የተዘጋጁ ቅመማ ቅመሞችን እንዲሁም የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና ባለቤት ወይዘሮ ኤልሳ ሀብቴ በቅርቡ በኢግዚቢሽን ማእከል በተዘጋጀው የኢትዮ አግሮ የበጋ መስኖ ስንዴና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝተዋል፡፡
በአገሪቱ የሚመረቱ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን በማቀራረብ የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመ የተባለውን ይህን ኤግዚቢሽን ወይዘሮ ኤልሳም በተመሳሳይ ተመልክተውታል። አምራችና እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርበውን ማህበረሰብ በማገናኘት በኩል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ወይዘሮ ኤልሳ ተናግረው፣ ‹‹በተለይም አርሶ አደሩን፣ ሸማቹንና እኛ ላኪዎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል›› ሲሉም ነው የገለጹት ፡፡
የቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤት ምርቶችን በማዘጋጀት እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚልኩት ወይዘሮ ኤልሳ፤ ኢግዚቢሽኑን ደላላ ጣልቃ ሰይገባበት በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘትም የሚያስችል ሆኖ አግኝተውታል፡፡ አምራቹ የገበያ መዳረሻውን ሲያውቅ በስፋት ለማምረት ይበረታታልም ይላሉ፡፡
ወይዘሮ ፋሲካ እንደነገሩን፤ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም በውጭ አገር እጅግ እንደሚፈለግ በገበያው ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያቶች ለማወቅ ችለዋል፡፡ እርሳቸውም በአውሮፓ ሰፊ ገበያ ፈጥረዋል፡፡ ለገበያ ካዘጋጁት ምርት 70 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ገበያ፣ ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ፡፡
ለገበያ ከሚያቀርቡት ምርትም በርበሬ በውጭው እጅግ ይፈለጋል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርበሬ ምርት ላይ ተከስቷል የተባለው አፍላቶክሲን (ፈንገስ) በገበያቸው ላይ ኡሉታዊ ተጽእኖ በመፍጠሩ እንደ ቀድሞው ገቢ እያገኙበት አይደለም፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን እሳቸው በተቀሩት ሽሮና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ላይ ጥሩ ገበያ በመኖሩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ለውጭ ገበያ ከሚልኳቸው ቅመማ ቅመም አይነቶች ደግሞ ጥቁር አዝሙድ፣ መከለሻ ቅመም፣ እርድና አብሽ ይገኙበታል፡፡
ሮዝመሪ የተባለውን ቅመም ይዘው በኤግዚብሽኑ ላይ የቀረቡት የስልጤ ዞን የቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ከይረዲን ያሲን እንዳሉት፤ በአካባቢው ከሚመረቱ የቅመማ ቅመም አይነቶች መካከል ሮዝመሪ እየተስፋፋና ምርታማነቱም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡
ከ2010 ጀምሮ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ከወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ልማቱ መስፋፋቱን ይናገራሉ፡፡ አቶ ከይረዲን እንደ ዞን የሮዝመሪ ልማት በ560 ሄክታር ላይ ይካሄድ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በ3ሺ082 ሄክታር መሬት ላይ ሮዝመሪ እየተመረተ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት፡፡
በ2010/11 ዓ.ም የተገኘው የምርት መጠን 4ሺ232 ኩንታል እንደነበረ ያስታወሱት ቡድን መሪው፤ አሁን ላይ 48ሺ 039 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። ምርታማነቱን በተመለከተም ከዚህ በፊት በአንድ ሄክታር ይገኝ ከነበረበት 16 ኩንታል በአሁኑ ወቅት ወደ 23 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
ምርቱ ከዚህ በፊት የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረለት ሴት አርሶ አደሮች በጓሯቸው አልምተው መጠነኛ የዕለት ገቢ ያገኙበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከይረዲን፤ በአሁኑ ወቅት ግን በተፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫና ስልጠና አማካኝነት የሚያለሙ አርሶ አደሮች ቁጥር መጨመሩን አመልክተዋል፡፡
በተለያዩ ንቅናቄዎች አማካኝነት ልማቱ መስፋት እንደቻለም ጠቅሰው፣ የገበያ ሁኔታው ግን ወጣ ገባነት እንደሚታይበት ይጠቁማሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ወጥነት ያለው የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ አምራች አርሶ አደሩ በአንድ ወቅት ጥሩ ገበያ ሲያገኝ በለሌላ ጊዜ ደግሞ ዋጋው የሚወርድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ለአብነትም በዚህ ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ጥቅምትና ህዳር ወር አካባቢ በጥራት ተዘጋጅቶ የደረቀ አንድ ኪሎ ሮዝመሪ ከ90 እስከ 95 ብር መሸጡን ጠቅሰው፣ በዚህም አምራቹ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡ ፡ አሁን ዋጋው ወርዶ አንድ ኪሎ ሮዝመሪ ከ60 እስከ 50 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይህም አርሶ አደሩ በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዳይችል በማድረግ አቅሙን የማዳከም ሁኔታ ፈጥሯል›› በማለት ጠንካራ የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ያለውን ችግር አመላክተዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ የቅመማ ቅመም ሰብል ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል በመሆኑ ከምርቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በገበያ ትስስሩ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የሮዝመሪ ምርት ወደ ውጭ ገበያ እየቀረበ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማስገኘት ሌላኛው የገቢ አማራጭ መሆን እየቻለ ነው፡፡ ለአብነትም፤ ባለፈው ዓመት ከዞኑ የተገኘውን 3ሺ625 ኩንታል ሮዝመሪ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከ725 ሺ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል፤ ዘንድሮም 8ሺ050 ኩንታል የሮዝመሪ ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ አንድ ነጥብ ሁለት ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
አገሪቷ አጠቃላይ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ዕምቅ አቅም እንዳላት የጠቀሱት የቡድን መሪው፤ ይህን ዕምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም የአርሶ አደሩ ምርት ገበያ እንዲያገኝ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በተለይም ለቅመማ ቅመም ዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በተለይም ቋሚ የገበያ ትስስር በመፍጠር አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆንና አገርም ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ይህን መሰል መድረኮች አስፈላጊ እንደሆኑም ነው የገለጹት፡፡
ከሀላባ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር የሀላባ በርበሬን ይዘው የቀረቡት በኢግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፉት አቶ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ በኤግዚብሽኑ ምርታቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስሰር ለመፍጠር መድረኩ አይነተኛ ሚና እንዳለው ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበሩ ምርቱን ለአካባቢው ነዋሪ ከማቅረብ ባለፈ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ጭምር በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ በማቅረብ የገበያ ትስስር ሲፈጥሩ ቆይቷል፡፡
በርበሬ አንዱ የቅመማ ቅመም ምርት እንደመሆኑ በኢትዮ አግሮ የበጋ መስኖ ስንዴና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን ላይ መገኘታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝላቸው ጠቅሰው፤ በተለይም ሰፊ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ኤግዚቢሽኑ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ አርሶ አደሩ በግሉ ያመረተውን ለዩኒየኑ በማስረከብ ዩኒየኑም በተመጣጣኝ ዋጋ ለነጋዴና ለሸማቹ እንደሚያቀርብ በመጥቀስ በዚህም አርሶ አደሩ ከሌሎች ምርቶች በተሻለ በበርበሬ ምርቱ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የቅመማ ቅመም ምርት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው በመረዳት፤ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የግብይት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ይገልጻሉ፡፡
ሃላፊው እንዳሉት፤ አገሪቷ በቅመማ ቅመም ዕምቅ ሀብት ያላት ቢሆንም፣ እስካሁን ከዘርፉ በበቂ መጠን ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም፡፡ በተለያየ መንገድ ለገበያ እየቀረበ ያለው የቅመማ ቅመም ምርት ከጥራትና ከአመራረት ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለው ሂደት ዘርፉ ከሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ አላስቻለውም። ለዚህም ነው ባለስልጣኑ ለዘርፉ የተለያዩ ማሻሻያዎችና ድጋፎችን በማድረግ እየሠራ ያለው፡፡ ከሥራዎቹ መካከልም ኤግዚብሽኖችን በማዘጋጀት ምርቶቹን ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር አንዱ ነው፡፡
አገሪቷ በቅመማ ቅመም ምርት ባላት እምቅ ሀብት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ በሌላ በኩል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም ከመጋቢት ስምንት እስከ አስር ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱ አንዱ ነው ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማም በተለይም የቅመማ ቅመም ምርቶችን በተመለከተ በአገሪቱ ምን አይነት የቅመማ ቅመም ሀብቶች አሉን የሚለውን በአገር ደረጃ ለማወቅ፤ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆንም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ የምርትና ምርታማነት ዕድገቱ ምን ይመስላል፤ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ምን አይነት ዕድሎች አሉ፤ ዕድሉን እንዴት መጠቀም አለብን የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የቅመማ ቅመም ስትራቴጂ በማዘጋጀት በዓለም ደረጃ እንዴት ማስተዋወቅ ይቻላል፣ የምርት አይነቶቹ ምን ያህል ናቸው የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ በተለይም ቅመማ ቅመም የሚያመርቱ አምራች ክልሎች፣ አርሶአደሮችና አልሚ ባለሀብቶች በጉዳዩ ላይ በሚገባ መወያየት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ ችግሮቹን በመለየት በጥራት ማምረት የሚስችላቸው ይሆናል፡፡ የቅመማ ቅመም እምቅ ሀብት ከቡና ቀጥሎ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ሌላኛው አቅም እንዲሆን ዕድል ይሰጣል፡፡ ለዚህም ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡
በአገር ውስጥ ያለው የቅመማ ቅመም ፍጆታ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ ወደ ውጭ ገበያ የሚላከውን መጠንም ከፍተኛ ለማድረግና በአገር ውስጥም ተጠቃሚ መሆን እንዲቻል ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮች ክልሎች አልሚ ባለሀብቶች በጋራ ተወያይተው ችግሮቹን በመለየት እንዴት መሻገር እንደሚቻል መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ኤግዚብሽኑ ያስፈለገው ምርቱን ከማስተዋወቅ ባለፈ ምርታማነቱን በማሳደግ ገዢ አገራት የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ አሟልቶ በማቅረብ አገሪቷ ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሻፊ ማብራሪያ፤ የምርት መጠኑን በጥራት ከማሳደግ በተጨማሪም በውጭ ገበያ ተደራሽ በመሆን በተለይም ነባር በሆኑ ገበያዎች ላይ መቆየት አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 43 ለሚደርሱ የዓለም አገራት የቅመማ ቅመም ምርቶቿን እየላከች ትገኛለች፡፡ የሚላኩት የቅመማ ቅመም አይነቶችም ከ 16 በላይ ናቸው፡፡ ለቅመማ ቅመም ዘርፍ ሲሰጥ የቆየው ትኩረት አናሳ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ ሰትራቴጂም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ይህም አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቅም ትርጉም ያለው እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት፡፡
የቡናና ሻይ ባለስልጣንና ግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጁትና በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል በቅርቡ በተካሄደው በዚህ ኢግዚቢሽን ላይ በርካታ የቅመማ ቅመም አምራቾች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች ተካፍለዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015