‹‹በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን›› የያዘውን ሰነድ የፍትሕ ሚኒስቴር ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ይፋ አድርጓል። በ54 ከተሞች ብሔራዊ ምክክር እንደሚደረግም ተገልጿል። በዚህም መሰረት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የሽግግር ፍትህ ዓላማው የተሟላ ሰላምን ማስፈን ነው። ከእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት ፣ በፖለቲካና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ማድረግ ስለመሆኑ ሰነዱ ያመለክታል። ይህን ሥርዓት ለማስፈን በሞከሩ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ሂደቶች ተግባራዊ በማድረጋቸው የሽግግር ፍትህ ሥርዓት መዘርጋቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ እና ፍትህ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም የሽግግር ፍትህ ሰነዱ ያመለክታል። በሌላ በኩል ደግሞ በሽግግር ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በደል የተሟላ መፍትሄ መስጠት አለመቻል አንዱ ችግር እንደሆነም ሰነዱ ያብራራል።
ለመሆኑ የሽግግር ፍትህን ለማስፈን ከማን ምን ይጠበቃል፤ ምን ያክል ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ምን ዓይነት ጉዳዮችን ሊመለከት ይችላል በሚሉት ላይ ባለሙያዎች ምሁራዊ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
የሕግ ባለሙያውና የፌዴራሊዝም መምህሩ አቶ ኑሩ መኩሪያ የሽግግር ፍትህ በታሪክ አጋጣሚ ወይንም ደግሞ ባልታሰቡ ሁኔታዎች ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶችን፣ አለመግባባቶችን፣ የጸጥታ መደፍረስና ጉዳቶችን፤ የህሕይወት መጥፋት፤ የንብረት ውድመትና በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሥርዓት ግድፈቶችና ለማረምና በዚያ ውስጥ ሰለባ የሆኑ አካላት ፍትህና ርትዕን እንዲያገኙ እንዲሁም የተረጋጋ ሰላም እንዲመጣ የሚደረግ ጥረት መሆኑን ያብራራሉ።
የሽግግር ፍትህ ፖለቲካዊ፣ ማህረሰባዊና ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ በውስጡ ታሳቢ እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ። በዚህ ሂደት ሆን ተብሎ የመብት ጥሰት የደረሰባቸው አካላት እንዲካሱ ወይንም ጉዳት ያደረሰባቸው አካላት ይቅርታን በመጠየቅ ወደ ቀደመ ማህበረሰባዊ እሴት እና አንድነት እንዲመለሱ በማድረግ የሚኖረው ማህበረሰባዊ እሳቤ የላቀ ስለመሆኑ ይናገራሉ። በመሆኑም የሽግግር ፍትህ ከማህበረሰባዊ እሳቤ አኳያ ትርጉሙ የተለቀና ሂደቱ ይህን ለማንበር የሚደረግ ሠላማዊ ሂደት እንደሆነ ይናገራሉ።
በሽግግር ፍትህ ውስጥ ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ ያላቸው ተግባራትም ሊከወኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ- አቶ ኑሩ። ለአብነትም ሆን ተብሎ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የተገለሉ አካላት በሽግግር ፍትህ የመደመጥ ዕድል ያገኛሉ። ተጎድተናል ብለው የሚያስቡትን ሁኔታ የሚያሳዩበትና በቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሽግግር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል የሚመቻችበት ነው። ይህም በኢኮኖሚ እሳቤ ተጎድተናል ብለው የሚያስቡ አካላት በአገር ሁለንተናዊ ተሳትፎ ውስጥ ተዋናይ የሚያደርጋቸው ይሆናል።
ኢትዮጵያን በመሰሉ ፌዴራላዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት ደግሞ ሽግግር ፍትህ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ለአብነትም በታሪክ አጋጣሚም ይሁን በሌሎች እሳቤዎች አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው የተገለለበት፤ የተጎዳበት አሊያም በእኩል ዓይን አልተዳኘሁም ብሎ የሚያምንበት ዕድል ካለ ሥርዓቱን ለማስቀጠል ፈተና ይሆናል። በመሆኑም የሽግግር ፍትህ የፌዴራል ሥርዓቱንም ለማስቀጠል፤ ለማጠናከርና አብሮአዊነትን የበለጠ ለማስተሳሰር ፋይዳው የጎላ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥም በርካታ አገራትም ያለፉ መሆኑም በመጠቆም አሁናዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገታቸው፤ ማህበረሰባዊ እሳቤያቸውና መተማመናቸው በጣም የላቀ እንደሆነም ያብራራሉ።
በአጠቃላይ ብዙሃኑ አምነውበት የሚሰፍን ሽግግር ፍትህ ተበዳዮችን በይቅርታ ካሳ አሊያም ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ቁሳዊና ሞራላዊ ካሳ የሚያገኙበት ከመሆኑም በተጨማሪ አገር ከማስቀጠልና አገራዊ የፖለቲካ ሥሪትን ከማጠናከር አኳያም የላቀ ትርጉም እንዳለው ያስረዳሉ ።
የሕግ ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት ነው ይላሉ። በአንድ አገር በግጭትም ሆነ በሌላ አጋጣሚ አስከፊ የሆነ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም ከነበረ ለአጭርም ሆነ ለረዥም ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደሚገነባበት ሠላማዊ ሁኔታ ለመሸጋገር የሚደረግ ሂደት ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ይኖራሉ። የሕግ እና የመብት ጥሰት የፈጸሙም ስለሚኖሩ ‹የተበደሉ ሰዎች ከዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚያልፉበት መንገድ ነው።› ባይ ናቸው። ለሽግግር ወቅት ፍትህ መሠረት የሆኑ ጉዳዮችም መጀመሪያ ላይ የሚቀመጠው ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማስፈን ነው። እርቅ ማውረድ ቀጥሎ የሚመጣ ነው። የተፈጸሙ ጥሰቶች በአግባቡ ተሰንደው በመልክ በመልክ እንዲታወቁም ይደረጋል። የተበደሉ አካላት በዋናነት አንድም ለጉዳታቸው ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኙበት፣ ሁለትም በአጥፊዎች ይቅርታ እንዲጠየቁ የሚደረግበት ሂደት ስለመሆኑም አቶ ያሬድ ለቢቢሲ አማርኛው በሰጡት ማብራሪያቸው ያስረዳሉ።
የሽግግር ፍትህ በውስጡ ትልቅ የሕግ እሳቤዎችን ያየዘ ስለመሆኑ የሚናገሩት ደግሞ የሕግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን ናቸው። የሽግግር ፍትህ በምን ያክል ጊዜ ይጠናቀቃል ብሎ ለመወሰን ግን ሂደቶች ይወስኑታል ይላሉ። የሽግግር ፍትህን ለማስፈን በመጀመሪያ ተፈጸሙ የተባሉ የሕግ ጥሰቶች ምንድን ናቸው ብሎ ማየት፣ መገምገም፣ መረዳትና መተንተን ይፈልጋል። በዚህ ሂደት በደፈናው ፍትህ ይሰፍናል ተብሎ የሚቀመጥበት ሳይሆን ላለፉት ጥፋቶችና ግድፈቶች የትኛው አካል ምን ድርሻ ነበረው የሚለውን ማየት ተገቢ ነው።
በአገሪቱ ሕገ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን የሚዳኙበት፣ የሚመዘኑበትና ፍትህ የሚሰፍንበት የሕግ መስመሮች በጥልቀት ከተመረመሩ በኋላ እነዚህ ጥፋቶች እንዳይደገሙ ከየትኛው አካል ምን ይጠበቃል የሚለውም በሂደቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስለመሆናቸው ያብራራሉ። ለአብነት በሽግግር ፍትህ ውስጥ ችግር ወይንም ግጭት በፈጠሩ ሁለት እና ከዚያ በላይ አካላት መካከል ፍትህ ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ወደ አለመግባባት ያስገባቸው መሰረታዊ ነገር ወይንም የሁኔታዎች ቅድመ ሁኔታ ምንድን ነው የሚለው ነው ። በዚህም ውስጥ ታሪካዊ ቁርሾዎች፣ የፖለቲካዊ መሪዎች ሚና፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ሥሪትና የሕግ የበላይነት የሚከበርበት ደረጃ፣ የማህበረሰቡ እሴትና ተግባቦት ያለበትን ደረጃ እንደመነሻ ማወቅና ለሽግግር ፍትህ እንደ አንድ እርሾ መጠቀም ይገባል።
እንደ አቶ በፍርዴ ገለጻ ከሆነ፤ የሽግግር ፍትህ በራሱ ከአንዱ ሁኔታ ወደ ሌላው ምዕራፍ የሚደረግ ሽግግር ወይንም ደግሞ የፖለቲካዊ አተያይና ማህበረሰባዊ አኗኗር የሚያመራ በመሆኑ የራሱ ሂደት ያለው መሆኑን ያብራራሉ። የፈጠነ ሽግግር ፍትህ ለማስፈን ያለፉት ሂደቶች ምን ነበሩ የሚለውን በሚገባ መገምገም ተገቢ ነው። በዚህም ውስጥ የተፈፀሙ ግድፈቶችና ስህተቶች ብዙም አጨቃጫቂ ካልሆኑ የፈጠነ የሽግግር ፍትህን ለማስፈን ያግዛል። ይሁንና ነገሮች በተቃራኒው ሆነው ከሆነ ዓመታትን የመውሰድ ዕድል ሊኖራቸው ይችላል። ለአብነትም ከፍተኛ የሆነ የጦር ወንጀል፤ ዘር ማጥፋትና የመሳሳሉት ሂደቶች ካሉ እነዚህን ማስታመም፤ በሂደት ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚካሱበትን መለየትና አግባብ የሆነ ፍትህ አሊያም ሽግግር ሂደትን ለማስፈን ሲባል ጽሞና ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ማህበረሰቡና በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ አካላት ስለ ሽግግር ፍትህ ያላቸው ግንዛቤ እና ፍላጎትም ሁኔታዎችን የማቅለል ወይንም ደግሞ ችግሩን የባሰ የማወሳሰብ አቅም አለው የሚል ዕምነት አላቸው ይላሉ አቶ በፍርዴ።
እንደ ምሁራኑ ሃሳብ ከሆነ፤ የሽግግር ፍትህ በአንድ አገር ውስጥ በማህበረሰባዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች ውስጥ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቀውሶችን አሊያም ደግሞ ግጭቶችን ለመፍታት ሲባል የሚደረግ ሠላማዊ የፍትህ ሥርዓት ነው። ይህን ለማስፈንም ሂደቶችን የሚጠይቅ ሲሆን እንደተፈጠረው ቀውስ ወይንም አለመግባባት የሽግግር ፍትህ ሥርዓቱም የመፍጠን እና የመዘግየት ዕድል አለው። የሆነው ሆኖ ግን መሰል ጉዳዮች አለመረጋጋት ውስጥ የገቡ አገራትን ወደ ተረጋጋና ሠላማዊ ሁኔታ የመመለስ አቅማቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ‹‹የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች›› የሚለው ሰነድም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የተለያየ ይዘት ያላቸው የሽግግር ፍትህ ስራዎች ተግባራዊ ሆነዋል። በተለይም በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ሀገራት የሽግግር ፍትህ አሰራሮች በተለያየ መጠን ተተግብረው በርካታ ተሞክሮዎች ተቀምረዋል። ከነዚህ አገሮች የተሳካ የሽግግር ፍትህ ልምድም ሌሎች ሀገራት ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት እና ሊከተሏቸው የሚገቡ ሂደቶችን ለመለየት ተችሏል ሲል በሽግግር ፍትህ ሰላምን ለማስፈን እየተሄደበት ያለውን ቁርጠኝነት ያስገነዝባል።
በሽግግር ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በደል የተሟላ መፍትሄ መስጠት መቻል ነው። ይህም በዋናነት ሙሉ ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋት እና ማህበረሰቡ ተመልሶ ወደቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ፣ መረጋጋት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከት ስለመሆኑ በማስገንዘብ፤ ኢትዮጵያም ይህን ለመተግበር መወሰኗን ይጠቁማል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2015