የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመት መሪ እቅድ የእድገት ማእዘኖች በሚል ከያዛቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎም በማእድን ሚኒስቴር በኩል ተቋማዊ የአደረጃጀት ለውጥ/ሪፎርም/ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴሩ በማእድን ጥናትና ልየታ፣ ልማት፣ አቅም ግንባታ፣ ወዘተ. ላይ ሰፋፊ ስራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሌላም በኩል የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ ሕገወጥ የወርቅ ግብይትና የመሳሰሉት የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውም እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በዛሬው የምድር በረከት አምዳችን ሚኒስቴሩ ሪፎርም ካደረገ በኋላ ያከናወናቸውንና እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባሮችን እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ከማእድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በወሰዳቸው የማሻሻያ (ሪፎርም) እርምጃዎች ያመጣቸውን አበይት የሚባሉ ለውጦችን ቢገልጹልን?
አቶ ሚሊዮን፤ ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ያላት ትልቅ ሀገር ናት፡፡ እንደ ወርቅ፣ ፕላቲኒየም፣ ኒኬል፣ ኮባልት፣ ብረት፣ ለማዳበሪያ ግብአት የሚውሉ ፖታሽ፣ ፎስፌት፣ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ፣ የእንፋሎት ኃይል፣ የመሳሰሉ ከፍተኛ የሆነ የማዕድን ሀብት ክምችት አላት፡፡ ይሁን እንጂ የሀብት መጠኑ ወይንም የማዕድን አለኝታው በውል በዝርዝር ተጠንቶ አላለቀም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም የኢትዮጵያ ሥነምድር መረጃ ካርታ ከ25 በመቶ አይበልጥም፡፡
ወደ ጥያቄው ስመለስ፣ በመንግሥት በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ዘርፎች ላይ የተመሰረተ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል የእይታ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የዛሬ አምስት ዓመት ካጋጠመው የኢኮኖሚ መንገራገጭ አንጻር ሲነጻፀር በመንግሥት የተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ትክክለኛ ነው፡፡በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የኢኮኖሚ መሠረት ተብለው የተለዩት ግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝም፣ እነዚህን የሚያስተሳስራቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ናቸው፡፡
ከዚህ መነሻ አንድም ውጤት ነው ብለን የምንወስደው ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የእድገት ደረጃ ሰፊ የሆነ ሀብት ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልግ ሀብት እንምጣ ከተባለ ደግሞ ኢንቨስትመንትን በማጠናከርና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ያለንን የተፈጥሮ ሀብት ማልማት ነው የሚለው ትክክለኛ እይታ ነው፡፡በዘርፉ ላይ ለዘላቂ ልማት ጥሩ በር እንደተከፈተ አድርገን ነው የምንወስደው፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በዘርፉ ላይ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት የተሻለ ሆኖ መገኘቱ አንዱ ውጤት ነው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የተሻለ የመዋቅር ማሻሻያ ወይም ሪፎርም አድርጎ ተልእኮውን ሊወጣ በሚያስችለው መልኩ ራሱን ዝግጁ ማድረጉም ሌላው ውጤት ነው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ለሰነቀችው ልማትም ሆነ ብልጽግና ተልእኮ ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኑ ተስፋ የሚሰጥ ጅምር ውስጥ ይገኛል፡፡
በእስካሁኑ ሥራ እንደ ስኬት ከሚጠቀሰው አንዱ ዘርፉ በራሱ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ መመረጡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ ለማገልገል መነሳሳት የፈጠረና ለነገ ተስፋ ያለው ዘርፍ እንደሆነ አድርጎ እንዲወሰድ አስችሏል፡፡ እነዚህ ሁሉ እንደ ውጤት ይወሰዳሉ፡፡
በ2013 በጀት ዓመት መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ በወርቅ ምርት ግዥ ላይ የወሰደው እርምጃ ወርቅ ከወደቀበት የምርት መጠን አንሰራርቶ ከስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቶም ነበር፡፡ ይህን ውጤት ከማስጠበቅ አንጻር በኋላ ላይ ችግሮች ቢያጋጥሙም ችግሮቹ ጊዜያዊ ናቸው ብለን እንወስዳለን፡፡ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ፣ የውጭ ኩባንያዎች በእንፋሎት ኃይል ላይ ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎት መጨመርና ሌሎችም የፖሊሲ ለውጦች መነሳሳትን በመፍጠራቸው ስኬቶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማሻሻያ እርምጃው ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንፃር ያስገኘው ውጤት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሚሊዮን፡- የዘርፉ የልማት ሥራ እንደ ግብርና እና ሌሎች የልማት ሥራዎች አይደለም፤ ይለያል፡፡ ሀገርን የሚለውጡ ትላልቅ ውጤቶች ለማስመዝገብ ጊዜ፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲሁም ትእግሥት ይጠይቃል፡፡ ከጊዜ አንፃር የማዕድን ፍለጋው 15 ዓመትና ከዚያም በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ትእግሥት ይጠይቃል ያልኩትም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ወደ ልማት ለመግባትም የኢኮኖሚ አዋጭነቱ ቀድሞ ይታያል፡፡ በገንዘብ ደረጃም ቢሆን በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል። ይህን ሁሉ ማሟላት የሚችል ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡
ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወኑት ተግባራት በእንፋሎት ኃይል ወይንም ጂኦተርማል፣ በሲሚንቶ ማምረት፤ በአጠቃላይ ወደ 60 የሚሆኑ ኩባንያዎች በተለያየ የማዕድን ልማት ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሥራ ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎች 13 የሚሆኑት በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ ሶስት ኩባንያዎች በሁለትና ሶስት ዓመት ጊዜ ማምረት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡
አንድ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ለመገንባት በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ግዙፍ የሆኑ ወደ ሶስት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት ምርት አቋርጠው የቆዩ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡም ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሥነምድር መረጃ ካርታ ከ25 በመቶ በላይ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከተጠቀሰው መረጃ በላይ ሊሆን ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ሚሊዮን፡- መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ማህበረሰቡ መገንዘብ ያለበትና በመገናኛ ብዙሃንም መታወቅ ያለበት፤ የሥነምድር መረጃ ካርታ ከሰሩ 50 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡ ካርታው በቅኝ ገዥዎች ነው የተሰራው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በቅኝ የተገዛች ሀገር አይደለችም፡፡
በራስ አቅም ለመሥራት ነው ጥረት የሚደረገው፡፡ ቀደም ሲል ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ሥራው አልተሰራም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጂኦሎጂ ኢንስቲትዩት ለሀገር ጠቀሜታ ያላቸውን የሥነምድር መረጃ ካርታዎች በመሥራት ሚናውን ይወጣል፡፡ ሰፊ ሀገር እንደ መሆኗ ኢንስቲትዩቱ መንግሥት በሚፈልጋቸው የማዕድን ዘርፎች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ነው የተደረገው፡፡
በኢንስቲትዩቱ የማይሸፈነውን በግሉ ባለሀብት ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኩባንያ ፍቃድ ተሰጥቶት ወደ ሥራ እንዲገባ ሲደረግ፣ ኩባንያው ፍለጋ ሲያካሂድ እኛ እንደሀገር አካባቢው ላይ ያለውን የከርሰምድር መረጃ የማግኘት፣ እንዲሁም የእኛ ባለሙያዎችና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ትምህርት የሚያገኙበትን እድል ይፈጥርልናል፡፡ በሁለቱም በኩል የሚከናወነው በቂ ባለመሆኑ ዘመናዊ አስተሳሰብ ለመከተል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
አካባቢውን ሁሉ ለመሸፈን የሚያስችል ‹‹ኤርቦርን ጂኦፊዚክስ››ን /ከአየር ላይ ሆኖ መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ/ ለመተግባር ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታትም በዚህ ላይ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተይዟል፡፡
በነገራችን ላይ የሥነምድር መረጃ ካርታ መሰብሰብ ብቻውን ግብ አይደለም፡፡ ያለውን ሀብት ለይቶ መረጃ ወይንም ዳታ ማግኘትም ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ መነጋገር የሚቻለውም ሆነ ኢንቨስተርን መሳብ የሚቻለው በመረጃ ነው፡፡ የዳታ ክምችታችንን መጨመር አለብን ከሚል እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ልማቱ ያላደገው ቴክኖሎጂ መጠቀም ባለመቻሉ እንደሆነ ይተቻል፤ በእዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሚሊዮን፡- ቴክኖለጂ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ለሥራው ከሚያስፈልግ የሥራ መሳሪያ ጋር ይያያዛል። በዚህ ረገድም ዘርፉን ለማጠናከር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፡፡ በዘርፉ ላይ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በመለየት ሥልጠናው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ቴክኖሎጂ ማሟላት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራቱ ወሳኝ በመሆኑ ነው ለዚህ ቅድሚያ የተሰጠው። በተለይ ደግሞ እያንዳንዱ አካባቢ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት መሠረት ያደረገ ሥልጠና የሚሰጥበት ሁኔታም ተመቻችቷል። ለአብነትም ወለጋ አካባቢ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አካባቢው ላይ ያለውን ማዕድን ለማልማት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል መሠረት አድርጎ እንዲያሰልጥንና የምርምር ሥራንም ጨምሮ ተልኦውን እንዲወጣ ነው የተመቻቸው፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢያቸውን የሚቃኝ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ ይፈልጋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ እንዲያስፈጽም ይጠበቃል፡፡ ሚኒስቴሩ የሀገር ሀብትን ማልማት በሚያስችል መልኩ እንዲቃኝ እየተደረገ ነው፡፡ በዘርፉ የሰው ኃይል የማፍራቱ ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛ ደረጃም በቴከኒክና ሙያ ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እንዲቻል በተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል የጌጣጌጥ ማዕድን በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በዘርፉ የተሰማሩትን በቴክኖጂ ታገዘው አሴት የተጨመረበት ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ከፍተኛ ድርሻ መወጣት ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ልማቱ በሚከናወንበት ስፍራ የተጠናከረ አደረጃጀት የለም የሚል ትችት ይቀርባል፡፡ በእዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሚሊዮን፡- ዘርፉ ገብቷቸው መዋቅራቸውን ያስተካከሉ ክልሎች አሉ፡፡ ለአብነት አማራ ክልልን ብንጠቅስ እስከ ወረዳ ድረስ የወረደ መዋቅር አለ፡፡ ይሄ የሚያሳየው ዘርፉ ትኩረት ማግኘቱን ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ግብይቱን ጨምሮ ምን መሰራት አለበት የሚለውን ያግዛሉ፡፡ እንዲህ ያሉ እድሎችን የሚያመቻቹ የተሻለ የማልማት እድል ይኖራቸዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደግሞ ተሞክሮዎች እንዲሰፉ ያግዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ሳይሆን ባለሙያውን ዘርፉ ላይ ለማቆየት የሚያስችል ነገር አለመኖር ነው የሚል ትችት የሚያነሱም አሉ፡፡ ለእዚህ ምላሽዎ ምንድነው?
አቶ ሚሊዮን፡- ቀደም ሲል ስላለው ማውራት አንችልም። በእኔ እምነት ቀደም ሲል እንደ አሁኑ እንቅስቃሴ አልነበረም። በዘርፉ ላይ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እየጨመረ የመጣው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከሰው ኃይል ጋር ይያያዛል፡፡ የሰው ኃይሉም ከዘርፉ ፍላጎት የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም መዘንጋት የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዘርፉ ልማት ሰላም ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነትና ካለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ዘርፉ መጎዳቱ ይታወቃልና ጉዳቱ እንዴት ይገለጻል? አሁን ደግሞ የተፈጠረው ሰላም በዘርፉ ላይ ምን ተስፋ አሳድሯል?
አቶ ሚሊዮን፡- የፀጥታው ችግር ሲሚንቶ ገበያ ላይ እንዳይገኝ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሀገሪቱን 21 በመቶ የሲሚንቶ ፍላጎት ያሟላ የነበረው የትግራይ ክልሉ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
ጉዳቱ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም፣ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የመጣው ሰላም ለዘርፉ ልማት ወሳኝ ነው። የማዕድን ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግ መንግሥት አቅጣጫ በማስቀመጡ ልማቱ ተስፋ ሰጪ ሆኗል፤ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ ገና የተሻለ ውጤት ይጠበቃል፡፡ ትላልቅ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች በመንግሥት ጭምር ይጠበቃሉ፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጌጣጌጥና በወርቅ ማዕድናት ላይ የሚታየውን ሕገወጥ ግብይት ለመቆጣጠር መንግሥት ግብረኃል አቋቁሞ ተንቀሳቅሷል፡፡ እርስዎን ጨምሮ የፕላን ሚኒስትሯ በተገኙበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገወጥነትን በመከላከል ላይ የተላለፈ መልእክትም ነበር፡፡ ይህ ስራ ምን ውጤት አስገኘ?
አቶ ሚሊዮን፡- መንግሥት በሀገራዊ ፀጥታ ሁኔታ ላይ ሲወጠር የውጭ ዜጎች ጭምር ከሀገር ውስጥ የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጋር በመመሳጠር የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሳጥተዋል፡፡ በወርቅ ላይ የምርት መቀነስ የተስተዋለው ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ችግሩ ተባብሷል፡፡
መንግሥት በሌላ ሥራ ቢወጠርም ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ እርምጃ ከመውሰድ አልተቆጠበም፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ ወደ 45 የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡ በድጋሚም በክልሉ ለመገኘት ተሞክሯል። ተጨማሪ ሕጋዊ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ሕገወጥነቱ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ይሄ ግን አይቀጥልም፡፡ ከፍ ባለ የፀጥታ መዋቅር ችግሩን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አቶ ሚሊዮን፡- የባህላዊ አምራቾችን ምርታማነት ከመጨመር አንጻርና ማነቆዎችን በጥናት ለይቶ እንዲያሳውቀን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረግነው ስምምነት መሠረት የመጀመሪያ ዙር ጥናት ውጤት አቅርቦልናል፡፡ ጥናቱን መነሻ በማድረግ ለልማቱ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ወይንም የሥራ ማሽን ለአራት ክልሎች አከፋፍለናል፡፡ የተከፋፈለውን ማሽን ከመጠቀም አንፃር ያለውንና ውጤታማነቱ ላይ ደግሞ ሁለተኛው ዙር ጥናት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በጥናት የተለዩትን በእቅድ ውስጥ በማካተት ይሰራል። የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ዘርፉን በእውቀት ለመምራት የሚያስችሉ በመሆናቸው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ወደ ተግባር ይለወጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦጋዴን ቤዚን የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ጉዳይስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሚሊዮን፡- የዚህ ጋዝ መልማት በርካታ ትርጉም ያለው በመሆኑ ልማቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቃል፡፡ የተረጋገጠ ሀብት ነው፡፡ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለማልማት የተለያዩ ሀገሮች ኩባንያዎች ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ዓለም አቀፍ አስተማማኝ ኩባንያ ይጠበቃል፡፡ መንግሥትም እየደገፈው ሥራ እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደፊት ከማዕድን ዘርፉ ምን እንጠብቅ?
አቶ ሚሊዮን፡- ቀጣይ ተስፋው ብሩህ ሆኖ ይታየኛል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኩምሩክ ላይ ከሁለት ዓመት በኋላ የግንባታው ሥራ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ የወርቅ ማዕድን የሚያለማ ኩባንያ ወደ ምርት ሲገባ በአማካይ በዓመት እስከ 9 ቶን ያመርታል፡፡ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ታሪክ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያን ጨምሮ በአጠቃላይ በባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚመረተው ወርቅ ከስምንት ቶን አይበልጥም። አሁን ግን በአንድ ኩባንያ ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት እድል እየተፈጠረ ነው፡፡
ይሄ ሀብት በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ ላይ የብረት፣ የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሀብቶችና ሌሎችም ሲደመሩ ያለን የመልማትና የማደግ እድል ተስፋ ሰጪ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭም ይሆናል፡፡ በማዕድን ዘርፉ ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር የሚያስችል እድል አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን፡፡
አቶ ሚሊዮን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2015 ኣ.ም
ለምለም ምንግሥቱ