
ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ኮረዳንና ለአቅም አዳም የደረሰን ጎረምሳ አንች ትብሽ በአንተ ይብስ በሚል ቃልኪዳን አስተሳስራ ገመናቸውን ሸፍና የምታኖራቸው፤ በደሴት ላይ ያለች መርከብ መሳይ ህይወት ናት። ተባብረው ጀልባዋን መቅዘፍ ከቻሉ ሞገዱን፤ ውሽንፍሩን፣ ማዕበሉን አሸንፈው ወልደው ከብደው አርጅተው ይኖሩባታል፡፡
ይችን በማዕበልና ሞገድ የተወጠረችውን፤ በእሳትና በውሀ የተከበበችን ህይወት ቅበላና ትንሳኤ ሲመጣ በአታሞው ድለቃ፣ በጥሩምባው ጩኸት፣ በዳስ በድንኳኑ ማጌጥ፣ በገበያ ትርምስምሱ፣ በጠጁ ሽታ፤ በበሬው በበጉ ጩኸት በሙሽራዎችና በሚዜዎች ዳንስ ልምምድና ልብስ ምርጫ የውል ቀኗ መድረሱ ይታወቃል፡፡
የውል ቀኗ ዕለት ይትባረክ እንደ አብረሃም ተብላ ተዘፍኖላት ተመርቆላት የታደሉት ጀልባዋን እየቀዘፉ በአብርሃምና በሳራ ቤት ሲኖሩ ያልታደሉት አቅጣጫ ጠፍቶባቸው ሲባዝኑ ቀሪዎች የማዘጋጃን ቤት ወረቀት ሲያጸዱ ይገኛሉ፡፡
ሶስት ጉልቻን የሚመሩበት ከትልቅ ውቅያኖስ ጥልቅ ማስተዋል አጥተው ማሬ ወደ ኮምዛዜ፤ ባባዬ ወደ ሰውዬ ቋንቋ ተደበላልቆባቸው፤ ንክሻና ንትርክ ጀልባቸውን አስምጦባቸው ‹‹አይንሽን ባየው ባየው አልሰለችህ አለኝ››፣ ብለው የጀመሩት ጀልባ ቀዘፋ ‹‹አይንሽን ላፈር፣ አይንህን ላፈር›› በሚል ስንክሳር ላይታደስ ይወድማል፡፡
የትዳር መፍረስ የልጆች የወደፊት እጣ ፈንታ ከማጨለም ባለፈ በአገር ላይ ትልቅ ኪሳራ የሚያደርስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀይማኖተኞች እና ባህላቸውን አጥባቂዎች የሚበዙባት አገር እንደመሆኗ መጠን ለትዳር ትልቅ ስፍራ ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍቺ በተለይ በከተሞች አካባቢ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። ይህ ማለት በገጠር አካባቢ ፍቺ የለም ማለት አይደለም።
የእንጀራ ዋጋ ስለተወደደብኝ ትዳር ልመሰርት ነው የሚሉም አልጠፉም፤ በዚህ ሁኔታ ትዳር የመሰረቱ ሰዎች የኑሮ ውድነቱ ሲስተካከል ተመልሰው ሊፋቱ ነው ብዬ አስብና ለራሴ እገረማለሁ፡፡ ታዲያ የሆነው ሆኖ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ፤ በመዲናይቱ ብቻ ባለፉት 6 ወራት አንድ ሺህ 342 ፍቺዎች መመዝገባቸውን አሳውቋል፡፡ ይህ ማለት በቀን ሰባት ትዳሮች በፍቺ ይቋጫሉ ማለት ነው፡፡
ዘንድሮ በ6 ወራት ብቻ የተመዘገበው የፍቺ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ተቀራራቢ ሲሆን፤ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ሺህ 623 የፍቺ ምዝገባዎች መደረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ መረጃዎች የሚያመላክቱት በመስሪያ ቤቱ በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡትን ብቻ ነው። ያልተመዘገቡትን ቤት ይቁጠረው።
በተለያዩ ቦታዎች በህጋዊም ሆነ በባህላዊ መልኩ ፍቺ እና ጋብቻ ይከናወናል፤ ነገር ግን ወደ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ መጥተው የሚመዘገቡት ቁጥራቸው አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል። በአዲስ አበባ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 16 ሺህ 35 ፍቺዎች እንደተካሄዱ የወሳኝ ኩነት መረጃ ያሳያል።
ለፍቺ ዋነኛ መንስዔዎች ተብለው የሚጠቀሱት የኢኮኖሚ መዳከም፣ አለመተማመን፣ የምዕራባውያን አገራት የባህል ጫና፣ ቅናት እና የወሲብ አለመጣጣም ናቸው ይባላል፡፡ ትዳሮች በተለያዩ ምክንያት የሚፈርሱ ቢሆንም እንኳን፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
በንብረት ላይ መጋጨት፣ አለመግባባት፣ እርስ በእርስ መጠራጠር እንዲሁም የቤተሰብና የሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት፤ በልጆች ቁጥር፣ በአኗኗር ሥርዓት፣ በመኖርያ ስፍራ ምርጫ ለባልና ሚስት የፍቺ ምክንያት መሆናቸውን ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው።
ነገር ግን ተጋቢዎቹ ከተግባቡ፣ ከተመካከሩና ከተከባበሩ ሦስተኛ ወገን ትዳርን ለማፍረስ ቦታ ይኖረዋል?፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ፍቅራችንን በቀለበት እንሰረው፣ በሰርግ እናድምቀው የሚሉትን ያህል ፍቺያችንን አጽድቁልን ብለው የፍርድ ቤት ደጃፍ የሚጠኑ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
የትዳሮች በፍቺ መጠናቀቅ በርካታ የማህበራዊ ቀውሶች መንስኤ ነው፡፡ ፍቺ በየትኛውም የእድሜ ክልል ለሚገኙ ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው የስነልቦና ጠባሳ ቀላል የሚባል አይደለም። የትዳር መፍረስ ልጆችን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን እና አገርን እንደሚጎዳ በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ። በፍቺ ምክንያት ሕጻናት ለአካላዊ፣ ለአእምሯዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ይጋለጣሉ።
የሁለቱንም ወላጆቻቸውን ክትትልና እንክብካቤ ማግኘት ስለማይችሉም በቀጣይ ህይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ከእናትና ከአባታቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትና ፍቅር ይቋረጣል። ይህ ደግሞ አእምሯቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር በቀሪው ዘመናቸው በድንጋጤ እና ፍርሃት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።
ልጆች የወላጆቻቸውን ፍቅር በጋራ ይፈልጋሉ ፍቺ ትውልድን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን ከመጉዳት አልፎ ለአገርም ትልቅ ጉዳት ነው። ወላጆች በጋራ ያፈሩትን ልጅ በመንከባከብ በስርዓት ማሳደግ እና ማስተማር፣ ለአገር እንዲሆኑ አድርገው መቅረጽ አለባቸው። ልጆችን በኃላፊነት ካላሳደግናቸው ጠንካራ ማኅበረሰብ ሊገነባ አይችልም። ጠንካራ ማኅበረሰብ የሌላት አገር ሁሌም ችግር ውስጥ መግባቷ የማይቀር ነው፡፡
እንደ እኔ እምነት ባለትዳሮች የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሁኔታ እስኪያገኙ ድረስ ልጅ ባይወልዱ የተሻለ ነው፡፡ ልጅ በእድሉ ይደግ በሚለው አባባል አላምንም፡፡ የኛ አገር ሰው በድህነት እየኖረ የልጁን ስም ተስፋዬና ሚሊዮን እያለ ሰይሞ በተስፋ ይኖራል፡፡
አንተ ሳታገባ ለፍቺ ምን አስጨነቀህ ያላችሁኝ እንደሆነ ጉዞዬም ወደዛው ነውና ስጋታችሁ ስጋቴ ነው፡፡ ትዳርን ከፍቺ አረንቋ ለማውጣት ግን ወላጆች የሚከፍሉት መስዋዕትነት እንደሚኖር ግልጽ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የፍቅር ሸማ የለበሰው ትዳር፣ የፍቺ ጸሐይ ከሞቀው ግን በመካከል ያሉ ልጆች እንዳይጎዱ ማህበረሰቡና መንግሥት ተገቢ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አምናለሁ።
ሁላችንም ቢሆን ትዳር በፈለግንበት ጊዜ ጎራ የምንልበት መሸታ ቤት አለመሆኑን ልንረዳ ይገባል። በእቅድና በትኩረት የተገነባ ትዳር ከሁሉም የበለጠ ጠንካራ መሰረት ይኖረዋል። ጋብቻ ማኅበራዊ ተቋም እንደመሆኑ ተጋቢዎች በሰከነ አዕምሮ ሊጠብቁት ካልቻሉ ሌላ አካል ማንም አይጠብቀውም፡፡
ፍቺ በሰው እና በፈጣሪ ፊት ቃልኪዳን ተግባብተው መልሰው ሲለያዩ የአደባባይ እውነታ ነው። ትዳር በፈጣሪ ፍቃድና ዓላማ በአዳምና ሄዋን ተመስርቶ እስካሁን የመጣ ትልቅና የከበረ ተቋም መሆኑን ሁሉም ሰው በመረዳት በጥበብና በጥንቃቄ መምራት ይጠበቅበታል። መንግስትም ቢሆን ፍቺን እየመዘገበ ይፋ የሚያደርግ ተቋም ማቋቋም ብቻ ሳይሆን፤ ትዳርን ከፍቺ የሚጠብቅ ተቋም ሊመሰርት ይገባል፡፡
የእምነት ተቋማትን ጨምሮ ጥብቅ ትምህርትና ስልጠና መስጠት፣ መንግስትም ትዳር ለአገር መሠረት በመሆኑ ስልት ቀይሶ ማስተማርና መገንባት ይኖርበታል፡፡ እንግዲህ የእምነት ተቋማትና የሀይማኖት አባቶች ስራችሁ ብዙ ነው፡፡
“ይትባረክ እንደ አብረሀም…” ብለን ሳንጨርስ… አለ አይደል… “ዓይንህ ለአፈር/ዓይንሽ ለአፈር” ተባባሉ ሲባል መልካም አይደለም፡፡ እና እላችኋለሁ ያገባችሁ በትዳራችሁ ፈጣሪ ያጽናችሁ፤ ያላገባችሁ ካላችሁ ቸር ትዳር እንዲገጥማችሁ ምኞቴ ነው፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015