የናይል ተፋሰስን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የሚገኙ ሐይቆችና ግድቦች ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በሚያስከትሉ የውሃ ላይ መጤ አረሞች (water hyacinth) እየተጠቁ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መጤ አረሞች መካከል ደግሞ የእንቦጭ አረም (Eichhornia crassipes) ዋነኛው ጉዳት አድራሽ ነው።
እንቦጭ በስፔን ጓዲአና ወንዝ ተፋሰስ አካባቢና በዙምባብዌ ሃራሬ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቺቬሮ ሐይቅ ላይ በመንሰራፋት በብዝሀ ሕይወት ላይ ዘርፈ ብዙ ጥፋት አስከትሏል። በኢትዮጵያም በጣና ሐይቅ ላይ የተዛመተው አረሙ የሐይቁን ውሃ ከመምጠጥ ባለፈ የአሳ ሀብቱ እንዲቀንስ ብሎም የውሃ ላይ ትራንስፖርት እንዲስተጓጎል ምክንያት እየሆነ ነው።
መጤ አረሙ አባይ ወንዝ ከጣና ለቆ በሚወጣበት ጨረጨራ ግድብ አካባቢ ጭምር ከመከሰቱ ባለፈ በሌሎች አነስተኛ ግድቦችና ሐይቆች ላይም መጠኑን እያሰፋ መሆኑን የእጽዋት ሳይንስ ባለሙያዎች ያመለክታሉ።
ያደጉ አገራት አረሙን ለማጥፋት ለባዮ ኢነርጂ ግብዓትነትና ባዮፈርቲላይዘር ምርትነት፣ የአረሙን ተክል ለእጅ ስራና ለቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች በማዋል እንዲሁም ለእንስሳት መኖና ሌሎች መተግበሪያዎች ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።
በኢትዮጵያም እንቦጭን የሚያጠፋ መድኃኒት አግኝቻለሁ የሚሉ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ብቅ ቢሉም ውጤታማነታቸው አሁንም ድረስ አጠያያቂ ሆኖ ቆይቷል።
በአማራ ክልል በተቋቋመው የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን እንቦጭን የማጥፋቱ ሂደት በአብዛኛው በአርሶ አደሮችና በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት በእጅ የመንቀል ስራ ላይ ያተኮረ ነው።
የሰው ኃይል በመጠቀም አረሙን በእጅ ማስወገድና በማሽነሪ የመጠቀም አማራጮች ሲተገበሩ ቆይተዋል። ለአረሙ ማስወገጃ ከውጭ አገራት በድጋፍ መልክ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ማሽኖች ግን ደለል ባለባቸው የሐይቁ ዳር አካባቢዎች የበቀሉ እንቦጮችን በማጥፋት ረገድ ውጤታማ አልሆኑም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በውሃ ላይ ተንሳፋፊ የሆኑት ማሽኖች በሐይቁ ዳር ያለው የውሃ ከፍታ በበቂ ሁኔታ እንዳይንቀሳቀሱ ስለሚያግዳቸው ነው።
በተለያዩ ዓለማት ተግባራዊ የሆነውና አዋጭ ሆኖ የተገኘው የመጤ አረም ማስወገጃ ስልት ደግሞ ስነ-ሕይወታዊ በሆኑ ባዮሎጂካል መንገዶች መጠቀም በተለይ መጤ አረሙን ማስወገድ ላይ ያተኮረ ነው። እንቦጭና መሰል የውሃ ላይ አረሞች እንዳይዛመቱ በባክቴሪያ፣ በፈንገስና በተለያዩ ተባዮች እንዲጠበቁ የሚደረግበት ሳይንሳዊ መንገድን ባደጉት አገራት ጥቅም ላይ ውሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ኬሚካል በመጠቀም አረሙን የማጥፋት ስልትን ጥቅም ላይ ያዋሉ የአውሮፓ አገራት አሉ።
የተለያዩ አገራት በውሃ አካሎቻቸው ላይ የእንቦጭ አረም የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ኬሚካልን፣ ባዮሎጂካል ማጥፊያ መንገዶችንና በማሽን የመንቀል አማራጮችን በአንድነት ቢጠቀሙም ከአረሙ ስነ-ሕይወታዊ ባህሪ የተነሳ እንቦጭን መቆጣጠርና የሚዛመትበትን መጠን መቀነስ እንጂ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አዳጋች ሆኗል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሴ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የእንቦጭ አረም በውሃ አካላት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን በመጥቀስ የአረሙን የመዛመት ሂደት ለመግታት ከእጅ ነቀላ ባለፈ የተለያዩ ሳይንሳዊ ዘዴዎችንም በዋነኛነት መጠቀም ይገባል ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ሰው የሚማረው አንድም ከፊደል አንድም ከመከራ ነው፤ አንድም በሳር ‘ሀ’ ብሎ አንድም በአሳር ‘ዋ’ ብሎ ነው” ሲሉ ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የተናገሩትን ጠቅሰው ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያም እንቦጭ ካደረሰባት ጉዳት ለመላቀቅ በምርምር የተፈተሹ ሳይንሳዊ መንገዶችን ወደተግባር ማስገባት እንዳለባት ይመክራሉ።
ፕሮፌሰር ሽመልስ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በተሰናዳ መድረክ ‹‹እንቦጭና ሌሎች ወራሪ ዕፅዋት ለታዳሽ ኃይል እና የአካባቢ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎች ያላቸው ፋይዳ፤ የኤሌክትሮ ኬሚስት ዕይታ›› የተሰኘ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው እንቦጭን ወደ ኃይልነት በመቀየር ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ተክሎችን ለተለያዩ የኃይል አማራጮች መጠቀም የሚቻልበት መንገድ እንዳለ ስዊድን አገር በተሳተፍኩባቸው የምርምር ስራዎች ዕውቀቱን አዳብሬያለሁ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ የምርምር ልምዱን በመጠቀም እንቦጭን ለታዳሽ ኃይል መዋል የሚቻልበት መንገድ እንዳለ በጥናቴ አሳይቻለሁ ይላሉ።
ሃሳባቸውን ሲያስረዱም በአሁኑ ወቅት ከኮምፒዩተር ጋር የተገናኙ መጠቀሚያዎች፣ ስልክ፣ ሰዓት፣ እንዲሁም ለተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች በኤሌክትሪክ አሊያም በፀሐይ ኃይል ቻርጅ የሚደረጉ ባትሪዎችን መያዛቸውን ይጠቅሳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚያ ባትሪዎች ደግሞ በውስጣቸው አካባቢን በሚበክሉና ዋጋቸው ውድ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የተሞሉ ናቸው። በተለይ ክሮሚየም የተባለውን ንጥረ ነገር ተጠቅመው የሚዘጋጁ የስልክና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን ለማንቀሳቀስ የሚረዳ የባትሪ ኃይል በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ በሳይንስ ተረጋግጧል።
ክሮሚየም አካባቢን የሚበክል ከመሆኑ ባለፈ ካንሰርን የሚያስከትል ኬሚካል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን ‹‹ኤሌክትሮቫለንት ክሮሚየም›› የተሰኘውን ኬሚካል ተጠቅመው ምርት የሚያዘጋጁ ፋብሪካዎች አሉ።
በሌላ በኩል ለኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ኃይል የሚሰጡ ባትሪዎች ሊድ በተሰኘ ኬሚካል አማካኝነት ነው የሚሰሩት። ሊድ ደግሞ በቀላሉ ሊወገድ የሚችል ባለመሆኑ አካባቢን የመበከል ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በተለይ ሊድ በአግባቡ ካልተወገደ የነርቭ ክፍሎችን በማጥቃት፣ የማየት ችሎታን በመቀነስና የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት በማምጣት እንደሚታወቅ ፕሮፌሰር ሽመልስ ያስገነዝባሉ።
