የምግብ ደህንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች ስጋት ላይ መውደቁን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ለእዚህም በዓለም የሚታዩ የለውጥ ሂደቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ፈጣን የከተማዎች መስፋፋት፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም የአገራት ለእነዚህ ሁኔታዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የምግብ ሥርዓት አለመዘርጋታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፤ እነዚህ ችግሮች የምግብ ደህንነት ችግርን አሳሳቢ ያደርጉታል:: ይህን ተከትሎም አገራት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው::
በኢትዮጵያም የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል የግብርና እድገት ፕሮግራም ምዕራፍ አንድና ምዕራፍ ሁለት በሚል በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሲተገበር ቆይቷል:: ፕሮግራሙ በተለያዩ አጋር አካላት ድጋፍ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ ሲሆን፣ በተለይም የግብርና እድገት ምዕራፍ አንድ በተመረጡ ወረዳዎች በዋናነት የግብርና ምርቶችን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እና ለሰብል እና ለእንስሳት ተዋጽኦዎች ገበያ በማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል:: ምዕራፍ ሁለት ደግሞ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ እና የአነስተኛ አርሶ አደሮች ምርቶችን የገበያ ችግር በመፍታት ረገድ ትኩረት አድርጎ ሠርቷል:: እነዚህ ሁለቱ ፕሮግራሞችም ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ እንደቻሉ ይነገርላቸዋል::
የግብርና እድገት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት ተኪ የሆነው የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በቅርቡ በድሬዳዋ ከተማ በይፋ ተጀምሯል:: በፕሮግራሙ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሔራዊ ሥራ አስኪያጅ (ማናጀር) ከበሩ በላይነህ እንዳሉት፤ የምግብ ሥርዓት ማለት ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን የእሴት ሰንሰለት የሚይዘው የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ነው::
የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ኤ ጂ ፒ) ቀጣይ ሲሆን፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምን ተከትሎ የተዘጋጀውን አዲሱን የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ እና እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2030 የሚተገበረውን የ10 ዓመት የግብርና ዘርፍ ፖሊሲ ለመተግበር እንደ ቁልፍ መሣሪያ የሚያገለግል ነው::
ፕሮግራሙ በዘጠኝ ክልላዊ መንግሥታት እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ከበሩ፤ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ ሲዳማ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ሐረሪ፣ እና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ማለትም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ውስጥ በሚገኙ 181 ወረዳዎች እና አራት ሺ 250 ቀበሌዎች እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2029 ለሰባት ዓመታት ተፈጻሚ እንደሚሆን አብራርተዋል::
እንደ አቶ ከበሩ ማብራሪያ፤ ፕሮግራሙ አነስተኛ መሬት ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፤ የእንስሳት እርባታ እና የሰብል ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ለመርዳት የሚውል ይሆናል:: ፕሮግራሙ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮኑ በቀጥታ፣ ሦስት ሚሊዮን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው:: ከተጠቃሚዎቹ መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ይሆናሉ::
ፕሮግራሙ በዋናነት በሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የግብርና ምግብ ሥርዓት ተወዳዳሪነትን ማሻሻል እና የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር የግብርና ቀውስ አስተዳደር (ማኔጅመንት) ከፕሮግራሙ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው::
ይህ የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በፊት ከነበሩት ሁለቱ ፕሮግራሞች በላይ ሰፊ ሕዝብና አካባቢን የሚያቅፍ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው የጠቀሱት አቶ ከበሩ፤ የግብርና እድገት ፕሮግራም የመጀመሪያው ምዕራፍ በአራት ክልሎች በ96 ወረዳዎች መተግበሩን አስታውሰዋል:: ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በስምንት ክልሎች በ157 ወረዳዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ አሁን በይፋ የሚጀመረው የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች 183 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ አካታች ፕሮግራም መሆኑን አመልክተዋል::
እንደ አቶ ከበሩ ማብራሪያ፤ የአገሪቱ ግብርና በአመዛኙ ዝናብ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ቆይቷል:: ይህም ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኖም ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስኖ እየተስፋፋ መጥቷል:: ቴክኖሎጂ እና የኤክስቴንሽን አገልግሎቶች እየተስፋፉ መጥተዋል:: በአዲሱ ፕሮግራም ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ መስኖ ላይ ብዙ ይሠራል:: ከመስኖ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂ ወሳኝ በመሆኑ የምርምር ተቋማት ቴክኖሎጂ የማፍለቅ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ይሠራል:: የመፈጸም አቅምም የማሳደግ ሥራ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል ይሆናል::
ማምረት ብቻውን የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደማያስችል የጠቆሙት አቶ ከበሩ፤ ግብይትም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት:: ከዚህ ቀደም በግብይት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት አንዳንድ ቦታዎች ምርት እያለ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ እጥረት የሚከሰትበት ወቅት ነበር ሲሉም ተናግረዋል:: የገበያ ችግር ለመፍታት ትስስር አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰው፣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የምርት ማቆያ መጋዘኖችን መገንባት፣ የገበያ ማዕከላትን መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል:: በመሆኑም ፕሮግራሙ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ክፍተት ያለበትን እየለየ እንደሚሞላ ጠቁመዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የቴክኖሎጂ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ ግብይት ላይ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም እንዲሁ ግብይት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል:: የዘርና የዘር ብዜት ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም ትኩረት በማድረግ የሚሠራ ሲሆን፤ የውሃ እና የማከማቻ ቦታ ችግር ባለበት አካባቢም እንዲሁ ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ያከናውናል::
በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ ተግባራዊ የተደረገው የግብርና ልማት ፕሮግራሞች በሰው ኃይልና በቁሳቁስ አቅም ከመገንባቱም በላይ ሰፊ ልምድ ተገኝቶበታል ያሉት አቶ ከበሩ፤ በቀደመው ሥራ የተገኘው ልምድ እና አቅም በአዲሱ ፕሮግራም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት::
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የፕሮግራሙ በጀት 685 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 600 ሚሊዮኑን የዓለም ባንክ የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደ 65 ሚሊዮኑን የሚጠጋው ደግሞ ከሌሎች የልማት አጋሮች የተገኘ ነው:: ተጠቃሚው ኅብረተሰብ ደግሞ በጉልበት እና በቁስ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ሥራ በመሥራት አስተዋጽኦ ያደርጋል::
ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞችን ከአገራዊ እቅድ እና ፕሮግራሞች ጋር የማጣጣም ክፍተቶች ይስተዋሉ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ግርማ፣ በዚህ ፕሮግራም ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ከሌሎች አገራዊ እና የዘርፉ ፕሮግራሞች ጋር የማጣጣም ሥራው ከንድፉ ጀምሮ መሠራቱን ገልጸዋል:: ይህም ፕሮግራሙን ከሌሎች ፕሮግራሞች ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል::
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ፕሮግራሙ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ እንዴት እንደሚተገበር፤ የክትትል እና የድጋፍ ሥርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት ከአሁኑ በግልጽ ተቀምጧል:: በፌዴራል ደረጃ በድሬዳዋ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ከተካሄደበት ቀን ጀምሮ ክልሎች በየክልሎቻቸው የማስጀመሪያ መርሃ ግብሮችን የሚያካሂዱ ይሆናል:: ፕሮግራሙ ባለፈው ታኅሣሥ ወር የተፈቀደ ሲሆን፤ በሁለት ወር ውስጥ አስፈላጊውን ዝግጅት በመጨረስ ወደ ትግበራ ገብቷል፤ የፕሮግራሙ በጀት ስለተመደበ የሀብት እጥረት አይኖርም፤ በሁሉም ክልሎች በአፋጣኝ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ወደማድረግ ይገባል::
እንደ ዶክተር ግርማ ማብራሪያ፤ ስሙም እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ፕሮግራሞች ምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የሚያግዙ ናቸው:: ፕሮግራሙ እንደ አገር የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ከሚያግዙ ፕሮግራሞች አንዱ ነው:: በቀጣይ ሰባት ዓመታት ይህኛውን ፕሮግራም እና ሌሎች ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ይረዳል:: አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማትንና ሌሎች ፕሮግራሞችንም የሚያግዝና የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ ነው::
ይህ ፕሮግራም ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማሳካት እንደሚያስችል ተስፋ ተጥሎበታል:: የዓለም ባንክ ተወካይ እና የሌሎች የልማት አጋር ተወካዮች በበኩላቸው ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሆኖ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማየት እንደሚፈልጉ ጠቁመው፤ ማንኛውም ተጨማሪ እገዛ ቢያስፈልግ ባንኩ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል::
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሱዳን እንዲሁም የደቡብ ሱዳን ተወካይ ሚስተር ኦስመኔ ዲኦኔ እንዳሉት፤ ባለፉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ እና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በትብብር መሥራቱ አገሪቱ ከሰሃራ በታች ካሉት አገራት መካከል ከፍተኛውን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ አስችሏታል:: ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት 5 ነጥብ 2 ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ከአንጎላ ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር እንድትሆን እንዳስቻላት ጠቁመዋል:: ይህ የእድገት ምጣኔ አገሪቱ የግብርና ዘርፍ ማነቆዎችን እየፈታች መምጣቷንም አመላካች ነው::
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ድጋፉ ለሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ልማት የሚውል ነው ብለዋል:: ኢትዮጵያ የብዝሃነቶች አገር ናት ያሉት የባንኩ ተወካይ፤ ከአገሪቱ ብዝሃነት መገለጫዎች አንዱ የመልክዓ ምድር ብዝሃነት ነው ብለዋል:: ቆላማ፣ ደጋማ እና ወይና ደጋማ የአየር ጸባይ ባለቤት መሆኗን በመግለጽ፤ የዓለም ባንክ ለአገሪቱ የግብርና ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ የአገሪቱን የአየር ንብረት ብዝሃነትን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል::
ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን እየደገፈ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ኦስመኔ፤ የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራሙ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እየተተገበረ ያለ ፕሮግራም አካል መሆኑንም አንስተዋል:: ፕሮግራሙ የፋይናንስ ችግር የሌለበት ፕሮግራም መሆኑን የጠቆሙት የባንኩ ተወካይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጨባጭ ለውጥ አምጥተው ማየት እንደሚፈልጉ አንስተዋል:: ባንኩ ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ መሥራቱን ይቀጥላል ብለዋል:: ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ዓለም ባንክ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል::
ፕሮግራሙ ይፋ በተደረገበት ወቅት ከተገኙት የልማት አጋሮች መካከል የዩኤስ አይድ፣ የኔዘርላንድስ እና የጀርመን ተወካዮች፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ይህኛው ፕሮግራም እንዲሳካ የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ክልሎችም ፕሮግራሙን ወስደው ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በመጠቆም ለሥራው በጣም ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት::
በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረሪ፣ የድሬዳዋ ተወካዮች በመጀመሪያውና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የአቅድ ዘመናት(በጂዲፒ አንድ እና በጂዲፒ ሁለት) ፕሮግራሞች ስኬታማ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በዚህም ሕዝባቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻላቸውን ጠቁመዋል:: በግብርና ልማት ፕሮግራም ምዕራፍ አንድ እና ምዕራፍ ሁለት የተገኙ ልምዶች እና ጥንካሬዎችን በመጠቀም የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራምን ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም