የቻይናውያን ሰፊ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ  ማሳያው ኢንዱስትሪ ፓርክ

የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት፣ በመሠረት ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት፣ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማበረታቻዎች እንዲሁም ሀገሪቱ ያላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የገበያ እድል፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል። ይህም ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።

የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠሩት የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተደምረው በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ አሳድረው ነበር።

በመንግሥት የተወሰዱ ልዩ ልዩ ርምጃዎች የኢንቨስትመንት ዘርፉ መልሶ እንዲያንሰራራ አስችለዋል። በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጫና አሳድረው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እያገኙ በመምጣታቸው በዘርፉ መነቃቃት እየታየ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል። ለአብነት ያህልም ባለፈው የበጀት ዓመት ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል። 329 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ተሰጥተዋል። ከሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች 115 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል። ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት ፍላጎት ካሳዩ 70 ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በዘጠኝ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ 205 ፕሮጀክቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ተከናውነዋል።

ወቅታዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ባስገባና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ክለሳዎች ተጠናቀው አዳዲስ ድርድሮች ተደርገዋል። ከአዳዲስ ቀጣናዊና ክልላዊ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል። የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አቅሞችና መልካም እድሎች በበርካታ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲተዋወቁ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በዘንድሮው የበጀት ዓመት አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዲሁም ለ341 ፕሮጀክቶች (ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጭ) አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን ለመስጠት ታቅዷል።

ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች በመቀጠላቸው፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (Foreign Direct Investment – FDI) እየጨመረ ይገኛል። ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ለምርት እድገት፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለገበያ ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።

በመንግሥት ተገንብተው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና በክልል መንግሥታት ከሚተዳደሩት 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በተጨማሪ በግል ባለሀብቶች የተገነቡና የሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ‹‹ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ›› (Eastern Industry Park) ነው። ኢንዱስትሪ ፓርኩ ዱከም አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በፓርኩ ውስጥ 153 ኩባንያዎች በምርት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከኩባንያዎቹ መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት በቻይናውያን ባለሀብቶች ባለቤትነት የተያዙ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የህንድ፣ የእንግሊዝና የሌሎች ሀገራት ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ አምራቾች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ‹‹ዲ ዩዋን ሴራሚክስ›› (Di Yuan Ceramics) ነው። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ሹ ቦ ፋብሪካው በ50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ከሰባት ዓመታት በፊት እንደተቋቋመ ጠቁመው፣ የግድግዳና የወለል ሴራሚክስ ምርቶችን እንደሚያመርት ይገልጻሉ። ለ800 ኢትዮጵያውያንና ለ50 ቻይናውያን የሥራ እድል ፈጥሯል። ኢትዮጵያውያን የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝም ያስረዳሉ። የመንግሥት ድጋፍ ለፋብሪካው ሥራ መቃናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ።

የ‹‹ሁዋጂያ አሉሚነም ኢንዱስትሪ›› (Huajia Aluminum Industry PLC) ዋና ሥራ አስኪያጅ ደቪድ ዡ እንደሚናገሩት፣ ፋብሪካው በ181 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል ከስምንት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ከ170 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥሯል። ፋብሪካው 16 ዓይነት የአሉሚንየም ፕሮፋይል ምርቶችን (Aluminum Profiles) አምርቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያለው የፋብሪካዎች ኢንቨስትመንት የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከርና የሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነትም ለፋብሪካዎቹ ውጤታማነት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ከመጀመሪያው ጀምሮ ለፋብሪካው ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየና ፋብሪካው ከአካባቢው ኅብረተሰብ፣ ከክልሉና ከፌደራል መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ይገልፃሉ።

የ‹‹ሊንደ ኢትዮጵያ›› ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ (Linde Ethiopia Garment PLC) ዋና ስራ አስኪያጅ ጄ ዪፋን በበኩላቸው፣ ፋብሪካው የተለያዩ ብራንድ ያላቸውን የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ እንደሚያቀርብ ጠቁመው፣ ከአንድ ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በፋብሪካው ተቀጥረው እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፕሮሞሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዘለቀ ተመስገን፣ ‹‹ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ተቀዳሚው መሆኑን ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ በፓርኩ ውስጥ ያሉት አምራቾች ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለወጪ ንግድ እና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በፓርኩ ውስጥ ባሉት ፋብሪካዎች ውስጥ አብዛኞቹ የምርት ሥራዎች የሚከናወኑት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ነው። ይህም የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እቅዱ በጥሩ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ትስስር ፈጥረው እየሰሩ ይገኛሉ።

እንደ ዶክተር ዘለቀ ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያላቸው 3309 የቻይና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ይገኛሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ325ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። የቻይና ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ብዛት፣ በካፒታል አቅም፣ በሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ቀዳሚውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች የዘርፉን እድገት ለማፋጠን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ የሚያስረዱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር በማሰብ የሕግ ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸው ይገልፃሉ። እንደሳቸው ገለፃ፣ የኢንቨስትመንት አዋጁ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ሊያሳድግ በሚችል መልኩ ተሻሽሏል። የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና አዋጅም ጸድቋል። ይህን ተከትሎ ኮሚሽኑ መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

በተሟላ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚተገበሩ አሰራሮች ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን የሚፈጥሩ እንደሆኑ የሚገልጹት ዶክተር ዘለቀ፣ የዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት የኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ12 በመቶ እድገት እንዳሳየ ይናገራሉ።

የኢንቨስትመንት ከባቢውን የበለጠ ምቹ ለማድረግ የተወሰዱ ርምጃዎች ለዚህ እድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ለባለሀብቶች ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ነው። የክትትልና ድጋፍ ሥራዎቹ ኢንቨስተሮች ሥራቸውን እንዲያስፋፉ እና ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ስለማድረጋቸውም ያስረዳሉ።

‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ተቀዳሚ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት። ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ መሰራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ። የሀገሪቱ አቅም በመንግሥት በኩል እየተወሰዱ ካሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጋር ሲደመሩ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ያስችላታል። በተለያዩ ዘርፎች ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በተለይ ስትራቴጂካዊ ተብለው በተለዩት ዘርፎች (በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም) ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየታየ ነው›› ይላሉ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሀገሪቱ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም እና የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች ተጠቃሽ እንደሆኑ ይገልፃሉ። አቶ ዳጋቶ እንደሚሉት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎቹ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ እድል የሚፈጥሩ ናቸው።

‹‹ባለሀብቶቹ ከውጭ ሲመጡ የተለያዩ አማራጮችን ታሳቢ አድርገው ነው። እኛ ደግሞ ባለሀብቶቹን ለመሳብ የተሻለ አማራጭ ማቅረብ አለብን። ከባለሀብቶች ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። የውጭ ምንዛሪው ጥሬ እቃ ለመግዛትም ሆነ ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት እጅግ አስፈላጊ ነው። በቅርቡ ሥራ ላይ የዋለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ ሰጭ ጅምሮች እየታዩ ነው›› ይላሉ።

አቶ ዳጋቶ እንደሚገልፁት፣ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለማሻሻል ከተወሰዱ ርምጃዎች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የንግድ ዘርፎች ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸው ነው። በዚህም የውጭ ባለሀብቶች በወጪ፣ በገቢ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ተወስኗል። ከውሳኔው በኋላ ከሐምሌ 2017 ጀምሮ 72 ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከእነዚህ መካከል 41 የሚሆኑት በገቢ እንዲሁም 31 ደግሞ በወጪ ንግድ ላይ ለመሳተፍ የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው። ፕሮፖዛል ካቀረቡ 22 ኩባንያዎች መካከል የ12 ኩባንያዎች ጥያቄ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይሁንታ አግኝቷል። ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካገኘላቸው መካከል ስምንቱ የቻይና ኩባንያዎች ናቸው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You