ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የነበሩትን የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳን (ልዩ ወረዳው አሁን በዞን ደረጃ ተደራጅቷል) በአንድነት በመያዝ በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ 11ኛው ክልላዊ መንግሥት ሆኖ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ከፍተኛ አቅም ያለው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ነው፡፡ በተለይም ክልሉ ያለው የቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የማዕድናት ሀብት ሀገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም ፀጋ ነው፡፡
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ክልሉ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ባለቤት ነው፡፡ ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በክልሉ በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትም ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ሀብቶች ናቸው፡፡ በአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ በመሆኑ ዘርፉ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የማዕድን ሀብቶችን ለይቶና አደራጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የክልሉ ቀጣይ የቤት ሥራ እንደሆነ ግንዛቤ ተይዞ ከወዲሁ እየተሰራ እንደሆነም የኤጀንሲው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ድርሻ ባለው በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ በስፋት እንዲሰራና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ በግዥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ መተካት እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛ ነው፡፡ ከፍተኛ የቡናና የማዕድን ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ ሀብቱ ከክልሉ አልፎ ለሀገርም የሚተርፍ ፀጋ ነው፡፡ ክልሉ አስደናቂ የሆነ መልከ ዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ የባለሀብቶችን ትኩረት እንደሚስብ ይጠበቃል፡፡ በየክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ፕሮሞሽን፣ ፈቃድና መረጃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይደነቅ ወልደሰንበት፣ ስለክልሉ የኢንቨስትመንት ሀብትና የዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴዎች፣ በተለይም ባለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ስለነበረው የኢንቨስትመንት ስራ፣ በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል ፡፡
የክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበርካታ ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ክልሉ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ያገኛል፡፡ በተፈጥሮ ሀብትም ታድሏል፡፡ በቡና መገኛነቱ የሚታወቀው ክልሉ፣ በተለያዩ ዘርፎች ለኢንቨስትመንት የሚሆን እምቅ የሆነና ገና ያልለማ አቅም አለው፡፡ ዓመታዊ ሰብል፣ ቡናና ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች (Export Items)፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችሉ ሀብቶችና የምጣኔ ሀብት መስኮች ናቸው፡፡
በክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ያለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ማዕድን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል እና ብረት ከማዕድናቱ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ክልሉ በአዲስ መልክ የተደራጀ በመሆኑ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በስፋት በማጥናት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ እስካሁን በተደረገው ማጣራት የታወቀና ባለሀብቶችን የሚጠብቅ ከ150ሺ ሄክታር በላይ መሬት አለ፡፡
የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችና የባለሀብቶች ተሳትፎ
ባለሀብቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ናቸው፡፡ ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተሰሩት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስራዎች ባለፉት ወራት በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በክልሉ ከ150 በላይ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷቸው በተለያየ የትግበራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በግብርና፣ በአምራችና እና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታልም አስመዝግበዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ከ45ሺ በላይ ጊዜያዊና ከ20ሺ በላይ ቋሚ የስራ እድሎችን የሚፈጥሩ ይሆናል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ላስመዘገቡ 89 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ወደ ስራ ሲገቡ ከ47 ሺ በላይ (12ሺ ቋሚ እና 35ሺ ጊዜያዊ) የስራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡
በክልሉ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ከሚገኙት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ክልሉ ለሰብል ልማት ምቹ ስነ ምኅዳር ያለው በመሆኑ በተለይ በዓመታዊ ሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በወጪ ንግድ ምርቶች (ቡናና ቅመማ ቅመም) እና በበጋ መስኖ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአምራች እና በአገልግሎት ዘርፎች ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶችም አሉ። በክልሉ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚሰሩ የውጭ ባለሀብቶችም አሉ። ፕሮጀክቶቹ አቅማቸው ታይቶና በቴክኒክ ኮሚቴ ተገምግሞ አስፈፃሚው አካል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡
ለባለሀብቶች ጥሪ ተደርጓል፤ ባለሀብቶችን ለመቀበል በዞን የአስተዳደር መዋቅሮች አማካኝነት ግንዛቤ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ሲመጡ ያለምንም መስተጓጎል ወደ ስራ እንዲገቡ በየጊዜው ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የባለሀብቶች ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ባለሀብቶች ምንም ዓይነት የቢሮክራሲ ችግር ሳይገጥማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለግብርና ዘርፍ ልማት ከፍተኛ አቅም ካላቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ በመሆኑ፣ ክልሉ ለግብርና ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅም የማስተዋወቅ፣ ባለሀብቶችን በፍጥነትና በጥራት የማስተናገድ፣ ጥሩ ፈፃሚዎችን የመሸለም፣ ችግሮችን በፍጥነት በመገምገም የእርምት እርምጃዎችን የመውሰድ እና ክትትሎችንና ድጋፎችን የማድረግ ተግባራት የዚህ ትኩረት ማሳያዎች ናቸው፡፡
የመሰረተ ልማት አቅርቦት
ክልሉ በበጋም ሆነ በክረምት ወቅቶች አብዛኞቹን አካባቢዎቹን የሚያገናኙ መንገዶች አሉት፡፡ ውስን ከሆኑ ቦታዎች በስተቀር አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች የመንገድ መሰረተ ልማት አላቸው፡፡ በክልሉ ከሚገኙት አስፋልት መንገዶች በተጨማሪ በሁሉን አቀፍ የመንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር (URAP) የተሰሩ መንገዶችም የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳለጥ ሁነኛ ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የስልክ አገልግሎትም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ነው፡፡ በኃይል አቅርቦት ረገድ ግን ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡
አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎችን ጨምሮ በፌደራል መንግሥትና በክልሉ መንግሥት ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የክልሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተሻሻለ ነው። አውሮፕላን ማረፊዎችም እየተገነቡ ነው፡፡ ይህ የመሰረተ ልማት አቅርቦት መሻሻል ደግሞ ለባለሀብቶች መነቃቃትን እየፈጠረና የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲያድግ እያደረገ ነው፡፡
የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች
ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ከሚፈጥሩ ግብዓቶች ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮችን በቅርበት በመከታተል፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ቀደም ሲል ችግሮች ሲፈጠሩ በፍጥነት ተደራሽ የመሆን ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ከፍተቶችን ለማረም በተከናወኑ ስራዎች የፀጥታ ስጋቶችን ማስወገድ ተችሏል፡፡ በሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ስራ አቋርጠው የነበሩ ባለሀብቶች በአሁኑ ወቅት ተመልሰው ስራቸውን መቀጠል ችለዋል፡፡ በዚሁ ምክንያት ቀደም ሲል ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያልሆኑ አካባቢዎች ጭምር የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየቀረቡባቸው ይገኛሉ፡፡ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ተግባር ከክልሉ መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከልም አንዱ ነው፡፡
የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች
ክልሉ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር የሚያደርጋቸው ማበረታቻዎች በአዋጅና በመመሪያ በተደነገጉ የማበረታቻዎች (Incentives) አሰጣጥ መሰረት የሚፈፀሙ ይሆናል፡፡ ባለሀብቶችን በቁጥርም ሆነ በጥራት ለማብዛት የሰላምና ፀጥታ፣ የቢሮክራሲ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪ፤ በሕግ ማዕቀፍ የተቀመጡ የማበረታቻ ስልቶችን መሰረት በማድረግ ትልቅ አቅም ያላቸውና በቁጥር የበዙ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ጥረት ያደርጋል፡፡ ቦታዎችን አዘጋጅቶ ለባለሀብቶች ማቅረብን ጨምሮ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባራትን ያከናውናል። ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ባለሀብቶች የምርት ስራቸውን ሲጀምሩ ክልሉ ተጨማሪ መሬት በማቅረብ ስራቸውን እንዲያስፋፉ ያበረታታል፡፡
ኢንቨስትመንትና ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነት
የክልሉ መንግሥት ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ሲያስገባ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው። ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ስራዎች በስራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል። ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
የዘርፉ መሰናክሎች
ቀደም ሲል በነበሩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ምክንያት የተፈጠሩ ስጋቶች ብዙ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችና ፕሮጀክቶች በጥቂት የክልሉ አካባቢዎች ላይ ብቻ እንዲከማቹ መንስዔ ሆነው ነበር፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሰፋፊና ለም መሬት ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሰራጩ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ክልሉ ከተመሰረተ ገና አዲስ በመሆኑ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማሳለጥ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የሎጂስቲክስ እጥረቶች አሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ስራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ አደረጃጀቶችን የማጠናከርና ግብዓት የማሟላት ስራ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ቀጣይ እቅዶችና የትኩረት አቅጣጫዎች
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስደናቂ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና ሀብት ያለው በመሆኑ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ክልሉ ሰፊና ለም መሬትና ውሃ ያለውና በበጋም ሆነ በክረምት መልማት የሚችል በመሆኑ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራው በስፋት ተጠናክሮ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ያልታወቁ ሀብቶች ጭምር ስላሉ ባለሀብቶችን በብዛት በመጋበዝ፣ ሀብቱን በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል ሕዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ ይደረጋል፡፡
ቡናና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ በሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች ዘርፍ ያለውን አቅም ለመጠቀም ሰፋፊ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ክልሉ አራት ዋና ከተሞች ያሉት ስለሆነ በየከተሞቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማዳረስ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ታቅዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የክልሉን አቅም በመጠቀም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግና ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሀብታዊ ሽግግርን ለማሳካት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015