ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርሶች ባለቤትና መገኛ ናት። ስልጣኔን፣ ዘመናትን የተሻገሩ የአገረ መንግስት ግንባታን፣ ባህልን፣ ታሪክንና የህንፃ ግንባታ ጥበብን እንዲሁም አገር በቀል እውቀትን የያዙ የመስህብ ሃብቶች መገኛ አገር ነች። እነዚህ ሃብቶች ከትውልድ ትውልድ ተሻግረው የቀደምት ኢትዮጵያውያንን ታላቅነትና የዚያን ዘመን የኢትዮጵያን የገዘፈ ማንነት ሊመሰክሩ ህያው ሆነው ይገኛሉ።
ከአገር አልፈው የዓለም አቀፍ ቅርስ የሆኑት እነዚህ በርካታ የመስህብ ሃብቶች የያኔው ዘመን ምስክር ከመሆን ባለፈ በዛሬው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻችን ላይ ጉልህ አስተዋፆኦ እያበረከቱ ናቸው። በተለይ ትውልድን በሚዳሰስና በሚጨበጥ ማስረጃ ለማስተማር፣ ለአገር ገፅታ ግንባታና ለቱሪስት መስህብነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ካላቸው ፋይዳ እኩል ግን ጥበቃና ከለላ እንደማያገኙ የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች አሉ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ካላቸው የላቀ ፋይዳ አንፃር በልኩ ትኩረት ሊሰጣቸው፣ ሊጠበቁ፣ አስፈላጊው እድሳት ሊደረግላቸውና ተገማች ከሆኑ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ጉዳቶች አስፈላጊውን ከለላ ሊያገኙ ይገባል። ከዚህ አኳያ በአገራችን የሚገኙ መካነ ቅርሶችም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚያመላክት ግልፅ የሆነ የጥናትና ምርምር ውጤት ከአንድ ቋት ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ እስከ ውስንነታቸው በጥቂቱም ቢሆን አመላካች ማስረጃዎች በየጊዜው ይወጣሉ።
ከዚህ ውስጥ በአማራ ክልል በጎንደር አካባቢ የሚገኙ መካነ ቅርሶች የሚገኙበት አሁናዊ ሁኔታን የሚያሳየው መረጃ ይገኝበታል። የዝግጅት ክፍላችንም ጥቅል የኢትዮጵያ መካነ ቅርሶች ወቅታዊ ሁኔታ ባያሳይም የተወሰኑ የእይታ መንሸዋረሮችን እንደሚያስተካክል በማመን የሚከተለውን ዳሰሳ ይዞላችሁ ቀርቧል።
በጎንደር ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ለባለድርሻ አካላትና ለቅርስ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቅርቡ ተሰጥቷል። በወቅቱም በአካባቢው የሚገኙ መካነ ቅርሶች ለሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚጋለጡባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው ተጠቁሟል። አስፈላጊው የጥንቃቄ ጥበቃ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አየለ አናውጤ ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ። ከትውልድ ትውልድ ተላልፈው እዚህኛው ትውልድ ላይ የደረሱት እነዚህ መተኪያ የሌላቸው ቅርሶች ከአራት ምእተ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ እንደ መሆናቸው በቆዩበት ዘመን ለተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችም የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ መሆኑን ዶክተር አየለ ይገልጻሉ። መካነ ቅርሶቹ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጣቸውንም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን የመጠገን ልምድ አናሳ መሆኑ፣ ቅርሶች የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው ለመታደግ እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚደረው ጥረትም እንዲሁ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ በመጠቆም፤ መንስኤዎችና መፍትሄዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፣ በአገሪቱ የሚገኙ እነዚህ በዓይነትና በብዛት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች የኢትዮጵያውያን ማንነት መገለጫ ህያው ምስክር መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ መተኪያ የሌላቸው፣ ከዘመን ወደ ዘመን ተሸጋግረው እዚህኛው ትውልድ ላይ የደረሱና ኢትዮጵያን ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር ያስተዋወቁ ቅርሶች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የተለያዩ አደጋዎች ተጋርጦባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በፌዴራል፣ በክልል፣ በወረዳ፣ በቅርሱ ባለቤቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ በግሉ ዘርፍ ውስጥ በተሰማሩ የቅርስ አስተዳደር አማካሪ ኮሚቴ እንዲሁም ቅርሶቹ በሚገኙባቸው አካባቢ የሚኖሩ ባለድርሻ አካላት በመካነ ቅርሱ ነባራዊ ሁኔታ ጥበቃ፣ ልማትና አስተዳደር ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ቅርሶቹን ከአደጋ መታደግ እንደሚያስፈልግ ሁለቱም የመንግስት አመራሮች አፅእኖት የሰጡበት ጉዳይ ነው።
የጎንደር መካነ ቅርሶች አሁናዊ ገፅታ
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የመካነ ቅርስ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሃይ እሸቴ ፋሲል ግቢ በጎንደር ዘመነ መንግስት የተሰሩትን አብያተ መንግስታትን የያዘ መካነ ቅርስ እንደሆነ ይናገራሉ። ቅርሱ እ.ኤ.አ ከጥቅምት 22 እስከ 26 ቀን 1979 በተካሄደው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ከስድስቱ የመምረጫ መስፈርቶች መካከል ሁለቱን በማሟላት ሶስተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን ያስረዳሉ። ቅርሱ በጎንደር ከተማ እና ከጎንደር ከተማ ውጪ የሚገኙ ዘጠኝ መካነ ቅርሶችን የያዘ መሆኑን ይገልፃሉ።
ዓለም አቀፍ ቅርሱ በህግ የተከለለ ጥብቅ (Core Zone) እና አዋሳኝ (Buffer Zone) ዞን፣ የረዥምና የአጭር ጊዜ የአስተዳደር ዕቅድ ሰነድና የቅርሱን የዕለት ከዕለት ክትትል የሚያደርግ የአስተዳደር መዋቅር እንዲሁም የስጋት አስተዳደር ሰነድ ያለው መሆኑን የሚገልፁት ዳይሬክተሯ ፣ ይህም በሚከተሉት የአገሪቱ መንግስት ህጎች የተደገፉ መሆናቸውን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በፀደቁ የዓለም አቀፍ ቅርሱ ጥበቃ አስተዳደር የህግ ማዕቀፎች (የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት እና 209/1992 አዋጅ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት 1995 በአንቀጽ 9 (4) “በኢትዮጵያ የፀደቁ ሁሉም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ ዋና አካል ናቸው” የሚለውን ጨምሮ አንቀጽ 41 (9) “መንግስት የአገሪቱን ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች የመጠበቅ እና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት” የሚሉትን እንደ ማስረጃ ያጣቅሳሉ።
አንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ እነዚህ ማእቀፎች ቢኖሩም አሁን ላይ መካነ ቅርሶቹን ለጉዳት የሚዳርግ ስጋት ተደቅኖባቸዋል። ዋናው የስጋት ምንጭም ከሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ የሚመነጭ እንደሆነ ይገልፃሉ። ሰው ሰራሽ ስጋቶች የሚመነጩት ከልማት ጫና፣ ከእርሻ ጋር በተያያዘ፣ ከአየር ብክለት፣ ከደካማ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ጠንካራ እና ተግባር ላይ የሚውል የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ችግር መሆናቸውንም ያብራራሉ።
ከልማት ጫና ጋር ተያይዞ በዋናነት የተስተዋሉት በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ምክንያት የሚፈጠር ንዝረት እና መሰነጣጠቅ፣ ቅርሱን እየተጋፋ የመጣው የከተማ መስፋፋት፣ ከእርሻ ጋር ተያይዞ ቅርሶች በሚገኙበት አካባቢ ተጠግቶ ማረስ እና የግጦሽ መሬት መስፋፋት (ሱሲንዮስ እና ጉዛራ)፣ የአየር ብክለትና በቅርሶች ላይ በየጊዜው የሚጨመሩ አዳዲስ ግንባታዎች ተገቢ ያልሆኑ እድሳቶች ናቸው። ከአስተዳደር ክፍተት ጋር ተያይዞ ከተወሰኑት መካነ ቅርሶች በስተቀር አብዛኞቹ ጥገና እና ክትትል የማይደረግላቸው ሲሆን ይህም የሚሆነው በቅንጅታዊ አሠራር ክፍተት መኖር፣ በአመዛኙ በግንዛቤ ውስንነት በሚመነጭ ቸልተኝነት ነው።
“ከተፈጥሮ ስጋቶች የተያያዙት ከዕድሜ ብዛት ከሚከሰት ብልሽት፣ መበስበስ እና መፈራረስ ናቸው” የሚሉት ወይዘሮ ፀሃይ፤ ከተፈጥሮ ስጋቶች ጋር ተያይዞ የንፋስ መሸርሸር፣ ከማይክሮ- ኦርጋኒዝም መበስበስ ጋር በተያያዘ፣ የግብረ-ህንጻዎች በድንገት መውደቅ፣ የዕጽዋት መብቀል እና በወቅቱ ያለመወገድ የሚጠቀሱ እንደሆኑ ያስረዳሉ።
ጎንደር- የቅርስ ዘላቂ ልማት
“ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ የቀደመው ትውልድ አሻራ እና የአሁኑ ትውልድ ህልውና የሆኑት ቅርሶች የቀደመውን ዕውቀት በመረዳት ለዘመኑ ችግር የመፍትሔ ምንጭ ናቸው” የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በፍጥነት እያደገ የመጣው ዘመናዊነት እና ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ለውጥ ምክንያት ቅርሶች ከአካባቢያቸው ተለይተው የሚኖሩ ስላልሆኑ ለሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
በመሆኑም የቅርሱን እሴት እና ከቅርሱ ወሰን ውጪ ያለውን አቅራቢያ ቦታ ከቅርሱ ጋር በማይጋጭ ሁኔታ በማልማት ቅርሶችን ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ በማዋል የአካባቢውን ህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል የቅርስ አስተዳደር ሥርዓቱ ዓላማ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
መካነ ቅርሶችን የሚጎዱት ነገሮች በአብዛኛው የሚነሱት ከቅርሱ ወሰን ውጪ በመሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን ታሳቢ በማድረግ የቅርሱን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሱት ወይዘሮ ፀሃይ፤ የቅርስ ቦታዎች የሚገኙት በህብረተሰብ መካከል በመሆኑ የቅርሶች ዘላቂ ደህንነት የሚረጋገጠው የአካባቢው ህዝብ በሚኖረው ተሳትፎና ተጠቃሚነት ልክ እንደሆነ ይገልፃሉ። በመሆኑም ስለቅርሶች እሴት እና ፋይዳ በቂ ግንዛቤ ያለው ህብረተሰብ በቅርሶች ጥበቃ እና ልማት ላይ ጉልህ ሚና አለው ይላሉ። በተቃራኒው ስለቅርሶች ፋይዳ በቂ ግንዛቤ የሌለው ህብረተሰብ ቅርሶችን ከመጠበቅ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይናገራሉ። ስለሆነም የአካባቢ ህብረተሰብ በሚኖረው የቅርስ ግንዛቤ ልክ ለቅርሱ ዘላቂ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ቀጣይነት ያለው ትምህርትና ስልጠና ያስፈልጋል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ማህበረሰብ – አቀፍ ቱሪዝም ለቅርስ ጥበቃ
የመካነ ቅርስ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሃይ፤ የቅርስ ልማት የአብዛኛውን የህብረተሰብ ፍላጎትን እና ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ እንዲሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ። ማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም በቅርሱ አካባቢ የሚኖሩ እና የቅርሱን እሴቶች የራሳቸው የማንነት መገለጫ እና ኩራት እንደሆነ የሚያምኑ እና የቅርሱን አስተዳደር እና ጥበቃ ዓላማ እና ግብ በሚጋሩ የአካባቢ ህብረተሰብ ተሳትፎ የሚመራ የቱሪዝም ዘርፍ እንደሆነ ያመላክታሉ። ይህንን ተግባራዊ ማድረግም ውጤታማ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
የቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊነት
ዳይሬክተሯ በመጨረሻ ባነሱት ሃሳብ “በአገራችን እያደገ የመጣው የልማት እና የከተሜነት ፍላጎት በቅርሶች አካባቢ የሚካሄድ የልማት ስራ እንዲጨምር አድርጓል” በማለት እነዚህን የልማት ስራዎች ከቅርሶች ደህንነት ጋር በማጣጣም ለአገሪቱ የተሟላ እድገትና ቀጣይ ልማት የሚኖራቸውን ሚና ማሳደግ ተገቢ እንደሚሆን ይጠቁማሉ። በቅርሶች አካባቢ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች በተለያዩ አካላት ባለቤትነት የሚከናወኑት በመሆኑ ለቅርሶች ደህንነት ስጋት ስለሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ። በመሆኑም ስለቅርሶች ጉዳይ በህግ ኃላፊነት የተሰጠው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በቅርሶች አካባቢ የሚካሄዱትን የልማት ስራዎች ከሚመሩት አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ዘለቄታዊ ልማትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው በዚያ አግባብ እንደሚከናወን ገልፀዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2015