
የሰው ልጅ መገኛና የቀደምት ስልጣኔ ምድር ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት። ሕዝቧም እንግዳ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ሰው አክባሪ፤ ሰው ወዳድ እንዲሁም ጨዋ ስለ መሆናቸው በየአካባቢያቸው የሚያንፀባርቋቸው ወጎቻቸው፤ ባኅሎቻቸው እና ልማዶቻቸው ይመሰክሩላቸዋል።
ከእነዚህ ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን፤ አንድነት፤ እንዲሁም አብሮነታቸውን ከሚያጠናክሩ እና ድንቅ እሴቶቻቸው መካከል የሠርግ፤ የለቅሶ፤ እርቅ እና ግጭት አፈታት ስርዓቶቻቸው በዋናነት ይጠቀሳል። በተለይ የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ፤ሰው ወዳድና አክባሪ ከመሆናቸው ባሻገር መንስኤው ምንም ይሁን ምን ” ከሰው ስህተት፤ ከብረት ዝገት ‘እንደሚለው ተረቱ በአብሮነት የሕይወት ዑደትና ሕይወታቸው ውስጥ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩበት ሁኔታ አይጠፋም።
የዘርፉ ምሁራን እንደሚናገሩት በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በግለሰቦች እና በቡድኖች መካከል የሚነሳ ሃሳብም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት ግጭቶች ይፈጠራሉ። ምሁራኑ እንደሚያስረዱት ሕዝቡ በአንድ አካባቢ በመከማቸት አብረው በሚኖሩበት ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ይፈጠራሉ። ለምሳሌ በንግድ ልውውጥ፣ በጋብቻ መተሳሰር በለቅሶ፣ በሠርግ እና በሌሎች ጉዳዮች የሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች በማሳያነት ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን ምሁራኑ እንደሚያመላክቱት አልፎ አልፎ በእነዚህ ማኅበራዊ ግንኙነቶ ች ው ስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ አንዳንድ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል። የድንበር ላይ ፤እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች አጎራባች ብሔረሰቦች ጋር ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነት ያላቸው እንደመሆኑ አንዳንዴ በመካከላቸው ግጭቶች የሚከሰቱበት ሁኔታ ይስተዋላል።
በተለይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች በየፊናቸው ከገዛ ቤተሰባቸው፤ ከጎረቤታቸው፤ በውሃ፤ በግጦሽ መሬት፤ በአጎራባች ድንበርም ፤ እለት ከእለት ከሚገናኝዋቸው ወገኖች ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ። በዚህም ከሁከት እና ግርግር መፈጠር አልፎ ተርፎም እስከ አካል መጉደል፤ መገዳደል በመድረስ እርስ በእርስ ደም እስከ መቃባት የዘለቀ ግጭት ላይ ሊወድቁ የሚችሉበት አጋጣሚም ብዙ ስለመሆኑ የመስኩ ምሁራን ያመለክታሉ።
እናም በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሁኔታው የሚሰፋና የሚጠብ ግንኙነት እየመሠረቱ፤ በየራሳቸው የተናጠልና የጋራ ሀገራዊ ታሪክ እየሠሩ የኖሩት እነዚህ ዜጎች በተለይ የ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ፤ እንደ አኗኗር ዘይቤያቸው እና ባሕላቸው ግጭት የሚፈቱበት ሥርዓት ያላቸው ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶችና መረጃዎች ያሳያሉ ። በዚህ በኩል በተለይም ባሕላዊ አስተዳደርና ዳኝነት እና እርቅ፤ እንዲሁም ግጭት አፈታት ሥርዓትን እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል። ይሄ ሥርዓት ታድያ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም የማኅበረሰቡ አባላት የዕለት ተዕለት ኑሮ የተረጋጋ እና ሠላማዊ እንዲሆን የተለያዩ ኃላፊነቶች አሉት። ከእነዚህ ኃላፊነቶች አንዱ በማኅበረሰቡ አባላት መካከል የሚፈጠሩ ፤ በግልና በቡድን የሚነሱ ግጭቶችን በዘለቄታ መፍታት ነው።
ለአብነት ሲዳማ አፍኒ፤ የተሰኘ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ሲኖረው ጉራጌ ፤ ቂጫ የተሰኘ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደዚሁም የባሌ ኦሮም ”ሴረጉማ‘ የተሰኘ እና ለግድያ ግጭት እንዲሁም ለእንስሳት ፤ ለአካል ጉዳት እና በስድብም ሆነ ስም በማጥፋት ለሚደርስ የስብእና መዋረድና መጓደል የሚያገለግል ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሲኖረው ሀዲያ በፊናው ሀዲያ የ”ጢጉላ‘ የተሰኘ ባሕላዊ ግጭት አፈታ ት በተጨማሪም ሶማሌ፤ አማራ፤ አፋር፤ ኦይዳ ብሔረሰብ የየራሳቸው ግጭት አፈታት ሥርዓት ሲኖራቸው ሽናሻዎች በፊናቸው « ኔሞ” የተሰኘ የራሳቸው የሆነ የግጭት አፈታት ሥርዓት እንዳላቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዚያት በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ግጭት አፈታት ላይ አተኩረው የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ለዛሬም ከነዚህ የማኅበረሰቡን የአብሮነት መስተጋብር በማጠናከር እና በሰላም አብሮ መኖርን እሴት በመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዲሁም እንደየ ብሔረሰቡና አካባቢው የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸው እየተሠራባቸው ካሉ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች መካከል “ኔሞ” የተሰኘውን የቦሮ ሽናሻዎች የግጭት አፈታት ዘዴ ከተለያዩ ጥናቶች ያነበብነው እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።
“ኔሞ” በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ማኅበረሶች ውስጥ ቦሮ ሺናሻ የተሰኙት ማኅበረ-ሰብ ሲገለገሉበት የኖረው እና አሁንም እየተገለገሉ የሚገኙበት የሽናሻ አባቶች የሀገር በቀል እውቀታቸውን ተጠቅመው በማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሚከላከሉበት እና ግጭቶች ሲከሰቱም እርቅ የሚያወርዱበት የዳበረ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው። ሥርዓቱ የቦሮ ሺናሻ ማኅበረ-ሰብ ለብዙ ሺ ዓመታት ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየው የራሱ መለያና መገለጫ የሆኑ ባሕል ፣ ወግና ትውፊትም ነው። ”ኔሞ” የተሰኘው ይሄው የቦሮ- ሺናሻ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ እና የራሱ ታሪክ ያለውም ስለመሆኑ ተወላጆቹ ይናገራሉ። ”ኔሞ” የባሕላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት ለሽናሻዎች እንደ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት ሆኖ ሲያገለግል የኖረ እና አሁንም እያገለገለ የሚገኝ ስለመሆኑም ይጠቀሳል።
“ኔሞ” ሽናሾች ግጭት ከመከሰቱ አስቀድመውም የሚከላከሉበት መሳሪያቸው ነው። ሊከሰት የሚችለውን ኃይለኛ እና ምን አልባትም ሊበርድ የማይችል ለአካል መጉደልና ለሕይወት መጥፋት መዘዝ የሆነ ግጭት ከመከሰቱ ቀደም ብለው ”እዚያው በጸበሉ‘ እንዲሉት አባባል ሳይከሰት እንዲቀር በሽናሽኛ ቋንቋ “ኔሞ ኔቶራ” ወይም በአማርኛ ”በሕግ አምላክ‘ በማለት ወንጀልን ከወዲሁ የሚከላከሉበት ሂደት አለ። ሽናሻዎች በ “ኔሞ” የተጣላን ያስታርቁበታል፤ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በባሕል ይዳኙበታል፤ ለሁሉም ግጭት እንደ ቁልፍ መፍትሄ የሚጠቀሙበትም ባሕላዊ የሕግ ሥርዓታቸው ነው።
“ኔሞ” ሽናሻዎች በማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ የሚያጋጥሙ አለመግባባት እና ችግሮችን አስቀድመው የሚከላከሉበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፤ ምንም ዓይነት አድሎ በሌለበት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚዳኙበት ባሕላዊ የሕግ ሥርዓት ነው። ሽናሻዎች የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸውንም በዚሁ በ”ኔሞ” ሥርዓት ታግዘው የሚፈጽሙበት ሁኔታ ስለመኖሩም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኙ ጥናቶች ያሳያሉ። በሺናሻ አንድ ሰው ሕግ እንዳይጥስ አስቀድሞ በሽናሽኛ ቋንቋ ”ኔሞን ኔቶራ” ወይም በአማርኛ በሕግ አምላክ ከተባለ ሕጉን አክብሮ ከጥፋት መታቀብ ይጠበቅበታል። አይበለውና ሰውዬው ሞገደኛ ሆኖ በሕግ አምላክ ሲባል አሻፈረኝ ብሎ ግጭት ከተከሰተ እና ጉዳት ወይም መጎዳዳት ከገጠመ ጉዳዩ “ኔሞ” የባሕላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት የሚስተናገድ ነው የሚሆነው።
ከ”ኔሞ” የባሕላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት አንዱ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት ተብሎ የሚጠቀስ ስለመሆኑ ጥናቱ ያመለክታል ። ይህ የባሕላዊ ዳኝነት ሥርዓት የተለያዩ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቶችን ስለመከተሉም ይነሳል። ሥርዓቱ አራት ደረጃዎች እንዳሉትም የተለያዩ ከሥርዓቱ ጋር ተያይዘው የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ አራት የዳኝነት ደረጃዎች የመጀመሪያው “ቡራ” ሲሰኝ ሁለተኛው ደረጃ ”ኔሞ” ሶስተኛው ደረጃ ደግሞ “ፄራ” እንዲሁም አራተኛው ደረጃ “ፋላ” በመባል ስለመታወቃቸው መረጃዎቹ ያስረዳሉ።
“ቡራ” የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ሲሆን አንድ ሽማግሌ ብቻውን ሆኖ የሚፈርድበት ባሕላዊ ችሎት ስለመሆኑም ያብራራሉ። በዚህ በ‘’ቡራ” የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ሂደት የሚዳኙ ባሕላዊ ዳኞች ግጭቶችን በፍትሃዊነት በመፍታት የታወቁ ስለመሆናቸውም መረጃው ይጠቅሳል። በዚህ የዳኝነት ሥርዓት ለመዳኘትም በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እና የብሔረሰቡን ባኅላዊ እሴቶችን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን እንዳለባቸውም ይነገራል። የ”ቡራ” ችሎት የመጀመሪያ ደረጃ ግጭት መፍቻ ሲሆን በቅርብ ግዜ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማየት ውሳኔ እየሰጠ የሚገኝበት ሁኔታ እንዳለም ነው መረጃዎቹ የሚያመላክቱት። በዚህ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ዳኛው ጉዳዩን መፍታት ካልቻለ ጉዳዩ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ፍርድ እንዲቀጥል የሚደረግበት የአሠራር ሂደት አለ።
ሌላኛው እና ሁለተኛው ደረጃ ባሕላዊ ዳኝነት ደረጃ ” ኔሞ” የተሰኘው ሲሆን ይሄ ኔሞ የተሰኘ ደረጃ ሶስት ሽማግሌዎች በጋራ ሆነው ፍርድ የሚሰጡበት ነው። በተጨማሪም በመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ በ “ቡራ” ዳኝነት ቅር የተሰኘ ሰው ካለም ይግባኝ የሚቀርብበትም ደረጃ ነው “ኔሞ”። በዚህም ፍርድ የሚሰጡ ዳኞች ግጭት ሲፈጠር በእውነት በመፍታት እና በማስታረቅ በብርቱ ይታወቃሉ፤ ይደነቃሉ ።
ሦስተኛው ደረጀ ዳኝነት ”ፄራ‘ የሚባል ሲሆን በዚህ ደረጃ ዳኝነት “ኔሞን” ችሎት መፍታት ያልቻለው ጉዳይ በጥልቀት እና የሚፈታበት ስለመሆኑ ይነገራል። ይህ ባሕላዊ ችሎት በአንድ ባሕላዊ ዳኛ የሚመራ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ። በተጨማሪም በይግባኝ ሰሚ ችሎት “ኔሞ” ለመፍታት ያልተቻሉና ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ወደ ‘ፄራ” የፍርድ ችሎት ተሸጋግሮ ቅሬታዎች የሚፈቱበት ሂደት ነው። በዚህ የፍርድ አሰጣጥ ደረጃ ላይ ፍትህ የሚሹ ሁለቱም ወገኖች ”ፄራ” የመምረጥ መብት አላቸው:: በ”ፄራ” የፍርድ ችሎት የሚዳኙት ሽማግሌዎች ከአባት፣ ከአያት፣ ከቅድመ አያት ባገኙት የግጭት አፈታት ዕውቀት የሚታወቁ ፣ ወንጀል ነክ ጉዳዮችን በማየት ልምድ ያዳበሩ ናቸው።
አራተኛው እና የመጨረሻው ባሕላዊ የሽናሻዎች የዳኝነት ሥርዓት “ፋላ” የሚሰኝ ነው። ይሄም “ፋላ” በሽናሻ ቤሔረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የዳኝነት አካል ተደርጎ የሚታይና የሚወሰድ ሲሆን በሶስቱ እርከኖች በሚሰጠው ዳኝነት ያልረካ ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ደረጃ ቀርቦ የሚዳኝበትም ነው ። በሽናሻ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት በ”ፋላ” የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ የመጨረሻ እና አስገዳጅ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሄን የመጨረሻውን ውሳኔ አልቀብልም የሚል ወገን ካለ ከማንኛውም ማኅበራዊ ተሳትፎ ተገልሎ እንዲቆይ የሚደረግበትን ሂደት አካቷል ።
ከብት ከከብት ጋር ወይም ልጅ ከልጅ ጋር እንዳይገናኝ፣ እንዲሁም እሳትና ውሃ ከጎረቤት እንዳይወስድ የሚገለል ከመሆኑ በላይ በዋናው የብሔረሰቡ አስተዳዳሪ ትእዛዝ አካባቢውን ለቅቆ እንዲሰደድ የሚያደርግ ማእቀብ ሁሉ ሊጣልበት ይችላል። በቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ ዘንድ በአብዛኛው የግጭት መንስኤዎች ተብለው በዋናነት የሚጠቀሱት ድንበር መተላለፍ ፣ ግጦሽ መሬት ፣ ነፍስ መግደል፣ እና እርስ በእርስ ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶች ሲሆኑ እነዚህን ለመፍታት በግጭት አፈታቱ ሂደት ዳኞች ከሚወስኑት ባሻገር እርቁን ለዘለቄታ ለማጽናት ሲባል ባሕላዊና ሐይማኖታዊ የእርድና ሌሎች ሥነስርዓቶችም ይከናወናሉ። መልካም ሳምንት!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም