አገራችን ገንዘብ አሳትማ መገበያየት የጀመረችው በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ። በዘመኑም የወርቅ፣ የነሐስና የብር ሳንቲሞች ነበሩ። በጊዜ ሂደት ውስጥ በገንዘብ የመጠቀም ባህሉ እየሳሳ ሲመጣ የመገበያያ ሳንቲሞች እየጠፉ ሄደዋል። ይህንንም ተከትሎ ዕቃን በዕቃ የመለዋወጥ ቀጥሎም በአሞሌ መገበያየት ተጀምሯል። በኋላም በማር ትሬዛ።
በገንዘብ የመጠቀም ልምድ እንደገና በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተጀመረ ሲሆን፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ሳንቲሞች ለግብይይት ዳግም መዋል ጀምረዋል። ከጥቂት አመታት በኋላም በአገሪቱ ባንኮች ተከፍተው ሥራ ጀምረዋል። የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባንክ የሚለውንም ቃል ሲፈታው ጥሬ ገንዘብና እንደ ወርቅ ያሉ ማዕድናት ተጠብቀው የሚቀመጡበት እንደ ሳጥን ያለ ዕቃ፤ ጥሬ ገንዘብን እንደውለታው ወለድ እየከፈለ ወይም ያለወለድ የሚያስቀምጥ ወይም ለደንበኞች በወለድ የሚያበድር፤ ልዩ ልዩ ሰነዶችንና ማዕድናትን በአደራ የሚያስቀምጥ የአገልግሎት ሒሳብ እያስከፈለ የሓዋላና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ድርጅት ይሉታል።
የመጀመሪያው ባንክ መከፈት ተከትሎ ቀስ በቀስ የባንክ አገልግሎት በአገሪቱ እየተስፋፋ መጣ። በተለይም በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ዘመን አገልግሎቱ በስፋት በመላው አገሪቱ መሰራጨቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በደርግ ዘመን እያቆጠቆጡ የነበሩ የግል ባንኮች በአዋጅ ተወርሰው አገልግሎቱ በመንግሥት ደረጃ ብቻ የሚሰጥ ሆኗል። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ነፃ የኢኮ ኖሚ ገበያን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር የግል ባንኮች ዳግም ወደ ሥራ መግባት ጀምረዋል። ሕዝቡም አማራጭ የባንክ አገልግሎትን ማግኘት የሚያስችል ዕድል አጋጥሞታል። የግል ባንኮቹ ወደ ሥራ መግባት በዘርፉ ተፎካካሪነትን መፍጠር ያስቻለ፤ በዘርፉ የተሰማሩ የፋይናንስ ተቋማት አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ፤ እንዲያዘምኑ አዎንታዊ ፉክክር እንዲያደርጉ አድርጓል። ዜጎች በዘርፉ የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ፤ በአገሪቱ ያሉ የባንክ ቅርንጫፍ እንዲጨምሩም ረድቷል።
በአዲስ አበባ ብቻ ከሰንጋ ተራ ጀምሮ ከብሔራዊ ባንክ በታች በቸርችል ጎዳና ለገሀር አካባቢ ጭምር ጎላ ጎላ ያሉት ረጃጅም ሕንፃዎች የባንኮችና የኢንሹራንሶች ዋና ዋና መሥሪያ ቤት ናቸው። ሕንፃዎቹ ሲሠሩ ለብዙ ዜጎች የሰጡትን ጊዜያዊ የሥራ ዕድልን ጨምሮ ፤ ሕንፃዎቹ ለከተማዋ ውበቷ ሆነዋል። ለአዲስ አበባ እንደ ስሟ እየደመቀች እንድትሔድ ረድተዋል። ስለ ባንኮቹ ከዚህም በላይ ማለት ይቻላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን እንደ ችግር የሚነሳባቸው ትልቁ ጉዳይ ብዙ ድሀ ዜጎች የቁጠባ ገንዘብ ለባለፀጋዎች (ሀብታሞች) የማበደራቸው እውነታ ነው። የድሀውን ገንዘብ ለሀብታም እያበደሩ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት የሚቻል አይመስለኝም። መሥራት እየቻለ የሚያበድረው ባንክ በማጣት ድህነትን ታቅፎ ቀን የሚቆጥር ዜጋ በበዛበት አገር የበንኮቹ አሠራር በብዙ መልኩ መፈተሽ እንዳለበት አምናለሁ።
