ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ልጆች ዛሬ ስራን ሳይንቅ ሰርቶ ራሱን የሚያስተምረውን ታዳጊ ላስተዋውቃችሁ ወደድኩ።
ጀልቀባ አበራ ይባላል፤ በአምቦ ከተማ የሚኖር የ14 ዓመት ታዳጊ ሲሆን የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ለምን ስራ ሰርቼ ራስን አልደግፍም የሚል ሃሳብ ወደ አዕምሮው ይመጣል። ከዚያም በአካባቢው ከሚኖር ሌላ ታዳጊ የመፋቂያ እንጨት ስራ እንዴት እንደሚሰራ ለተወሰኑ ቀናት ልምድ ለመውሰድ አብሮ እየሰራ ከተማረ በኋላ ራሱን ችሎ መስራት እንደሚችል እርግጠኛ ሲሆን ስራውን ያለጓደኛው እርዳታ ብቻውን መስራት ጀመረ። ስራውን በደንብ ከለመደ በኋላ ገቢ ማግኘት ሲጀምር ሃያ ጫጩት ዶሮዎች ገዝቶ ማርባት ጀመረ፤ አሁን ላይ የገዛቸው ዶሮዎች አድገው ትልልቅ ሆነውለታል።
ይህ ታዳጊ በአምቦ ከተማ ውስጥ የጥርስ መፋቂያ በመሸጥ ለራሱ ስራ ፈጥሮ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ በመሸፈን ቤተሰቦቹ ያለባቸውን የኑሮ ጫና ለማገዝ የሚሞክር ታታሪ ታዳጊ ነው። የሚሸጠውን የጥርስ መፋቂያ እንጨት ጉደር ከምትባል ቦታ በመሄድ ካመጣ በኋላ ቆራርጦ በማስተካከል ለገበያ ያቀርባል። ልጆች ጉደር ከአምቦ ከተማ ራቅ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነው። ታዲያ ጀልቀባ የመፋቂያ እንጨቱን ለማምጣት ከአምቦ ጀምሮ ጉደር ድረስ የሚሄደው በእግር ጉዞ ነው።
እንጨቱን ይዞ ሲመለስም የሚጓዘው በእግሩ ነው። የመፋቂያ እንጨቱን ጉደር ድረስ ሄዶ ካመጣ በኋላ በሚያማምር ቅርፅ ቆራርጦ በማዘጋጀት ለገበያ ዝግጁ ያደርጋቸዋል። ከዚያ በኋላ ትምህርት የሚማሩት በፈረቃ በመሆኑ ትምህርት ቤት የሚሄደው ጠዋት ከሆነ ሲመለስ ከሰዓት በኋላ የሰራቸውን የጥርስ መፋቂያዎች ይዞ ወደሚሸጥበት ቦታ ይሄዳል። ትምህርት ቤት የሚሄደው ከሰዓት በኋላ ከሆነ ደግሞ ጠዋት ስራውን ሲሰራ ይቆይና ሰዓቱ ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል።
ጀልቀባ ይህንን ስራ የጀመረው በሀምሳ ብር ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በቀን ከሰማንያ እስከ መቶ ብር ያገኛል። ቤተሰቦቹ ሰባት ልጆችን ስለሚያሳድጉ ጀልቀባን በሚፈልገው መጠን ለመደገፍና የሚፈልገውን አሟልተው ለማሳደግ አቅም የላቸውም፤ በመሆኑም ሰርቶ በሚያገኘውን ብር ሳሙና የትምህት ቤት ዩኒፎርምና የተለያዩ ልብሶችና የሚያስፈለጉትን ይገዛል። ደብተር፣ እስክሪብቶና እርሳስም ቢሆን የሚገዛው እራሱ ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ ነው። ልጆችዬ ጀልቀባ ታታሪነቱ በስራ ብቻ እንዳይመስላችሁ በትምህርቱም ቢሆን ጎበዝ ተማሪ ነው።
የሚሰራው ስራ ከትምህርቱ ጋር እንዳይጋጭበት የስራና የትምህርት ሰዓቱን ከፋፍሎ ይጠቀማል፤ ትምህርት ባለበት ሰዓት ወደ ትምህር ቤት ይሄዳል ከትምህርት ቤት ሲመለስ ደግሞ ስራውን ይሰራል። ማጥናት ባለበት ሰዓትም ትምህርቱን በአግባቡ ያነባል። ወደፊት በትምህርቱ ጠንክሮ ጥሩ ውጤት በማምጣትና ጎበዝ ሰራተኛ በመሆን በጉደር እና በአምቦ ከተማ ላይ የራሱን ትልልቅ ህንፃዎች ገንብቶ ስራውን እየሰራ መኖር ይፈልጋል። ይህንን ለማሳካትም ካሁኑ የስራ ባህሉን እያሳደገና በርትቶ እየተማረ ይገኛል።
ልጆች ጠንክሮ መስራት የራስን ችግር ከማሸነፍና የስራ ባህልን ከማዳበር ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች ላይ ክብርና ሞገስን እንደሚያጎናፅፉ ታውቃላችሁ አይደል? ታዳጊ ጀልቀባም ለስራ የሰጠው ክብር እና ስራን ሳይንቅ ዝቅ ብሎ በመስራቱ ክብር ተሰጥቶታል። ባሳየው የስራ ትጋትና ማንንም ሳያስቸግር የራሱን ስራ ፈጥሮ በመስራቱ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት መድረክ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እጅ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተቀብሏል።
ታዳጊ ጀልቀባ ልጆች መስራት አለባቸው ስራ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፤ ስለዚህ ልጆች አቅማቸው የሚችለውን በመስራት እና ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ ከልጅነታቸው ጀምሮ የስራን ባህል ማዳበር አለባቸው በማለት መልዕክቱን ያስተላልፋል። ልጆች እናንተም የስራ ባህልን ከልጅነታችሁ ጀምሮ ማዳበርና ስራን መስራት ልትለማመዱ ይገባል። ነገር ግን የግድ ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ መስራት አለብኝ ብላችሁ ቤተሰቦቻችሁን ማስቸገር የለባችሁም ቤት ውስጥ ቤተሰቦቻችሁን በማገዝም ስራን መለማመድ ትችላላችሁ። ለዛሬ በዚሁ ላብቃ ሳምንት በሌላ ፅሁፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2015