ትምህርት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት ሶስት ወይም አራት ዓመት ጊዜ ውስጥ አስር የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እቅድ ይዟል። በዚህ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ፤ የባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል። አንጋፋው እና ከተቋቋመ ከሰባ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የዚሁ ዕቅድ አካል ሆኖ የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የዩኒቨርሲቲዎች “ራስ ገዝ” መሆን፤ የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነጻነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ የትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጽ ቆይቷል። አስተዳደራዊ ነጻነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የራሳቸውን አደረጃጀት እና መዋቅር የመዘርጋት ስልጣን እንደሚሰጣቸው በማንሳት፤ በዚህ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮቻቸውን ጨምሮ በመዋቅራቸው ውስጥ የሚያስፈልጓቸውን የአመራር እና የአስተዳደር አካላትን በራሳቸው መመደብ እንደሚያስችላቸው ጭምር ተጠቅሷል።
እንዲሁም ለትምህርት ጥራት፣ በተቋማቱ መካከል የትብብር እና የፉክክር መንፈስ በማምጣት ልሕቀትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው። አጠቃላይ ድምር ውጤቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲን ዕውን ለማድረግ እንደሚረዳ ታምኖበታል።
ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚንስትሮች ምክር ቤት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻ ሆነው ስለአካዳሚክ ስራዎቻቸው በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራ የዳበረ ዕውቀት የሚገኝባቸው እንዲሆኑ፤ ሕብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኝባቸው፤ የራሳቸውን የገቢ ምንጮች በማስፋት በሂደትም በራሳቸው በጀት የሚተዳደሩ እንዲሆኑ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ነው። ቀስ በቀስ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚተገበር ረቂቅ አዋጅ ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል። ምክር ቤቱም ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሁለት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል። የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ እንደሚናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ፋይዳው በተለይ ጥራት ያለው ምርምር ለማከናወን እንዲሁም ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ብቁ ተማሪ ለማስመረቅ ዩኒቨርሲቲዎች አሰራራቸውን በራሳቸው መወሰናቸው ትልቅ እምርታ ነው። እንደ ምሳሌ ሲያነሱም ዩኒቨርሲቲዎች ምን አይነት አቅም ያለው ተማሪ ነው ተቀብለን አስተምረን የምናበቀው፣ የሀገራችን የትኩረት አቅጣጫ እንዳለ ሆኖ በምን አይነት የትምህርት መስክ የሚለውን ሁሉ በራስ መወሰን መቻል አንድምታው ብዙ ነው ይላሉ። ከእነማን ጋር አጋር ሆነን ምን አይነት ምርምር እንስራ የሚለውን ለመወሰንም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ለአብነት አውሮፓ እና አሜሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በጣም ፐሮግሬስቭ የሆኑ የትብብር ምርምሮች አሉ፤ እነኚህን እና መሰል ስራዎችን በተገቢው መልኩ ለመስራት ራስ ገዝ የመሆኑ ሁኔታ ስራዎችን የሚያፈጥንልን ነው የሚሆነው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እንደሚያሳድገው የተነገሩት ዶክተር ጀማል በዚህ ረገድ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት ራስ ገዝ እንዲሆኑ የተጀመረውን ጥረት ታሳቢ በማድረግ የራሱን ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል። በዚህም እንደ የዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ሥራ ያደረግነው ራስ ገዝ የመሆን ሀሳቡን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ማስገንዘብ ነው። በዚህ ረገድ የተለያዩ የውይይት መድረኮችና ዝግጅቶች ተካሂደዋል፤ በራስ ገዝነት አስተዳደር ዙሪያ የአዕምሮ ዝግጁነት እንዲመጣ በተለያዩ መድረኮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል። በተለይም ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከምሥረታው ጀምሮ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት የነበረው በመሆኑ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ እንዴት ሀብት ማሰባሰብ እንደቻሉና በምን መልኩ ሥርዓቱን ማስኬድ እንደቻሉ ለማወቅ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ዶክተር ጀማል እንደሚናገሩት፤ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን መርጠው መምጣት እንዲችሉ ዩኒቨርሲቲው ያለውን የሰው አቅም በመገንባት፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንም በማሟላትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ በመሥራት ላይ ነው። ከዚህ ባለፈ በተጓዳኝ አገልግሎቶች የዩኒቨርሲቲውን የፋይናንስ አቅም የማጠናከር ሀብት የማመንጨት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። በዚህ ረገድ በእጃችን ያሉ ፈስሊቲዎች አሉ፤ በግብርና በተለይ በስንዴ ዘር አቅርቦት፣ በሕክምና እና በተለያዩ ሴክተሮች ላይ ሀብት ለማመንጨት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው። የገቢ ምንጭን ከማስፋት አንጻር ዩኒቨርሲቲው ያለውን የእርሻ ሀብቶችን በመጠቀም ምርቶችን በማሰባሰብ፣ ምርጥ ዘርን በማዘጋጀትና ተደራሽ በማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያ ሆስፒታል የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ተጨማሪ ገቢ ለመፍጠር የሚያስችል ዕድል አለው።
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን ከሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባለው አግባብ የራስ ገዝ ሆኖ መሥራት እንዲችል የሚረዳ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ጀማል፤ ዩኒቨርሲቲው በእራሱ የንግድ ድርጅት አማካኝነት ገቢ ማመንጨት የሚያስችለው መመሪያ ተዘጋጅቷል፤ የተዘጋጀው መመሪያ በዩኒቨርሲቲው ቦርዱ ከጸደቀ በኋላ እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት ራሱን ችሎ መዋዕለ ነዋዮችን በማንቀሳቀስ፣ ሀብት እንዲያመነጭ የሚያስችል ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና እስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆን በራሱ ምን ማለት ነው የሚለውን ሲያብራሩ፤ ከዚህ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚተዳደሩት ሙሉ በሙሉ በመንግስት እና በሲቪል ሰርቪስ ስር ነው የሚተዳደሩት እንደማንኛውም የሲቪል ሰርቪስ ስር እንዳለ ተቋም ነው። በራሳቸው ነጻነት የላቸውም። በበጀት፣ ባለሙያ ቅጥር፣ በመሳሰሉት የሲቪል ሰርቪስን ህግ ተከትለው ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት፤ ይሄ ደግሞ በብዙ መልኩ አሳሪ ነው። የዩኒቨርሲቲ ነጻነትን ይገድባል። ለትምህርት ጥራትም የራሱ የሆነ ውስንነት እንዲኖር ያደርጋል።
አዲሱ አሰራር ግን እነዚህን ጉዳዮች በመቀያየር መንግስት የሚያደርጋቸው የበጀት እና ሌሎች ድጋፎች እንዳሉ ሆነው፤ የራሱን የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ነጻነትን ያጎናጽፋል። ያም ሆኖ ግን የመንግስት በጀት እስከ ወዲያኛው ይቀጥላል ማለት አይደለም። በየዓመቱ እንደ አፈፃፀማቸው እየታየ በየጊዜው እየተቀነሰ በሚሄድ ደረጃ በጀት አሁንም ከመንግስት የሚመደብላቸው ሆኖ የውስጥ አሰራራቸውን ማለትም የሰራተኛ ቅጥር፣ የደመወዝ ጉዳይ እና መሰል አሰራሮችን ለማዘመን ከግዥ ጋር በተገናኘ ያሉትን በጣም ጊዜ የሚወስዱ ጉዳዮችን ለማሳጠር የሚያስችሉባቸው የራሳቸው የሆነ አካሄድ እንዲመሰርቱ የሚያበረታታ አስራር መሆኑን ይናገራሉ።
ዶክተር ዘውዱ ሲያስረዱ ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ በሙሉ በመንግስት በሚተዳደሩበት ጊዜ መንግስት እንደሚመድበው በጀት ተማሪዎችንም ይመድባል። በአጠቃላይ ከላይ ወደ ታች የሚመጡ ነገሮች ይበዛሉ። አሁን በራስ ገዝ መተዳደር ሲጀምሩ ግን ከመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩትን ተማሪ በራሳቸው ይመርጣሉ፤ ይመጥናሉ ለዚህም ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለባቸው። ይህ ብቻ አይደለም መምህራንም ሆነ ሌሎች የአስተዳደር ሰራተኞችም ቢሆን ይሄ “ጥሩ ቦታ ነው” ብለው ዩኒቨርሲቲውን መርጠው እንዲመጡ ዩኒቨርሲቲዎች መስራት እና በሌሎችም ተመራጭ መሆን አለባቸው።
ይህ የሚሆነው ደግሞ መጀመሪያ የትምህርት ጥራታቸው ሲያድግ ነው። ስለዚህ የትምህርት ጥራታቸው፣ የካሪኩለም፣ የመማር ማስተማሩ፣ የምርምር፣ አጠቃላይ የማኔጅመንት ጉዳዮች ሁሉ ከነበረበት ደረጃ ከፍ ያለ ሆኖ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳድሮ ገበያ ላይ ተመራጭ ሆኖ መገኘት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ የራስ ገዝ ስርዓቱ የሚያመጣው አንዱ ጥቅም ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ካሉበት አቅም የተሻለ ተመራጭነትን ለማምጣት የበለጠ እንዲሰሩ ያደርጋል። የትምህርት ጥራትን ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የውስጥ የሰው ኃይል (ነባሩም ሆነ አዲስ) የሚመጣው ሰራተኛ አቅሙን በማሳደግ ለሙያዊ እድገት ለመልካም ነገር ሁሉ የሚተጋበት ስርዓት ይፈጠራል። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎች መንግስት ከፍቷቸው ስማቸውን ብቻ ይዘው የመቀጠል ብቻ ሳይሆን የመኖር እና ያለመኖር ጉዳያቸው ዛሬ ላይ በሚያደርጓቸው መልካም ተግባራት የሚወሰን ይሆናሉ ማለት ነው።
ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ላይ ተጠራቅመው ሲታዩ አወንታዊ የሆነ ፉክክር እርስ በእርሳቸው ላይ ይፈጥር እና በጣም ላቅ ያለ አቅም ያላቸው ሆነው በአገር አቀፍ፣ በአህጉርም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማት ኢትዮጵያ ማግኘት እንደምትጀምር ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ዘውዱ ገለጻ፤ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በዚህ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እየጨመረ ሄደ ማለት እንደ ሀገር ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ጥራት ያለው ምርምር ይሰራል ማለት ደግሞ በሀገራችን ውስጥ ላሉ ውጥንቅጦች ሁሉ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ምርምሮች ይሰራሉ ማለት ነው። ይህ በሌላ ቋንቋ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሀገሪቱ እድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና በመጫወት ለችግሮች መፍትሔ ሰጭ ሆነው መቆም ይችላሉ የሚል መረዳት ነው ያለው።
በዚህ ረገድ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዝግጅት ምን እንደሚመስል ያነሱት ዶክተር ዘውዱ፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነባር እና የውጭ ሀገር ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰሮች ያሉበት አንድ የዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ የዝግጅት ቡድን አቋቁሞ እየሰራ ነው። የዚህ ቡድን ኃላፊነት በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ከዚህ ጋር ተያይዞ ያሉትን ልምዶች በማጥናት ሌሎች የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነትን ለማምጣት ምን ሲያደርጉ ቆዩ ? የትኞቹ ተግዳሮት ገጠመቸው? የትኞቹ የተሳካ ሂደት ነበራቸው በሚል በርካታ ጥናቶችን እያጠኑ ለዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ የማስገንዘብ ስራ ተሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት የትምህርት ሚንስቴር ሚንስትር ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ የትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል። አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል ዶክተር ዘውዱ።
ምሁራኑ እንደስጋት ያነሱት፤ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን አዲስ አሰራር በመሆኑ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ አሰራር በቀጣይ ካለው ሀገራዊ ጠቀሜታ አንፃር ሊያገጥሙ ለሚችሉ ተግዳሮቶች የመፍትሔ ሀሳቦችን በማፍለቅ መስራት ይጠበቃል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው በውድድር መንፈስ በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ በትኩረት መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሁለቱም ምሁራን እንደሚስማሙበት፤ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን የተለያዩ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም፤ ከሁለም በላይ ግን ለትምህርት ጥራት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው። ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግም ሀገራዊ ችግሮችን የመፍታት ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ይናገራሉ። በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የውድድር መንፈስን መፍጠርና ጠንካራ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲኖር ማድረግ በራሱ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015