የሲዳማ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው። ለውጪና ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው የቡና ሀብቱ፣ የቱሪስት መስህብ የሆነው የሀዋሳ ሀይቅና ፍል ውሃዎቹ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ:: የሲዳማ ብሔረሰብ ቱባ ባህልም ሌላው ተጠቃሽ እምቅ ሀብቱ ነው::
ክልሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ባሉት መሰረተ ልማቶችም ይታወቃል፤ በሀገሪቱ ሞዴል የኢንዱስትሪ ፓርክ በመባል የሚታወቀው ግዙፉ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የይርጋ አለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የሌሎች በርካታ ኢንዱስትሪዎችም መገኛ ነው::
ሌሎች እምቅ አቅሞቹን በማጥናት ወደ ልማት ለማስገባት ክልሉ በትኩረት እየሰራ ይገኛል:: ክልሉ ያለበትን የመሬት ጥበት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደ መስኖና ማዕድን ባሉት ላይም ልማቱን አጠናክሮ ለመቀጠል እየሰራ ነው::
የማዕድን ዘርፍን ብንመለከት በክልሉ በማዕድን ዘርፍ የአለኝታ ጥናቶችን በማካሄድ የማዕድን እምቅ አቅምን ለመለየትና ለማልማት የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ ይገልጻሉ::
በክልሉ በማዕድን ሀብቶቹ ላይ በተደረጉ ጥናቶች የወርቅ፣ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ማዕድናት እንደሚገኙ መለየት መቻሉን ጠቅሰው፣ የክምችቱን መጠን ለማወቅም ተጨማሪ ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው ይላሉ:: አንዳንዶቹን ማዕድናት የማልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል::
ዋና ዳይሬክተሩ በተለያዩ የማዕድን አለኝታ ጥናትና ልማት ስራዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ያጋሩን ሲሆን፣ በዚህ ጽሁፍ በተለይ በወርቅ ማዕድን ጥናት፣ ልማትና ግብይት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ይዘን ቀርበናል::
የማዕድን አለኝታ ጥናትና ልየታ
እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ በዋናነት በትኩረት እየተሰራ ያለው በማዕድን አለኝታ ጥናት ላይ ነው:: ጥናቱም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል:: ሲዳማ በክልልነት ከተደራጀ ወዲህ ባሉት ሁለት አመታት ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ/ የፌዴራል ተቋም ነው/ ጋር በመሆን በተለይ በወርቅ ማዕድን ላይ ጥናት አድርገናል:: በ2015 ዓ.ም የቅድመ ጥናት የቦታ ልየታ ስራ ለማከናወን ጥናት የሚካሄድበትን የቅድመ ጥናት ቦታ ልየታ ስራ አብረን ሰርተናል:: በወርቅ ላይ ከጂኦሎጂካል ሰርቬ,ይ ጋር የሚደረገው ይህ ጥናት ይቀጥላል::
ሌላው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተከናወነ ያለው ስራ ነው:: የዩኒቨርሲቲው የጂኦሎጂካል ትምህርት ክፍል ከኛ ጋር ካለፈው አመት ጀምሮ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመን በተለይ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ ጥናት ማካሄድ ተጀምሯል። ስምምነቱን የተፈራረምነው በየአመቱ ጥናት ለማድረግ ነው።በቀጣይም በጂምስቶን /የጌጣጌጥ ማዕድናት/ እና በኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድኖች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በኮንስትራክሽን ማዕድናት ላይም ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ እድል አለ::
ትልቁ የመጀመሪያ ስራችን ያለን የማዕድን ሀብት በጥናት ሙሉ ለሙሉ ያልተለየ በመሆኑ እንደ ክልል ሙሉ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን:: ስለዚህ የመጀመሪያ ስራችን ያለንን ሀብት በጥናት መለየት ነው። ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው በጥናት ላይ መሆኑም ለዚህ ነው::
በጥናት የተለዩ ማዕድናት
የተጠኑ ቦታዎችን ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እየተጠቀምንባቸው ነው፤ ከወጣቶቹ አቅም በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ጎን ለጎን ባለሀብቶች እንዲይዙት እናደርጋለን፤ በኛ ደረጃ ያሉትን በኛ ደረጃ፣ ከኛ ደረጃ በላይ የሆኑትን እንደ ጂምስቶን ያሉትን የጌጣጌጥ ማዕድናትን የፌዴራል መንግስት ፈቃድ እየሰጠን በውክልና እናስተዳድራለን፤ እያመቻቸን፣ እያቀናጀን በጋራ እንሰራለን ሲሉ አቶ መስፍን ያብራራሉ::
ባለሀብቶችም ጥናት አድርገው የሚሰሩበት ሁኔታም እንዳለም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቀሱት። በጽንሰ ወርቅ ጥናት ላይ ሁለት ኩባንያዎች እየሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ ኩባንያዎች ጽንሰ ወርቁን እያጠኑ ያሉት በፌዴራል መንግስት ፈቃድ መሰረት ነው:: ኩባንያዎቹ እኛ ቦታ እያስረከብን እየደገፍናቸው ጥናታቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ:: እኛ ለወጣቶች የምንሰጠው የደለል ወርቅ ነው::
የአነስተኛ የወርቅ ማዕድን ልማት
ወጣቶቹ እየሰሩ ያሉት በአነስተኛ የወርቅ ልማት ላይ ነው:: በዚህም ላይ በርካታ ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩ ናቸው:: የወጣቶቹን አቅም ለማጎልበት ሲባልም ወጣቶቹ ከባለሀብቶች ጋር ተቀናጅተው በልዩ አነስተኛ ደረጃ እንዲሰሩ እየተደረገ ያለበት ሁኔታም አለ::
በወጣቶች ደረጃ የምንሰጠው ፈቃድ ባህላዊ ፈቃድ ነው:: በባህላዊ ፈቃዱም ከአቅም በላይ የሚሆነውን በማሽን እንዲያጥቡ ኤክስካቫተር መጠቀም እንዲችሉ ወደ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራችነት እናሳድጋቸዋለን፤ ወጣቶቹን ከባለሀብቱ ጋር ሰባ በሰላሳ በሚል አቀናጅተን እንዲሰሩ እናደርጋለን::
ወርቅን በተመለከተ በሲዳማ ክልል በስፋት እየሰራን ያለነው በደለል ወርቅ ላይ ነው፤ የደለል ወርቅ መጠኑ አነስ ይላል፤ የጽንሰ ወርቁ እስከሚገኝ ድረስ የደለል ወርቁን እንሰራለን:: የሚመረተው ወርቅም ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ይደረጋል::
ወርቅ የሚመረትባቸው የክልሉ አካባቢዎች
ወርቅ በክልሉ የገናሌን ወንዝ ይዞ በበንሳ ወረዳ ጫፍ፣ ጨቤ ጋምቤልቱ ወረዳ፣ አኮ ወረዳና በተወሰነ ደረጃ አሮሬሳ በሚባለው ወረዳ ላይ ይገኛል:: በአብዛኛው በጥናት ላይ ነው ያለው፤ ማምረቱ ላይ ገና ብዙም አልተገባበትም:: በዚህ አመት ከጂኦሎጂካል ሰርቬር ጋር በመሆን በአብዛኛው በአሮሬሳ ወረዳ ላይ ጥናት እያደረግን እንገኛለን። በወርቅ ላይ የተለየውና እና እየተሰራበት ያለው በጨፌ ጋምቤልቱ ወረዳና አብኮ ወረዳዎች ነው::
ወርቅ እየተመረተባቸውና እየተጠኑ ያሉት አካባቢዎች ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር ኩታ ገጠም ናቸው:: አካባቢዎቹ የሚገኙት የገናሌን ወንዝ ተከትለው ነው:: ከወንዙ ማዶ ጉጂ ነው፤ በወዲህ በኩል የሲዳማ ክልል የተጠቀሱት ወረዳዎች አሉ። ከወንዙ ማዶም ወዲህም በወርቅ ላይ እየተሰራ ነው።
በርካታ ማህበራት ወደ ስራው ገብተዋል። በተለይ በጨቤ ወረዳ ላይ ከ10 በላይ ማህበራት ይሰራሉ:: በአኮ ወረዳ ላይም ወደ ስድስት ማህበራት እየሰሩ ናቸው:: አንዳንዶች ፈቃድ ወስደው ባለሀብት እያፈላለጉ ያሉበት ሁኔታም አለ። ከመሬቱ አቀማመጥ አኳያ ከብዶናል ብለው ወደ ስራ ያልገቡም አሉ:: እነዚህ ገና ባለሀብት እያፈላለጉ ናቸው::
የአቅም ግንባታ ድጋፍ / የወርቅ ማቅለጫና ማጠቢያ ማሽን
የተለያዩ የድጋፍ ፓኬጆችን ቀርጸን እየሰራን እንገኛለን:: ለባለሙያዎች ድጋፍ እናደርጋለን፤ ባለሙያ እንዲደግፋቸው እንዲሁም ከተሻለ ማህበር ተሞክሮ እንዲያገኙ ይደረጋል፤ በማምረቻ ቁሳቁስም ይደገፋሉ:: ለምሳሌ በዚህ አመት የወርቅ ማቅለጫ ልንገዛላቸው በጀት ይዘናል:: ለተወሰኑ ማህበራት ማሽኑን ገዝተን በሁለቱም ወረዳ አስቀምጠን የወርቅ ማቅለጫ አገልግሎት በነጻ ለማቅረብ እየሰራን ነው።
የወርቅ ማቅለጫው ፋይዳው ብዙ ነው። ማቅለጡ አንድ ነገር ነው፤ ወርቅ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይወሰድም አስተዋጽኦ ያበረክታል:: የተመረተውን ወርቅ በቀጥታ ወደ ባንክ ለማስገባት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የወርቅ ማቅለጫው አምራቾቹ የወርቅ ምርታ ቸውን ለመሸጥ ወርቅ ቤቶችን ሲፈልጉ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ በአቅራቢያቸው ማቅለጥ እንዲችሉ ጠቀሜታ አለው። እርስ በርስ ለመተማመንም የማሽኑ ሚና ከፍተኛ ነው::
በቅርቡ የወርቅ ማቅለጫ ገዝተን ለማቅረብ አቅደናል፤ ፋይናንስ ጨረታ ለማውጣት በሂደት ላይ ይገኛል:: ማቅለጫው ከመጣ በኋላ እንዴት እንደሚጠቀሙበት ስልጠና እንሰጣለን:: ቀደም ሲልም በማህበራት አደረጃጀት ዙሪያ፣ በተለይ ከባለሀብቶች ጋር እንዴት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም የእነሱ ሚና ምን መሆን እንዳለበት፣ ባለሀብቱ ምን መስራት እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ስልጠና ሰጥተናል፤ በዚህ መሰረትም እየሰሩ ናቸው::
የወርቅ ማዕድን ጠቋሚ ማሽን ለመግዛትም ታቅዶ ነበር:: በተለይ በ2013 ዓ.ም የወርቅ ማሽኑን ለመግዛትም ታቅዶ ለግዥውም ጨረታ አውጥተን ተወዳዳሪ ባለመቅረቡ አልተሳካም። የወርቅ ማጠቢያ ማሽን እኛ አላቀረብንም። ማሽኑን ማቅረብ ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር ግን ወጣቶቹን አቀናጅተናል:: በክልሉ ሶስት ቦታዎች ማጠቢያ ማሽን ይዘው የገቡ ባለሀብቶች አሉ:: ሌሎች ባለሀብቶችንም እያቀናጀን ማሽን እያስገቡ ናቸው::
የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ገዝቶ ለማቅረብ ዋጋው ውድ ነው:: በመንግስት ደረጃ ለማህበራት የወርቅ ማሽን ገዝቶ ማቅረብ ይከብዳል:: በፌዴራል ደረጃም የተያዘው ስትራቴጂ እንደዚህ ከበድ ባለ አካባቢ ላይ የሚሰሩ ማህበራት ከባለሀብት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግ ላይ ነው፤ እኛም ያንን አቅጣጫን እየተከተልን ነው::
የወርቅ ምርት
ባለፈው አመት ወደ 14 ኪሎ ግራም ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የጠቀሱት አቶ መስፍን፣ እኛ ጋ የደለል ወርቅ ነው የሚመረተው፤ ስፋቱ ያንሳል፤ በዚህ በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አምስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገብቷል፤ በአምስት ወሩ አራት ነጥብ ስድስት ኪሎ ግራም ሪፖርት ስለመደረጉም አብራርተዋል።
የወርቅ ምርት ግብይት
የተመረተው ወርቅ በብሔራዊ ባንክ ውክልና በተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረጋል:: ወርቁ ወደ ባንኩ እንዲገባ የሚደረገው በሁለት መልኩ ነው:: ማህበራቱ ለአዘዋዋሪዎች ካስገቡ በአዘዋዋሪዎቹ በኩል ወደ ባንክ እንዲገባ ይደረጋል:: ሂደቱን ወረዳዎችም እኛም እንከታተላለን፤ ከ50 ግራም በላይ ወርቅ ከሆነ ደግሞ ማንኛውም ማህበር ለአዘዋዋሪ አልሰጥም ካለ ራሱ ባንክ ማስገባት ይችላል።
በወርቅ አምራች ክልሎች አካባቢ የወርቅ ህገወጥ ግብይት ስለመኖሩ ይታወቃል:: በወርቅ ማጠቢያ በኩል ከባለሀብት ጋር አስተሳስረን እየሰራን ያለንበት ሁኔታ ህገወጥ ግብይቱን ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን ሲሉ አቶ መስፍን ይገልጻሉ:: ምክንያቱም ሁለቱም ድርሻ ስላላቸው ይጠባበቃሉ፤ እዚያም ወርቁ እንዳይሰረቅ የመጠበቅ ሁኔታ ይኖራል:: አጣቢዎቹ የሚጠብቁበትም ሁኔታ አለ።ባለሀብቶቹ ማሽን ኤክስካቫተር ብዙ ወጪ አውጥተው ነው ያቀረቡት፤ ስለዚህ የመጠባበቅ ሁኔታ ስላለ የተሻለ ነገር አለ።
ከዚህ በተረፈ ወርቅ አካባቢ ላይ ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ ግብይት አለ አንልም የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በእርግጥ ወረዳ ላይ ባለሙያዎች አሉ፤ እኛም ወደ አካባቢው ባለሙያ እየላክን ክትትል እናደርጋለን፤ ከዚያ ባሻገር ህሊና የማይወቅሰው፣ ሀገርን የሚገዳ ድርጊት የሚፈጽም ሰው ህገ ወጥ ግብይት አይፈጽምም ብለን አናምንም ሲሉ ያብራራሉ። ለዚያም ነው ከወረዳዎች የእያንዳንዱን ማህበር አፈጻጸም በየሳምንቱ የምንሰበስበው፤ ወረዳዎችም በየእለቱ ያለውን አፈጻጸም ይሰብስባሉ ይላሉ::
አቶ መስፍን እንደሚሉት፤ ከባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራበት ሁኔታ ህገወጥ ግብይቱን ይቀንሰዋል:: ለእዚህም ነው እኛም አምራቾቹ ምንም አይነት ወጪ ሳያደርጉ የማቅለጫ ግዥም የምንፈጽመው:: ማሽኑን ጽህፈት ቤት አስቀምጠን ያለምንም ክፍያ እንዲያቀልጡ እናደርጋለን። ማቅለጫው ጽህፈት ቤት መቀመጡ ወርቁን በቀጥታ ወደ ባንክ ገቢ ለማድረግ ያለውን ሁኔታ ወረዳው የማወቅ እድሉን ሰፊ ያደርግለታል::
ህገ ወጥ ግብይቱን ለመቀነስ በትኩረት እንሰራለን፤ በተለይ አነስተኛ አምራቾች ከባለ ሀብቶች ጋር እንዲሰሩ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ህገ ወጥነቱን ለመቀነስ እያስቻለ ይገኛል:: ይህ ተሞክሮ በፌዴራል ደረጃም መያዝ ይኖርበታል ሲሉ ይጠቁማሉ::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015