ሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራቷን ተያይዛዋለች። ለእዚህም በእያንዳንዱ የግብርና ወቅት ላይ መሰረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። ዘንድሮም በመኸር እርሻ ስራ ላይ ርብርብ ሲደረግ ቆይቶ አዝመራ በመሰብሰብ ስራው ተጠናቋል። አሁን ደግሞ በበልግ ወቅት የግብርና ስራ ላይ ርብርብ እየተደረገ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የተቀናጀ ስራ የሚካሄድበት ተግባር ሆኗል። በአሁኑ ወቅትም የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አዝመራ እየተሰበሰበ ይገኛል።
የግብርናውን ዘርፍ የሚመራው አካልም አስፈላጊውን ግብዓት፣ ቴክኖሎጂና የመሳሰለውን ማቅረብን ጨምሮ ሥራውንም በመከታተል እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ እንደ ሀገር በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንዲህ ያለው የልማት ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ክትትልና ድጋፍ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። አሁን ወቅቱ የበልግ ነው። ለእዚህ የሚያስፈልገው ዝናብ ተገኝቷል። የግብርናውን ዘርፍ የሚመሩት አካላትም ፊታቸውን ወደ በልግ አብቃይ አካባቢዎች መልሰዋል። የግብርና ሥራው ዝናብን መሠረት ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም የሚጥለውን ዝናብ እንዲሁም የጣለውን ዝናብ ተከትሎ የተፈጠረውን እርጥበት በጊዜው ለመጠቀም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ግድ ይላል። እኛም ከዝግጅት ምእራፍ ጀምሮ በበልግ የግብርና ሥራ ላይ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ቃኝተናል።
እንደ ሀገር በበልግ የግብርና ሥራ ትልቅ ሽፋን ካላቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ የአማራ ክልል ሲሆን፣ በክልሉ በበልግ ከፍተኛውን ሽፋን የሚይዙት አካባቢዎች ደግሞ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ናቸው። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በክልሉ የበልግ ዝናብን በወቅቱ ለመጠቀም እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ሲገልፁ፤ ቀደም ባሉት የበልግ ወቅቶች ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መቆራረጥ ይከሰት እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም በግብርና ሥራው ላይ ተግዳሮት መሆኑን ተከትሎ ተደጋጋሚ ጉዳት የተስተናገደባቸው ጊዜያቶች እንደነበሩ ይናገራሉ።
እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳያጋጥሙ በዚህ የበልግ ወቅት የተገኘውን ዝናብ በወቅቱ በአግባቡ ለመጠቀም የቅድመ ዝግጅት ሥራው የተጠናከረ መሆኑን ይጠቁማሉ። የሚያጋጥመውን የዝናብ መቆራረጥ ችግር ለመፍታት የውሃ አማራጮች የሆኑ እድሎችን ሁሉ ለመጠቀም ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። እንደ አቶ ቃልኪዳን ገለጻ፤ በክልሉ በዚህ የበልግ የግብርና ሥራ በተያዘው ቅድመ እቅድ ወደ 218 ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ይሸፈናል፤ ከዚህም አራት ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብም በእቅዱ ተካትቷል። በእስካሁኑ እንቅስቃሴም ወደ 123ሺ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥም ትልቁን የዘር ሽፋን የያዙት ገብስና ስንዴ ሰብሎች ሲሆኑ፣ 54ሺ ሄክታር መሬት በገብስ፣ 23ሺ ሄክታር መሬት ደግሞ በስንዴ ሰብሎች ተሸፍኗል። ቀሪው መሬት ደግሞ በትንሽ እርጥበት ምርት በሚሰጡ ሰብሎች እንዲሸፈን ይደረጋል። በዚህ የበልግ ወቅት ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞኖች በመሬት ስፋት ሰፋ ያለ ሽፋን አላቸው። በአጠቃላይ በበልግ የግብርና ሥራ የታቀደውን መሬት በዘር ለመሸፈን እንቅስቃሴው ተጠናክሯል።
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የቅድመ ዝግጅት ሥራውና የሚጠበቀው የዝናብ ወቅት የተጣጣመ አይደለም። የዝናብ ስርጭቱም ሁሉንም የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሸፈነ አይደለም። በዚህ ረገድም ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ የተወሰኑ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። ዝናብ የጣለባቸው አካባቢዎችም ቢሆኑ ወደ ዘር ሥራ ከገቡ በኋላ ዝናቡ መቆራረጥ እያሳየ ነው። በቀሪው ጊዜ መሻሻል እንደሚኖር ይጠበቃል። ቀድሞ በጣለው ዝናብ እርጥበት የያዘውን መሬት በማረስ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሰብሎች እንዲዘሩ በማድረግ እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው።
ክልሉ የእስካሁኑን የበልግ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ ገምግሟል። ይህንኑ በተመለከተም አቶ ቃልኪዳን እንዳስረዱት፤ የበልጉ የዝናብ ወቅት ገና በመሆኑ ከዝናብ አኳያ ተስፋ ስላለው የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው አቅጣጫ የተቀመጠው። ከዚህ አንጻርም በጣለው ዝናብ የተያዘውን እርጥበት ጥቅም ላይ በማዋል፣ ዝናቡ ሲጥል ደግሞ ፈጥኖ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆን ከአርሶ አደሩም ሆነ ልማቱን በተለያየ መንገድ ከሚደግፉ አካላት የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው። ከግብዓት ጋር በተያያዘም በተለይም አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እንዲጠቀም እየተበረታታ ነው። ጎን ለጎንም ማዳበሪያ፣ የተሻሻለ ምርጥ ዘርና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው።
ባለፉት ጥቂት የምርት ወቅቶች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የግብርና ስራዎች ተስተጓጉለው እንደነበር ይታወሳል። አሁን ሰላም በመስፈኑ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆነው የግብርና ልማቱ በተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች ላይ የተለየ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ስለመሆኑ አቶ ቃልኪዳን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች ሁሉ ልማቱ ይከናወናል። በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበረው ሰሜን ጎንደር አካባቢ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ዝናብ ባለመጣሉ በቀጣይ በሚጠበቀው ዝናብ ልማቱን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል›› ብለዋል።
በዚህ የበልግ ወቅት የግብርና ሜካናይዜሽን ከመጠቀም አኳያ ስላለው እንቅስቃሴም በተመለከተ በመኸሩም ሆነ በበልጉ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ባላቸው አካባቢዎች መሬቱን ለማረስ ትራክተር የመጠቀም ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል። ከዚህ የበልግ ወቅት ጎን ለጎን እየተከናወነ ባለው የበጋ መስኖ ልማት የደረሰው ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም የስንዴ ልማቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል። በአጠቃላይ በመስኖ ልማቱ የተሻለ ውጤት መኖሩን ጠቁመዋል። ለሁለተኛ የመስኖ ልማት ዝግጁ የሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ሌላው በልግ አብቃይ የሆነው የደቡብ ክልልም በተመሳሳይ ወቅታዊ ከሆነው የበልግ የግብርና እንቅስቃሴን በተመለከተ ግምገማ አካሂዷል። የግምገማውን የትኩረት አቅጣጫና እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ያነጋገርናቸው የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊን አቶ አድማሱ አወቀ እንዳሉት፤ የግምገማው አንዱ አላማ ንቅናቄ መፍጠር ነው። ንቅናቄ መፍጠር ያስፈለገው ባለፉት የበልግ ወቅቶች በከፍተኛ ሁኔታ አጋጥሞ በነበረው የዝናብ መቆራረጥ በበልጉ ብቻ ሳይሆን በመኸሩም ጊዜ በሰብል ልማቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ስለነበር ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ የሚፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ጥቅም ላይ በማዋል ያለፈውን ለማካካስ በንቅናቄ እንዲሰራም ነው።
ውጤታማ የሆነ አፈጻጸም ለማስመዝገብም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል ላይ ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም የሚስተዋሉ የምርታማነት ማነቆዎችን ለመፍታት፣ በነዚህ አቅጣጫዎች ላይ ቀድሞ ተነጋግሮ ወደ ሥራ በመግባት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጭምር ነው የግምገማ መድረኩ የተካሄደው ሲሉም ያብራራሉ። የበልግ ዝናብ መቆራረጥም ሆነ የመብዛት ሁኔታ ስለሚያጋጥም ይህንን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ዝግጅት መደረጉን ይገልጻሉ።
የልማቱ ሥራ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ እንዲከናወን፣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አድማሱ፤ የግብርና ሥራው ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ እንዲሆን ለማስቻል በማሳ ውስጥ የዝናብ ውሃ ለመያዝ እንዲቻል እንዲሁም እርጥበት ለማቆየት የሚያስችል የተለያየ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ግብረ ኃይሉ መዋቀሩን አስረድተዋል። የሚያጋጥመውን የውሃ ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ውሃ ሲኖር ውሃውን ወደ ውጭ የማስወጣት ሥራዎችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በሂደት ያጋጥማሉ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይም መድረኩ እንደተነጋገሩበት ገልጸዋል።
የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም አቶ አድማሱ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ባለፉት ጊዜያቶች አጋጥሞ የነበረው የዝናብ እጥረት በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይም የራሱን ተጽእኖ ያሳደረ በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለውን ችግርና በተለያየ ምክንያት ሊነሳ የሚችል ወረርሽኝንም ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ዝግጅት ተደርጓል። በተለይም የምርጥ ዘር አቅርቦቱን ከአርሶ አደሩም በመፈለግ ጭምር ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ይደረጋል። የአፈር ማዳበሪያ እስከ ሰባት መቶ ሺ ኩንታል ያስፈልጋል። ግብዓቱ ወደ ክልሉ እየገባ ሲሆን፣ እስካሁንም ከሶስት መቶ ሺ ኩንታል በላይ ገብቷል። በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ከወዲሁ ለመግለጽ ባይቻልም እጥረት ይኖራል የሚል ስጋት ግን አለ።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፤ በበልግ የግብርና ሥራ አንድ ሚሊዮን 44ሺ 888 ሄክታር መሬት ለማረስ የታቀደ ሲሆን፣ መሬቱንም እንሰትን ጨምሮ ወደ 13 በሚሆኑ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን ታቅዷል። ከነዚህ ውስጥም በስፋት የሚጠበቁት የሰብል ምርቶች በቆሎ እና ማሽላ ሲሆኑ፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ይከናወናል። በአጠቃላይ ከሚለማው መሬት ወደ 102ሚሊዮን 489ሺ 692 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። እቅዱን ለማሳካት ከንቅናቄ ሥራ ጀምሮ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ወደ ተጠናከረ ሥራ አልተገባም።
የዝናብ ስርጭቱ አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ የሚባል እንደሆነም ጠቅሰው፣ ክልሉ ሁሉም አካባቢ በልግ አብቃይ እንደሆነ፣ ለልማቱም ዝግጁ እንደሆኑና አርሶ አደሩን በተለያየ መልኩ የሚያግዙ ባለሙያዎችም ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከግብዓት አቅርቦት ዝግጅት አኳያም ለ2015/2016 የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደብ ላይ ከደረሰው አጠቃላይ ማዳበሪያ ውስጥ 90 በመቶው ማዕከላዊ መጋዘን መድረሱን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ሰሞኑን መግለጻቸው ይታወሳል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ መንግሥት ለማዳበሪያ ግዥ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል። ድጎማው አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ሲሆን፣ በአማካይ በእያንዳንዱ የማዳበሪያ ኩንታል ዋጋ ላይ የ1 ሺህ 566 ብር ድጎማ ይሸፍናል።
ምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተም 370 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ከፌደራል ተቋማት እና የምርጥ ዘር አባዢዎችን በማቀናጀት ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል። ጉድለቶቹን ለመሙላት የክልል ምርጥ ዘር አባዢዎችን እንጠቀማለን ሲሉም ተናግረዋል። የግብርና ግብዓትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ባለፉት ጥቂት አመታት በኮቪድ- 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የግብርና ግብዓት ተደራሽነት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር በመፍታት የምርጥ ዘርና የግብርና ግብዓቶቹን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በዚህ የበልግ ወቅት ለመሸፈን በእቅድ ስለተያዘው መሬትና ስለሚጠበቀው የምርት መጠን ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀውን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበልግ ለመሸፈን ታቅዷል። ከዚህም ወደ አራት ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። እስካሁን በተከናወነው የግብርና ሥራም ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሬት ታርሷል። በበልግ የግብርና ወቅት በስፋት የሚለሙት በቆሎ፣ ማሽላና ስንዴ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከሚሸፈነው መሬት አብዛኛው አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ማሳ መሆን ተናግረዋል። ቀሪው ላይ የሚከናወነው ደግሞ ለሀገራዊ ምርት ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም