጥራትን ለሚያሻሽሉ ተግባራት ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ላኪዎች በቡና ምርት ላይ ውበት ያለው አስተሻሸግ ዘዴ በመጠቀም እሴት ጨምረው ለወጪ ገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በዓለም ገበያ ይበልጥ እንድትሳተፍ እንደሚያደርጋት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከቀደሙት ዓመታት ከፍተኛ ብልጫ ያለው ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። ‹‹በቀጣይም የሚገጥሙ ፈተናዎች ሳያቆሙን በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንሰራለን›› በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ ‹‹ግብርናችን ከእጅ ወደ አፍ መሆኑ ቀርቶ አሁን ላይ ወደ ውጭ ምርቶችን በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ማሳደግ ተችሏል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የቡና ሽያጭ አማራጭ እንዲሰፋ በመደረጉ እና አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን የላኪነት ፍቃድ አግኝተው ወደ ውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግ በመቻሉ በዘርፉ አበረታች ውጤት መመዝገብ ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዘርፉ በተሰራው የሪፎርም ሥራ ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችለዋል፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊየን አዳዲስ የቡና ችግኞች ተተክለዋል፤ የኢትዮጵያ የቡና ልማት ጥራትና ምርታማነቱ አድጎ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም ከፍተኛ ጭማሬ እያሳየ መጥቷል።

በአምራች አርሶ አደሮች አንድ ኪሎ ግራም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ከ100 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከቡና የእሴት ሰንሰለት የሚያገኙት ድርሻም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም በዓለም ደግሞ ሦስተኛ የቡና አምራች ሀገር በመሆን በተወዳዳሪነት መጠቀሷን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የጂ-25 ቡና አምራች ሀገራትን በሊቀ መንበርነት በመምራት ላይ እንደምትገኝ ተናግረው፣ ቡና የአፍሪካ 2063 ስትራቴጂክ የንግድ ምርት ሆኖ እንዲሰየም ለሕብረቱ ጉባዔ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት ማግኘቱን አመላክተዋል። ይህም መሠረት በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ሂደት በቀዳሚነት ወደ ግብይት ከሚገቡ ምርቶች መካከል ቡናን ቀዳሚ እንደሚያደርገው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ከመድረኩ አስቀድሞ በሰጧቸው መግለጫዎች ቡና ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል። ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት የመሪነቱን ሚና የሚጫወት ወሳኝ የግብርና ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

መንግሥት የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና ጥራቱን በማሻሻል በዓለም ገበያ ተፎካካሪነቱን የበለጠ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን ዕውን ለማድረጉ ሂደት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ሲሉም ጠቅሰው፣ በዚህም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የቡናን ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ፍጹም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባለፈው በጀት ዓመት 300 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ አንድ ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል። ለዚህም ስኬት መመዝገብ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትልቅ ትኩረት አንዱ ሲሆን፤ ባለሥልጣኑ የሰራቸው የሪፎርም ሥራዎችም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ወደ ውጭ የሚላከውን የኮሜርሻል ቡና መጠን በመቀነስ የስፔሻሊቲ ቡናን መጠን ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ መሰራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በዚህም ውጤት ማምጣት እንደተቻለ አስታውቀዋል። የዛሬ ሶስት ዓመት የኮሜርሻል ቡና መጠን በመቶኛ ሲታይ 70 በመቶውን ይሸፍን እንደነበር አስታውሰው፣ የስፔሻሊቲ ቡና መጠን ደግሞ 30 በመቶ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ዛሬ ላይ ግን የስፔሻሊቲ ቡናን ከፍ በማድረግ 60 በመቶ ማድረስ እንደተቻለና የኮሜርሻሉን ደግሞ ወደ 40 በመቶ ማውረድ መቻሉን ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ከቡና ልማት ጀምሮ ቡናውን ለውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ ማቅረብና ገበያ ማስፋፋት ድረስ ትርጉም ያለው ሥራ እየሰራ መሆኑን አመልክተው፣ በተለይም የእሴት ሰንሰለቱን በመከተል ልማቱ እንዲጨምርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የገበያ መዳረሻዎች እንዲሰፉና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እንዲያድግ በተደረገው ጥረት ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። የምርት ጥራትን በማስጠበቅና ብክነትን በመከላከል እንዲሁም በእሴት ጭመራ ላይ በተከናወኑ ተግባሮች ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና መጠን ማሳደግና ከቡናውም የሚገኘው የወጪ ምንዛሪ መጠን እያደገ እንዲመጣ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

ባለሥልጣኑ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በዋናነት ከሰራቸው ሥራዎች መካከል ግብይቱን አንቀው የያዙና ልማቱ ውስጥ የሚገኙ እንዲሁም ግብይት ውስጥ ያሉና ልማቱ እንዳይስፋፋ ያደረጉ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት አንዱ መሆኑን አመልክተው፣ ለዚህም የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት በዋናነት ስድስት የተለያዩ ምሰሶዎችን በመለየት ልማትና ግብይቱን የማሳደግ ተግባሮች መከናወናቸውን አስታውቀዋል። ምርትና ምርታማነት ከፍ እንዲል፣ የምርት ጥራት እንዲጨምርና ዘርፉ በምርምር እንዲደገፍ፣ የእሴት ሰንሰለቱን የማሳጠር፣ በምርቱ ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንዲሁም ገበያን የማስፋፋት ሥራ በስፋት መሰራቱንና አሁንም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለሥልጣኑ ባደረገው ሪፎርም በተለይም የቡናው ዘርፉ ከዓመት ዓመት የተሻለ ውጤትና ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። ወደ ውጭ የሚላኩ የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች በመጠን እየጨመሩ፣ ከእነዚህ ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝትም በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 300ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች። ይህ ውጤትና ስኬት የተመዘገበው ብዙ ጥረትን በጠየቀው የሪፎርሙ ሥራ ነው። ሪፎርሙ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ከ180 እስከ 190 ሺ ቶን ቡና ብቻ ለውጭ ገበያ ይላክ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እስከ 300 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ መቶ ሺ ቶን የተጣራ ቅሽር ቡና ለውጭ ገበያ በሚላከው ቡና ላይ መጨመር የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ዘርፉ የእሴት ሰንሰለቱን በማሳጠር ያስመዘገበው ትልቅ ስኬት ነው።

ባለሥልጣኑ ለ2017 በጀት ዓመት ጥራት ያለውና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ቡና በከፍተኛ መጠን የመላክ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በ2016 በጀት ዓመት ሶስት መቶ ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ ከተመዘገበው ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ከፍ በማድረግ፣ በ2017 በጀት ዓመት 326 /ሶስት መቶ ሃያ ስድስት/ ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ባለሥልጣኑ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ሐምሌ እና ነሐሴ ወራትም የዘርፉ ስኬት ቀጥሏል። እሳቸው እንዳሉት፤ በእነዚህ ሁለት ወራት ብቻ 56 ሺ ቶን ቡና በመላክ 260 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ባለሥልጣኑ አቅዶ፣ 83 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ ችሏል፤ ከዚህም ከእቅዱ በላይ 380 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በተላከ ቡና መጠን ሲታይም ከእቅድ በላይ ተጨማሪ ከ30 ሺ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ገበያ ተልኳል። በቀጣዮቹ ወራት አሁን በተመዘገበው ውጤት ልክ ማስመዝገብ ከተቻለ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ማሳካት እንደማይከብድም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You