ሰው በባህሪው ስልቹ ነው፣ ሰው ወረተኛ ነው፣ ዛሬ የያዘው ወርቅ ነገ መዳብ ይመስለዋል። ዛሬ ያመሰገነውን ነገ ሊኮንነው ይችላል። አሁን የሳመውን አፍታም ሳይቆይ ይነክሰዋል። ሰው ወረተኛ ብቻ አይደለም፣ ራስ ወዳድም ጭምር ነው። ምንም ነገር ቢሆን የሚፈልገው ለእሱ እስከተመቸውና እስከሆነለት ብቻ ነው።
ሰው ተለዋዋጭ ፍጥረት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ የወረተኝነትና በአንድ ሃሳብ ያለመጽናት ዝንባሌ እንዳላቸው ጥያቄ የለውም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ተለዋዋጭ የሚሆኑት ክፉና ወረተኛ ስለሆኑ ላይሆን ይችላል፡፡ የወቅቱ እውነታ፣ የሚለዋወጠው ሁኔታቸውና እይታቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆኑ ጉዳዮች በላያቸው ላይ ስለሚለዋወጡ እነሱም ከመለወጥ ውጪ ምርጫ እንዳይኖራቸው ይገደዳሉ፡፡
ዓለምም ሕይወትም ወረተኛ ናቸው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ስለዚህ ሰው በተፈጥሮው ሁሌም አዲስ ነገር ፈላጊ እንደመሆኑ ወረት ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። አንዳንዴ ግን ወረተኛ መሆናችን ሳይሆን ወረተኛ የምንሆንባቸው ጉዳዮች አስገራሚ ናቸው። በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ወረተኛ የሆንባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እነዚህ ወረተኛ የሆንባቸው ጉዳዮች ደግሞ የሚጠቅሙንና አንድ ጊዜ ጀምረን የተውናቸው ነገሮች መሆናቸው ነው። እስቲ እንደ ማህበረሰብ ጀምረን በወረት የተውናቸውን ጠቃሚ ነገሮች አንድ ሁለት እያልን መለስ ብለን እንታዘብ።
እንደ ማህበረሰብ የሆነ ጊዜ ጀምረን ብዙ ሳንቆይ እርግፍ አድርገን ከምንተዋቸው ጉዳዮች አንዱ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት (ማስ ስፖርት) ነው። ከሆኑ አስርት አመታት በፊት እነ ኃይሌ ገብረሥላሴና እነ ደራርቱ ቱሉ በኦሊምፒክ አሸንፈው አገራቸውን ሲያኮሩ ሚዲያው ሁሉ ስለሩጫ ሲዘግብ ውሎ ያድራል። ያኔ ከተሜውም ገጠሬውም ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት ማለዳ እየተነሳ ይሮጣል። እስከ ቅርብ ጊዜም እንደ ድሮው ባይሆንም የአትሌቶቻችን ድል ሲሰማ ሁሉም ሯጭ ለመሆን ሲሽቀዳደም ማየት የተለመደ ነው።
ውሎ ሳያድር ግን የአትሌቶቻችን የድል ስሜት ግለቱ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ማለዳ ተነስቶ ይሮጥ የነበረና አትሌቲክስን ባህሉ አድርጎ ለመቀጠል ቃል የገባ ሁሉ ከአልጋው ተነስቶ እንኳን ለመሮጥ ወደ ሥራም ወደ ትምህርት ቤትም ለመሄድ ዳገት ይሆንበታል። የሩጫውን ከጠቀስን አይቀር የኳሱንም እናክልበት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ከሰላሳ አንድ አመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ አገር ምድሩ ሁሉ ኳስ ተጫዋች ሆኖ ነበር። በሳምንቱ የእረፍት ቀናት ለኳስ ጨዋታ አውራ ጎዳናዎች ሳይቀሩ በየቦታው ሲዘጉ አይተናል። በእርግጥ አሁንም ኳስን የሚወዱ ወጣትና ጎልማሶች ይሄ ልምዳቸው ቢዘልቅም ብዙዎች ወረት ሆኖባቸዋል።
በማስ ስፖርት ጉዳይ ላይ ማህበረሰብ ብቻም ሳይሆን መንግሥትም ወረተኛ ነው። የሆነ ወቅት ላይ በየከተማው እሁድ እሁድ ማስ ስፖርትን ለማስፋፋትና ባህል ለማድረግ የመንግሥት አካላት የሚያደርጉት ቅስቀሳ ቀላል አይደለም። ይህ ግን ከወር ያለፈ ዕድሜ ሳይኖረው እንዲያው ወረት ሆኖ ሲቀር በቅርብ ጊዜ እንኳን ታዝበናል። ለብስክሌት ብቻ የተፈቀደ መንገድ የመቀየስ ጉዳይም ከዳር ደርሶ አላየንም። በሳምንቱ የእረፍት ቀናት ጎዳናዎችን ከተሽከርካሪ ነፃ በማድረግ ማህበረሰቡ በእግሩ እንዲንቀሳቀስ የተወጠነው መልካም ሃሳብስ የት ደረሰ?።
ሌላው የፅዳትን ጉዳይ የተመለከተ ነው። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ከተማን የማፅዳት ጉዳይ የአንድ ወቅት ግርግር መሆኑ ይገርማል። አንድ ወቅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጎዳና ወጥተው አስፋልት በመጥረግ ተነሳሽነት ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። እሳቸውን ተከትለውም ለጥቂት ሳምንታት ብዙ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ ተግባር ሲፈፅሙ ታይተዋል። ሕዝብም ይህን ተግባር እሰየው ብሎ አካባቢውን ቢያንስ በሳምንት አንዴ ለማፅዳት መጥረጊያውን ይዞ ሲወጣ አይተናል። ይህም ብዙ ሳይዘልቅ ወረት ሆኖ አሁን አሁን የአዲስ አበባን ጎዳና ለማፅዳት በከተማዋ እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ትልልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱበትን ወቅት እየጠበቅን ነው።
የበጎ ተግባር ወይም በጎ ፍቃድ አገልግሎት ጉዳይም የወረት ሆኖብናል። ኮቪድ-19 በተከሰተበትና ሁሉ ነገር በተዘጋጋበት ወቅት የበጎ ተግባርና በጎፍቃድ አገልግሎት እጅግ አስደናቂ እንደነበር ማንም አይዘነጋውም። በወቅቱ መንግሥት ለአቅመ ደካሞች ሲያደርግ ከነበረው ድጋፍና ማዕድ ማጋራት ባሻገር የተለያዩ ወጣቶች በየጎዳናው ድጋፍ በመሰብሰብ ግሩም የሆነ የረድኤት ተግባር ላይ በስፋት ተሰማርተው ታይተዋል።
በዚህም የስንቱን አቅመ ደካማ ሕይወት እንደታደጉ ወደ ፊት ታሪክ ይዘክራቸዋል። ያም ሆኖ ይህ መልካም ተግባር ዛሬ ላይ በእጅጉ ቀዝቅዟል። በእርግጥ እንደ ድርቅና ሌሎች ችግሮች የሆነ ቦታ ሲከሰቱ የበጎ ተግባር ሥራዎችን ለማከናወን በርካታ ሰዎች ሲረባረቡና ሲያስተባብሩ በቅርቡ እንኳን ተመልክተናል። ነገር ግን የበጎ ተግባር እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ሁሌ ችግሮች እስኪገጥሙን መጠበቅ አለብን? በተለይም በኑሮ ውድነት፣ በጦርነትና ግጭቶች ከመኖሪያ ስፍራው ተፈናቅሎ የዕለት ጉርሱን እንኳን ለማግኘት የሚቸገር በርካታ ሕዝብ ባለበት አገር የበጎ አድራጎትና በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ከምንጊዜውም በላይ መጠናከር እንጂ የወረት መሆን አይገባቸውም ነበር።
አንዳንዴ የአገር ፍቅርም ወረት የሚሆንባቸው ሰዎች አሉ። ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር አገር አንድ ችግር ሲገጥማት ብቻ ገንፍሎ የሚወጣባቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በችግር ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ለአገራቸው ሕይወታቸውን ጭምር እንደሚሰጡ ፉከራቸው ልብ የሚያሞቅ ነው። እነዚሁ ሰዎች ደግሞ በደህናው ጊዜ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች ሲጋጋሉ አገር ካላፈረስን ብለው አገር ይያዝልን ሲሉ እናያቸዋለን። ከሁሉም የከፋው ለአገር ያለን ፍቅር የወረት ሲሆን ነው፣ ይህ ፈፅሞ መሆን የሌለበት ነው። ሌሎቹም ጉዳዮች ቢሆኑ አገርና ሕዝብን እስከጠቀሙ ድረስ የአንድ ወቅት ግርግር ሆነው በወረት እንዳይቀሩ ይታሰብባቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም