ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከምትታወቅባቸው መልካም ማንነቶች መካከል በርካታ አማኝና ለእምነቱ ተገዢ የሆነ ህዝብ ያላት መሆንዋ ነው። እነዚህ ቤተ-እምነቶች ዘመናት ያስቆጠረ የግዙፍ ታሪክና እሴት ባለቤቶች ከመሆናቸውም ባሻገር አንዱ የእምነት ተከታይ የሌላውን እምነት አክብሮ በጋራ አገርን በማቆም ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑም ተጠቃሽ ነው።
ህዝቡ በፍቅር፤ በመከባበርና በመተሳሰብ እንዲኖር በማድረግ ረገድ የእነዚህ ተቋማት ሚና የላቀ ነው። በተለይም ቅዱስ መፅሓፍትን መሰረት ያደረጉ አስተምህሮችና መመሪያዎች ህዝብን በመልካም ስነ-ምግባር በማነፅ ረገድ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው። ከእነዚህም መካከል አፅዋማትና በወቅቱ በአማኙ የሚተገበሩት ሃይማታዊ ተግባራት ዋነኞቹ ናቸው።
በዛሬው አገርኛ አምዳችንም ዳሰሳ የሚያደርገው በትናንትናው እለት ህዝበ ሙስሊሙ አንድ ብሎ የጀመረውን 1ሺ444ኛውን የረመዳን ፆም ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ በአማኞቹ መከናወን በሚገባቸው ሃይማኖታዊ ተግባራት ዙሪያ ነው። ለዚህም ማብራሪያ እንዲሰጡን የሃይማኖት መምህር የሆኑትን ኡስታዝ አቡበከር አህመድን አነጋግረናቸዋል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የረመዳን ጾም ከሌላው አፅዋማት የሚለይባቸውና ዋና ዋና ሃይማኖታዊ መርሆቹ ምን ምን እንደሆኑ ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ኡስታዝ አቡበከር፡- በቅድሚያ ለሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺ 444ኛው ዓመት የረመዳን ጾም በሰላም አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ወደ ጥያቄሽ ስመለስ እንግዲህ ረመዳን በእስልምና ዘመን አቆጣጠር 12 ወራቶች ውስጥ አንደኛውና በቅዱስ ቁርዓን ጾም ግዴታ የተደረገበት ወር ነው። አላህ በቅዱስ ቁርዓን ላይ ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች ላይ የፆም ግዴታ እንደሆነ በእናንተም ላይ የረመዳን ፆም መፆም ግዴታ ሆነባችሁ›› ይላል። ከእስልምና መሰረታዊ መመሪያዎች ተብለው ከሚጠሩት አንዱ የረመዳንን ፆም መፆም ዋነኛው ሲሆን ማንኛው አቅም ያለው፤ ጤነኛ የሆነ ሰው፤ እድሜው የደረሰ መፆም ይገደዳል። ይህም ጎህ ከቀደደችበት ጊዜ ጀምሮ ፀሃይ እስከምትጠልቅ ድረስ የሚፈጸም የፆም ተግባር ነው። በአጠቃላይ የእምነቱ መሰረት ስለሆነ ፆም ግዴታ ነው።
የረመዳን ፆም ትልቁ አላማው የፈጣሪን ትዕዛዝ መፈፀም ነው። ፈጣሪን መፍራትና ለፈጣሪ ያለንን ታማኝነት ከምናረጋግጥባቸው መሰረታዊ አምልኮተ-ስርዓቶች አንዱና ዋናው መፆም ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ፆም ከምግብና ከመጠጥ መከልከል ብቻ ሳይሆን የትኛውም ጾመኛ መላ አካሉ ከሃጥያትና ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ መጠበቅ አለበት። ሰው ምግብ ሲከለከል በመራብ ውስጥ የሚያሳልፉ የሌሎችን ህይወት ለማስታወስ ይገደዳል። በሁለተኛ ደረጃ ለፈጣሪ ያለው ታማኝነትና ታዛዥነት በ11 ወራቶች ውስጥ የተበላሹ የአመጋገብ ስርዓትና የአኗኗር ዘይቤን ጭምር የሚስተካከል ነው። ነብያችን መሀመድ በሃዲሳቸው ‹‹ጾሙ ጤነኛ ትሆናላችሁ›› ይላሉ። ይህም አንድ ሰው ጤነኛ ለመሆን መፆም እንዳለበት ያስገነዝባል።
እናም ፆም ለፈጣሪ ያለን ታዛዥነት ውስጣችን ታማኝነት፣ ርህራሄና ይቅርባይነት የምናሳይበት ነው። በተለይ በሳለፍናቸው 11 ወራት ውስጥ በንግግራችንና በተግባራችን የተገለፁ ጥፋቶች፤ ከፈጣሪ ያፈነገጡ ተግባራት፣ የእምቢተኝነት ባህሪያት፣ በሰው ላይ ያለፍናቸው ድንበሮችና በአጠቃላይ ፆም የተበላሹብንን ነገሮች ለማስተካከልና ራሳችንን በትክክለኛ መንገድ ለማነፅና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚረዳ መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ነው።
አስቀድሜ እንደገለፅኩት መራብና መጠማት ባለፈ እንደአማኝ የሚጠበቅብን ነገር አለ። ነብያችንም በሃዲስ ላይ በግልፅ ይናገራሉ። ‹‹አላህ ከእናንተ መራብና መጠማት ጉዳይ የለውም›› ይላሉ። ሰው ምግብ ስለተከለከለ ብቻ ፆመ አይባልም። ፆመ የሚባለው በአካልም፤ በመንፈስም ከመጥፎ ነገሮች ሲቆጠብ በተቃራኒው መልካም ነገሮችን በመስራት ሲበረታና ሲያዘወትር ነው። ከዚያ ባሻገር ረመዳን የእዝነት ወር ነው። ይህም ማለት እርስበርስ የመተዛዘን፤ የመረዳዳት፤ የመደጋገፍ ወር ነው።
ነብያችን ‹‹የገሃነምን እሳት ተጠበቋት፤ በከፋይ ቴምር እንኳን›› ይላሉ። ይህም ሲባል ክፋይ ቴምር ለሰጪውም አይጎዳ፤ ለተቀባዩም አይጠቅምም፤ ግን የስጦታን ትልቅነት ነው የሚያሳየን። ትንሽ ነገር ቢኖረን እንኳን ለሎች መኖር መለማመድ አለብን። ለሌች ተስፋ መሆንና መደገፍ ይጠበቅብናል። አንዲት ጉንጭ ውሃ እንኳን ብትሆን በመስጠት፤ በማስፈጠር ከገሃነም እሳት ራሳችንን እንድንጠብቅ ነብያችን ያስተምራሉ። ይህ ወር ከመተጋገዝ፤ ከመረዳዳት ባሻገር አላህ ጋር ለመቀራረብ በጎ ተግባራትና መልካም ስራዎች የሚበረክቱበት ነው። በዚህ ጊዜ የሚሰሩ ተግባራት በ11 ወራት ከሚሰሩት ሁሉ በፈጣሪ ዘንድ እጥፍ ድርብ ዋጋ ያላቸው ናቸው። በረመዳን ውስጥ የተሰራ አንድ መልካም ስራ በሌላ ጊዜ ከሚሰራው የ70 ግዜ እጥፍ ነው በፈጣሪ ዘንድ ያለው ዋጋውና ምንዳው።
አዲስ ዘመን፡-ከሃይማኖታዊ ግዴታው ባለፈ መረዳዳትና መደጋገፍ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደመሆኑ በዚህ ወቅት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ኡስታዝ አቡበከር፡- እንግዲህ የአብሮነት፤ የመተጋገዝ ባህል የኢትዮጵያውያኖች አንድ መገለጫ ነው። ረመዳን ወርም ሙስሊሙ ህብረተሰብ የእምነቱ ግዴታ የሆነውን ዘካውን (አስራቱን) የሚያወጣበት ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም አቅም ያለው ሰው ዘካ ይሰጣል፤ ወይም ደግሞ ሰደቃ ያወጣል። ይህንን ተግባር በረመዳን ወቅት መስጠት ይጠበቃል። በነገራችን ላይ ዘካ ሲሰጥ ዋና አላማው በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የህዝብን ችግር ለመፍታት ነው። ይህም ሲባል በምፅዋት ደረጃ ዝም ብሎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰዎችን እያቋቋሙ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ሰዎች ከችግርና ከተረጂነት የሚወጡበትን ስርዓት ለማበጀት ዘካ በአግባቡ እንዲሰጥ ነው እስልምና የሚያዘው። ዘካ ድህነትን ለመከላከል እስልምና እንደመፍትሔ ካቀረባቸው መከላከያ መንገዶች አንዱ ነው።
የማንኛውም ሰው ያለው ገንዘብ የአላህ ገንዘብ ነው፤ ምክንያቱም ፈቅዶ የሰጠው እሱ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ካለን ሃብት 2ነጥብ5 በመቶ የሚሆነውን ለተቸገሩ እንድንሰጥ ያዘናል። ይህም ደግሞ ለትክክለኛው ዓላማ መዋል ስላለበት ተበታትኖ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ ለባለቤቶቹ ደርሶ ሰዎች እንዲለወጡበትና ከተረጂነት ወደ ረጂነት እንዲሸጋገሩ፤ ስራ ላይ ውጤታማ የሚሆኑበትን የማቋቋም ስራ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም አሁን በአገራችን ላይ ከተከሰተው ድርቅ፣ ረሃብ፣ መፈናቀል፣ መሳደድ በበዛበት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሰደቃ ማውጣት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚጠበቅ ነው። እነዚህ ወገኖች ትናንት ሰጪ የነበሩ ዛሬ ግን ለማኝ ሆነው ሰው ደጅ ላይ እንዲቆሙ ተገደዋል። እነዚህ ወገኖች የእኛ ወንድምና እህቶች በመሆናቸው ለእነሱ አለኝታ መከታ መሆን የበለጠ ልንረዳቸው፤ ልንደርስላቸው ይገባል።
ይህንን ማድረጋችን ደግሞ በአላህ ዘንድ የበለጠ ምንዳው ከፍ ያለ ነው። ነብያችንም በዚህ ወቅት የምስኪኖችን በር እንድንቆረቁር (እንድናኳኳ) ያዙናል። በረመዳን ወቅት ስንፆም የረሃብን ልክ የምናውቀው በመሆኑ በተፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የተቸገሩትን ሰዎች መደገፍ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ቅዱስ መፅሓፍት መታዘዝንና መደጋገፍን እንደግዴታ ቢያስቀምጡም በአሁኑ ወቅት ከመደጋገፍ ይልቅ መለያየት ነው የተበራከተው። በተለይ በእምነት ተቋማት መካከልና በውስጣቸው የሚታዩት መለያየቶች እንደአገርም የሰላም እጦት ምንጭ ሆነው ይታያሉ። የዚህ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ኡስታዝ አቡበከር፡– እንግዲህ እነዚህ መርሆዎች ፈጣሪ ለአማኞች የሰጠው ሰዎች በመልካም ስነ-ምግባር ለማነፅና ወደእሱ ፍቃድ እንዲጠጉ ለማድረግ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ የፆም ዋናው አላማው የተበላሹ ማንነቶቻችንና መስተጋብሮችን መግራት ነው። ሰዎች አካላቸው ሲደክም መልካም ማሰብ፤ ጥሩ ነገርን መፈለግ ውስጥ ይገባሉ። በመሰረቱ ሰው ሲጠግብ እኮ ነው ብዙ መጥፎ ነገሮችን ማሰብ የሚጀምረው። መድከም፤ መራብና መጠማት የበለጠ ለፈጣሪ ቅርብ እንድንሆን ያደርጋል። በሁለተኛ ደረጃ እንደአገር እየኖርንበት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የፈጣሪያችን መመሪያዎች ግልፅና የማያሻሙ ናቸው። እስልምና ፍቅርንና ሰላምን ይሰብካል፤ የኢስላም መገለጫም ሰላም ነው። የሌላውን እምነት እንዲያከብር የእምነቱ ግዴታ ነው ግን ደግሞ በእምነት ማስገደድ አይፈቀድም። ሰዎች እኔን ካልመሰልክ ተብሎ ሊገደዱ አይገባም። ሁሉም ሰው የፈለገውን የማመን መብት የተሰጠው ከፈጣሪ ነው። ታዲያ ፈጣሪ ለእኛ ምርጫውን ሰጥቶን እያለ እኛ በሌላው ምርጫ ውስጥ ልንገባ አንችልም።
እኔ የማስተምረው ነገር ስለፍቅርና ሰላም ነው፤ ከዚያ ባለፈ ግን የእኔን እምነት ካልተከተለ ብቻ የእኔ ተቃራኒ ነው፤ የእኔ ጠላት ነው ብዬ እንዳስብ ግን አልታዘዝኩም። በተለይ በእስልምና አስተምህሮቶች ውስጥ ‹‹የመፅሓፍ ባለቤት›› እያለ በክብር ነው የሚጠራቸው። እነሱ ጋር ያለ መልካም ግኑኙነቶችን በጣም በሚያምር ቃል ነው አላህ የሚገልፀው። ‹‹እነዚያ ቀሳውስትና መነኮሳት ያላቸው ክርስቲያን ነን ያሉ ለእንናተ ለወዳጅነት ቅርብ ናቸው›› ይላል። በአጠቃላይ በመካከል ሊኖር የሚገባው ግኑኝነትና መተሳሰብ ቁርዓን በግልፅ አስቀምጦታል። አንዱ አንዱን መጥላት በእስልምና አይፈቀድም። ደግሞም እኛን የምታገናኘን የጋራ አገር አለችን። ማህበራዊ ግንኙነትና ቤተሰባዊ ትስስራችንም ጠንካራ ነው።
ከሁሉ በላይም በሰላም ተከባብረን፤ ተዋደን እንድንኖር የእምነታችን መመሪያ ነው። ቅዱስ ቁርዓን ‹‹ለጎረቤቱ የማያዝን ሰው አማኝ አይደለም›› ይላል። ጎረቤቱ ተርቦ እሱ ጠግቦ ያደረ ሰው እንዳለመነ ነው የሚቆጠረው። እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ቁርዓን ‹‹ጎረቤት›› አለ እንጂ ሙስሊም፤ ክርስቲያን የእከሌ ዘር ብሎ አለየም። ይህ ነው የእስልምና መመሪያ። ያ ማለት ማንንም በእምነቱም ሆነ በማንነቱ ሳንለየውና ሳናገለው መልካም መመኘትና መልካም መዋል፤ ከመጥፎ ነገር መጠበቅና መከላል የእምነቱ መሰረታዊ ግዴታ ነው።
ከዚያ ውጭ ያሉ መገፋቶች የእምነት መገለጫ ወይም አካል ናቸው ብዬ አላስብም። ሰዎች እምነታቸውን ሲለቁ ስሜታቸውን ይከተላሉ። ዛሬ ‹‹የፍቅር አምላክ የሆነውን እየሱስን እከተላለው›› ያለ የክርስትና እምነት ተከታይ እንዴት ብሎ ነው ሌላውን ጠልቶና ደም አፍስሶ የእሱን ፍቅር ለማግኘት የሚችለው?። ‹‹የሰላም እምነት አለኝ›› ብሎ የሚያስብ ሙስሊም የሌላን ደም አፍስሶ፤ የሌላን ህይወት ጉዳት ላይ አጋልጦ ሊያገኝ የሚችለው ምንም አይነት የእምነት መገለጫ የሆነ ፈጣሪ ዘንድ ቅርበት አይኖረውም። እምነቱን ባለመረዳት የሚፈጠሩ ክፍተቶች ይኖራሉ፤ እምነቱ ግን ይህንን ነው የሚያዘው። በየትኛውም እምነት አማኞች ፍቅር፤ መተሳሰብ፤ ሰላምና መከባበር በማስጠበቅ አብሮ እንዲኖሩ ነው የሚገደዱት። በማይመሳሰሉበት ነገር ላይም አንዱ ለሌላው እውቅና ሰጥቶ ተከባብረው መኖር ይጠበቅባቸዋል።
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን ናት፤ አንዱ ሌላው ገፍቶ ሊኖር የሚችልባት አይደለችም፤ ይህችንን የጋራ አገር የማልማት፣ የማሳደግ፣ ሰላሟን ደህንነቷን የመጠበቅ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። በዚህች አገር ላይ ሁላችንም ደርሻ አለን፤ ስለዚህም በጋራ ልንሰራ ግዴታችን ነው። እምነታችንም የሚያዙን ይህንን ነው። ረመዳን አንዱ ካሉት በረከቶች መካከል በሰዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትንና ትስስር እንዲሁም አብሮነት እንዲጠናከር ዋነኛው ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ላለው ችግር በተለይ ቤተ እምነቶችና የሃይማኖት አባቶች ትውልዱን በሚገባቸው ልክ ያለመቅረፃቸው መሆኑን ይነሳል። ይሄን እንዴት ያዩታል?
ኡስታዝ አቡበከር፡- ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር አላቸው ከሚባሉ አገራት አንዷ ናት። ወጣቱ የዚህች አገር ትልቁ የለውጥ ኃይል ነው። ይህችንን አገር የሚረከብ ፤ ነገ ኃላፊነቱን ወስዶ አገርን ማስቀጠል የሚችል ማንነት አለው። እርግጥ ነው፤ ወጣቱ መጠቀሚያ ሊሆን የሚችልበት እድሎች አሉት። በተለያየ መልኩ ወጣቱን ለጥፋትና ለመጥፎ ዓላማ ሊጋብዙ የሚችሉ ስራዎች ይሰራሉ። ዛሬ ጥፋትም የሚያጠፋው፤ አገርም የሚያለማው ሁሉም ይፈልገዋል። ይህ ወጣት ደግሞ የበለጠ ትክክለኛውን መስመር ተከትሎ እንዲኖር፤ የተፈጠረበትን ዓላማ ሳይዘነጋ ባለው አቅም ለመልካም ነገር እንዲጠቀም ለማድረግ እንዲሁም የሰብእና ከፍታ ላይ እንዲቀመጥ ቤተ-እምነቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው።
በስነ-ምግባር የማነፅና የመቅረፅ ኃላፊነት የቤተ-እምነቶችና የሃይማኖት አባቶች ድርሻ ነው። ዛሬ እየከፈልን ያለነው ዋጋ ትናንት ባልሰራነው የቤት ስራ ምክንያት ነው። ስራችንን በአግባቡ መስራት ባለመቻላችን ነው አማኝ የሆነ ማህበረሰብ አለ በሚባልባት አገር ላይ የሚፈፀመው ግፍ ማሰብ ከሚቻለው በላይ ከባድ የሆነው። ትውልዱ ላይ ምን ሰራን? ብለን ልንጠይቅ ይገባል። ዛሬ አገር የሚያምሰው፤ አገር የሚያጠፋው፤ በማህበራዊ ሚዲያው ጠብንና ጠላትነትን እንዲሁም እርስበርስ መበላላትን የሚሰብከው ወጣት የእኛው ስሪት ውጤት ነው።
ከየትም አላመጣነውም፤ በእምነቱም ቢሆን ይህንን ወጣት ክርስቲያን ወይም ሙስሊም የሌላ ቤተ-እምነት ተከታይ መሆኑ አይቀርም። ይህ አካል ይህችው ምድር ያበቀለችው፤ በእኛው ቤት ውስጥ ያደገ፤ በእኛ እጅ የተገነባ ነው። ስለዚህ ምንአይነት ስራ ሰርተን ነው ይሄ ትውልድ በዚህ ደረጃ የወረደው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ኡስታዝ አቡበከር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015