አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች አነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጦች በተለይ እንደ ጫት ያለ ቅጠላ ቅጠል፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ፣ ምግብና ወዘተ ስንሸምት ለመያዣነት የምንጠቀመው የፕላስቲክ ከረጢቶችን (ፌስታል) ነው፡፡ ቀድሞ ካኪ/ኪስ ወረቀት እንጂ ፌስታል ለቁሳቁስ መጠቅለያነት አይውልም ነበር፡፡
ከልኳንዳ ሥጋ ሲገዛ ኪሎው ተመዝኖ በጋዜጣ ተጠቅልሎ ይሰጥ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ቅቤ እንኳን ሲሸጥ መያዣው የኮባ ቅጠል ነበር፡፡ መርካቶ ዱባይ ተራና ሚሊተሪ ተራ ጨርቃ ጨርቅ ብትገበዩ፤ ሸራ ተራም ሆነ አመዴ ገበያ ጫማ ብትሸምቱ በጋዜጣ ተጠቅልሎ አልያም ትንሽ ሳጥን በሚመስል ጠንከር ያለ ካርቶን እንጂ ፌስታል ለመያዣነት አይውልም ነበር፡፡ ያኔ አብዛኛው ነጋዴ ጋዜጣ እየገዛ ዜናውንና መረጃውን ካነበበ በኋላ የሚሸጠውን ቁሳቁስ ለመጠቅለያነት ያውለው ነበር፡፡ እናቶች እንኳን ለዕለት፣ ለሳምንት በሉት ለወር የሚሆን አስቤዛ ሲሸምቱ ከሰሌን የተሠራ ዘንቢል አልያም በስስ ጨርቅ የተሠራ አነስተኛ ዕቃ መያዝ የሚችል ጨርቅ ነገር ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይህን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተክቶ አሁን ላይ የትም የሚገኘው ስስ ፌስታል በገበያ አልነበረም፡፡ አልፎ አልፎ ቢኖር እንኳን ከካኪ ወረቀት የማይተናነስ ጠንካራ ፌስታል ነው፡፡
ፌስታል ገበያ ላይ ውሎ በየቦታው እቃ መያዣ መሆን ከጀመረ ቢበዛ ሦስት አስርተ ዓመታት አይሆንም፡፡ የዛሬን አያርገውና ሳንቲሞች አቅም ሳያጥራቸው በፊት አንዱ ፌስታል 15 ሳንቲም ይሸጥ ነበር፡፡ ይህም ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ቀስ በቀስ የፌስታል ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲሄድ ቀድሞ የካኪ ወረቀት የሚሰጠውን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዲተካ አድርጎታል። አሁን ላይ የትኛውም ቁሳቁስ ሲሸመት መያዣው ፌስታል ነው። ሥጋ እንኳን በጋዜጣ ቀርቶ በፌስታል ተጠቅልሎ ነው የሚሰጠው። ያውም ከመሳሳቱ የተነሳ የያዘውን ሸቀጥ ከሱቅ ቤት ድረስ የማድረስ አቅም በሌለው።
ፌስታል አገልግሎቱ ባልከፋ ነበር። ከአገልግሎቱ በላይ በአካባቢ ብክለት የሚያደርሰው ጉዳት አንድና ሁለት አይደለም። ለመጪው ትውልድ ጭምር ዘመን ተሻጋሪ ችግር ጥሎ የሚያልፍ ነው፡፡ በፌስታል መጠቀም ጊዜያዊ ችግር ቀባሪ ቢመስልም ዘላቂ ችግር ፈጣሪ ነው። ፌስታልና ሌሎች ላስቲኮች በመቶ ዓመት እንኳን አለመበስበሳቸው ለመሬት መከላት ዋነኛ ምክንያት ናቸው። በተለይ በገጠር አካባቢዎች የወዳደቁ ፌስታሎች ለእርሻ ትልቅ ተግዳሮት ናቸው። ፌስታሎች በወደቁበት አካባቢ ሳር፣ ቅጠላ ቅጠል እንዳያድግና እንዳይለመልም ምክንያት ይሆናሉ።
እንደ ጎረቤታችን ኬንያ የመሳሰሉ አገሮች በፌስታል መገበያየት የታገደ ስለሆነ አይታሰብም፡፡ በዚህም ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ጎን ለጎን ለከተሞቻቸው ንጽሕና ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡
እኛ አገር ከተማው ገጠሩ ሳር ቅጠል ሳይሆን በፌስታል የተሞላ ነው። የፌስታል ችግር ይበልጥ የሚገባን በክረምት ወቅት ነው፡፡ በክረምት እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች ፌስታሎች በየቦታው ተጥለው ይታያሉ፡፡ በየአጥሩ ጥጋ ጥግ ፣ በፍሳሽ ቱቦዎች መተላለፊያ ውስጥ እና በከተማዋ ወንዞች ሁሉ ፌስታል የተጣለ ሳይሆን ከዝናብ ጋር ከሰማይ የወረደ ሊመስል ይችላል፡፡
በእምነት ቦታዎች፣ በኳስ መጫወቻ ሜዳዎች፣ በወንዞች፣ በፍሳሽ ቱቦዎች በፌስታል ተሞልተው ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ዝናብ ሲዘንብ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በፌስታል ስለሚደፈኑ በዚያ ላይ ፍሳሽና ጎርፍ ሲጨመር ፍሳሹ ትቦውን ጥሶ አስፋልት ላይ እንዲፈስ ያደርጋል።
ወደ ገጠር ከተሞች የሚያደርሱ ዋና ዋና የአስፋልት መንገዶች ዳርቻ በፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች› እና በፌስታል እየተሞላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግብርናውንና የአካባቢ ብክለትን ከመጨመሩ ባሻገር ከብቶች እየበሉት የሚጎዱበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም።
በአገራችን እያንዳንዱ ዜጋ በዓመት በአማካይ 238 ፕላስቲክ ሻንጣዎችን እንደሚጠቀም የቅርብ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህ ብዛት 97.000 ቶን ይሆናል፣ በዚህ ሁሉ ብክነት እንደገና ጥቅም ላይ የዋለው 10% ብቻ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ስርጭትንና መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ጉዳዮችን የማስተማር አስፈላጊነት ግን አልተሠራበትም፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥረት ቢደረግም ፕላስቲክ ከረጢቶችን መልሶ የመጠቀም ባሕል በጣም አነስተኛ ነው፡፡
በፕላኔታችን ላይ በብዛት በብክለት ደረጃ ከሚጎዱና የሰው ልጆች በስፋት ከሚያመነጩት አካባቢያዊ ችግሮች መካከል አንዱ የፕላስቲክ ከረጢቶች ሲሆኑ በምድራችን በየትኛውም ማዕዘን እየተከማቹ እንደሚገኙ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ ማለት ከአካባቢ አልፎ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ዓለም አቀፍ ብክለትን ያስከትላል ማለት ነው፡፡
አንድ የፕላስቲክ ሻንጣ ለአያያዝ አመቺና በቀላሉ የሚቀመጥ በመሆኑ ብክለት አያመጣም ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በፕላስቲክ ከረጢቶች የውሃ መበከል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን፣ እንስሳትን፣ ኤሊዎች እና አዕዋፎችን ለሞት ይዳርጋል፡፡
የፕላስቲክ ከረጢቶችን ለማምረት ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ያስፈልጋል፣ እናም የእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች ከዘይት የሚመነጩ ንጥረ ነገሮች የአካባቢ ጠንቅ ሆነው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መርዛማ የብረት ቅሪቶችን የያዙ የፕላስቲክ ከረጢቶች ግን ዛሬም ያለ ምንም ዓይነት ቁጥጥር በየቦታው ይጣላሉ፡፡
ሀገራት የፕላስቲክ ከረጢቶችን አጠቃቀም ለመቀነስ የተለያዩ መንገዶችን እያጤኑ ነው፡፡ አንደኛው መፍትሔ በእነዚህ ሻንጣዎች ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ሊበሰብሱ በሚችሉ ሌሎች ንጥረ ነገሮች መተካት ነው። እኛም ትኩረት አልሰጠነውም እንጂ ቢያንስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንጠቀምባቸውን የፕላስቲክ ከረጢቶች መጠን መቀነስ እንችላለን፡፡
ለዚህም የጨርቅ ሻንጣዎችን ወይም አንዳንድ ተመሳሳይ ቁሳቁሶችን ብንጠቀም አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ወደ ገበያ በምንሄድበት እያንዳንዱ ጊዜ ብዙ የፕላስቲክ ሻንጣዎችን መጠቀም አያስፈልገንም ማለት ነው ፡፡
የራሳችንን የግዢ ሻንጣ ይዘን ወደ ሸመታ ብንወጣ፣ ጥቂት ነገሮችን ብቻ የምንገዛ ከሆነና እጃችን ሊሸከም ከቻለ የፕላስቲክ ከረጢቶችን አለመጠቀምም ካሰብንበት ቀላል መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015