የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን፤ የጉባኤው ዋና አጀንዳም የመንግሥትን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት በማዳመጥ በሪፖርቱ ላይ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በማንሳት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽና ማብራሪያ ማድመጥ ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም የመንግሥትን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡ ሲሆን፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከልም፡-
የዜጎችን ደህንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ዝቅተኛው የመንግሥት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ፣ ቤታቸው ይፈርሳል፣ ንብረታቸው ይወድማል የሀገር ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ የጎረቤት ሀገራት ሠራዊቶች በኢትዮጵያ ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈፅመዋል።… አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደህንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት ዋና ስጋት እልባት ለመስጠት ምን እየተሠራ ይገኛል? ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል፤ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ፤ ከታጣቂ ኃይል ጋር በሚካሄደው ግጭት በርካታ ሕይወት እና ንብረቶች ወድመዋል፣ እየወደሙ ይገኛሉ። ይህንን ግጭት በሰላም ለመፍታት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት የኦነግ ሸኔ አመራር ጥሪውን በመቀበል አዎንታዊ ምላሽ ቢኖርም፤ በሁለቱ በኩል ትርጉም ያለው የሰላም ሂደት አልተደረገም ወይም ሲደረግ አልተስተዋለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ይህን ከፍተኛ የሰላም እጦት መንስኤ የሆነውን ችግር ለመፍታት እና ተጨባጭ ሰላም ለማምጣት የፌደራል መንግሥቱ ምን አይነት ስትራቴጂ እየተከተለ ይገኛል?
እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት በክልሉ የተከሰተው የጤና፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎችን በተደራጀ እና በተሻለ መልኩ ለማቋቋም መንግሥት ምን ለማድረግ አቅዷል? «በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል ብልጽግና አንድ ሆኖ ሁለንተናዊ እድገትን ከማምጣት ይልቅ፤ ከመግለጫዎች ጀምሮ ጎራ የመያዝ፤ ማለት የሆነ የመደበላለቅ ስሜት ይታያል። በኦሮሚያ ክልል አሁንም መፈናቀል፣ ስደት፣ ሞት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በተለይ በአማራ ክልል በሁሉም ኅብረተሰብ፤ በተለይ በወጣቱ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ይታገታል። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከኅብረተሰቡ እየተለመነ አንዳንዱም ይለቀቃል፣ አንዳንዱም ይሞታል። ይሄ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነበር።
ታመው ሪፈር ወደ አዲስ አበባ የተጻፉ ሕመምተኞችም ሳይደርሱ ቀርተው በመንገድ ሞተዋል። በተለይ አሁንም አርሶ አደሩ ምርቱ ወደ ገበያ እያወጣ በተለይ ወደ አዲስ አበባ እየሸጠ አይደለም። ነጋዴውም ግብይቱን አቁሟል፣ አርሶ አደሩም በወቅቱ ምርቱን ሽጦ ኑሮውን ከመምራት እና የማዳበሪያ ዋጋ ግብዓት በወቅቱ ከፍሎ፣ ገዝቶ፣ ምርትን እና ምርታማነትን ከመጨመር አንጻርም ሌላ እንቅፋት እየሆነ ነው።
ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ ሰብል ባለመግባቱም፤ አዲስ አበባ ያለውን የኑሮ ውድነት በጣም ስላጋሸበው ሕዝቡ ላይ አሁን እየደረሰበት ያለው ጫና በጣም ሰፊ ነው። …የሕዝባችን ያለአግባብ መፈናቀል እና መሞት የሚቀረው ክልሎችን በአንድ ሆነው ተናበው የሚሠሩት መቼ ነው? የሕዝባችንን ሰላም የሚያውኩ ኃይሎች ውስጥ የአመራሩ እጅ የለበትም ብለው ያስባሉ? ይህንን ችግር ለመቅረፍስ ምን እርምጃ እየተወሰደ ነው? ቀጣይስ ምን ታስቧል? ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቃል?
ሕገ ወጥ ታጣቂ ኃይል እና ሕገ ወጥ መሣሪያ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስገብተው በማደራጀት መዲናችንን የሁከት እና የብጥበጥ ማዕከል ለማድረግ እና ›ትኩረታችሁን ወደ አራት ኪሎ ቤተመንግሥትfi የሚል ቅስቀሳ እና ፋይናንስ በማድረግ በሕዝቦች መስዋዕትነት የተገነባውን መንግሥት በኃይል አፍርሰው ›ሥልጣን እንይዛለንfi ብለው ያሉ ኃይሎች እንዳሉ ይነገራል።
እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ለመመከት በመንግሥት በኩል ምን እየተሠራ ነው?፤ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ለእነዚህና ሌሎችም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል። እኛም ይሄንኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
የተከበሩ አፈ ጉባኤ፤ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዕድል ስላገኘሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የሰላም እና መረጋጋት፤ የልማት ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ቦታ ያላቸው ቢሆኑም፣ ሰላምን በሚመለከት ተደጋግሞ ስለተነሳ ይበልጡን ብንወያይበት መልካም ይሆናል። የኢኮኖሚ ጉዳዮችም ቢሆኑ ከሰላም እና መረጋጋት ጉዳዮች እና ጥያቄዎች አንፃር የተነሱትን በመለየት ቅድሚያ መስጠት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ስድስት ወር ከነበረው በእጅጉ የተሻለ የሰላም ሁኔታ አለ። የዛሬ ስምንት ወር ከነበረው በእጅጉ የተሻለ ሁኔታ አለ። ሰላም አንፃራዊ ነው።
ወደ ተሟላ ሰላም ለመሄድ በርካታ ሥራ መሥራት የሚኖርብን ቢሆንም፣ በንፅፅር ግን የሰላም ሁኔታው ሻል ያለ መሆኑን የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት የሚጠፋችሁ ባይሆንም ደግሜ ማስታወስ እፈልጋለሁ። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው፣ በርካታ ሰዎችን የፈጀ ጦርነት መቆሙ አንድ ደረጃ ወደ ፊት የወሰደ፤ እንዲሁም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በዚሁ የማየቱ አግባብ ከባለፈው የተሻለ ተብሎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ወደ ተሟላ ሰላም ለመሄድ በጣም በርካታ ሥራዎች ይጠበቁብናል። እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሀገር፣ እንደ መንግሥት፣ ተሰናስለን ሰፋ ያለ ሥራ ካልሠራን በስተቀር በየጊዜው የሚያጋጥሙ ግጭቶች የሰው ሕይወት ከመቅጠፋቸውም ባሻገር እንደ ሀገር ወደ ፊት ለመጓዝ ያለንን ፍላጎት እየገቱ ስለሆነ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።
ከዚህ አንፃር በየመሐሉ የማብራራው አዳዲስ ጅማሮዎች አሉ። እነዚህም ውጤት እንደሚያመጡ ተስፋ አደርጋለሁ። ሰላምን በሚመለከት ተኩስ ሲቆም፣ ግድያ ሲቆም፣ ወዲያውኑ የሰላም አየር ይነፍሳል ማለት አይደለም። የድህረ ግጭት ዐውድ ጫና አለ። ሰው የሞተባቸው፣ የቆሰለባቸው፣ ንብረት የወደመባቸው ሰዎች ግጭቱ የዛሬ ወርም ቢሆን ድህረ ጦርነት፣ ድህረ ግጭት የሚያሳድረው ቁስል በቀላሉ የሚሽር፤ የሚደርቅ ባለመሆኑ ቶሎ የሚዘነጋ አይደለም። በጥያቄዎቻችሁ ስታነሱ እንደነበረው፣ በየቦታው፣ በንብረትም በሰውም የደረሰው ጉዳት ወዲያው የሚረሳ ባለመሆኑ በንፅፅር አሁን ያለው ሁኔታ ሻል ያለ ቢሆንም፣ በአንድ ጊዜ ግን ቁስሉ ሽሮ የሰላም አየር ተንፍሰናል ብሎ ለመረጋጋት የሚያስችል አይደለም። ባሕርያዊ ነው። ከጦርነት በኋላ ወዲያው የሰላም አየር በተሟላ መንገድ ማግኘት ይከብዳል።
ሁለተኛው የጦርነት ነጋሪት አብዝተው የሚጎስሙ፤ በጣም በርካታ ዜጎች ያሉበት ሀገር ስለሆነ በተደጋጋሚ ግጭት፣ ጦርነት ስለሚነገር የሰላም አየር እና ዐውድ እንዳለ ለመቀበልና ለማመን ማሰብ ያስቸግራል። ሰላም ውስጣዊ ስለሆነ በርግጥ እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ ጦርነት የሚጎስሙ ኃይሎች ጦር ሜዳ ሄደው የሚዋጉ አይደሉም። ጦርነትን በቅርበት የሚያውቁም አይደሉም። በርቀት ሆነው ግጭትን በስፋት የሚሰብኩና ሰው የሰላም መንፈስ እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው።
