የሚኒስትሮች ምክር ቤት «የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት» አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር መወሰኛ ደንብ በቅርቡ አውጥቷል። ደንቡ የኢንተርፕራይዝ ልማቱን ስልጣንና ተግባር በዘረዘረበት አንቀጽ ልማቱ ኢንተርፕራይዞች እርስ በእርስና ከከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣ ከሌሎች ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በግብአት፣ በገበያና በቴክኖሎጂ የሚተሳሰሩበትን ስልቶች እንደሚቀይስና ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስቀምጧል።ይህ ተቋም የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍ ያለ ድርሻ እንዳለውና ተኪ ምርቶችን በማምረትም ሚናው የጎላ መሆኑ ይታመናል። የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ጳውሎስ በርጋ በ”ተጠየቅ “አምዳችን እንግዳ በማድረግ በተቋሙ እየተሰሩ ያሉትንና ሊሰሩ የታቀዱትን ስራዎች አስመልክተን ቆይታ አድርገናል።መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ጳውሎስ፡– የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በቅርቡ በአዲስ ደንብ በደንብ ቁጥር 526/2015 ተቋቁሟል። ከአዲሱ ደንብ በኋላ መዋቅር ተጠንቶ ሊፀድቅ ዝግጅት ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ቀደም ሲል ከነበረው አቅም በላይ እንዲያስፈፅማቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል።
ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ክላስተር ግንባታ፣ ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን፣ ወደውጭ የሚላኩ ምርቶች፣ ተኪ ምርት መከታተልና ክልሎችን የመደገፍ ተጠቃሾች ናቸው። ይህ ቀደም ሲል በነበረው የተቋሙ አቅም ያልነበረና አዲስ አሰራሮችን የሚፈጥር ነው። ተቋሙ አሁን በተጨመረው አዳዲስ አቅሞች በመታገዝ አዳዲስ አሰራሮችን በመስራት ላይ ይገኛል። የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ በጀርመን መንግስት ድጋፍ እየተጠና ይገኛል።
ተቋሙ፣ እስካሁን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም የማምረቻ ማዕከላትን የመገንባት፣ የማስተዳደር እና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ስራዎችን እንዲሰጥ ተጨማሪ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፤ በመሆኑም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ፍኖተ ካርታው ትልቅ አቅም ይሆነዋል።
ፍኖተ ካርታው ዘርፉን በውጤታማነት ለመምራትና ከጊዜው ጋር የተጣጣመ ድጋፍ ለማድረግ ምቹ የሆኑ አሠራሮችን፣ የችግር መፍቻ መንገዶችን እና ውጤታማ ቅንጅታዊ አካሄዶችን ለማሟላት እንዲቻል በዘርፉ ተሞክሮ ባላቸው የአገር ውስጥና የውጪ አገር ባለሙያዎች እየተዘጋጀ ነው።በመሆኑም ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት በተለይ የፌዴራል ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አጋር አካላትና መሠል ባለድርሻዎች አስተያየታቸውን እንዲሠጡበት የተለያዩ መድረኮችም ተዘጋጅተው ነበር።
የዘርፉ ልማት የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ፣ የማምረቻ ቦታ፣ የስልጠና፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና መሰል ድጋፎችን በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብር አስፈላጊ ነው። ይህ እንዲሆንም ተቋሙ ቀጣይነት ያለው የምክክር መድረኮችን ለማመቻቸት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በራሱና ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ የሚያከናወናቸውን ስራዎች ቢያብራሩልን?
አቶ ጳውሎስ፡-ተቋሙ በራሱ የሚያከናውናቸውና ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራቸው በርካታ ስራዎች አሉት። ለአብነት ያህል ኤሌክትሪክ ሲፈለግ ከመብራት ኃይል ጋር እንዲሁም መሬት ሲፈልግ ከመሬት አስተዳደርና ሌሎች ስራዎችንም
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራል። በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በዋናነት የሚሰራው የአቅም ግንባታ ስራዎችን ነው። በሁሉም ክልል ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን የሚደገፉትን የማብቃት ስራን ይሰራል። በተቋሙ የተለያዩ የተግባር ስልጠናዎች ወጣቶች እንዲያገኙ በማድረግ ልማት ባንክ ከሚያመቻቸው የብድር ፕሮግራም ጋር ያስተሳስራል።
ሌላው የተለያዩ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ጥናቶች በማስጠናት ለመንግስት የፖሊስ አቅጣጫ የማሳየት ስራ ይሰራል። ለምሳሌ የማሽነሪ ሊዝ በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበት የሆነው ተቋሙ ባስጠናው ጥናት ነው። የዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ የጀመረውም ይህ የስራ እድል ፈጠራ ስራ በተለመደው መንገድ ሊካሄድ እንደማይችል በተጠና ጥናት ነው። በዚህም የዓለም ባንክ በመጀመሪያ 276 ሚሊዮን ዶላር አሁን ደግሞ 200 ሚሊዮን ዶላር ከአገሪቱ መንግስት ጋር ተፈራርሞ ለኢንተርፕራይዞች እንዲከፋፈል የተደረገውም በጥናት ነው።
የኛ ተቋም ስራውን በመምራት ከላይ የጠቀስኳቸውን ስራዎች ይሰራል። አሁን አዲስ የተሰጠው ኃላፊነት ክላስተር ግንባታ /መሠረተ ልማት የተሟላለት የሥራ ቦታ ማዘጋጀት/ ነው። በዚህም ግንባታው በተቋሙ ተሰርቶ ለግል አልሚ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። ተቋሙ በሚያከናውነው ተግባር ማነቆዎች የሆኑበት በአብዛኛው ቢሮክራሲ ሲሆን፣ ይህም ከአገልግሎት ሰጪዎች ቅንነት ማጣት የተነሳ የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው። የአገር ውስጥ ግዢ ከሚያደርጋቸው ግዢ በአገር ምርት ሊተኩ የሚችሉትን ለጥቃቅንና አነስተኛ ክፍት ቢያደርግ ተቋማቱን ማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከመነሻው አነስተኛና ጥቃቅን ተብሎ ሲቋቋም ስራ አጥ ዜጎች ከትንሸ ደረጃ ተነስተው እስከ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ አላማ አድርጎ ነው። ነገር ግን ሁሉንም ኢንተርፕራይዞች በእኩል መጠን የገበያ ትስስር አለመፍጠር፤ የተለያዩ ድጋፎችም ለአንዱ በከፍተኛ ሁኔታ ለአንዳንዱ ለይምሰል ሲደረግ ይታያል፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ጳውሎስ፡– እንደ አገር ከጥቃቅን ጀምሮ መካከለኛ ከፍተኛ ተብሎ ሲቋቋም ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ባለሀብትነት ለመቀየር ታስቦ ነው። ስራው ሲጀመር እያንዳንዱ ስራ ፈጣሪ ይሆንና በውስጡ ከፍተኛ ፍላጎት ኖሮት ወደ ስራ የሚገባ አለ። ሌሎች ደግሞ ስራ አጥ ተብለው የተደራጁ ወጣቶች አሉ። ሌላው በራሱ ገንዘብ ኖሮት በትንሽ ድጋፍ ከመካከለኛ የጀመረም አለ። ስኬታቸውም ሆነ ውድቀታቸው እንደየ ስራ አጀማራቸው እና ጥንካሬያቸው ይወሰናል።
በኢንዱስትሪው ሁኔታ ግን ከታች በርካታ ስራ አጦችን የያዘ ጥቃቅን ሲኖር መሀል ላይ አነስተኛ ጥቂት ቁጥር ይይዛል። ከፍተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፍም ይከተላል። ይህ በየትኛውም አገር የተለመደ የፒራሚድ ቅርፀ ያለው አይነት አካሄድ ነው። ይህ የሆነው የመክሰም መጠኑ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የእውቀት ማነስ፣ የቢሮክራሲው ማነቆነት እና የእርስ በእርስ ግንኙነት ነው። በአብዛኛው ግን ከተደራጁት ይልቅ ስራ ፈጣሪዎቹ እንቅፋቶችን ተቋቁሞ በማለፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች እውቀታቸውን በማሳደግ ችግሮችን በመጋፈጥ ወደ ላይ ይወጣሉ።
እንደ አገር ጥቃቅን ላይ የተደራጁ እንደ ህፃናት ልጅ እንክብካቤ የሚፈልጉ ወጣቶች አሉ። እነርሱ በቀላሉ ተስፋ ቆርጠው ስራውን እንዳያቆሙ በተቻለ መጠን ስልጠናንና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ይደረጋል። በአብዛኛው ግን እውቀት ሳይኖር ብሩን ለማግኘት ብቻ የሚደራጁት ይከስማሉ።
ሌላው ጥቃቅንና አነስተኛ ላይ የሚሰሩት በእድገታቸው ልክ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ሲያድጉ ግብር ከፋይ ይሆናሉ። ስለዚህ ማደግን አይፈልጉም። በማደጋቸው ቀደም ሲል የሚያገኙትን ለስኬታቸው አጋዥ የሆነውን ጥቅም ማጣት አይፈልጉም። ከግብር ከፋይነት በላይም ሲያድጉ የመስሪያ ሼዱን ስለሚለቁ ከማደግ ይልቅ አለማደጋቸውን ምርጫ አድርገዋል።
ሆኖም ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ተቋሙ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ አሁን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በመጀመሪያ ስልጠና በመስጠት በቂ እውቀት ይዘው ከፍ እንዲሉና ጠንካራ የስራ ፈጣሪነት ስነ ልቦና እንዲኖራቸው አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ቢገልፁልን?
አቶ ጳውሎስ፡- ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል በአገር ውስጥ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ልምድ ካላቸው ጋር አቀናጅቶ ውጤታማ ማድረግ አንዱ ነው። አብዛኛዎቹ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ካሉባቸው በርካታ ተግዳሮቶች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ረገድ ያለው ችግር እጥረት መኖር ብቻ ሳይሆን ለብድር ዋስትና ማስያዣነት አምራቾች እንዲያቀርቡ የሚጠየቁት መስፈርትም ካለው ነባራዊ ሁኔታና ከአምራቾች አቅም አንጻር ሲመዘን ተገቢ አይደለም። በአንድ ወገን ብድር ለመበደር ከሚፈልጉት መጠን ከሁለት እስከ ሰባት በመቶ ተቀማጭ እንዲኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህንን በአይነት ለማስያዝ የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ቤትና መኪና ብቻ በዋስትና ማስያዝ ይፈቀድላቸዋል።
ይህ ገና በዓመታት እቅድ ውስጥ ጥሪት ቋጥሮ ራሱን ችሎ ሀብት ወደ ማፍራት ብሎም መኪናና ቤት ለመግዛት ለሚውተረተር አምራች እንኳን የሚሞከርም የሚታሰብም አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ ለመበደር እድሉን የሚያገኝ አምራች ቢኖር እንኳን ወለዱ አስራ ስምንት በመቶ የሚደርስ በመሆኑ ሰርተው ለመለወጥ ላሰቡ ጀማሪዎች የሚሞከር አይሆንም። በሌላ በኩል ኢንዱስትሪው እንደ አጠቃላይ ካለበት ችግር ስልሳ በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የግብአት እጥረት ነው። ዛሬም ቢሆን በአብዛኛዎቹ አምራቾች የሚጠቀሟቸው ግብአቶች በዶላር እንደ ህንድና ቻይና ከመሳሰሉ አገራት ተገዝተው የሚመጡ ጥሬ እቃዎችና መለዋወጫዎችን ነው። የውጪ ምንዛሬ እጥረት ደግሞ ለአምራች ኢንተርፕራይዝ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ያለ ፈተና ላይ ያለንበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የውጪ ምንዛሬ ከባንኮች እየጠበቁ ከመኖር ይልቅ የውጪ ምንዛሬ ሊያስገኝ የሚያስችል መንገድ ካለ ማማተርና ያለውንም የውጪ ምንዛሬ በአግባቡ ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ብቻ በቁጠባ መጠቀም ያስፈልጋል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በማምረት አቅም አጠቃቀም ረገድም ሰፊ ክፍተት አለ፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ኢንተርፕራይዞች እየሰሩ ያሉት ከማምረት አቅማቸው ሀምሳ በመቶ ብቻ ነው። በገበያው ውስጥ እንዲቆዩ የሚረዳቸው በዋናነት ገበያው ውድድር የሌለበት በመሆኑና እጥረት መኖሩ ሲሆን፣ በአቅማቸው ባለማምረታቸው የሚጨምረውን የማምረቻ ዋጋ የሚያካክሱት በተገልጋዩ ላይ ዋጋ በመጨመር ይሆናል።
በሌላ በኩል በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከአስራ ሁለት በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል። በእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እየገቡ ያሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ናቸው። አንዳንዶቹ በተለያዩ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ያሏቸው ናቸው። በመሆኑም ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የግብአት እጥረት የሌለባቸው ገበያ የማግኘት ጉዳይ የሚቸግራቸው ባለመሆኑ በቂ የገበያ ትስስር የቴክኖሎጂ አጠቀቃምና ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ናቸው።
ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች አንዳንድ ጊዜ እነሱ በዋናነት ከሚያመርቱት ምርት በተጨማሪ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በቀላል ማሽኖች ሊመረቱ የሚችሉ ስራዎችም ይኖራቸዋል። እነዚህን ፋብሪካዎቻቸውን ባቋቋሙባቸው አገራት ለሚገኙ አምራቾች በማስተላለፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በሌሎች አስመርተው ለገበያ ያቀርባሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የግብአት አቅርቦትንም ሆነ የተመረተውን ምርት በወቅቱ የሚቀበሉት እነሱ በመሆኑ ከላይ የተነሱት የግብአትና የገበያ ችግሮች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መሰናክል አይሆንም። የገበያ ትሰስር ብቻ ሳይሆን ፈጣንና ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር የውጪ ገበያ ልምድ እንዲኖር የሚረዳ ይሆናል። በአንጻሩ ትልልቆቹም ኩባንያዎች የሚፈልጓቸውን ምርቶች በከፍተኛ ወጪ ከሌሎች አገራት ከማስገባት በመዳን በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ እድል እስካሁን በኢትዮጵያ በሚጠበቀው ደረጃ ጥቅም ላይ ሳይውል የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በልማቱ በኩል ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች እንደሚያመለክቱት፤ በቅድሚያ ትልልቆቹ ኢንዱስትሪዎች አመኔታ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ለዚህም ኩባንያዎቹ ስምምነት ከማድረጋቸው በፊት ፋብሪካው ያለበት ሁኔታ፣ የሰራተኛ አያያዝ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የተረፈ ምርት አወጋገድና ተያያዥ ጉዳዮችን ማጣራት ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትም በአገሪቱ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማጎልበት ትስስር እንዲኖር ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል። ይህ አካሄድ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ከዓመታት በፊት ተሞክሮ ውጤት ያስመዘገበ ነው። በአሁኑ ወቅትም ከልማት ባንክ ጋር በመሆን የህግ ማእቀፍ ከማሰናዳትና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ከማድረግ ጀምሮ ዘርፉን በትስስር ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
በተጨማሪም በኢንተርፕራይዞች መካከል ያለው ትስስር መዳበር የጎንዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችልም ይሆናል። በዚህም በሂደት አነስተኛ ከአነስተኛ፣ አነስተኛ ከመካከለኛ፣ መካከለኛ ከከፍተኛ፣ ከፍተኛ ከከፍተኛ፣ የማስተሳሰር ስራዎች የሚሰሩ ይሆናል። ይህ የሚጠቅመው የአንዱ ምርት ለሌላው ግብአት ስለሚሆን እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም በቀጥታ የውጪ ገበያውን ለመቀላቀል ከመሞከር ይልቅ ልምድ ካካበቱት ጋር በቅንጅት በመስራት አቅማቸውን ካዳበሩ በኋላ ቢሞክሩት የተሻለ ውጤታማና ዘላቂ ስለሚያደርጋቸው ነው። ይህ ሂደት ለአገር ውስጥ አምራቾች ከብዛት ለረጅም ጊዜ ማትረፍ የሚያስችላቸው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከላይ በጠቀሷቸው ጉዳዮች ላይ የልማት ባንክ እያከናወነ ያለው ተግባር ምንድን ነው?
አቶ ጳውሎስ፡– ልማት ባንክ እንደሚታወቀው የፖሊሲ ባንክ ነው። የፖሊሲ ባንክ ማለት የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስራዎችን የሚሰራ ባንክ ነወ። ከዚህ አንፃር በልማት ባንክ በኩል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የፋይናንስ ፕሮጀክት ይዞ እየሰራ ነው። መጀመሪያ ላይ ወደ 76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በዓለም ባንክ ብድር መጥቶ ለተቋማቱ የስራ ማስኬጃና የማሽነሪ ብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ይሰራል።
ልማት ባንክ በዚህ መልኩ እነዚህን ተቋማት በመደገፍ የስራ እድል እንዲፈጠር ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲያበድሩ የሚያደርግባቸው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችም አሉ። እነዚህን አበዳሪ ተቋማት በአገሪቱ አጠቃላይ ባሉት ቅርንጫፎች ብድር እየሰጡ ይገኛል።
ማሽነሪ አቅርቦትም ቢሆን አራት ማሽን አቅራቢ የሆኑ ልማት ባንክን ጨምሮ አምስት ተቋማቱ 20 በመቶ ቁጠባ ካካሄዱ በኋላ ሌላ መያዣ ሳይጠየቁ ማሽኑ ራሱ መያዣ ሆኖ ይቀርባል ማለት ነው።
በአጠቃላይ ልማት ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የመስሪያ ማሽንንና ስራ ማስኬጃ ገንዘብ በማቅረብ ስራቸውን እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ችግሮች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል አንደኛ ኢንተርፕራይዞቹ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ የአበዳሪ አበዳሪ መሆኑ በራሱ ችግር አለው። ይህ ሲባል ልማት ባንክ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ያበድራል፤ እነሱ ደግሞ ለተቋማቱ ያበድራሉ። በዚህ ሂደት የመበደሪያ የወለድ ምጣኔው እስከ 18 በመቶ እንዲሄድ ሆኗል። ስለዚህ የመንግስት ፖሊሲውን የማስፈፀሙ ነገር አጠያያቂ ይሆናል።
አሁን ያለው የኢኮኖሚ ስርአት ገበያ መር ቢሆንም ገና ስራ ጀምረው ወደ ምርት ያልገቡ አነስተኛ አምራቾች ግን ድጋፍ ካልተደረገላቸው ተወዳዳሪነታቸው ቀርቶ ከገበያ ሊወጡ ይችላሉ። ለስራ እድል ፈጠራ ጠቀሜታ ያላቸው እነዚህ ተቋማት ድጋፍ ካልተደረገላቸው የታሰበው የስራ አጥ ቁጥር የመቀነስ ነገር አይሳካም እንደማለት ነው።
የልማት ባንክ ሲበደር በውጭ ምንዛሪ ይበደራል፤ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ግን በብር ነው የሚሰጠው። ከውጭ ግብኣት ማምጣት የፈለገ አምራች የውጭ ምንዛሪን ስለማያገኝ ይህም ለስራው ተግዳሮት ይሆናል።
ኢንተርፐራይዞቹ ብድር ተበድረው አይመልሱም ይባላሉ፤ ግብአት ካላገኙ እንዴት አድርገው ሊመልሱ ይችላሉ? ብድር ዛሬ ጠይቀው የዛሬ 6 ወር የሚደርስ ከሆነ የዋጋ ግሽበቱ ጋር ካልተመጣጠነ ምን ዋጋ አለው? ዛሬ የአንድ ሚሊዮን ብር ፕሮጀከት የዛሬ ስድስት ወር አራት ሚለዮን ብር ሊሆን ይችላል። ብድር የሚጠይቅበት ጊዜና ገንዘቡ እጅ የሚገባበት ጊዜ ረጅም መሆኑ የራሱ ተግዳሮት አለው። በአጠቃላይ ዘርፉ በአስፈላጊ ግብአቶች ረገድ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት እየተበረታታ አይደለም። ይህ ችግር መኖሩንም እንደ ተቋም ለልማት ባንክ አቅርበናል፤ ፖሊሲው መሻሻያ ከተደረገ በኋላ ለውጥ ሊኖረው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በብድር መያዣ ረገድ ተቋሙ የሄደበት ርቀት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጳውሎስ፡- በብሄራዊ ባንክ በኩል ለብድር መያዣነት ሌሎች ነገሮችም ያስያዙ እንዲሆኑ እየተሞከረ ነው። ለምሳሌ ለአርሶ አደር ከሆነ እንስሳቱን ማስያዝ እየተፈቀደ ነው። ስለዚህ ከቤትና ከመኪና ውጪ የሆኑትን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ሀብቶችን ለማስያዝ እየተሞከረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአገር ውስጥ አምራቾች እንኳን ወደውጭ አገር ለሚልኩት ምርት ይቀርና ለአገር ውስጥ የሚያቀርቡት ምርት ላይ የጥራት ጉዳይ አጠያያቂ እየሆነ ነው፤ እዚህ ላይስ ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ነው?
አቶ ጳውሎስ፡– በአደጉት አገራት የጥራት ጉዳይ ለድርድር ስለማይቀርብ ከጥራት ደረጃ በታች ምርቶች አይመረቱም። በእኛ አገር ግን ምንም አይነት እቃ ቢመረት ገቢ የማያጣበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ፤ አንዳንዴም አማራጭ ማጣትም ስለሆነ ያለ ምንም ጥያቄ ገበያ እንዲያገኝ ሆኗል።
ማህበረሰቡ ጥራት የሌላቸውን ምርቶች ባይጠቀሙ ግን አምራቾች የጠራ ስራ መስራት ይችላሉ። ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ካለው በጥራት የማይደራደር ማህበረሰብ መፈጠር ከቻለ ጥራት ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶችም በጥራት የተሻሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ሁሉም አምራቾች ለውጭ ገበያ እንዲያመርቱ ከማድረግ ይልቅ የተወሰኑት ለአገር ውስጥ፤ ሌሎቹ ደግሞ ተነጥለው ለውጭ ገበያ አቅርቡ ቢባልና በዚህ ልክ ድጋፉም ጥራቱም ላይ ቢሰራ የተሻለ አማራጭ አይሆንም?
አቶ ጳውሎስ፡– በእርግጥ ሁሉም ምርት ወደውጭ እንዲሄድ አይደረግም። ለምሳሌ የመከላከያ ልብስ፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ስራዎችና ሌሎችም ወደውጭ እንዲሄድ አይደረጉም። አሁን ለውጭ ገበያው የሚቀርበው በመሰረታዊነት የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ነው። ኤክስፖርት ማድረግ በራሱ ግን ለጥራት የሚሆኑ ምርቶች ገበያው ውስጥ እንዲበዙ፤ የአገራችንም ኢንዱስትሪዎች እያደጉ እንዲሄዱ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ተቋሙ የሰራቸው ስራዎች ምን ምንድን ናቸው?
አቶ ጳወሎስ፡- የተቋሙ ግብ የተቀመጠው አንደኛ የስራ እድል በመፍጠር ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ተኪ ምርቶችን ማምረት ነው። በበጀት ዓመቱ የስራ እድል ከሰባ በመቶ በላይ ተሳክቷል።ውደ ውጭ አገር የሚላኩ ምርቶችን ማምረት 72 በመቶ፤ ተኪ ምርት ግን ገና ምንም ያልተሰራበት ነው።
እንደ አገርም መተካት የሚለው ሀሳብም በደንብ ግንዛቤ ያልተያዘበት ነው።ሁሉም ምርት ይተካል አይተካም የሚለው እንዲሁም የትኛውን ለመተካተ ታቅዷል የሚለውን እያስጠናን ነው። በአጠቃላይ ግን የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም አርኪ የሚባል ነው።
አዲስ ዘመን፡- “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መርህ በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘ ትልቅ ንቅናቄ መኖሩ ይታወቃል፤ በዚህም በርካታ ተኪ ምርቶች እንደሚመረቱ ተነግሯል፤ በዚህ ረገድ ምን አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው?
አቶ ጳወሎስ፡– አዎ! ኢትዮጵያ ታምርት የሚል ንቅናቄ ተፈጥሯል። እሱ ግን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኃላፊነት ስለሆነ መልሱን እነሱ እንዲመልሱ ብናደርግ መልካም ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት የአገሪቱ ኢኮኖሚ መፈተኑ የሚታወቅ ነው፤ ዘርፉ በዚያ አስከፊ ወቅት ችግሮቹን የተቋቋመው እንዴት ነበር?
አቶ ጳወሎስ፡– ኮቪድ 19 በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ አስከትሎ ነበር። በተለይ አምራች ኢንዱስትሪውን የጎዳበት ሁኔታ አለ። ወደ እኛ አገር ስንመጣ አምራች ኢንዱስትሪው ተጨማሪ እድል ያገኘበት ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ በአነስተኛ ደረጃ ጋርመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ማስክ በማምረት ወደ ውጭ እስከመላክ የደረሱበት ሁኔታ ነበር።
ሳኒታይዘር ማምረት እንዲሁም የጽዳት መጠበቂያ እቃዎችና በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ስለነበር አነስተኛ አምራቾች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አልደረሰባቸውም። በጦርነቱም ሆነ በኮረና ግን ጉዳት የደረሰባቸው ድጋሚ እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። በዚህም ውጤት እየታየ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ጳወሎስ ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም