ለማዕድን ዘርፉ በትክክለኛ ወቅት የመጣ ማሻሻያ

በኢትዮጵያ ከሚመረቱ ማዕድናት መካከል የወርቅ ማዕድን አንዱ ነው። በሀገሪቱ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ወርቅ በስፋት ይገኛል፤ በአብዛኞቹም በስፋት እየለማ ይገኛል።

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፡- ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት አላት። እስካሁን በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። ይህ የወርቅ ሀብት በመጪዎቹ 20 እና 25 ዓመታት የሚለማ ነው፡፡

ወርቅ በቀላሉ የማይገኝ የአሰሳና የፍለጋ ሥራው ረጅም ጊዜያት የሚፈጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ክምችቱን ለማረጋገጥ በራሱ ከ15 ዓመታት በላይ ይፈጃል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በወርቅ ማዕድን ላይ የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉም ይገኛሉ፡፡

ሀገሪቱ በጥናት የተረጋገጠና ገና በጥናት ያልተረጋገጠ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላት ብትሆንም፣ በሕገወጥ የወርቅ ልማትና ግብይት፣ ልማቱ ከባሕላዊ መንገድ ያልተላቀቀ በመሆኑና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ይህንን ሀብቷን ጥቅም ላይ በማዋል ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳታገኝ ኖራለች።

መንግሥት የማዕድን ዘርፉ ለምጣኔ ሀብቱ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በተለይ በወርቅ ልማትና ግብይት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር ለመፍታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ሕገ ወጥ የወርቅ ልማትና ግብይት ለመቆጣጠር የሚያስችል ግብረ ኃይል በማቋቋም ተሠርቷል፤ በዚህም በርካታ ሕገ ወጦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ በማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንዲታይ አድርገዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ሕገ ወጥ ግብይቱን በማስቀረት፣ የማዕድናት ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግና ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በማድረግ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የዘርፉ ልማት አበረታች መሆኑን ተከትሎም በአነስተኛ ደረጃ ይመረት የነበረው ወርቅ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ አስችሏል፤ ይህን ተከትሎም የወርቅ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንዲሁም ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ የሚገኘውም የውጭ ምንዛሬም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል።

በዚህም የታየው ለውጥ ቀደም ሲል ሀገሪቱ ከወርቅ ማግኘት ያለባትን ብዙ ጥቅም በሚገባ እንዳታገኝ ሲያደረግ እንደነበረም አመላክቷል። ከማሻሻያው በኋላ ብሔራዊ ባንክ ለአነስተኛ ወርቅ አምራቾች ተጨማሪ ማበረታቻ በመስጠቱ በአንድ ወር አራት ነጥብ ሶስት ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ያደረገበት ሁኔታም ነበር።

በተለይ በማዕድን ኤክስፖርት ቀደም ካሉት ዓመታት በማይወዳደር መልኩ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል። በተለይም ወደ ውጭ ከሚላኩ የማዕድን ምርቶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ወርቅ ላይ እምርታዊ ለውጥ እንዲታይ ሆኗል። ለአብነት በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 26 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የማዕድን ሚንስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ እንዳሉት፤ መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማዕድን ዘርፉን ከኢኮኖሚው ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ መውሰዱ ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ያደርጋል። በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ ትልቅ እምርታን ፈጥሯል። አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮች በመሳብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተለይ ወርቅ ላይ የነበረው ችግር እንዲፈታ በማድረጉ በዚህ ዓመት በወርቅ ልማትና ግብይት ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንዲታይ ምክንያት መሆኑን ያመላክታሉ። ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆንም አዳዲስ በርካታ የወርቅ ግዥ ጣቢያዎች መከፈታቸውንም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ወደ ብሔራዊ ባንክ ካስገባችው ወርቅ በላይ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይገባል ብለው እንደሚያሰቡም አስታውቀዋል።

ይህም ሀገሪቱ ያላትንና ይባክን የነበረው ምን ያህል ሀብት እንደነበር እንደሚያሳይ ገልጸው፤ የተደረገው የፖሊሲ ለውጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ያመጣውንም ለውጥ ማየት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ሚንስትሩ እንዳብራሩት፡- አሁን ላይ ሦስትና አራት የወርቅ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ። እስከ አሁን በወርቅ ላይ የመጣው ውጤት የመጣው በትላልቅ ፋብሪካ ደረጃ ሳይሆን በአነስተኛ ደረጃ በሚመረት ነው። አሁንም ቢሆንም ብዙ መሥራትና መስተካካል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ሆኖ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየመጣ ያለው ወርቅ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው።

ለማዕድን ዘርፉ ብዙ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ እንደ መሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ያላቸው ልምድ፣ ሀብትና ቴክኖሎጂ ይዘው መጥተው የሚሠሩበት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በተለይ በኤክስፖርቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሀገራችን ያላት አቅም ከዚህ በብዙ እጥፍ የበለጠ ነው። ይህ የሚነግረን ያለመጠቀማችንን፣ ፖሊሲያችንን አለማስተካከላችን መዘግየታችን ነው። አቅማችንን ገና አልተጠቀምን›› የሚሉት ሚንስትሩ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማዕድን ዘርፉ በትክከለኛ ጊዜ የመጣና ተስፋ ሰጪ ለውጦች የታዩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የወርቅ ኤክስፖርት እንዲጨምር ካደረጉት በዋነኛ ምክንያቶች መካከል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና ብሔራዊ ባንክ ያደረገ የዋጋ ማሻሻያና ማትጊያ እንዲሁም ሕገ ወጥነት በመከላከል ረገድ የተደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር መሆናቸው የዘርፉ ባለሙያ ይናገራሉ።

የሥነ ምድር ተመራማሪው (ጂኦሎጂስት) አቶ ሳዲቅ ከቢር ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ በወርቅ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ይገልጻሉ። የወርቅ ዋጋ ከውጭ ምንዛሬ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማሻሻያው የወርቅ ምርትንም ሆነ ወደ ውጭ የሚላከው የወርቅ መጠን በእጥፍ እንዲጨመር ማድረጉን ይገልጻሉ። ቀደም ሲል የነበረው የወርቅ ምርት በእጅጉ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ የሚያስገኘው ገቢ እዚህ ገባ የሚባል እንዳልነበር ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ መደረጉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በእጥፍ እንዲጨምር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ መንግሥት በሕገ ወጥና በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ እየወሰደ ያለው ሕጋዊ ርምጃና ቁጥጥር መጠናከሩ ሌላኛው ምክንያት መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ማበረታቻ ብዙ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ አድርጓል። ባንኩ ወርቅ ለሚያቀርቡ አካላት ያደረገው ማበረታቻ ብዙዎቹ አምራቾች ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያበረታታና የሚያተጋ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላት ቢሆንም፣ ከሕገ ወጥነትና ከሌሎች ችግሮች ጋር ተያይዞ ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተደርጎ ቆይቷል ሲሉ የሚገልጹት አቶ ሳዲቅ፤ ከለውጡ በኋላ መሻሻሎች መታየታቸውን ይገልጻሉ።

በተለይ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይገልጻሉ። አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለው የወርቅ ዋጋ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት የወርቅ ዋጋ ሳይቀር የተሻለ እንዲሆን እያደረገ ነው እንደሚባል አስታውቀዋል። ከጎረቤት ሀገራት ወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱም አቶ ሳዲቅ ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ መንግሥት ሕገ ወጥ የወርቅ ዝውውርን በመከላከል ረገድ በየክልሉ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ርምጃም ሲወስድ ቆይቷል፤ ክልሎችም ወርቅ በማምረት ሥራ ላይ በተሠማሩ ባሕላዊና አነስተኛ አምራች ማህበራት ላይ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በማስቀመጥ ጭምር ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ ናቸው። በዚህም አንድ ማህበር በዓመት ምን ያህል ወርቅ ማስገባት አለበት የሚለው እንደ ግዴታ ተቀምጧል፤ ማህበራቱ ይህንን ግዴታቸውን እንዲወጡ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ ናቸው።

‹‹አሁን ላይ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በእጥፍ መጨመሩ የሚያሳየው ምርቱ መጨመሩን አይደለም፤ ቀደሞ ሲልም ቢሆን ምርቱ ነበረ፤ በሕገ ወጥና በኮንትሮባንድ ንግድ ያለ አግባብ ወደ ውጭ ይወጣ እንደነበር ያመለክታል ››ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሕገ ወጥነት በመከላከል ረገድ እየተደረገ ያለው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ክልሎች የወርቅ አምራቾችን በተመለከተ ያስቀመጡት ግዴታ በወርቅ ላይ ለመጣው ለውጥ የራሳቸውን ሚና መጫወታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በወርቅ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ዘንድሮ ለውጭ ገበያ ከተላከው ወርቅ ከታቀደው በላይ ገቢ ለማግኘት ያስችላል። በኢትዮጵያ የወርቅ ክምችቱ በደንብ አለ፤ የወርቅ ምርት ችግርም የለም። ወርቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ በደንብ ከተሠራና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከታሰበው በላይ ሊገኝ ይችላል።

በአሁኑ ወቅት በባሕላዊና በአነስተኛ አምራቾች የሚመረተው የወርቅ መጠን ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት አቶ ሳዲቅ፤ በጋምቤላ ክልል ወደ ሥራ የገባው የኢት ማይኒንግ ዓይነት የወርቅ ፋብሪካ የወርቅ ምርት በእጥፍ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። ሌሎችም ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግ ከታቀደ በላይ ገቢ ለማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በተለይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በወርቅ ማምረት ላይ እንዲሠማሩ ቢደረግ በወርቅ ኤክስፖርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ወርቅ አምራቾች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና ማበረታቻዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ወርቅ ብዙ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት መሆኑን ገልጸው፣ በመንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ሳይቀሩ ጥብቅ ቁጥጥር ቢያደርጉ ከዚህ በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

ወርቅ ከሚቆፈርበት ቦታ ጀምሮ ባሉ ስንስለቶች ላይ የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አስገንዝበው፣ ‹‹እንደ ሀገር ከወርቅ እየተጠቀም ነው ማለት አይቻልም፤ አሁን ላይ 50 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው እየተመረተ ያለው። ሌላው ቀርቶ 70 እና 80 በመቶ ያህል እንኳን ቢመረት ብዙ መጠቀም እንችላለን›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ የወርቅ ማዕድን ክምችት ያለባት ሀገር መሆኗን እሳቸውም ጠቅሰው፣ ማዕድን ዘርፉ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ብዙ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም አመላክተዋል። በዘርፉ ልምድ፣ አቅምና ቴክኖሎጂ ባላቸው ከፍተኛ ደረጃ አምራቾች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዘንድሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በወርቅ ልማትና ግብይት ላይ ከፍተኛ ለውጦች ታይተዋል። ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ ያለው የወርቅ መጠን እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወርቅ ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ መሆኑንም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

ይህንን አበረታች ውጤት ማስቀጠል ሀገሪቷ ከወርቅ ምርት ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንድታገኝ ያስችላል። ይህም መንግሥትን ጨምሮ ከልማቱ ለብሔራዊ ባንክ እስኪገባ ድረስ ባሉት ሂደቶች ውስጥ የሚሠሩ የሚመለከታቸው አካላትን የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃል።

በወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You