የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንታት ታሪኮችን እያስታወስን ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ደጃዝማች ዑመር ሰመተርን አይተናል፡፡ የዚህ ሳምንት ክስተቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጦር አዋቂነት፣ በአስተዳዳሪነት፣ በዲፕሎማትነትና በታሪክ ፀሐፊነት፣ በአትሌትነት እና በብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝነት የሚታወቁ የተለያዩ ሰዎች ናቸው፡፡
ከ77 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓ.ም በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› እየተባለ በሚጠራው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበረው የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኙ ዋለልኝ መኮንን ተወለደ፡፡
ከ51 ዓመታት በፊት በዚሁ ሳምንት መጋቢት 12 ቀን በአትሌትነት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝነት ጭምር የምትታወቀውና የምክትል ኮሚሽነርነት ማዕረግ የተሰጣት አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተወለደች፡፡
በዚሁ ሳምንት የነበረ ሌላ የመወለድ ዜና እንጨምር፡፡ ከ124 ዓመታት በፊት መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም መምህር፣ የሕግ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ጸሐፊ፣ ፖለቲከኛ፣ የሐይማኖት ሊቅ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ የነበሩት ሁለገቡ ባለሙያ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ተወለዱ፡፡
ራስ መኮንን እና ራስ ዳርጌ ደግሞ በዚህ ሳምንት ያረፉ ናቸው፡፡ የሁለታቸውን ታሪክ ዘርዘር አድርገን እናያለን፡፡ ከራስ መኮንን እንጀምር፡፡
የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው፡፡ እኚህ ሰው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ናቸው፡፡ ራስ መኮንን ወልደሚካኤል በዚህ ሳምንት ይታወሳሉ፡፡ ያረፉት ከ117 ዓመታት በፊት መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ነው፡፡
ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም በሸዋ ግዛተ አፄ፣ ጎላ ወረዳ፣ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው፡፡ ገና በወጣትነታቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ጋር ተዋውቀው ቤተሰባዊና ዝምድናቸውን አጸኑ፡፡
በፀባያቸው ታጋሽና አስተዋይ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ልዑል ራስ መኮንን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመሆን እንደ አባትና ልጅ ይተያዩ ጀመር፡፡ የሐረርጌን ግዛት በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ አገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ሆኑ፡፡ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለሆነው የ‹‹ራስ›› ማዕረግም በቁ፡፡
ልዑል ራስ መኮንን የአጼ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ አገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለአጼ ምኒልክም አሳውቀዋል።
የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሰራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ እንደሚያደርጓቸውም ይወራ ነበር፡፡
ነገር ግን አጼ ምኒልክ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ሞታቸው በንጉሰ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (አዲስ አበባ) በተሰማ ጊዜም ከፍተኛ ሀዘን ሆነ፡፡ ንጉሥ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አምርረው አለቀሱ፡፡ በወቅቱም ይህንን የተመለከቱ ሰዎች እንዲህ ብለው ገጠሙ …
‹‹ዋ አጤ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ፣
በየበሩ ቋሚ ከላካይ ሞተብዎ፡፡
ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ፣
ምን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ፡፡
ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው፣
እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው፡፡››
ከአልቃሾቹ መካከል አንደኛው ደግሞ የልዑል ራስ መኮንንን ደግነት ለማስታወስ እንዲህ ብሎ ሙሾ አወረደ …
«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፣
መኮንን አይደለም ድሀ ነው የሞተው፡፡»
ተብሎላቸዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2015