እነዚህ ኃይሎች ግጭት ይፈበርካሉ፤ ቀድመው ያቅዳሉ፤ ግጭት ይፈፅማሉ። አብዝተውም በስፋት ይዘግባሉ። ገድለው ሞትን ይላሉ። በዚህ ምክንያት የሰላም አየር በተሟላ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈን የራሱ የሆነ ፈተና ሲሆን ቆይቷል። ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት አምሳ፣ ስልሳ ዓመታት ያለው ፖለቲካ የመጠላለፍ ፖለቲካ ነው፤ መጠላለፍ ሁለተኛው ሴራ ነው። የሴራ ፖለቲካ ነው። ሦስተኛው የጉልበት ፖለቲካ ነው። በሃሳብ ልዕልና፣ በንግግር፣ በውይይት ፍላጎትን ማረጋገጥ ሳይሆን ጉልበት ነው ያለው። ጉልበት ደግሞ ከሌለ ሴራ ነው። ሴራው ደግሞ በንጹሐን ደም ላይ የሚሸቀጥ ነው። የሚጨበጥ፣ የሚታይ ለውጥን አለማመን፣ መካድ ነው ያለው። ስትዋጋ በአስቸኳይ ጦርነት ይቁም፤ ሰላም አምጡ የሚሉ ኃይሎች ሰላም ሲመጣ ደግሞ እንዴት ሰላም ይመጣል ይሏችኋል። ይሄ የሤራ ፖለቲካ ውጤት ነው። የሚሆነውን ነገር ሁሉ ተቃርኖ መቆም እንጂ፤ ለዘላቂ የሀገር ጥቅም፣ ለዜጎች ጥቅም የመቆም ዝንባሌ ውስንነት አለ።
የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት እንድትገነዘቡት የምፈልገው ጉዳይ ሰላም እንደጦርነት ጀግንነትን ይፈልጋል። ሰላምን ማምጣት ቀላል ሥራ አይደለም። በጦርነት ጊዜ በቀላሉ ሰዎችን መሰብሰብ ይቻላል። ቢዋጉም ባይዋጉም ሰዎች በድጋፍ ሊሰለፉ ይችላሉ። በሰላም ጊዜ ሰዎችን አሳምኖ ለሰላም መዝመት ቀላል ነው። ሰላም ከጦርነት ያልተናነሰ ሥራ፣ ትጋትን ይጠይቃል። እንዲሁ በከንቱ አይመጣም። በውሃ ላይ ዳክዬ ስትዋኝ አይታችሁ ከሆነ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ያለ አይመስልም። ሰላማዊ ጉዞ የምታደርግ ነው የምትመስለው። ነገር ግን ወደ ውስጥ ገብታችሁ ብታዩ ያን ሰላማዊ የመሰለ ጉዞ ለመጓዝ በእግሯ በጣም በርካታ ሥራዎችን ትሠራለች። የረጋ ሰላማዊ ነገርም እንዲሁ አይመጣም። በሥራ ነው የሚመጣው። ትጋት፣ ሥራ ይፈልጋል። በተለይ ደግሞ አዎንታዊ ሰላም (ፖዘቲቭ ፒስ) በፖዘቲቭ ፎርስ (አዎንታዊ ኃይል) ወይም በኃይል ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም። ፖዘቲቭ ሰላም የምንሻ ኃይሎች ብዙ ከእኛ ይቅር ከሰላም የምናተርፈው ይበልጣል ብለን ማመን እንዳለብን ይጠይቃል።
አንዳንድ ጊዜ ለሰላም የሚደረገው እንቅስቃሴ የነበረውን ግጭት፣ የነበረውን እልህ አስጨራሽ ሂደት በመዘንጋት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የነበረው ሂደት በጣም አሳዛኝ እንደነበር እየታወቀ ያንን አሳዛኝ ሁኔታ ከማቆየት እና ከማዝለቅ የሚሻለውን ነገር ለማምጣት ለሰላም ብንሠራ ይሻላል በሚል እሳቤ የሚደረግ መሆኑን በክብር ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ።
ሰላምን በሚመለከት ሁላችንም ከልብ በአወንታዊ እሳቤ ከእኛ ይቅር በሚል አብረን እንድንተጋ አደራ እላለሁ። እናንተ ሰላምን የማትደግፉ እና ለሰላም የማትቆሙ ከሆነ ከዚህ በታች ያለው ማኅበረሰብ በምን ያህል ደረጃ ሰላም ማስፈን እንደሚቸገር ለእናንተ መናገር አያስፈልግም። ምን ጊዜም ሰላም ሲባል የአንድ ሰው ሕይወት ማትረፍ ስለሆነ፣ እኛ ቀድመን ግንባር ቀደም ሆነን፣ ለዚህ ሰላም የምንተጋ መሆን አለብን።
ያ ከእናንተ ይጠበቃል። ውክልናችሁም እንደዚህ አይነት ጉዳይ ለመሥራት ስለሆነ ለመንግሥትም ለሕዝብም የምታደርጉት ድጋፍ የጎላ ይሆናል ብየ አስባለሁ። ሰላምን በሚመለከት እየተጓዝን ያለነው የተሟላ ሰላም ለማምጣት ነው። አንጻራዊ ነው ሰላም። አወንታዊ ሰላም ለማምጣት የሚያስፈልጉ የምክክር፣ የንግግር፣የመቀራረብ፣ የመተማመን ሥራዎች በስፋት ተጀምረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሚዲያን በሚመለከት የተነሳው ጥያቄ ነው። ሚዲያ ፓራዶክስ ኦፍ ቾይዝ (የምርጫ ጉዳይ) ነው። በጣም በርካታ ሚዲያዎች ከወትሮው በተለየ መንገድ በዓለም ላይም በእኛም ሃገር በስፋት አሉ። ሰው መርጦ መስማት አለበት። መርጦ መስማት ካልቻለ ያልተገቡ መርዞች ወደ ውስጡ ይወስዳል። ሁሉ አማረሽን ወደ ገበያ አታውጧት የሚባለው ያየችውን ሁሉ ልግዛ ስለምትል ነው።
በዩቲውብ ያየነውን ሁሉ ለመስማት መሞከር፤ ለማየት መሞከር አደገኛ ነው። መርጠን፣ ታማኝ የሆኑ ጠቃሚ፣ አስተማሪ ጉዳዮችን የሚያሰራጩ ሚዲያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ከእነዚህ አንፃር አድማጩም ኃላፊነት አለበት ማለት ነው። መርጦ፣ ለይቶ ማድመጥ ካልቻለ ሚዲያ ስለሆነ ብቻ የሚያዳምጥ ከሆነ፣ አብዛኛው፣ ቅድም አንዳልኩት በመጠላለፍ ፖለቲካ፣ በሴራ ፖለቲካ የተመሠረተ፤ እነዚህ ኃይሎች ፋይናንስ የሚያደርጉት ሚዲያ ስለሆነ ያልተስተካከለ ዘገባ እንድናደምጥ ያደርጋል።
ሁለተኛው የሚዲያ ነፃነት የሚባለው ጉዳይ እስከምን ድረስ ነው። የማባላት ነፃነት፣ የመዋሸት ነፃነት፣ ጦርነት የመቀስቀስ ነፃነት ማለት ነው ወይ? የሚዲያ ነፃነት፣ የእምነት ነፃነት፣ የሃገር ነፃነት የሚባለው ጉዳይ ጠቅልሎ ቀንበር መጣል ማለት አይደለም። አሉታዊ የሆነውን ነፃነት ወደ አዎንታዊ ነፃነትም ማምጣት ነው። ሰው የተሸከመልንን ቀንበር እኛ ለመሸከም መሞከር እንጂ ቀንበር አልቦ መሆን አይደለም።
ፈረንጆች ስለ ነፃነት (ፍሪደም) ሲያስቡ “ፍሪደም ኢዝ ኤ በርደን” ይላሉ። ነፃ ሚዲያ ማለት መንግሥት ሴንሰርሺፕ ከሚያደርግ እኛ በራሳችን ሕግ እና ሙያ ሴንሰርሽፑን (ሳንሱሩን) እንከውናለን። ቀንበራችንን እኛ እንሸከማለን ማለት ነው እንጂ ሴንሰርሺፕ (ሳንሱር) ጠቅልሎ ይጠፋል ማለት አይደለም። ነገር ግን ነፃነትን በሚመለከት ሰዎች ነፃ ለመሆን የሚፈልጉት ቀንበር አልቦ ለመሆን ነው። እንጂ ኃላፊነት ለመውሰድ አይደለም።
ለምሳሌ፣ በአፍሪካ በርካታ ሀገራት የዛሬ 50 እና 60 ዓመታት በኮሎኒ ከያዟቸው ኃይሎች ነፃ ወጥተዋል፤ ታግለው ነፃ ወጥተዋል። ዛሬም ግን በአንዳንድ ጥፋት ይህ ጉዳይ ለምን ተፈጸመ ሲባል የኮሎኒያል ፓወር ያደረሰብን ጥፋት ነው፤ በዚያ ሳቢያ ነው ይህ ችግር እየገጠመን ያለው ሲሉ በስፋት ይደመጣል። ይህ በአንድ ወቅት የነበረን ችግር ኃላፊነት ወስዶ ተሻጋሪ እንዲሆን፣ የሚዘልቅ እንዲሆን እየፈቱ የመሄድ ዝንባሌ ከሌለ የሰው ጠፍንጎ ገዥ ይነሳልን ካሉ በኋላ ሌላ የራስ የሆነ ጠፍንጎ ገዥ ማስቀመጥ ዋናው ፍላጎቱ ጠፍናጊውን ማስቀመጥ ሳይሆን መቀየር ነው የሚሆነው።
ዲክታተሩን ማጥፋት ሳይሆን ዲክታተሩን መቀየር ነው የሚሆነው። ይህ በልጆችም ይታያል፤ ወላጆች ለሕፃናት ሲጠነቀቁ፣ ሲይዟቸው ልቀቁኝ ብለው ያለቅሳሉ፤ ለመጓዝ ፈልገው። እናት ብትለቅና ቢወድቅ ግን የሚያለቅሰው ልክ እናት እንደጣለችው የእርሷ ጥፋት እንደሆነ አስቦ ያለቅሳል። ጎረምሳም ሰው ያመሻል፤ የት አመሸህ ሲባል ይቆጣል። ቀጥሎ ግን ራት አምጪ ይላል። ካመሸ ራቱን ራሱ መመገብ እንዳለበት አናስብም። ነፃነቱን ሲፈልግ ከነፃነት ጋር የሚመጣውን ኃላፊነት አብሮ መውሰድ ያስፈልጋል። ዝም ብሎ ነፃ የሚባል ነገር የለም። እኔ መሸከም የምችለውን ቀንበር ሌላ ሰው አይሸከምልኝ ማለት ጭራሽ ቀንበር የሚባል ነገር አልሸከምም ማለት አይደለም።
የእኛ ሚዲያዎች ከዚህ አንጻር በስፋት ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ሰፊ ችግር ነው ያለው። አንደኛ ግጭት ይፈጥራሉ። የሌለ ግጭት ይፈጥራሉ። ያልሞተ ሰው ገድለው ይዘግባሉ። ይህ ሟርት ማለት ነው። ሟርትን ደግሞ ሰው ፈጽሞ ማዳመጥ የለበትም። ያጋጫሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሾማሉ፣ ይሽራሉ። እንደ እነዚህ አይነት የጥፋት ሚዲያዎች ራሳቸውን በደንብ ማየት አለባቸው። አድማጩም እየነጠለ መስማት አለበት፤ ዋናው ገበያ ፍለጋ ስለሆነ። ግጭት መፍጠር ብቻ ሳይሆን ግጭት ያባዛሉ። አንድ ሰው ከሞተ 50 ይላሉ፤ 50 ከሞተ ሺህ ይላሉ። ግጭት ያበራክታሉ። ግጭት ደግሞ ካጡ ታሪክ ይመዛሉ። የዛሬ 50 ዓመት እኮ ብለው ታሪክ መዝዘው ያጣላሉ። አሁን የሚታይ ግጭት ከሌለ ወደ ኋላ ይመለሳሉ።
እነዚህ ሚዲያዎች ከአንገት ላይ ሐብል ለመውሰድ አንገት የሚቆርጡ ሚዲያዎች ናቸው። ሐብሉን መቁረጥ ወይም መፍታት ሳይሆን አንገት ቆርጠው ሐብል መውሰድ የሚሹ ሚዲያዎች ናቸው። ይህን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚዲያዎች ሚና ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ ኢትዮጵያ ተቀምጠን ስለ ዓለም እንድንገነዘብ ማድረግ፣ የማናውቀውንና ያልሰማነውን እንድናውቅ ማድረግ መሆን ሲገባው ወደ ጥፋት እየሄደ ያለውን ባለማድመጥ ልንቀጣቸው እንችላለን።
ከሕግ ባሻገር፤ ከሕግ አንጻርም ያው እንደምታውቁት የሚዲያ ነፃነት ይስፋ፤ ይለመድ በሚል እሳቤ እንዝህላልነቶች ቢኖሩም የብሮድካስት ባለሥልጣን አሁን በጀመረው መንገድ ጠንካራ የሆነ ሕግ የማስከበር ሥራ መሥራት ይኖርበታል። ሚዲያዎች በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብን ሰላም የማያረጋጋ ሚና እየተጫወቱ ስለሆነ። መርጠን እንስማ፤ ሕግ እናስከብር፤ እነሱ ወደተሻለ ወደሚያዛልቀው ነገር እንዲያተኩሩ በጋራ ግፊት ብናደርግ መልካም ይሆናል። አሁን ያለው ግን የጥፋት ጉዞ ሰላም የሚያመጣ ሳይሆን ሰላም የሚያደፈርስ መሆኑ እሙን ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በነፃ መዘዋወርን በሚመለከት ከአንድ አካባቢ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ በነፃ መዘዋወር መብት ነው። ማንም ሰው ከአንድ ስፍራ ሌላ ስፍራ ተንቀሳቅሶ ሕጋዊ በሆነ መንገድ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሠርቶ ማደር መብቱ ነው። ይህ መብቱ እንዲከበር አብዝተን መሥራት ይኖርብናል። በነገራችን ላይ ፍልሰቱም ቀላል አይደለም። እንደሚባለው ሳይሆን ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ በዚህ ሁለት ዓመት ያለው ፍልሰት አምስት ስድስት ዓመት ካለው ይበልጣል።
ተዘጋ ሲባል እንቅስቃሴ የቆመ እንዳይመስላችሁ። በቅርቡ ጥናት አጥንተን ነበር። አዲስ አበባ አካባቢ አብዛኛው ላስቲክ አንጠፈው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚኖሩ ሰዎች 96 በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አይደሉም። እና ፍልሰቱ ጭራሹኑ የቆመ አድርገን አናስብ። በስፋት እንቅስቃሴዎች አሉ። ተሻግሮ ማልማቶችም አሉ። ለልማት በምንቀሳቀስበት ወቅት ከክልላቸውም ባሻገር የሚያለሙ ሰዎችም በስፋት ይታያሉ።
ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረግ አለብን፤ አዲስ አበባ ውስጥ ኹከት ካላስነሳን በስተቀረ በቀላሉ መንግሥትን መነቅነቅና ሥልጣን መያዝ አንችልም የሚሉ በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ በርካታ ሙከራዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ያንን ለመከላከል ሰፊ ሥራ ሠርተናል። ውጤትም አምጥተናል። ነገር ግን ይህ ሥራ በስጋት እና በአፈጻጸም ውስንነት ድብልቆሽ ውስጥ ያለ ነው።
በአንድ በኩል ሰግተን ግጭት ለማስቀረት የምናደርጋቸው ጥረቶች አሉ። በሌላ መንገድ ደግሞ በአፈጻጸም የሚበላሹ ጉዳዮች አሉ። ይህን ጀብሎ የያዘ ነው። ነገር ግን ምንም መረጃ ሳይኖረን የሠራናቸው ሥራዎች አይደሉም። በስፋት መረጃዎች እናገኛለን። ከዚያም ተነስተን ግጭት ለማስቀረት በሚደረጉ ሥራዎች ስጋት እንገታለን። መጉላላት የማይገባቸው ንጹሕ ዜጎች ደግሞ የሚጉላሉባቸው አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች አሉ። እነሱ መታረም አለባቸው።
ለምሳሌ፣ በአንድ ቀን፣ በአንድ ቀበሌ፣ በአንድ ሰው ፊርማ አንድ ሙሉ ባስ(አውቶቡስ) በወረቀት ልኮ ይዘን እናውቃለን። ቀድመን መረጃውን ስላገኘን። መሣሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንይዛለን፤ ፈንጅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንይዛለን፤ ገንዘብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንይዛለን፤ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ደግሞ አንድ አካባቢ መሰብሰብ፣ ሲበተኑ ሰለሚሳሳ ሰብሰብ ለማለት በሚያደርጉት ጥረትም እንዲሁ እንይዛለን። ዝም ብሎ መረጃ አልቦ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
በዚህም ብዙ ሕይወት መታደግ ተችሏል። አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ከወለጋም ይምጣ ከጎጃም ብጥብጥ የሚያስነሳው ሰውዬ የአንዲት ምስኪን እናት ልጅ ወይ ይቆስላል፣ ወይ ይሞታል። በአንድ በኩል ሰላም ማስከበር አለበት መንግሥት እየተባለ፤ በሌላ መንገድ ሰላም ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ሙሉ በሙሉ (ስህተቱን ማረም ሳይሆን) ሙሉ በሙሉ እንዳልተገባ ከወሰድን ሁለቱ አብሮ አይሄድም።
አብዛኛው እነዚህ ኃይሎች ሰኔና ሰኞ የተገናኘ ሲመስላቸው፣ የሕዝብ በዓላት ያሉበት ጊዜ ሲሆን አበል እየከፈሉ በስፋት ሰው ያስገባሉ። ይሄን ነገር ለመታደግ ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ወደፊትም ይጠናከራል። የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ፤ የአዲስ አበባን ሰላም ለማስጠበቅ አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር የሚያስቡ ኃይሎች ሁከት መፍጠር እንዳይችሉ የተጠናከረ ሥራ ይሠራል። ያንን ሥራ ስንሠራ ደግሞ ንጹሐን ዜጎች እንዳይጉላሉ የነበሩ ስህተቶችን እያረምን እያስተካከልን ዜጎች እንዳይጉላሉ፣ ጥፋተኞች ደግሞ ጥፋት እንዳያጠፉ ወደሚያደርግ ደረጃ እንወስደዋለን።
ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በከፍተኛ ቁርኝት መሥራት ይኖርባቸዋል። ቤት ያከራየናቸው ሰዎች ሲሰባሰቡ አይተን እንዳላየን፤ እየሰማን እንዳልሰማን ዝም ብንል ግጭቱ ሲያጋጥም ተጎጂ እንሆናለን።
ይሄ እንዳይሆን በትብብር ማንኛውም ሰው ሲንቀሳቀስ ለሰላም ሲንቀሳቀስ፣ ለሥራ ሲንቀሳቀስ ሀገር ለማየት ብቻ እንዲሆን ማድረግ አለብን። ይህ መብት ስለሆነ። በሰላም መንቀሳቀስ መብት ነው፤ መከበር አለበት። ለጥፋት ሲሆን ግን ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ለከተማ ሳይሆን፣ ከመኝታ ቤት ሳሎንም ቢሆን አይፈቀድም። አጥፊዎች እንዳሻን ለምን ልናጠፋ አልቻልንም ብለው የሚያደርጉትን ጩኸት የተከበረው ምክር ቤት መለየት አለበት። ጥፋተኞችም ገብተው እንዳያጠፉ ማድረግ ይኖርብናል። ያን ካላደረግን ጉዳቱ ለሁላችንም ይሆናል።
ከዚህ አንጻር ባለፈው የነበረውን ሁኔታ በተደጋጋሚም ተገምግሟል፤ ይጠነክራል። ፍተሻው ይጠነክራል። ጥፋተኞችን መያዙ ይጠናከራል። ንጹሐን ዜጎችን ማጉላላት እንዲቀንስ እንዲታረም ይደረጋል። በዚህ አግባብ ቢታይ ጥሩ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የሁለት ብሔሮች አካባቢዎች ለተባለው፣ ኢትዮጵያ የእከሌ የእከሌ ሀገር አይደለችም። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ሀገር ነች።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ሀገር ውስጥ ሠርቶ የመኖር፣ የመንቀሳቀስ የፖለቲካ ስልጣንን የመሻት ተግባራዊ የማድረግ መብት አለው። እንዳላችሁት በኦሮሞ እና በአማራ ያሉ ጽንፈኞች ሁል ጊዜ እነርሱ ብቻ የሀገር ባለቤት የሆኑ ይመስላቸዋል። እና የማይገባቸውን ድርሻ ይፈልጋሉ። ይሄ አደገኛ ነገር ነው። የጋራ ሀገር እንገንባ ለዳሰነችም ሀገር የሆነ ለአፋሩም ሀገር የሆነ፤ ለሌላውም ሕዝብ ሀገር የሆነ ኢትዮጵያዬ ብሎ የሚያምንበት ሀገር ከገነባን ኢትዮጵያ በቂ ናት። ያለው አላስፈላጊ ሽሚያ ግን ጥፋት ያመጣል።
እነዚህ ወገኖች መተባበር ነበር የሚገባቸው። እንደተባለው ይበልጥ በታሪክ ሒደት ውስጥ ሰፋ ያለ ቅርርብ፣ ውህደት፣ መጋባት ያላቸው ሕዝቦች፣ መተባበር እና አንድ መሆን ሲገባቸው ታላቅነትን በማቀፍ፣ የብዝኃነትን ችግር መፍታት ሲገባቸው፣ በተቃራኒው የሚሄዱ ግለሰቦች እና ቡድኖች መታረም አለባቸው፤ አስፈላጊ አይደለም። የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ቁጥር በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ቁጥር ነው። ጥያቄ የለውም እሱ። ይህን ትልቅ ቁጥር ለልማት፣ ይህን ትልቅ ቁጥር አነስተኛዎችን ለማገዝ ነው መጠቀም ያለብን እንጂ ለጥፋት መሆን የለበትም፤ እንደዛ ባይሆን ይመረጣል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየቦታው የሚታገቱ ሰዎችን በሚመለከት ሕገወጥ የታጠቁ ኃይሎች እዚህም እዚያም በስፋት ስላሉ የሚገደሉ፣ የሚዘረፉ፣ የሚታገቱ ሰዎች አሉ። አልፎ አልፎ ራሳቸውን የሚያግቱ ሰዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአብዛኛው ግን እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች እገታ ያካሂዳሉ። ያን ለመፍታት እንደምታውቁት አብዛኛው ኃይላችን፤ አብዛኛው ወታደራዊ ኃይል የነበረው አንድ አካባቢ ስለነበር፣ በኋላ እመጣበታለሁ፣ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ ትጥቅን፣ በየቦታው ሰው መግደልና መዝረፍን መከላከል በሚያስችል አሰፋፈር የሀገር መከላከያና የፌደራል ፖሊስ አብዛኛውን ወሳኝ (ክሪትካል) ቀጠና በሚይዙበት መንገድ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ጅማሮ ውጤቶች ይታያሉ። ግን በሚቀጥሉት ጊዜያት የበለጠ ይጠናከራል የሚል ተስፋና እምነት አለኝ።
ኃይሉ ቦታ ቦታውን እየያዘ ሲሄድ ከአንድ አካባቢ ከተሰበሰበበት ሲበተን፣ በድፍን ኢትዮጵያ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስተካከል እድል ይሰጣል። ከዛም ባሻገር በሥራ አስፈፃሚ ተገምግሞ በተወሰነው መሠረት በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኃይሎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት በያሉበት አካባቢ፣ በልካቸው እንዲሆኑ የተጀመረ ሥራ አለ። ያም ችግሩን በከፊል ይቀንሳል የሚል እምነትና ተስፋ አለኝ።
ነገር ግን አሁን አልፎ አልፎ የሚታዩ አጋጣሚዎች (ኢንሲደንቶች) እንዲጠፉና እንዲቀንሱ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል። የእናንተም ድጋፍ ቢታከልበት ጥሩ ነው። የአማሮና ኮሬ አካባቢ ያለው፣ ከጉጂ አካባቢ የተነሳው ግጭት ጉዳይ፣ ጥያቄውን ያነሱት የምክር ቤት አባል በደንብ እንደሚገነዘቡት፣ ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በአካባቢው ግጭቶች ነበሩ።
አሁን ተጨማሪ ኃይል አስገብተን የተረጋጋ ነገር ያለ ቢሆንም፣ በማንኛውም እዛ አካባቢ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚፈጠር ችግርን መፍታት የሚያስችል ሰፋ ያለ ኃይል ገብቷል። የተሻለ፣ የተረጋጋ ነገርም ለጊዜው ያለ ይመስላል። ይሄን ማጠናከር ይኖርብናል። ነገር ግን ግጭትን ቦግ ብሎ እልም እንደሚል ጉዳይ ማየት የለብንም። ግጭት በዛፍ ቢመሰል የዛፉ ስር መነሾ፣ ግንዱ ዋናው ችግር፣ ቅጠሉ ደግሞ ውጤት ቢሆን ነው። ግንዱን ቆረጥን ማለት ችግር ጠፋ ማለት አይደለም። ግንዱን ብንቆርጥ ስር ስላለው በብዙ ሊባዛና ሊያብብ ይችላል።
ከመሠረቱ ችግርን የመፍታት አካሄድ ካልተከተልን በስተቀር አንዳንዱ ጉዳይ በምንፈልገው ፍጥነት ላይሄድ ይችላል። እና እዛ አካባቢ የጀመርነውን በአንድ በኩል ሰላም የማምጣት፣ የንግግር ጉዳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፀጥታ አካላት ገብተው የሕዝቡን ሰላም ከማረጋጋት አኳያ የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር ይኖርብናል፤ የሚገባውም እሱ ነው።
ይሄ ችግር እያጋጠመ ያለው ሰላም ከሰፈነ መረጋጋት ከመጣ ሕልማችን አይሳካም፤ በተቻለ መጠን በየቦታው ግጭት፣ ሰልፍ፣ ብጥብጥ መኖር አለበት። መንግሥት በሚያውቀውም፣ በማያውቀውም፤ በማያገባውም፣ በሚያገባውም ተጠያቂ መሆን አለበት። አንዳንዶች እንዲያውም ደጋግመን ከረበሽን መንግሥት ስልጣን በቃኝ ሊል ይችላል ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። በእንደ እነዚህ አይነት እሳቤዎች የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ይሄን ነገር በሕግ አግባብ ለመግራት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፤ የተሠራውንም ውጤት በጋራ እናያለን።
ሙስናን በሚመለከት ያው አብዛኛው የሙስና ኮሚቴ ከተቋቋመ በኋላ ያለው የሚዲያ ጩኸትና ውጊያ ለምን በሙስና ላይ ውጊያ ጀመራችሁ፤ ይሄንን ምክር ቤቱ በደንብ መገንዘብ አለበት። ከውስጥ ያለውና ከውጭ ያለው አርበኛ ተቀናጅቶ፤ በሁሉም አጀንዳ ይሄ ነገር ብርጭቆ አይደለም፤ ድንጋይ ነው። ውሃ አይደለም … ብሎ የሚጮህብን ሁሉ አቁሙ ነው እሚለው። ሙስና እሚባል ነገር አታንሱ ነው። እንደተባለውም ብዙዎች እየተያዙ ነው። እየተጠየቁ ነው። ሙስና ውስጥ በጣም ብዙ፣ ቅድም ያልኳቸው ሴራዎችም አሉበት።
ጉዳዩ ቀላል ባይሆንም እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ኮሚቴዎችን በሚመለከት መቶ ፐርሰንት ምንም እንከን የለውም ማለት አይቻልም። ሰው ስለሆነ የሚሰይመው አንድ አንዴ ሊቀላቀል ይችላል። እያዩ፣ እያጠሩ በሥራ መሄድ ይፈልጋልና ሙስና አሰቸጋሪ ጉዳይ ነው። መቀረፍ አለበት፤ መቀነስ አለበት። ልማታችንን ለማፋጠን እንቅፋት ነው። ነገር ግን በቀላሉ የምናጠፋው ጉዳይ ደግሞ አይደለም። ምክንያቱም በውስጣችን የተንሰራፋ ስለሆነ በውስጥና በውጭ ባለው ትስስር ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።
ሰውየው በሙስና ይጠረጠራል። ሰውየው የሚያወራው ግን ስለሰዎች ሞት ይሆናል። ሰውየው የሚያወራውና ዋናው ችግር ስለሚለያይ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቀላሉ የምንፈታው ጉዳይ እንዳልሆነ ከግምት ወስጥ ብናስገባው ጥሩ ነው።
ጤናን በሚመለከት በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት እንደቀረበላችሁ መሠረታዊ (ቤዚክ) የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት፣ መድኃኒትን ለማስፋፋት ሙከራዎች እየተደረጉ ነው። አጠቃላይ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ላብራቶሪና መድኃኒት አካባቢ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ይታወቃል። ግን በቀረበላችሁ ሪፖርት መሠረት በስፋት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው። በፕራይቬት ሴክተሩም፤ በመንግሥትም ይሄ አሁንም ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ሴክተር ነው።
ጤና ገና ብዙ ልንሠራበት የሚገባ ሴክተር ስለሆነ በተሟላ መንገድ ውጤት አምጥተንበታል ብለን የምንናገርበት ጉዳይ አይሆንም። ትምህርትን በሚመለከት ያው የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ፍኖተ ካርታውን ታስታውሳላችሁ፤ ፍኖተ-ካርታው ላይ በተቀመጠው መሠረት ዩኒቨርሲቲን አናስፋፋም፤ ታች ጥራትን እናስፋፋለን፤ ፈተናን እናጠራቅማለን (አኩምሌት እናደርጋለን) በሚል ላለፉት ሦስት አራት ዓመታት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ቆይቷል።
መዋዕለ ሕፃናትን (ኬጂን) የማስፋት፤ አንደኛ ደረጃን የማስፋት፤ ከ/2ኛ ደረጃን የማስፋት፤ በተቻለ መጠን የትምህርት ቤት ምገባን የማስፋት ሙከራዎች እየተደረጉ ነው። አሁንም የትምህርት ጥራት ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ስለሆነ በመጽሐፍም፤በኢንተርኔትም፤ በተሻሉ መምህራንም ገና ሰፋፊ ሥራዎች ይጠበቁብናል። ጅማሮዎች የሚታወቁ ናቸው። እነዛን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን በሚመለከት አጠቃላይ ክልልነትን በተመለከተ ያለው ችግር የፖለቲካ ሰዎች ክልል እንሁን ሲሉ መንገድ ይመለስልሃል፣ ልማት ይመጣልሃል፣ ችግር የለውም ብለው ይቀሰቅሳሉ። ከቀሰቀሱ በኋላ ክልል ይፈጠራል። ክልል ሲፈጠር ወዲያው ዞን፣ ወረዳ እየተባለ ይስፋፋል። በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ደርግ ወድቆ ኢሕአዲግ ሲመጣ 230 ሺ ገደማ ነበር የመንግሥት ሠራተኛ።
ባለፉት ሠላሳ ዓመታት አሁን ላይ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደርሷል። ሰው ሁሉ መዋቅር እየፈጠረ በዛ ውስጥ ካልተሾመ በስተቀር የሕዝቡ መብት አልተከበረም፣ የአካባቢ መብት አልተከበረም። መብት እንዲከበር እሱ መሾም አለበት። ይህን በሁለት ሦስት ዓመት ጭምር በተደጋጋሚ ስናገር ጭምር የነበረ ጉዳይ ነው።
ክልልነት በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባጠናነው ጥናት ቢያንስ ስድስት ሚሊዮን በአንድ ክልል ውስጥ ከሌለ ያ ክልል ገቢውን አሳድጎ አሁን ባለው ሁኔታ ደመወዝ መክፈል ይቸገራል። ለዚህ ነው ክልል ከተሆነ በኋላ ሳምንት አይቆይም ደስታውና ጩኸቱ። ወዲያው የደመወዝ ጥያቄ ይከተላል። የፌደራል መንግሥት የምታውቁት ነው። ካለው ገቢ ውጪ ከየትም አምጥቶ ሊያከፋፍል አይችልም። ቀመር የሚሠራው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በጀት የሚወሰነው እናንተ ጋር ነው።
የእኛ ሥራ እሱን ማስተዳደር እንጂ አዲስ ክልል ሲፈጠር በጀት አብሮ መስጠት እንቸገራለን። ከዚህ አንፃር ይህ የክልልነት ጥያቄ ትንሽ ሰብሰብ እንዲል የሚፈለገው አሁን ባለው የኢኮኖሚ አቅም ወደፊት ሊፈታ ይችላል። የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መልሶ ግንባታ ከግጭት ጋር ተያይዞ ተነስቷል። የመልሶ ግንባታ በጀትም በውስን በእናንተ ፀድቆ የጋራ እቅድና ዝርዝር እቅድ ተዘጋጅቷል። በቅርቡ የምንወያይበት ይሆናል። ረጂዎችን ለምነን፤ የሀገር ውስጥ አቅምንም ሰብስበን ያጋጠሙ ችግሮች በየቦታው መልሰን ለመገንባት ጥረት ይደረጋል። እዚህ ጋር ግን ወለጋ ያለ ሰው ወለጋ ብቻ ነው ግጭት ያለው፣ ወለጋ ብቻ ነው የወደመው፣ ወለጋ ላይ ብቻ ቅድሚያ ሰጥታችሁ ገንቡ ይላል።
ከወልዲያ የመጣው ወልዲያ ብቻ ነው ጦርነት ያለው ስለዚህ ወልዲያ ያለውን ገንቡ ይላል። ከአፋር የመጣው ሰው አፋር ብቻ ነው ይላል። ከትግራይ የመጡት ደግሞ ትግራይ ነው ይላሉ። ብዙ ቦታ ችግር አለ። ይህን በተመጣጠነ መልኩ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ሕዝቡን አቅም፣ የመንግሥት አቅም፣ የአጋር ድርጅቶች አቅም ደምረን የምንጠቀምበትን አቅም ማየት ጥሩ ይሆናል። ተጀምሯል። መጠናከር አለበት። መሠራት አለበት። ግን ሁሉን ችግር ለመመለስ ደሞ ያለውን የአቅም ውስንነት ከግምት ማስገባት ጥሩ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግሥት ሀገርን ሊያፈርስ እየሠራ ነው፤ መንግሥት ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ሳይሆን ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው የሚሠራው የሚል ጥያቄ የተነሳው በጥያቄ ደረጃ የተከበረ ጥያቄ ነው ነገር ግን የዓመቱ ምርጥ ቀልድ አድርጌ ነው የምወስደው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ መንግሥታችን የሚከፈለውን መስዋዕትነት ዓለም የሚያውቀው ነው። ይሄ ምክር ቤት ዘንግቶት ቢሆንም ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ነው።
ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ያን ሁሉ የአንድ ቡድን፣ የአንድ ኃይል ሳይሆን የዓለምን ውጊያ የኢትዮጵያን ክብር ለድርድር አላቀርብም ብሎ የቆመን መንግሥት ሊያፈርሰው ነው የሚሠራው ብሎ መጠየቅ ጥሩ ቀልድ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይሰጠውም። ልትገነቡ ልታንፁ ሞክራችሁ ያልቻላችሁት ነገር አለ እናግዛችሁ አስተካክሉ አርቁ ችግር የለውም። አስባችሁ ነው የምታፈርሱት ከሆነ ማን አቆምን ታዲያ። እኛ ሀገር ለማፍረስ የምንሠራ ከሆነ ማነው ሀገር ሊከላከል የሚያቆመን ኃይል? ‹‹አለ?›› ይህ ብዙ ጠቃሚ አይመስለኝም።
አንደኛ ዓለም በሙሉ በዚያ ልክ ሲጮህብን የለም ኢትዮጵያውያን ደሃ ብንሆንም ክብር አለን አንነካም ብለን ነው የቆምነው። ሁለተኛ ጦርነቱ አዲስ አበባ ደርሷል፣ አዲስ አበባ ወድቃለች መውጫ መንገድ እናበጅላቸው ሲባል የለም አለመደብንም ብለን የዘመትን ሰዎች አሁን ሀገር ልታፈርሱ ነው ቢባል ብዙ ትርጉም ያለው አይመስለኝም።
ይቀጥላል …
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015