በሰለጠኑት አገሮች ፕሮፖዛል ቀርጸው ጭምር ገንዘብ ላጠረው ባንኮች ያበድራሉ። በግሉ ፕሮፖዛል የቀረጸውንም አዋጪ መሆኑን ገምግመው ያበድሩታል።ለተበዳሪውና ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ባንኮቹም ተበዳሪዎቹም አገሪቱም ትርፋማ ይሆናሉ። አንዳንድ ባንኮች በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያመጡ ሰዎችን መርጠው በተመረቁበት ሙያ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ፕሮፖዛል ቀርጸው አበድረው በጋራ እንዲሠሩ ያደርጋሉ። በዚህም የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። በእኛ አገር ባንኮች ይህንን አሠራር ሊተገብሩ ይገባል ባይ ነኝ። አሁን አሁን የባንኮቹ ፉክክር ሠራተኞችን በመያዝ እና ሰዎችን የባንክ ሒሳብ በማስከፈት ላይ ያተኮረ ብቻ ይመስላል።ለዚህም በከተሞቻችን አሁን አሁን ባንክ ሂሳብ ክፈቱልን የሚሉ (የባንክ ሠራተኞች ይመስሉኛል) በየመንገዱ ሰዎችን አስቁመው የሚወተውቱና የሚማፀኑ ሠራተኞች ማየት ይበቃል። እኔ ሳላውቀው መንገድ ዘግተውብኝ ወረቀት ነገር ሲያሳዩኝ ቸኩዬ ስለነበር ትኩረት ሳላሰጣቸውና ሳልሰማቸው ‹‹እግዜር ይስጥልኝ!›› አልኳቸው።
ሰዎቹ ሳቁብኝ፤ ምንቸገረኝ ? እኔ ሰዎቹ ምጽዋት የሚጠይቁኝ መስሎኝ ነው። ወደፊት እየሄድኩ እንዳለ የባንክ ደብተር የያዙ ሰዎች ሳይ ያላፍኳቸው ሰዎች አጋሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። የተማጸኑኝ እንድመጸውታቸው ሳይሆን የባንክ ሂሳብ እንደከፍትላቸው ነበር። በየመንገዱ የባንክ ሂሳብ ክፈቱ እያለ የሚማጸነው ‹ተፎካካሪ› ባንክ ስለበዛ ያው ዞሮ ዞሮ ልመና ቢመስለኝ እንዳትቀየሙኝ። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጥ አድርጎ የያዘው ግብርና ነው ሲባል እሰማለሁ። እኔ ግን ምን ቸገረኝ ያሻቸውን ይበሉ። ብሰማም አልስማማም። ግብርናው ኢኮኖሚውን ቀጥ አድርጎ ሳይሆን እየተንቀጠቀጠ ነው የያዘው። ወዳጄ ግብርናው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በእርግጥ ቀጥ አድርጎ ቢይዘው ኖሮ፤ አገርህ እርዳታና ብድር ፍለጋ ወደ አደጉ አገሮች ጠጋ ጠጋ አትልም ነበር።
የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት በመንቀጥቀጥ የያዘውን ግብርናን፤ ቀጥ ለማድረግ በእርግጥ ባንኮች ለገበሬዎች የሚጠቀስ ሥራ አልሠሩም። ያደረጉት አበርክቶ አይታየኝም። (ይቅርታ ግን ለአበባ እርሻ አበደሩ ሲባል እሰማ ነበር፤ መዐዛው የጠፋው የአበባው እርሻ ረገፈ ? ተቀጠፈ ? ተረፈ ወይስ አተረፈ እንበለው ? ለካ ይሄም ግብርና ነውና?)። ገበሬ እርሻውን ላዘምን ቢል ሊያበድረው የሚችል ባንክ የለም። ዘመናዊ ማረሻ፣ ሰብል ማጨጃ፣ እና መከስከሻ መሣሪያዎች እንዲሁም ለመስኖ የሚሆን የውሃ ማጠጫ ጄኔሬተር ሊገዛ ቢፈልግ ዐቅሙ አይፈቅድለትም።ገበሬዎች በጋራ ተበድረው የውሃ ማጠጫ ጄኔሬተር ቢገዙ የመስኖ እርሻው ይሳለጣል፣ ድህነት ይጠፋል፤ ኑሮ ውድነት ይቀላል።
በመስኖ የሚለሙ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ድንችና ሽንኩርት፣ ጎመንና ካሮት እያመረቱ ለከተሞች ይተርፉ ነበር።ከብቶቻቸውን በመቀለብና በማደለብ እየሸጡ ከባለሀብቶች ጎራ ይቀላቀሉ ነበር። ባንኮችም እያተርፉ ሂሳብ ክፈቱ ብሎ በከተሞች ከመማጸንም ከመለመን ይተርፉ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን የወጣው መግለጫ በአገሪቱ 109 የፋይናንስ ተቋማት እንደሚገኙ ያስረዳል።31 ባንኮች ሲሆኑ አምስቱ ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ደረጃ፣ አንድ የጠለፋ ዋስትና የሚሰጥ ተቋምን ጨምሮ 18 ኢንሹራንስ ድርጅቶች አሉ። አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት 44 ናቸው። ካፒታል ጉድስ ሊዚንግ ኩባንያ (የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ) ስድስት ናቸው፡፡
በሰኔ 2014 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የግልና የመንግሥት የባንኮቹ ቅርንጫፎች ምጥጥን በሕዝብ ብዛት አንድ ቅርንጫፍ ለ11ሺህ 516 ሰዎች ያገለግላል። የኢትዮጵያ ባንኮች ካሏቸው ሙሉ ቅርንጫፎች 35.5 በመቶ በአዲስ አበባ ብቻ እንዳሉ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል። ከዚህም ውስጥ ትልቁ የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኮች ቅርጫፍ በብዛት የሚታየው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው። ማለትም በመርካቶ የንግድ አካባቢ። ይህም በቀን በአካባቢው የሚዘዋወረውን የግብይት ብር ለመተመን ያስችላል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ለአስቀማጮቻቸው ከዋጋ ንረት በእጅጉ ያነሰ ወለድ በመክፈል ይተቻሉ። በአማካይ 35 በመቶ በሆነ የዋጋ ንረት ባንኮች ለአስቀማጮች 7 በመቶ ብቻ ወለድ በመክፈል ተበዳሪዎች ከዋጋ ንረት በታች ብድር እየሰጡ ባንኮቹ በጣም አትራፊ ይሆናሉ። ሰው ባንክ ገንዘብ ማስቀመጡ ለወለድ በማሰብ ሳይሆን ለደህንነት በማሰብ ነው ። ማለትም ‹‹ሌባ ቀማኛ እንዳያጠቃኝ እንዳይቀማኝ›› ብሎ ። የወለድ መጠኑን ከፍ በማድረግ ሰዎች ወጪ ከማድረግ ይልቅ ብር ገቢ እንዲያደርጉ ማድረግ ይቻላል። በዚህም ብዙ ሰዎችን የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ ማድረግ ይቻላል። ብር ባንክ ማስቀመጥ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠሪያ አንዱ መንገድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት እውነታ ነው። የኮሮና ወረርሽኝ በመጣ ሰሞን፤ ዜጋው ገንዘብ እጅ በእጅ ከመቀባበል በባንክ እንዲያስተላለፍ በመንግሥት መመሪያ በመውጣቱ ብዙዎች የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ አስችሏል።
ሰሞኑን ብሔራዊ ባንክ የግማሽ በጀት ዓመቱ አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸሞች ውስጥ የተበዳሪዎች ቁጥር ዕድገት ያላሳየ መሆኑ ያስረዳል።የባንኮችና የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ተበዳሪዎች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት በ7.8 በመቶ ቀንሶ 4.87 ሚሊዮን መሆኑ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ለተበዳሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከነበረው አለመረጋጋት በተያያዘ ያጋጠመ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በፈረንጆቹ 2021 የዋጋ ንረቱ 26 በመቶ፤ በ2022 ደግሞ ወደ 37 በመቶ እንዳደገ መረጃዎች ያሳያሉ። የአገራችን የዋጋ ንረት በአማካይ በዓመት 37 በመቶ እየጨመረ ለገንዘብ አስቀማጮች በአማካይ ሰባት በመቶ ብቻ በዓመት ወለድ መክፈል ፋይዳ ቢስ ነው። ከዓመት በፊት በባንክ ያስቀመጥከው 50ሺህ ብር ስታወጣው የተወሰነ ወለድ ጨምሮ የመግዛት ዐቅሙ ግን ተዳክሞ ታገኘዋለህ ።
የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በጤናማ አቋም ላይ የሚገኙ ናቸው ቢባልም፣ የባንኮችና የአነስተኛ የብድር ተቋማት ተበዳሪዎች ቁጥር በ7.8 በመቶ መቀነሱን የፋይናንስ ተቋማቱ ጤና ይጠና ያሰኛል። በተለይም ባንኮቹ በልማት ሂደት ውስጥ ያላቸውን ከፍያለ ድርሻ መወጣት በሚያ ስችል ቁመና ላይ መገኘት ካልቻሉ በየአመቱ የሚነግሩን የትርፍ ቁልል በራሱ ትርጉም አይኖረውም። ይህ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር አገርን እንደአገር የሚጎዳ ትልቅ ስብራት ሆኖ መከሰቱ የማይቀር ነው። ከዚህ አደጋ አገርን ለመታደግ ባንኮቻችን ካሸለቡበት ሊነቁ ይገባል !። ለዚህ ደግሞ የሚመለከተው አካል በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም