የሲዳማ ክልል በቡና፣ ቱሪዝም እና ኢንዱስትሪው ዘርፎች በእጅጉ ይታወቃል። ከክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ይቀርባል። የሀዋሳ ሀይቅ፣ የክልሉ ሕዝብ ባህላዊና ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የሚጠቀስ አርገውታል፤ ክልል ግዙፉን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ተቋማት ባለቤትም ነው።
ክልሉ ያሉትን እምቅ አቅሞች በማልማት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በመስኖ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ያሉትን ትላልቅ ወንዞች፣ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትና የሀዋሳን ሀይቅን ለመስኖ ልማት ለማዋል መስራቱን ተያይዞታል። ለእዚህም ሰፋፊ የአለኝታና የዝርዝር ጥናት ስራዎችን እያካሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ ወደ መስኖ ልማቱም ተሸጋግሯል።
በሲዳማ ክልል ከመስኖ መሰረተ ልማት አኳያ የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በግድብና ለመስኖ በሚውል አካባቢ ጥናት፣ በጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የሀዋሳ ሀይቅን ለበጋ ስንዴ ልማት በማዋልና በመሳሰሉት ላይ እየተከናወኑ ባሉ ተግባሮች ዙሪያ ከክልሉ መስኖ ልማት ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በላይነህ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በወቅታዊ አምዳችን ለንባብ አብቅተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በክልሉ ለመስኖ ልማት እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ በተለይ የመስኖ ልማት ሊካሄድባቸው በታሰቡ አካባቢዎችና ለእዚህም በሚያስፈልጉ የመስኖ መሰረተ ልማቶች ዙሪያ በጥናትና ልየታ በኩል እየተከናወነ ስለሚገኙ ተግባሮች ጠቅለል ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን።
አቶ ዮሴፍ፡- ከመስኖ አኳያ በክልሉ አንደኛ ደረጃ አድርገን የምንሰራው በመስኖ ሊለማ የሚችል ምን ያህል አቅም እንዳለ መለየት ነው። በገጸ ምድር እና በከርሰ ምድር ውሃ መልማት የሚችለውን መሬት በመለየት ይሰራል። የትኛው ውሃ ምን ያህል መሬት ያለማል በሚለው ላይ የአለኝታና ዝርዘር ጥናት እንሰራለን።
ወደ ዝርዝር ጥናት ሳይገባ ያለውን አቅም ለማወቅ የሚሰራ ቅድመ ጥናት የሚባል ነገር አለ። በክልሉ ዝናብ አጠር ወረዳዎች አሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ምን ያህል በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አለ፤ ለእዚህ የሚሆን ምን የውሃ አቅም አለ በሚለው ላይም በሰባት ወረዳዎች የጥናት ስራዎችን ጀምረናል። በእነዚህም ከጥቁር ውሃ እስከ ዳራ ወረዳ ባሉት የታችኛው የክልሉ ወረዳዎች ለመስኖ ሊውል የሚችል ምን ያህል መሬት አለ የሚለው ጥናት ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን በወረዳዎቹ የተካሄዱት ጥናቶች ምን አመላከቱ። በቀጣይስ ምን ለመስራት ታስቧል?
አቶ ዮሴፍ፡- በዚህም ጥናት በወረዳዎቹ በከርሰ ምድርና በገጸ ምድር ውሃ በመስኖ ሊለማ የሚችል 27 ሺ ሄክታር መሬት መኖሩ ታውቋል። ይህ ልይታ ከተደረገ በኋላም ወደ ዝርዝር ጥናት ተገብቷል።
ዝርዝር ጥናት ከሚካሄድባቸው መካከል በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የሚካሄደው የከርሰ ምድር ውሃ አንዱ ነው፤ ሌላው ደግሞ መካከለኛ መስኖ ነው፤ ይህም በጂጌሳ ወንዝ ላይ የሚገነባ ነው። ዋንሞሌ ወንዝ ላይ የሚገነባም አለ። የጠቀስኳቸው ፕሮጀክቶች ትላልቅ ናቸው። ጊዳቦ እና ኮላ ወንዝ ላይ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶችም አሉን። አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እየገነባን የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላት አንችልም፤ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት አለብን ብለን እነዚህን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለመገንባት እየሰራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ዝርዝር ጥናት እየተካሄደባቸው ያሉ ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ዮሴፍ፡- ወደ አስራ ስምንት የሚሆኑ የመካከለኛና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጥናቶች በተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄዱ ናቸው። ጥናታቸው ሲጠናቀቅ እንደሚገኘው የመንግስት በጀት ወደ ግንባታ ይገባል፤ ለተለያዩ ድጋፎች ለሚመጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሆኑ ጥናቶችን አድርገን ሰነዶቹን መደርደሪያ ላይ እናስቀምጣለን። ይህም ገንዘብ ይዘው ለሚመጡ አካላት ጥናት የለንም የሚል ምላሽ ከመስጠት ያወጣናል። የሚመጣ ሀብትን ፈጥነን ለመጠቀም ያስችለናል።
በተጨማሪም ክልሉ ከተለያዩ ረጂ ተቋማት ያገኛቸው ወደ 40 የሚሆኑ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች አሉት። እነዚህ የውሃ ፓንፓች ከ30 ሄክታር የማያንስ ማልማት ያስችላሉ። በክልሉ አንድ አርሶ አደር 30 ሄክታር የለውም፤ ሁለት አርሶ አደሮችም ሆነው 30 ሄክታር መሬት አይኖራቸውም። እነዚህን ፓምፖች አርሶ አደሮችን አደራጅተንና አስተሳስረን 30 የሚሆኑ አርሶ አደሮች መሬት ተደምሮ 30 ሄክታር እንደሚሆን ታስቦ ለእነሱ ለመስጠት ስርዓት ለማበጀት እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመስኖ ልማት ኤጀንሲው በኩል ምን ያህል ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ናቸው?
አቶ ዮሴፍ፡- በሲዳማ ክልል መስኖ ልማት ኤጀንሲ ስር ወደ 26 የግንባታ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ሲጠናቀቁ ከአራት ሺ 355 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ያስችላሉ። ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ቢሆኑም እስከሚጠናቀቁ መጠበቅ ውስጥ አልተገባም፤ አንዳንዶቹ በከፊል አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ግንባታቸው ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን፡- የፕሮጀክቶቹ የግንባታ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ዮሴፍ፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች በሁለት መሰረታዊ ችግሮች በተባለው የጊዜ ሰሌዳ በውሉ መሰረት እየተፈጸሙ አይደሉም፤ የኮንትራክተሮች የመፈጸም አቅም ዝቅተኛነት አንዱ ተግዳሮት ነው። ሁለተኛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከሲሚንቶ ጋር በተገናኘ የሚታየው የአቅርቦት ችግር ነው። እንደሚታወቀው የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ መጠን ያለው ሲሚንቶ ይፈልጋል። በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረትና ውል ሲገባ የተያዘው ገንዘብ መጠን በመቶና ሁለት መቶ በመቶ መጨመሩ ከእኛ ጋር ውል ገብተው በሚሰሩት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። በዚህም የተነሳ ተቋራጮቹ በአግባቡ መስራት አልቻሉም።
በውላችን መሰረት ስራዎች እንዲከናወኑ ተገቢውን ክትትልና እርምጃ እየወሰድን ቢሆንም፣ እነዚህን ነገሮች ለመፈጸም የአቅም ውስንነት አጋጥሟል። ከእዚህም የተነሳ አንዳንድ ተቋራጮች ከውሉ ውጭ ዋጋ እንዲስተካከል ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፤ እነዚህ ችግሮች ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ አድርገዋል። ሲሚንቶና የአቅም ውስንነት ትልቅ ችግር ሆኖብናል። በአጠቃላይ ችግሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተገንብተው ለአርሶ አደሮችም ሆነ ለፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ክፍሎች እንዳይደርሱ እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጊዳቦ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መመረቁ ይታወቃል። ይሁንና በሲዳማ ክልል በኩል ያለው የግንባታው ስራ እንዳልተጠናቀቀና የሚፈለገውን ልማት ለማካሄድ እንዳልተቻለ እየተነገረ ይገኛል። ግንባታው አለመጠናቀቁ በግድቡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በዘመናዊ መስኖ ለማሰማራት በሚያስችለውና በቅርቡ ወደ ስራ በገባው ፕሮጀክት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ ስጋት አሳድሯል። ግንባታው ለምንድን ነው ያልተጠናቀቀው?
አቶ ዮሴፍ፡- በፌዴራል መንግስት እየተገነባ ያለው የጊዳቦ ግድብ የክልሉ አንዱ የመስኖ መሰረተ ልማት ነው። ይህ ፕሮጀክት የሚገነባበት አካባቢ ስትራቴጂክ አካባቢ ነው። ሆኖም የጊዳቦ ግድብ ፕሮጀክት በሚፈለገው ጊዜ ተጠናቆ የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። አሁንም ድረስ በግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ መጓተት ይታይበታል። ግድቡ በሲዳማ ክልል በኩል አምስት ሺ ሄክታር ሊያለማ ይችላል። ይህ ቀላል አይደለም። ከአምስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያለምንም ስጋት በዝናብ እጥረት እና በመሳሰለው ሳይባል ያለምንም የውሃ ችግር አምርተን ለገበያ ማቅረብ ስንችል በግድቡ ግንባታ አለመጠናቀቅ ሳቢያ ማልማትና ለገበያ ማቅረብ አልቻልንም። ይህ ልንታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው። ፕሮጀክቱ የራሱ በጀት አለው። የሚያስፈልገው ክትትል ከተደረገለት ተጠናቆ ለህብረተሰቡ መድረስ ይችላል።
ወጣቶችን አደራጀተን በዚያ አካባቢ በዘመናዊ የመስኖ ልማት ለማሰማራት እየተንቀሳቀስን ነው። በዚህች ሀገር ስራ አጥነት ምን ያህል አስቸጋሪና ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ወጣቱን አደራጅተን እናሰማራበታለን ያልነው ፕሮጀክት እስከ አሁን ግንባታው ባለመጠናቀቁ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ይህን ፕሮጀክት በባለቤትነት እያስገነባ ያለው የፌዴራል መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ነው። ግንባታውን እያካሄደ ያለውም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ነው። ሁሉቱም የመንግስት ተቋማት ናቸው። አማካሪውም የመንግስት ተቋም ነው። ስለዚህ ይህንን ችግር ልዩ ትኩረት በመስጠት መፍታት እየተቻለ መሄድ ያለበትን ያህል እየሄደ አይደለም የሚል ግምገማ አለን። በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ተወያይተንበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁንስ መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?
አቶ ዮሴፍ፡- ይህን ፕሮጀክት በተመለከተ ያለው ተስፋ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል፤ ስለዚህ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ፕሮጀክት ስለመጣ ለእዚህ ፕሮጀክት ለምናደርገው ርብርብ ተጨማሪ አቅም አግኝተናል እላለሁ። ቀጥሎ የተሻለ ተስፋ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ቀሪ ስራዎችን የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፍላጎቶች አሳይተዋል፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ባንክ ጋር ግንኙነት መፍጠር ከተቻለ ተስፋ ይኖራል።
ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል የሚል እምነት ቢኖረንም፣ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ መሬቱ ወደ ስራ ገብቶ ቢሆን ተጨማሪ አቅም ማግኘት እንችል ነበር፤ ያንን ሀብት አጥተናል። በቀጣይም በእዚህ አካባቢ ላይ በትኩረት ይሰራል፤ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ጋር እየተናበብን ያለንበት አግባብም አለ።
አዲስ ዘመን፡- የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በቆላማው የሀገሪቱ አካባቢ ተጀምሮ በደጋና ወይናደጋው አካባቢም በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። በክልሉ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚውሉ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ከመገንባትና ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ ምን እየተከናወነ ነው?
አቶ ዮሴፍ፡- በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል። ልማቱ በሰፊው ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነው። ይህን ለመስራት ከሀዋሳ ሀይቅ በሶስት መስመር ውሃውን በሞተር ፓምፕ በመውሰድ በሀይቁ ዙሪያ ያለውን መሬት እንዲያለማ አድርገናል።
ሁለተኛ በዚሁ አካባቢ አምስት መቶ ሜትር ጥልቀት ካለው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውሃ አውጥተናል። ጉድጓዱ በሰከንድ አንድ መቶ ሊትር ውሃ ማምረት ያስችላል። ይህ ውሃ ማለት ትልቅ ሀብት ነው፤ ለበጋ መስኖ ልማት ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ወቅት መጠቀም የሚያስችል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጥቶበት የተሰራና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችልም ነው። ሌላም አምስት መቶ ሜትር ጥልቀት ያለው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ግንባታ በዚሁ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ እያስገነባን እንገኛለን። በወረዳው 240 ሜትር ጥልቀት ያለው ሌላ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድም አስገንብተናል። አካባቢው ቆላማ ነው፤ እንደ ክልል በዚያ አካባቢ ዝናብ ጠብቀን ብቻ ለምን እናለምለን የሚል አቋም ተይዞ ነው ወደዚህ ስራ የተገባው። በዚህም በኮንስትራክሽን በኩል ውጤታማ ተግባር ተከናውኗል።
የተገኘው ውሃ ምን ያህል ያለማል ለሚለው እንደ የአጠቃቀማችን ነው የሚወሰነው። በሰከንድ 100 ሊትር ማለት ቀላል አይደለም። ያላለቁ ፕሮጀክቶችም አሉን። አንዱ ያለቀው ማልማት ጀምሯል፤ ሄዶ ማየት ይቻላል። ነገር ግን ዘንድሮ ለበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እየተጠቀምን በዘላቂነት አርሶ አደሩ በማይጠቀምበት ሰዓት ገንዳ ተገንብቶ ውሃው የሚጠራቀምበት ከዚያም ሌላ ስትራክቸር ተገንብቶለት ውሃው ወደሚፈለገው ቦታ የሚሄድበት ስራ በቀጣይነት የሚከናወን ይሆናል።
የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሄድ ይጎላል የሚባል ነገር አለ። እነዚህ ጉድጓዶች ግን እንደእዚህ አይነት ባህሪ የላቸውም። ውሃቸው አይጎልም፤ ስለዚህ ማልማት የምንችለውን ያህል ማመንጨት እንችላለን። ይህ ማለት ለጥልቅ ውሃው የምናስገባቸው የውሃ መሳቢያዎች በቀን ከ16 እስከ 18 ሰዓት የሚሰሩ ከሆነ በማታውም ፈረቃ ውሃውን ማውጣት እንችላለን። የተወሰነ ሰዓት እያሳረፍን ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ጉድጓዱ ብዙ መሬት ያለማል ብለን እንገምታለን። ሎካ አባያ ወረዳ አካባቢም እንዲሁ ተመሳሳይ ስራ እየተሰራ ነው። በአጠቃላይ እነዚህን በተመለከተ ለበጋ መስኖ ለዘንድሮ ብቻ ተብሎ የሚሰራ አይደለም። እነዚህ ስራዎች ዘንድሮ በተገነቡበት አካባቢ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሌላ መሰረተ ልማት እንዳይጠይቁ አርገን ነው የሰራናቸው። በዚህ አቅድ መሰረት በእነዚህ አካባቢዎች ስንዴ ተዘርቷል።
አዲስ ዘመን፡- ውሃውን ለመስኖ አገልግሎት በመጠቀም በኩል ከመስኖ ቴክኖሎጂ አንጻርስ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ዮሴፍ፡- ቅድም ያነሳሁልህ እየተገነቡ ያሉ 26 የመስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለሚፈለገው ቦታ ውሃ የሚያደርሱት ደረጃቸውን የጠበቁ ካናሎች ተገንብተውላቸው ነው። ሀዋሳ ዙሪያ ላይ ከድሪፕ ወይም ስፕሪንት የቱ ይሻላል በሚለው ላይ ጥናት እየተደረገ ነው። የሀዋሳ ዙሪያ አፈር በካናል የሚችል አይነት ስላልሆነ ነው ጥናት ማድረግ ያስፈለገው። ሌሎች የመስኖ መሰረተ ልማቶች ግን ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ተደርጎላቸዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችም በአካባቢዎቹ ይካሄዳሉ።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ መስኖ በስፋት ይካሄድባቸዋል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ለአካባቢዎቹ የታሰቡት የመስኖ መሰረተ ልማቶቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ዮሴፍ፡- በቀጣይ በስፋት ይሰራሉ ተብለው በመስኖ ልማት በኩል ከሚታሰብባቸው አካባቢዎች አንዱ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነው። በወረዳው የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶችን በስፋት ወደ ስራ እናስገባለን። አለታ ጩኮና ዳራ ቶልቻ የሚባለው ወረዳ ውስጥ ያለውን ጂጌሳ የሚባል ወንዝ ለመስኖ ለመጠቀም በፌዴራል ተቋም ጥናት እያሰራን ነው። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ሰፊ መሬት ያለማል ብለን ተስፋ አድርገናል። ወደ ግንባታ ለማስገባት ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ዳሌ እና ሸበዲኖ ወረዳዎች ላይም እንዲሁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አሉን።
አዲስ ዘመን፡- በመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ያጋጥማል ብላችሁ ያሰባችሁት ተግዳሮት አለ? ተግዳሮቱ ካለ እንዴት ልትፈቱት አስባችኋል?
አቶ ዮሴፍ፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ሲገቡ እንደ ሲዳማ ክልል ተግዳሮቶች ይገጥሙናል ብለን አስበናል። እንደሚታወቀው በሲዳማ ክልል ሕዝብ ያልሰፈረበት መሬት የለም። መሬቱ አርሶ አደሩ ቡና፣ እንሰትና የመሳሰሉትን ተክሎ በንብረት ይዞታል። ወደ ግንባታ በሚገባበት ጊዜ ይህን ሁሉ አርሶ አደር አስነስቶ ግንባታውን ማካሄድ ፈተና ሊሆን ይችላል። ለአብነትም አንድ “ቢሳንዲማ” የሚባል ፕሮጀክት አለን። ይህ ግድብ ለሚሰራበት ቦታ ብቻ 72 ሄክታር መሬት ያስፈልገዋል። በዚህ 72 ሄክታር መሬት ላይ ቡና፣ እንሰት፣ ጫትና የመሳሰሉት ቋሚ ተክሎች አሉበት፤ አርሶ አደሩም ቤት ሰርቶ ይኖራል። ለእዚህ አርሶ አደር ካሳ ከፍለህ፣ አንስተህ ሌላ ቦታ አስፍረህ ካናሉን ተከትሎ ካለው አካባቢ አርሶ አደሩን ማንሳት ትልቅ ፈተና ነው። ይሄ ፈተና በሌሎች አካባቢዎች እንደሚስተዋለው አይነት አይደለም፤ ሲዳማ ውስጥ የመሬት ጥበት አለ። ይሄ ትልቁ ፈተናችን ይሆናል ብለን እናስባለን።
ፈተናው ቢኖርም ፈተናውን ተጋፍጠን፣ የሚገነባውን ገንብተን አርሶ አደሮቻችን ካላሻገርን በመደበኛው መንገድ የምንሄድ ከሆነ አርሶ አደሩ ከተለመደው የግብርና ስራ ሊወጣ አይችልም፤ ይህ ደግሞ ለውጥ ማምጣት አያስችልም። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ስራዎች ሲሰሩ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፤ ለዚህም አርሶ አደሩ እንዳይፈናቀል የሚያስችል ተገቢውን የካሳ ስርዓት ዘርግተን እንሰራለን። የዚህ መሰኖ ፕሮጀክት ጥናት ከ75 በመቶ በላይ ተጠናቅቋል። ፕሮጀክቱ በፌዴራል መንግስትና በክልሉ በበጀት የሚደገፍና ከፍተኛ ካፒታል የሚፈልግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመሰረተ ልማት ግንባታ በባህሪው ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይናንስ ይፈልጋልና ከዚህ አኳያ በፋይናንስ በኩል ምን ታቅዷል?
አቶ ዮሴፍ፡- ሁለት እጥረቶች ይከሰታሉ ብለን እናስባለን። አንደኛው ሰፊ ነጻ መሬት አለመኖሩ ነው። ሁለተኛው የካፒታል እጥረት ነው። የጊዳቦ ግድብ ቀሪ ስራዎችን ለመጨረስ ብቻ ከ900ሚሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል፤ ሰከንዳሪና ተሪሸሪ ካናሎችን ለመገንባት።
የመስኖ ስራ የግድብ ግንባታ ሊያስፈልገው ይችላል፤ የካናል ግንባታ አለው። በባህሪው ቢሊየን ብሮችን ይፈልጋል። ስራ ላይ የሚውሉት ግብአቶች አብዛኞቹ የፋብሪካ ውጤቶች ናቸው። ይሄ ከፍተኛ የመነሻ ካፒታል ይፈልጋል። ግንባታዎቹ ጥሩነቱ ከተጠናቀቁ በኋላ ብልሽት ሊያጋጥማቸው የሚችልበት ሁኔታ ዝቅተኛ ነው። ስታንዳርዱ ተጠብቆ በቂ ክትትል ተደርጎለት ከተሰራ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ ይቆያል። አንዴ ከተሰራ ለረጅም ጊዜ መጠቀም ያስችላል። ከፋይናንስ ምንጭ ጋር በተገናኘ ሁለት እድሎች ይኖራሉ። አንደኛ እንደ ሀገር ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ይዘን እቅድ ስናቀርብ ይታያል፤ ዘመኑ ደግሞ እንደ ክልልም ለመስኖ ትኩረት ሰጥቷል። ሁለተኛ ከፌዴራል መንግስት ጋር ከፌዴራል “ኤስዴጂ” ከተባለ ፕሮግራም ጋርም ይሰራል፤ ቅድም የጠቀስኳቸው ከሁለትና ሶስት ፕሮጀክቶች ውጪ ያሉት 26 ፕሮጀክቶች በእዚህ መልኩ የሚሰሩ ናቸው።
ኤሲዲጂ በሚባል ፕሮግራም ከገንዘብ ሚኒስቴር ለሁሉም ክልሎች የሚሰጥ በጀት አለ። በዚህ በጀት ነው ስራዎቹ እየተሰሩ ያሉት። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለአነስተኛ ፕሮጀክቶች ብቻ ከምናውል ብለን መካከለኛ ለሚባሉ ፕሮጀክቶችም አስገብተን የክልሉን አቅም አክለን ለመስራት አቅደን እየሰራን ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚታዩት ጥናታቸው ተጠናቆ ለሚመለከታቸው አካላት ሲቀርቡ ነው። ያኔ የፕሮጀክቶቹ አዋጭነት ሲታመንበት የገንዘብ ምንጩም ይታያል። ሁለተኛ ጥናት ሲያልቅ ለፌዴራል ቆላማ አካባቢና መስኖ ሚኒስቴር እናቀርባለን። እነሱ በክልሎች ፕሮጀክቶችን ስለሚገነቡ ለእዚህም ድጋፍ እንዲደረግልን እንጠይቃለን።
አዲስ ዘመን፡- በጊዳቦ ግድብ በአሁኑ ወቅት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ዮሴፍ ፡- የጊዳቦ ግድብ እስከሚጠናቀቅ እኛ የምናስተዳድረው ዲዛይኑን እና ስትራክቸሩን ነው። ባለሀብቶች እየሰሩ ያሉበት ሁኔታ አለ። የክልሉ መንግስት በአካባቢው እየሰሩ ካሉት ባለሀብቶች ማነው ውጤታማ በሆነ መልኩ እየሰራ ያለው የሚል ጥናት እያካሄደ ነው።
አካባቢው ቀደም ሲል የኢንቨሰትመንት ኮርደር በሚል የተያዘ ነበር። ኢንቨስተሮች በአካባቢው የተሰማሩት በደቡብ ክልል ስር በነበረበት ወቅት ነው። ፕሮጀክቱ እያለቀ ሲመጣ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ይሁኑ ሲባል መንግስት ትኩረት አድርጎ ይህን ችግር በመፍታት ለወጣቶች ለማስተላለፍ አቋም ይዟል። ስለዚህ በዚህ በኩል ብዙ ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም።
አዲስ ዘመን፡- ሲዳማ ክልል ጥሩ ዝናብ አለው፤ ትላልቅ ወንዞችም አሉት ይባላል፤ እነዚህን እምቅ አቅሞች እንዴት ልትሰሩባቸው አስባችኋል፤ ጊዳቦ ላይ ሌላ ግድብ የመስራት ሀሳብ አለ።
አቶ ዮሴፍ፡- ሰፊው የሲዳማ ክፍል በቂ የዝናብ መጠን ያገኛል፤ ዝናቡ ግን ወጣ ገባነት አለበት። በእዚህ የተነሳም የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየቀነሰ ነው። በዝናብ እጥረት የሚቸገሩ አካባቢዎችም አሉ። ይህን ችግር ለመፍታት ውሃ በመያዝ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ ይቻላል ተብሎ እየተሰራ ይገኛል።
ሲዳማ ውስጥ ያሉት ወንዞች አብዛኞቹ ሸለቆ ውስጥ ናቸው። በቀላሉ አውጥተን የምንጠቀማቸው አይደሉም። ከወጡም በኋላ የሚያለሙት ሜዳማ መሬት አያገኙም። እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ውሃ ስትለቅ አካባቢውን አጥቦ ይሄዳል። ስለዚህ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። በመስኖ ስራ ውስጥ የመሬት አቀማመጥ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የመስኖ ልማት ማካሄድ ምን ያህል አዋጭ ነው ብለው ያምናሉ።
አቶ ዮሴፍ፡- እንደሚታወቀው አዋጭ ነው፤ ምን ያህል ተጨማሪ አቅም ይሆናል ለሚለው አንድ አርሶ አደር አንድ ሄክታር ቢኖረው በአመት አንዴ የሚያርስ ከሆነ የሚያለማው አንድ ሄክታር ነው። ተጨማሪ ውሃ አግኝቶ በሚፈለገው ውሃ ማረስ ቢችል በአመት በአንድ ሄክታር ላይ የሁለት ሄክታር ምርት ያመርታል። ሶስቴም ሊያመርት ይችላል። ሶስት ሄክታር ይሆንለታል። ስለዚህ የመስኖ ልማት ለእንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ተብሎ ይወሰዳል። የመስኖ ልማት ለትናንሽ ማሳዎች ትልቅ ፋይዳ አለው። አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን በተደጋጋሚ መጠቀም ያስችላቸዋል።
አዲስ ዘመን ፡- የሀይቅ ውሃንና የጥልቅ ውሃ ጉድጓድን ለመስኖ ማዋል ከጨዋማነት ጋር ተያይዞ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። ክልሉ የሀዋሳ ሀይቅንና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን ለመስኖ ልማት እያዋለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ ችግር እንዳያጋጥም ምን እየተከናወነ ይገኛል? በሀይቁ ውሃስ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ዮሴፍ፡- ከሀዋሳ ሀይቅ ጋር በተገናኘ እየተከናወነ ያለው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ስራ ገና አልተጠናቀቀም። ይህን የሚሰራው ተቋም በመጀመሪያ ከሀይቁ ጋር የውሃ ባላንስ ስራ ይሰራል። ምን ያህል ውሃ ወደ ሀይቁ ይገባል? በፓምፕ ከሀይቅ ወስደን ለማልማት ምን ያህል ውሃ እንወስዳለን? የሚለው ይታያል። የውሃ ባላንስ ሲባል አንዳንዴ የሀይቁ ውሃ በጣም ይሞላል፤ አንዳንዴ ደግሞ ይሸሻል። ሀይቁ ምን ያህል ውሃ ይይዛል፤ ምን ያህል ውሃ ይወጣል የሚለው ይጠናል። በዚህ ላይ በመመስረት የሚሰራ ይሆናል።
ሁለተኛው ከጨዋማነት/ ሳሊኒቲ/ ጋር የሚታዩ ነገሮች አሉ። በተለይ ከጨዋማነት /ሳሊኒቲ/ ጋር በተያያዘ ሀዋሳ ሀይቅ አካባቢ ጥናት እየተካሄደ ነው። ጥናቱ ተሰርቶ በቀጥታ ወደ ቁፋሮም አይገባም፤ የውሃው ኬሚካል ባህሪም ተጠንቶ ይቀርባል። የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ውሃ መኖር አለመኖሩን እንጂ የሚያሳይህ ውሃው ምን አይነት ኬሚካል እንዳለው አያሳይም፤ ውሃው ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ ናሙና ተወስዶ ይመረመራል፤ እንዲህ አይነቱን ችግር በሂደት እናየዋለን።
በሌላ በኩል ደግሞ የሀዋሳ ሀይቅን አርሶ አደሩ ለረጅም ጊዜ ትናንሽ ፓምፓችን በመጠቀም ለመስኖ ሲያውለው ቆይቷል፤ ይህ ማለት ጨዋማነት አላቆመውም። ይህ አንድ የጥናት አካል ነው፤ ሁለተኛ የሼህ መሀመድ አላሙዲ የመስኖ ልማት ጥቁር ውሃ አካባቢ ከሀይቅ ማዶ አለ። ልማቱ በከርሰ ምድር ውሃ ነው የሚካሄደው፤ ከዚህም ናሙና ተውስዷል። በሀዋሳ ዙሪያ ከተቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችም ናሙና ተወስዷል፤ ከእነዚህም የሚያሰጋ ነገር አላገኘንም። ጥናቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ እናየዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ትብብር ስላደረጉልን እናመሰግናለን።
አቶ ዮሴፍ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም