ለበርካታ ዓመታት በውሃና መስኖ ላይ ሰርተዋል። ታላቁ የአባይ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ለስኬታማነቱ በሙያቸው ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በመጀመሪያ ስራ የተቀጠሩት የኢትዮጵያ ሸለቆዎች ልማት ጥናት ባለስልጣን በሚባል ተቋም ውስጥ ነው። ይህ መስሪያ ቤትና የውሃ ሀብት ባለስልጣን በመባል የሚታወቀው መስሪያ ቤት ወደ ውሃ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሲያድግ ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በባለሙያነት፣ በቡድን መሪነት፣ በፕሮጀክት አስተባባሪነት እንዲሁም በመምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል።
ሁለት የተለያዩ ዳይሬክተሮችን በተለያየ ጊዜ በምክትል ዳይሬክተርነት መርተዋል። በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ስር ካሉ ሶስት ተቋማት አንዱ የሆነውን የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጣናዊ ጽህፈት ቤቱን በስራ አስኪያጅነት ለሰባት ዓመት አገልግለዋል። በአባይ ግድቡ ላይ በተደራዳሪነት ለተወሰነ ዓመት የሰሩ ሲሆን፣ በብዙ የትብብር መድረኮች ደግሞ አትዮጵያን ወክለው በቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴነት የሚጠበቅባቸውን ተውጥተዋል – የዛሬው የዘመን እንግዳችን የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው አቶ ፈቂ አሕመድ ነጋሽ።
አቶ ፈቂአሕመድ፣ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ዙሪያ ሰበታ አካባቢ ዳለቲ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ነው። አካባቢዋ ከመሃል አዲስ አበባ 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዚያው በዳለቲ ቀበሌ ነው። ሁለተኛ ደረጃን የተማሩት ደግሞ ሰበታ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአለማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በእንግሊዝ አገር በክራንፊልድ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት እየሰሩ ያሉት በግል በውሃ ሀብት አስተዳዳር ላይ የማማከር ስራ ነው። ከዚሁ ከውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ከካበተ ልምዳቸው ልንጋራ እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ ያለው ዓለም አቀፍ ህግና መርህ ምን ይመስላል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– በዓለማችን በጣም በርካታ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። ቁጥራቸው ምንም እንኳን ተለዋዋጭ ቢሆንም ከ280 በላይ ይሆናሉ። የወንዞቹ ቁጥር ተለዋዋጭ የሚሆንበት ምክንያትም አዳዲስ አገሮች ሲፈጠሩ ቁጥሩ ከፍ ይላል፤ አገራቱ ሲቀነሱ ደግሞ ቁጥሩ ዝቅ ስለሚል ነው። የዓለማችን 60 በመቶ የመሬት ስፋት፣ የዓለማችን 50 በመቶ የውሃ ሀብትና 40 በመቶ ያህሉ የዓለማችን ሕዝብ የሚኖረው በእነዚህ በወሰን ተሻጋሪ ወንዝ ነው።
እነዚህን ውሃዎች ለማስተዳደር ዓለምአቀፍ የውሃ ሕግ ተብሎ ዓለም በሙሉ የተማመነበት ሕግ የለም፤ ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግስታት እኤአ በ1997 ያወጣው የዓለም አቀፍ የውሃ ድንጋጌ አለ። ይህ የውሃ ድንጋጌ በአሁኑ ጊዜ የዓለም አቀፍ የዘልማድ የውሃ ሕግ ተብሎ የሚወሰደው ነው።
እዛ ላይ ድንበር ተሻጋሪ ውሃን ለመጠቀም ዋና ተብለው የተነሱትና መሟላት ያለባቸው ነጥቦች ሶስት ናቸው። አንደኛው መሰረታዊ የተባለው ነጥብ ትብብር ነው። በተፋሰሶቹ ውስጥ የሚገኙ አገራት ቀናነት በተሞላበት መልኩ ውሃውን አጠቃቀም ላይ መተባበር አለባቸው የሚለው ነው። ሁለተኛው በወሰን ተሻጋሪው ወንዝ ውስጥ የሚገኙ አገራት በሙሉ ውሃውን ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆኑ መልኩ መጠቀም ይችላሉ የሚል ነው። ሶስተኛው መሰረታዊ ጉዳይ በአጠቃላይ በአጠቃቀም ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚል ነው። እነዚህን መርሆዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም አገራት የሚጠቀምባቸው መሰረታዊ መርሆዎች ተብለው የሚታወቁ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ህግና መርህ አኳያ ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የያዘችው አቋም በመርህ ደረጃ እንዴት ይታያል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– የአባይ ውሃ ብለን በምንወስድበት ጊዜ የባሮ አኮቦን፣ የተከዜን እና የመረብን ተፋሰሶች ውሃ ያጠቃልላል፤ አባይ ሲባል ናይል ወይም ጥቁር አባይን ብዙውን ጊዜ ስለምንቀላቅል ነው። ኢትዮጵያ ይህን ውሃ ለመጠቀም በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ማዕቀፍ የምትጠቀመው ፖሊሲ አላት። ይኸውም የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ በሚል የሚታወቅ ነው። ይህ ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት እየተከለሰ ነው። ነገር ግን እኤአ በ1999 የወጣ የኢትዮጵያ የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ አለ። ይህ ፖሊሲ የድንበር ተሻጋሪ ውሃን በተመለከተ የራሱ የሆነ ማዕቀፍ አለው። በዛ ማዕቀፍ ውስጥ ዋና ዋና አንኳር የተባሉት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ከተጋሪ አገራት ጋር መተባበር፣ ወንዞቹን ምክንያታዊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም፣ ዓለም አቀፍ የውሃ ሕጎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ የገባችበት ዓለም አቀፍ ሕጎችን ማክበርን የመሳሰሉ በጣም አንኳር የሆኑ ሕጎች ስላሉ ኢትዮጵያ በፖሊሲ ደረጃ የምትከተለው አካሄድ ወይም አቅጣጫ ከዓለም አቀፍ ውሃ ሕግ ጋር የተያያዘ ነው።
በተግባር ደረጃ በምናይበት ወቅት በሁሉም ተፋሰሶች ውስጥ አሊያም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውስጥ ኢትዮጵያ ከተጋሪ አገራት ጋር በተለያየ መልኩ ትብብር እያደረገች ነው። ለምሳሌ የናይልን ብንወስድ የናይል የትብብር መድረክ አለ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በትብብሩ ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው። ስለዚህ ትብብሩ ውስጥ አለችበት። በሌላ በኩል ደግሞ ሕጋዊ ማዕቀፉ ላይ በተደረገው እንቅስቃሴ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ላይ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፤ ተደራድራለች፤ ፈርማለች፤ ብሎም አጽድቃለች። ከዚህ በላይም ፋናወጊ ነበረች። ሌላ ደግሞ የውሃ ሀብት አጠቃቀሟን በተመለከተ በተቻለ መጠን ከአገራቱ ጋር ተነጋግራ ጥቅም ላይ የምታውልበት ሁኔታ አለ። ይሁንና ከአንዳንድ አገራት ጋር ጉዳዩን ማከናወን አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ባመነችበት ይህ አጠቃቀሜ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ነው፤ በሌሎች ላይ ጉዳት አያደርስም ብላ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጋ ነው እየተንቀሳቀሰች ያለችው። በዛ መልኩ ብዙም ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ የሆነ ነገር እያደረግን አይደለም የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን እውነታ በአባይ ተፋሰስ አገራት ተግባራዊ ለማድረግ የተዳረጉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ? እያጋጠማቸው ያለው ተግዳሮትስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ከአሁን በፊት በጣም በርካታ የትብብር ተግባራት ተደርገው ነበር። በተለይ እኤአ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ሶስት የትብብር ስራዎች ተሰርተዋል። እነዚህ የትብብር ስራዎች ግን በግብጽ እና ሱዳን የተመሩ እንዲሁም በአጋሮቻቸው የታገዙ ናቸው። በተለይም በአብዛኛው በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያላተኮሩ፤ የተፋሰሱን አገራት አቅጣጫ ለማንሳት ወይም ለማደናገር የተዘጋጁ ትብብሮች ስለነበሩ ኢትዮጵያ በዛ ላይ የተሳታፈችው በታዛቢነት ብቻ ነው። ታዛቢ መሆን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም መረጃ ይገኛል። የራስንም አቋም የማሳያ መድረክ ስለሚሆን ጠቃሚ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ የተሳተፈችው በታዛቢነት ብቻ ነው።
እኤአ 1990ዎቹ መጨረሻዎቹ ላይ ግን ኢትዮጵያ እዛው ታዛቢ ሆና ከተወሰኑ የላይኛው ተፋሰስ አገራትና በተለይ ከዓለምአቀፍ የልማት ድርጅት ማለትም ከተባበሩት መንግስታት አንዱ ተቋም ጋር በመሆን ባደረገችው ጥረት የናይል ትብብር መድረክ እንዲቋቋም አድርጋለች። መድረኩ እስካሁን በስራ ላይ ነው። መድረኩ ከመቋቋሙ በፊት ግን በተለይ 1997 የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ድርድር እንዲጀመር ያደረገችው ኢትዮጵያ ወትውታ ነው። ስለዚህ በናይል ውስጥ በትብብርም ሆነ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ በመፍጠሩ ደረጃ ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሆና ኢትዮጵያ በጣም በርካታ ስራ ሰርታለች። እስካሁንም እየመራች ነው ያለችው።
እነዚህ ሁለቱ በተለይ የትብብር ስራውም ሆነ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፉ በተለይ ዓለማአቀፍ ሕግ ተፋሰስ ውስጥ በማስፈን የውሃ አጠቃቀሙ በሕግና በስርዓት እንዲመራ እንክብካቤውም፣ ልማቱም፣ ጥበቃውም ሁሉም ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ እንዲመራ የሚያደርጉ ስለሆኑ ብዙ ስራዎች በተፋሰሱ አገራት ተሰርተዋል። ብዙዎቹም ይህንን ስምምነት ተቀብለውታል። ከ11ዱ ውስጥ ወደስድስት አገራትም ፈርመውታል። አራቱ ደግሞ አጽድቀውታል። ሶስት አገራት ደግሞ የማጽደቅ ሒደት ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳ የዘገየ ቢመስልም ጥሩ አቅጣጫ ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በግብጽ በኩል በአባይ ወንዝ ውሃ ፍትሀዊ አጠቃቀም እንዳይኖር የሚደረገው ያልተገባ አካሄድ በዚህ ዘመን ምን ያህል አዋጭ ነው?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– ግብጽ በተፋሰሱ ውስጥ የምትከተለው የራሷ የሆነ ፖሊሲ አላት። አብዛኛው ፖሊሲዋ ራሷን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግና ሌሎችንም የተፋሰሱ አገራት በተለይ ውሃ አመንጪዎችን አግላይ የሆነ አቅጣጫ ነው እየተከተለች ያለችው። ከእነዚህ ስራዎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሌሎቹን ያላከተተ ስምምነት ማካሄድ
ነው። እኤአ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት ስምምነቶች የቅኝ ግዛትና የድረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች ናቸው። ዛሬም የቅኝ ግዛት በጠፋበት ዘመን ግብጾች በዚህ ስምምነት ላይ ለመንጠልጠል ይሞክራሉ። ራሳቸው መንጠልጠል ብቻ ሳይሆን ስምምነቱን በሌሎችም ላይ ለመጫን ሙከራ ያደርጋሉ። ይህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተረሳውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ይዞ መጓዝ በየትኛውም መመዘኛ የሚያዋጣ አይደለም።
ሌላው እነሱ የሚፈልጉት የላይኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ በጣም ድሃ፣ ደካማ እና ተጋላጭ ሆና እንድትቀጥል ነው። ለዚህም በርካታ የራሳቸው ስልቶች አሏቸው። እንዲያም ቢሆን በተለይ ዓለም እንደ አንድ መንደር በሆነበት ብሎም በሳይንስና በቴክኖሎጂ በረቀቀበት ዘመን እንዲህ አይነት ኋላቀር አስተሳሰብ ይዞ አንድን አገር ለመጉዳትና ለማፍረስ የሚደረጉ ጥረቶች በምንም መልኩ ተቀባይነት የላቸውም።
በተፋሰሱ ውስጥ ያለ የውሃ ሀብት የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሀብት ነው። ይህ በግልጽ መታወቅ መቻል አለበት። ሁሉም አገር ባለው ሀብት ላይ ሉዓላዊ መብት አለው። ውሃን በተመለከተ ግን ይህ ሉዓላዊ መብት ውስንነት አለው። ለምሳሌ እኛ የላይኛው ተፋሰስ አገር ነን። ውሃው የሚነሳው በአብዛኛው ከእኛ አገር ነው። እኛ በዚህ ውሃ አጠቃቀም ላይ ሉዓላዊ መብት አለን። ይህ ሉዓላዊ መብታችን ግን ውስንነት አለው። ምክንያቱም ውሃውን ሙሉ በሙሉ እንጠቀም ካልን ውሃው ለብዙ ሚሊዮን ዓመታት ወደታችኛው ተፋሰስ አገራት እየሄደ በዛ ውሃ ላይ ሕይወት መመስረት ተችሏል። በዚሁ እድገቱም ስልጣኔውም ስለተመሰረተ ያንን ማጥፋት እንዳይሆን ያንን ሳያጠፋ እኛ የምንጠቀምበት ሁኔታ ነው መፈጠር ያለበት።
ግብጾቹም ቢሆኑ ማሰብ ያለባቸው በዛ መልኩ ነው። ውሃ የሚሄደው ከዚህ ከኢትዮጵያ ነው፤ እዚህም ሕይወት አለ፤ ልማትና እድገትም አለ። ተስፋና ፍላጎትም እንዲሁ አለ። በዚህ መልኩ መተሳሰብ ካለ አብሮ መጠቀም ይቻላል። ካልሆነ ግን እኛ ብቻ እንጠቀም የሚባል ከሆነ ተጎጂ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። ምክንያቱም ውሃ የሚሄደው ከዚህ ነው። የላይኛው ተፋሰስ አገራት ትክክል ናቸው፤ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ለታችኛዎቹ ተፋሰስ አገራት ያስባሉ፤ ይጨነቃሉም። ይህ ሁኔታ ግን ከላይኛዎቹ ተፋሰስ አገራት እየተጠበቀ አይደለም።
ሁሌም የታችኛዎቹ ተፋሰስ አገራት የላይኛዎቹ ተፋሰስ አገራት ትንሽ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚያዩት በፍራቻና በጥርጣሬ እንዲሁም በተቃርኖ ነው። ይህ አይነቱ አተያይ የሚቀረፍበት ሁኔታ ነው መመቻቸት ያለበት። ይህ ካልሆነ ግን በአሁኑ ያውም በ21ኛ ክፍለ ዘመን ይሄ አስተሳሰብ ኋላቀር በመሆኑ መተው አለበት ። መጠላትም ያለበትና በፍጹም የማያዋጣ መንገድ ስለሆነ በተቻለ መጠን ያንን በመተው ወደ ትብብር የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በተለይም ከድርቅ ጋር በተያያዘ ፈታኝ የሆነ አገራዊ ችግር እየታየ ነው፤ ይህን በዘለቄታ ለመፍታት የውሃ ሀብታችንን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ይጠቀሳል፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው፤ ለዘመናት ዜጎቻችን ሲያልቁ፣ ሲጎዱና ሕይወት ሲጠፋ እንዲሁም በኑሮ ሲጎሳቆሉና ሲፈናቀሉ እናያለን። ይሄ ሁኔታ ሲከሰት መደገም የለበትም በሚል በጣም ብዙ ጥናቶች ወዲያው ተከናውነው ዝግጅቶችም ተደርጓል፤ ነገር ግን ወደተግባር ልንቀይራቸው አልቻልንም።
አሁንም ምናልባት ከ1966 ዓ.ም ልናፍርበት ከተገባው የረሃብ ክስተት በኋላ ይህ ሲከሰት እንዲሁ እያስተዋልን ነውና በዓለም አቀፍ ፊት ቆሞ እህልም ሆነ እርዳታ መለመን እንደ አገር በእውነቱ በጣም ሞራል የሚነካ ጉዳይ ነው። ሁሌም ይህን ነገር እንቀርፋለን፤ እናቆመዋለን ብለን ከመፎከር በዘለለ ጉዳዩ ልክ ሲያልቅ እንረሳና የምንሄደው ወደሌሎች ተግባራት ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ጉዳይ ማንሳት እፈልጋለሁ። የዛሬ አስር ዓመት ገደማ የተፋሰሱ አገራት ባለሙያዎችን ግቤ አንድ፣ ሁለት እና ሶስትን ለማስጎብኘት ይዣቸው እሄድ ነበር። ወሩ ነሐሴ ነበር። ወደስፍራው የሄድነው በመኪና ነው። አቅጣጫችንም ወደጅማ መስመር ነበርና ሶኮሩ አካባቢ ግቤ አንድ የሚባለው ቦታ እስክንደርስ ድረስ ዝናብ ይዘንባል። ውሃ በከፍተኛ ሁኔታ የሚተኛበት አካባቢ አለ። ሜዳው በሙሉ በውሃ ተጥለቅልቋል። ልክ እዛ ስንደርስ አብረን ስንጓዝ የነበሩት ከመኪና ወረዱና እኔንም ጠርተውኝ ‹‹ለምን ግን?›› የሚል ጥያቄ ነው የሰነዘሩት። ሌላ ምንም አላሉም። ‹‹ለምን ግን?›› የሚለውን ጥያቄ የሰነዘሩልኝ ምክንያት ምን እንደሆነ ገባኝ። እሱ ማለት ይህ ሁሉ ውሃ እና መሬት እያለ ለምንድ ነው የምትራቡት ማለታቸው ነው። በቃ የእኛ ስህተት ነው፤ የፖሊሲ አውጪዎች ስህተት ነው። ሕዝባችንን ለዚህ ያጋለጥነው እኛ ነን ነው ያልኩት። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይ እያንዳንዱ የመማር እድል ያገኘ ኢትዮጵያዊ ይህን ነገር የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። በሕዝቡ ግብር ነው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እየተማረ ያለው፤ የዘነጋውም እሱን ነው።
የተራቡ ሰዎች በረሃብ እንዳያልቁ እያንዳንዱ ተጠያቂነቱን ማወቅ መቻል አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ ማወቅ ያለበት እሱን ነው። ሁለተኛ ደረጃ ረጅም ጊዜ እቅድ ማውጣት ብሎም ያንን እቅድ መተግበር ነው። እያንዳንዱ ተፋሰስ ላይ የረጅም ዓመት እቅድ አለ። ያ እቅድ ተቀምጦ አቧራ እየጠጣ ነው። ለምሳሌ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በየተፋሰሱ እቅድ አለው። እነዚህ ድርቅ የገባባቸው ቦታዎች በሙሉ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ተቀምጧል። ያንን የመተግበር ጉዳይ ነው። ስለዚህ የፖሊሲ ችግር የለብንም። የስትራቴጂም ሆነ የእቅድም ችግር የለብንም። ችግሩ ያለው ግን አመለካከት ላይና አስተሳሰብ ላይ ነው። በዛ በኩል አንድ ቀን ገብቶን ዜጎቻችንን እናድናለን የሚል አመለካከት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የውሃ ሀብታችንን ለመጠቀም በምናደርገው ጥረት በግብጽ በኩል ተግዳሮቶች እያጋጠሙን ከመሆናችን በተጨማሪ ተግዳሮቶቹ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ቀን ከለሌት እየሰራችም ነው፤ ይህ በአገራቱ መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሀዊ አሰራር እንዳይሰፍን እያደረገ አይደለም ይላሉ?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– ወደኋላ መለስ ልበልና ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የምንጠቀመው ግብርና ዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው። በአሁኑ ጊዜ የዝናብ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም። ከከባቢ የአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ መጠኑ በጣም ቀንሷል። ስርጭቱም በጊዜም ሆነ በቦታ በጣም ተዛብቷል። ስለዚህ በዝናብ ላይ የተመሰረተ እርሻ በአብዛኛው አስተማማኝ አይደለም፤ አዋጭም አይደለም። በተቻለ መጠን ውሃችንን አከማችተን ልንቆጣጠረው በምንችለው የግብርና ዘዴ ላይ ማተኮር አለብን። እሱም የመስኖ ልማት ነው። በጣም ትልልቅና ሰፋፊ መስኖዎች መገንባት አለባቸው። እነዚህ መስኖዎች በዓመት ሁለቴ ወይም ሶስቴ ማምረት የሚያስችሉ ናቸው። የሚመረተው በዝናብ ከሆነ በዓመት አንዴ ነው። እሱም ደግሞ ዝናብ ሊዘንብም ላይዘንብም የሚችልበት አጋጣሚ አለና አስተማማኝ አይደለም። በዝናብ በሔክታር የምናገኘውን ምርት መስኖ ብናለማ እስከ ሶስትና አራት እጥፍ ማሳደግ ይቻላል። ከዚህ ጎን ለጎን የሚያድገው የምርት ጥራትም ነው። የሚፈለገውንም አይነት ምርት ማምረት እንችላለን። ይሄ አንድ አቅጣጫ ነው መሆን ያለበት።
ከትልልቅ መስኖ ባለፈ ደግሞ ውሃ በተለይ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ እያከማቸ የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ መፍጠር መቻል አለብን። ይህ ሲደረግ በዘመቻ መሆን የለበትም። ከአሁን በፊት በዘመቻ ተጀምሮ ጉዳይ ውድቅ ሲሆን ታይቷል። እዚህ አገር ላይ ዘመቻ በየጊዜው ይካሄዳል። የሚሰሩ የዘመቻ ስራዎች ግን ውድቅ ሲሆኑ ተስተውሏል።
ከዚህ ቀደም የውሃ ማቆር ተብሎ ዘመቻ ተካሄደ፤ ያ ፕሮግራም ግን ወድቋል። ስለዚህ በተጠና ሁኔታ ለእያንዳንዱ አካባቢ የተዘጋጀ ቴክኖሎጂ ተሰርቶና ተግባራዊ ተደርጎ አርሶ አደሩ ቤቱና ማሳው አካባቢ ውሃ አጠራቅሞ የሚያመርትበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በተለይ ደግሞ እነዚህ ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች በቂ ዝናብ ስለማይኖራቸው የከርሰ ምድር ውሃ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ካልሆነም ደግሞ ውሃ ካለበት ወደሌለበት ከተፋሰስ ወደተፋሰስ የማሻገር ስርዓት ማካሄድ ነው። ያንን ተግባራዊ እያደረጉ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል።
እንግዲህ ግብጾች በጣም በርካታ ስልት አላቸው። በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ውሃ አጠቃቀሟ ዓለማአቀፋዊ ይዘት እንዲኖርም የሚያደርጉት ጥረት አለ። ውሃው የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሀብት ነው። የሚመከረውም የተፋሰሱ አገራት ተቀምጠው በግልጽነትና ቀናነት በተሞላበት ሁኔታ ውሃውን በጋራ መጠቀም ነው። አንደኛው የሌላኛውን ስጋት፣ ፍርሃት ብሎም ፍላጎት ከተረዳ አብሮ መጠቀም ይቻላል። ውሃው ደግሞ በጣም በቂ ነው። ስለዚህ በጋራ ከተጠቀምን የጋራ ተጠቃሚ እንሆናለን። በጋራ ካልተጠቀምን ግን ሁላችንም እናጣለን።
ሶስተኛ አካል ማስገባት አግባብ አይደለም። ሶስተኛው አካል የእኛን ፍላጎት አይጋራም፤ የእኛን ፍርሃትም አይጋራም። ሶስተኛ አገራትን እዚህ ውስጥ መክተት የማይደገፍ ተግባር ነው። ግብጾች እያደረጉት ያለው ሩጫ በፍጹም የማይደገፍ ነው። ጫና ሊያመጣ ይችል ይሆናል፤ ግን ውጤት አያመጣም።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ግብጽ የአባይ ግድብን ጉዳይ በአረብ ሊግ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ጥሪ አቅርባ አጸድቃለች፤ ይህ ከአህጉሪቱ አልፎ የሄደ በመሆኑ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አይሆንም?
አቶ ፈቂአሕመድ፡- የአረብ ሊግ የተቋቋመበት የራሱ የሆነ ዓላማ ይዞ ነው። በአረብ አገራት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጫና እከላከላለሁ ነው የሚለው። ነገር ግን የአረብ አገራት በሌሎች ላይ የሚያደርሱት ጫና ካለ የእሱ ጉዳይ አይሆንም። ስለዚህ በጣም በጠባብነት ላይ የተመሰረተ ተቋም ነው። ለምሳሌ የአረብ የውሃ ምክር ቤት ተቋም የሚባል አለ። ይህ ምክር ቤት የአረብ ውሃ የሚላቸው ወንዞች አሉ። እነዚህ ወንዞች ለምሳሌ ጤግሮስና ኤፍራጥስ ቱርክ ውስጥ የሚገኙ የአረብ ውሃ ናቸው ይላል። እስራኤል ያለችበት የዮሮዳኖስን ውሃ የአረብ ነው ይላል። ኢትዮጵያ ያለችበትን የመረብን፣ የአባይን፣ የተከዜን፣ የባሮ አኮቦን ውሃ የአረብ ነው ይላል።
ለዚህ በምክንያትነት የሚያስቀምጠው ግብጽና ሱዳን የአረብ ሊግ አባል ስለሆኑ ነው በማለት ነው። ከዚያ ያልፍና ዋቤ ሸበሌን እና ገናሌ ዳዋን የአረብ ውሃ ነው ይላል። እንዴት ሲባል ደግሞ ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል ስለሆነች ነው የሚል አመክንዮ ይሰጣል። የአረብ ሊግ አገራት በቂ ውሃ ስለሌላቸው እነዚህን ውሃ የትኛውም አካል እንዳይነካው ይላል። ይህ አባባሉ ተቀባይነት የሌለው፣ ኋላቀር የሆነና ኢሰብዓዊም ጭምር ነው። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚያራምድ ተቋም ስለሆነ አግባብነት የሌለው ነው ባይ ነኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ እጁን መክተቱ ምንም የሚያመጣው ጥቅም የለም፤ ይልቁንም የሚያመጣው ጉዳት ነው። የመጀመሪያው ነገር ጉዳዩ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የአረብ ሊግ አባል አይደለችም። ስለዚህ ምንም የሚፈጥሩት ነገር አይኖርም።
በሌላ በኩል ግን የተቋሙ በዚህ ጉዳይ እጁን መክተት በሶስቱ አገራት ውስጥ ያለውን መተማመን፣ መተሳሰብና መተጋገዝ ያሻክራል እንጂ አንዳች የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ከዚህ ውጭ ተቋሙ እርባና አለው ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- የአባይ ግድብ ዘንድሮ 12ኛው ዓመቱን መያዙ ይታወቃል፤ አንዳንዶች ረጅም ጊዜ ወሰደ ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ በጥሩ ሁኔታ እየተጠናቀቀ ነው ይላሉ፤ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– ይህን ጉዳይ በሁለት መልኩ መውሰድ ይቻላል፤ ግድቡ ሲጀመር በሰባት ዓመት ማለትም በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በ2010 ዓ.ም ያልቃል ነበር የተባለው። ከዛ ባለፈ ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ እንደ አባይ አይነቱ ውስብስብ ግድቦች ተጀምረው በወቅቱ የመጠናቀቅ እድላቸው አነስተኛ ነው። ምክንያቱም በባህሪያቸው ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው። እንኳን የሀብትና የቴክኖሎጂ ችግር እያለብን ቀርቶ እንደዚህ አይነት ግድብ ሲገነባ በዓለምአቀፍ ደረጃም የሚያሳየው ተሞክሮ ፈጥኖ አለማለቁ ነው። እንደእነዚህ አይነት ፕሮጀክቶች ከ40 እስከ 60 በመቶ ያህል በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠናቀቁ አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከ40 እስከ 60 በመቶ በገንዘብ ደረጃ ተጨማሪ ክፍያን የሚጠይቁ ናቸው ይባላል። ስለዚህ ይህ የአባይ ግድብ በ10 እና በ11 ዓመት ውስጥ ቢያልቅ በጣም ትክክል ነው ማለት ይቻላል። ከዛ አኳያ ሲታይ አንድ ዓመት ዘግይቷል። በአጠቃላይ በተወሰነ ደረጃ ዘግይቷል ብሎ መውሰዱ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአባይ ግድብ በእስካሁኑ ጉዞው በግብጽም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተጋፈጣቸው የመጣው ተግዳሮት ይታወቃል፤ ይህ ተግዳሮት የታለፈበትን አካሄድ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ፈቂአሕመድ፡– ግድቡ የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጦለት እንደሚገነባ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ከግብጽና ከሱዳን በተለይ ከግብጽ ከፍተኛ ጫና ነበረው። ይህንን ጫና ለመቋቋም ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ አካሄድ ነበራት። ያንን ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ የጀመረችው ግልጽነት በማስፈኑ ላይ ነው። እነሱንም ባላቸው ባለሙያዎች ደረጃም ሆነ በሚኒስትርም ደረጃ ለማሳተፍ ሞክራለች። በመሪዎች ደረጃም በጣም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ፕሮጀክቱን ሄደውም እንዲጎበኙት ተደርጓል። ብዙም ተመክሯል፤ ተዘክሯልም። ነገር ግን አልተቻለም። ጊዜ በሔደ ቁጥር ግብጾች ሲሞክሩ የቆዩት በራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጫና ለመፍጠር ነው።
በመጀመሪያ የዓለም ባንክን ለማስገባት ሞከሩ። ኢትዮጵያ በዚህም በዚያም ብላ ለማስቀረት ሞከረች። በኋላ ላይ ደግሞ የዓለም ባንክንና የአሜሪካ መንግስትን ለማስገባት ጥረት አደረጉ። የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት እንዲገቡ በተደረገው ጥረት ላይ የእኛ ኢትዮጵያውያንም እጅ አለበት። በኋላ ላይ በማስወጣቱ በኩልም ያየነው ትልቅ አበሳ ነው። በቀላሉ እንዳስገባናቸው በቀላሉ ሊወጡ አልቻሉም። እንደምንም ግን የእነርሱ ጫና እንዲቀንስ ተደርጎ ጉዳዩ ወደአፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ ተደረገ። ግብጾችም በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት የላቸውም። የአፍሪካ ሕብረትና የናይል ቤዚን የትብብር መድረክ የሚባለው በጥቁር አገሮች የሚመራ ህብረት ስለሆነ ለአረባዊቷ አገር ግብጽ ፍትሃዊ አይሆንም የሚል እምነት አላቸውና ሊያምኑት አልቻሉም፤ አሁንም መልሰው ወደተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ወስደው የነበረ ቢሆንም ወደ አፍሪካ ህብረት መልሷቸዋል። የአረብ ሊግ ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ሁሌም መግለጫ ያወጣል።
ዋናው ነገር እኛ በዚህ ዙሪያ አገራዊ አንድነትን መፍጠር፣ ለሰላምና አንድነት መትጋት አለብን። እንደ ድርቅና ረሃብ ያሉ ነገሮች በአገራችን እንዳይከሰቱ የምንወድ ከሆነ ለአገራዊ አንድነት በመትጋት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ላይ መስራት ይጠበቅብናል። ግብጾች በየጊዜው መግለጫ በማውጣት ሊያስፈራሩን የሚሞክሩት እኛ አንድነታችንን ያጣን በመሰላቸውና በተቸገርን ጊዜ ነው። በተለይ መረጋጋት ያጣን በመሰላቸው ጊዜ መጮህ ይጀምራሉና መሰራት ያለበት ሰላማችንም ላይ ነው ብዬ አምናለሁ። ያንን ማድረግ ከቻልን የእነርሱንም ጫና ሆነ የሌላውንም ጩኸት ጭምር ያለምንም ጥርጥር ማዳከም እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ፈቂአሕመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015