ለጤና ጎጂ የሆኑትን የባትሪ ኃይል ግብዓቶች ሊድ እና ክሮሚየምን አካባቢን በማይበክል ንጥረ ነገር ለመቀየር ደግሞ ተክሎች አማራጭ ሆነው በሰለጠነው ዓለም ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። ባትሪዎቹ አካባቢን የማይበክሉና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ በሆነ ግብዓት እንዲዘጋጁ የደን ሀብቶችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበት ሳይንሳዊ ምርምር በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእስያ ተግባራዊ ሆኗል ይላሉ።
ለአብነት ቻይና በቀርከሃ ምርት ትታወቃለች። የዓለምን ሁለት ሶስተኛ የቀርከሃ ምርት የምታዘጋጀውም ይህች ሀገር ናት። ቻይናዎች ቀርከሃን በተለየ መንገድ በላብራቶሪ ሂደት በማቃጠል የሚገኘውን ኬሚካል ለባትሪ ድንጋይ ምርት ግብዓትነት እየተጠቀሙ ነው።
በእኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ ጠቃሚ የሆኑትን ደኖች ለባትሪ ኃይል ግብዓት ከማዋል ይልቅ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙ እንቦጭና በተለምዶ ወያኔ ዛፍ የተሰኙ አረሞችን ለዚህ አገልግሎት ማዋል ቢቻል የአረሞቹን ስርጭት በመቆጣጠር በተጓዳኝ ጥቅም ላይ ወደሚሰጥ ስራ መቀየር የሚያስችል ሁለት አላማ ይኖረዋል ሲሉ ያስረዳሉ።
በዚህ ረገድ እንቦጭ ተክል በኢትዮጵያ ለባትሪ ምርት ግብዓት የሚሆኑ የኬሚስትሪ ውጤቶችን በመተካት ረገድ የላብራቶሪ ምርምር ማድረጋቸውን ነው ፕሮፌሰር ሽመልስ የሚጠቁሙት።
ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው የደን ውጤቶች ላይ ለባትሪ መስሪያ የሚያገለግለውን ግብዓት ከምናወጣ /Extract/ ይልቅ የእንቦጭ ተክልን በመጠቀም አስፈላጊውን የባትሪ ማምረቻ ግብዓት ማግኘት እንችላለን በሚል በተካሄደ ምርምር አጥጋቢ ውጤት መገኘቱን ይጠቁማሉ።
እንደ ሌሎች ተክሎች ሁሉ እንቦጭ ውስጥ የሚገኘውን “ሊግኒን” የተሰኘውን ንጥረ ነገር በመጠቀም አካባቢን ሳይበክሉ መወገድ የሚችሉ የባትሪ ድንጋይ ግብዓቶችን ማምረት ይቻላል።
በላብራቶሪ ሂደት የእንቦጭ ተክልን ምንም አየር በሌለበት መንገድ በማቃጠል የሚፈለገውን የባትሪ ኃይል የሚሰጥ ካርበን ማግኘት ተችሏል። ይህን ግብዓት በአግባቡ መጠቀም የሚችል ኢንዱስትሪ በመገንባት ለሀገር የሚተርፍ ውጤት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ አለ ሲሉ ተመራማሪው ያስረዳሉ።
እንቦጭን ማጥፋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ስናጠፋው ደግሞ ለሌላ ጥቅም እያዋልነው ሲሆን የበለጠ አዋጭ ይሆናል። የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ጣና ሐይቅን ጨምሮ በበርካታ የውሃ አካላት ብዝሀ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን አረም ለማስወገድ ደግሞ የኬሚስትሪ ምርምሮች ወሳኝነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ ጥናቶች በተለይ ከተለያዩ የመኪና ባትሪና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ጋር ተያይዞ ጥቅም ላይ የዋለው ሊድ በተለያየ ባዮሎጂካል መንገድ ወደአፈር ውስጥ ብሎም ወደምንጠጣው ውሃ የመግባት ዕድል አለው። ይህ ሊድ በተለይ የህጻናትን የማሰብ ችሎታ የመቀነስና የማስታወስ ችሎታ የማዳከም እንዲሁም በአዋቂዎች ላይ የደም ግፊትና የተለያዩ የጤና ጉዳቶችን የማስከተል አቅም አለው።
በተጨማሪ ከእንቦጭ የሚገኙ የተለያዩ የኬሚካል ውጤቶች ደግሞ አካባቢን የማይበክል ባትሪ ለማዘጋጀት ከመዋላቸው ባለፈ በሊድ ኬሚካል አማካኝነት የተበከለ ውሃን ለማጣራት እንደሚረዱ ነው ፕሮፌሰር ሽመልስ የሚገልጹት።
ስለዚህ እንቦጭ ከጎጂ አረምነቱ ባለፈ በሳይንሳዊ ሙከራዎች ወደተለያዩ ጥቅም ሰጪ ግብዓቶች መቀየር እንደሚቻል በኬሚስትሪ ዘርፉ ምርምር ተደርጓል። ይህን የሳይንስ ምርምር ውጤት በስፋት ወደተግባር ለማዋል ደግሞ ከኢንዱስትሪዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል። በዋናነት እንቦጭን ተጠቅሞ አካባቢን የማይበክልና በዋጋ ደረጃም አዋጭ የሆነ የባትሪ ኃይል ለማምረትና አረሙን ለተሻለ ውጤት ለመጠቀም የምርምር ውጤቱን የሚቀበሉ አምራቾች ያስፈልጋሉ።
በዚህ ረገድ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ኃይል የሚሰጥ ባትሪም ሆነ የመኪና ባትሪ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችና ግለሰቦች የምርምር ውጤቱን እንዲጠቀሙበት አስፈላጊውን ስራ በትብብር ለማከናወን ዝግጁ ነኝ ሲሉ ፕሮፌሰር ሽመልስ ይጠቁማሉ። በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ የሚከናወኑ የሳይንስ ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር በመቀየር ለአገር የሚጠቅም ስራ ላይ ማዋል ይገባል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነፍሳት ሳይንስ ላይ ያተኮረው የኢንቶሞሎጂ ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱ በበኩላቸው፤ እንቦጭን በሳይንሳዊ ምርምር ለኃይል አማራጭ ግብዓትነት ለመጠቀም የተከናወነው ምርምር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከዚህ ባለፈ ግን እርሳቸውና ጓደኞቻቸው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ መጤ አረሞችን ማጥፋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ጥናት ማድረጋቸውንና በምርምራቸው በውሃማ አካላት ላይ የተንሰራፉ እንደ እንቦጭ ያሉ አረሞችን በሳይንሳዊ መንገድ ለማዳበሪያነት ማዋል የሚቻልበት አማራጭ መኖሩንም ማረጋገጣቸውን ያመለክታሉ።
ከዚህ ባለፈ እንቦጭን ለባዮ ኢታኖል ምርትና በላብራቶሪ ሂደት በማሳለፍ ተክሉ እንዲፈጭ ተደርጓል። ከዚህም የፕሮቲን መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ንጥረ ነገር ስላለው፤ ለእንስሳት መኖነት ማዋል ይቻላል። በዚህና በተለያዩ መንገዶች አረሙን መቆጣጠር የሚቻልበት ሳይንሳዊ መንገዶችን ማዳበር ያስፈልጋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ እንቦጭን ለኃይል አማራጭነት መጠቀም እንደሚቻል ያሳየውን ምርምር በስምጥ ሸለቆ አካባቢ እየተሰሩ ከሚገኙ ጥናቶች ጋር በማቀናጀት አረሙን ከማጥፋት ባለፈ ለተሻለ ጥቅም የሚውለበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ያለምፀሐይ መኮንን በበኩላቸው፤ ብዝሀ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሱ በሚገኙ እንደ እንቦጭ ያሉ መጤ አረሞች ላይ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮችን መጠቀም የሚጠበቅብን ጊዜ ላይ ነን ሲሉ አመልክተው፣ በዚህ ረገድ ስለሀገሩ የሚያስብ ጆሮ ያለው ሁሉ ሊሰማ ይገባል ይላሉ።
ሳይንሱን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከአገር ግንባታ፣ ከጤናና ከአካባቢ ጥበቃ ረገድ ውጤት ማግኘት ይቻላል። ለዚህም ተመራማሪዎችን በመደገፍና የላብራቶሪ ጥናታቸውን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተጉበሩት ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ ፕሮፌሰሯ ገለጻ፤ ሳይንሳዊ ግኝቱ አረሙን ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ እየተመረቱ ያሉ ለጤና ጎጂ የሆኑ የባትሪ ግብዓቶችን ለመተካት የሚረዳ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ምርምር ነው። ሳይንሳዊ ግኝቱ ተፈላጊውን መፍትሄ እንዲያመጣ ምርምሩን አጠናክሮ መቀጠልና በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015