
ውብ ሀገሬ፣ ውብ ሀገሬ፣ ውብ ሀገሬ፤
ባንች እኮ ነው መከበሬ፣ መከበሬ፤
እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤
እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል፤
…. ውብ ሀገሬ፣ ውብ ሀገሬ ……
ይሄንን መዝሙር ያኔ ተንኮል ሸር በሌለበት፣ ምቀኝነት ክፋት ባልሰለጠነበት፣ ሴራ ባልተጎነጎነበት ንጹሕ ወረቀት በሆነው የልጅነት አዕምሯችን ዘምረን ያደግን የምናስታውሰው ነው። መዝሙሩ የሚያስረዳው ሰው ያለ ሀገሩ ባዶ እንደሆነና ሀገር ከዕምነት፣ ከቋንቋ፣ ከዘር፣ ከእናት አባት፣ ከወገን ከዘመድ በጥቅሉ ከምንም በላይ መሆኑን ነው። ኃዘን፣ መከራ፣ ችግር፣ ረሀብ፣ መታረዝ፣… ሀገር ካለች ሁሉ በሀገር ላይ ይቻላል። አይደለም ደስታ ልቅሶ በሀገር ያምራል። የሀገሬው ሰው “ሞቴን በሀገሬ አድርገው” ብሎ ፈጣሪውን የሚማጸነው ለዚህ ነው። ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሁሉ ነገራችን የመጨረሻዋ ቋጠሮ ብርቱ ክንድ ናት።
ይህቺን የነጻነት ቀንዲል የጥቁር ሕዝቦች ወይም ማኅበረሰብ የነጻነት ዓርማ የሆነች ሀገር ታፍራና ተከብራ ለዛሬ እንድትደርስ የትናንት አባቶቻችን መራራ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። እንዲህ በዋዛ ዳር ድንበሯ፣ ሕዝቧ፣ መልክዓ ምድሮቿ ተጠብቀው በነጻነት ለዛሬ አልደረሰችም። ይልቁንም በትውልድ ቅብብሎሽ በተከፈለ መራራ መስዋዕትነት የተገነባች የማትደፈር ተራራ ናት።
ታዲያ ሳትደፈር በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ እኛ ላይ ደርሳለች። እናም ይች ሀገራችንን ዛሬን በአንድነት ተከባብረን ኖረን፣ የራሳችን የታሪክ አሻራ አኑረን፣ ለነገው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት እያንዳንዳችን አለብን። ምክንያቱም ትናንት ለኛ እንድትደርስ ዋጋ የከፈሉ አባቶች እዳ አለብንና ነው። ይህን ባናደርግ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ሀገር ነጻነቷ ተጠብቆ ለዛሬ እንድትደርስ ያደረጉ አባቶቻችን አጥንታቸው ይረግመናል።
ነገር ግን ሀገር ነጻነቷ ተጠብቆ ለዛሬ እንድትደርስ የተከፈለውን ዋጋ ዘንግተን አንዴ በሃይማኖት፣ ሌላ ጊዜ በቋንቋ፣ ሻገር ሲልም በብሔርና በዘረኝነት ልክፍት ታውረን እርስ በእርስ ስንጋጭ እንዲሁም በሴራ፣ በአፍቅሮተ ንዋይ፣ በስግብግብነት እርስ በእርስ እየተጠላለፍን . . . ወ.ዘ.ተ ሀገራችንን እጃችን ላይ አጥተናት ማጣፊያው አጥሮብን እንደቃየል ስንቅበዘበዝ ለመኖር እየተሯሯጥን እንገኛለን።
በዚህ ክፉ መንገዳችን ደግሞ ሀገራችን የሞት አፋፍ ላይ ቁማ እያጣጣረች ትገኛለች። ገዳዮቿ ደግሞ ማሯን ልሰን፣ ወተቷን ጠጥተን፣ ሥጋዋን በልተን በጉያዋ አቅፋ ያሳደገችን እንዲሁም አፈርና ውሃዋን ተራጭተን እንደ እንቦሳ ጥጃ ቦርቀን በደጇ ያደግን እኛው ልጆቿ ነን።
ብዙዎች የሚያፈርሷት የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቿ ናቸው ይላሉ፡፡ ነገር ግን እኔ “የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቿ ሊያፈርሷት ነው” የሚለውን አልቀበልም። “ለምን?” ቢባል ጠላት ሁሌም እንዳለ ይታወቃል። ጠላት የትኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ለማሸነፍ ይጥራል። ነገር ግን “ጠላት ለማሸነፍ ወይም ለማጥቃት የሚመጣበትን የትኛውንም መንገድ መመከት ነው” አሸናፊ የሚያደርገው። ነገር ግን “ለሥልጣን አልያም የአፍቅሮተ ነዋይ ጥሙን ለማርካት” ሲባል ሀገርን ለማፍረስ፣ የወገንን አንገት ለማስደፋት ከጠላቶቻችን ጋር የምንተባበረው እኛው በደጇ ቦርቀን ያደግን የእናት ጡት ነካሽ ልጆቿ ነን። ጦራቸውን አዝምተው ለመውረርና ለማፍረስ ያልተሳካላቸው ታሪካዊ ጠላቶቿ በሴራ ሀገሪቱን ለማፍረስ፣ ሕዝቧን ለማዋረድ እኛው ልጆቿን ነው የሴራቸው ማስፈጸሚያ አድርገው እየተጠቀሙብን ያሉት።
ታዲያ “የዚህ የሴራቸው ማስፈጸሚያ ያልሆነ ሰው ማነው?” ብለን ስንጠይቅ ብዙዎቻችን በአንድም በሌላ መንገድ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሴራ ማስፈጸሚያ ሆነና ባይ ነኝ። ምክንያቱም ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ተባብሎ በአንድ የኢትዮጵያ ጥላ ሥር ተዛዝኖና ተከባብሮ የመኖር ባሕላችን ጠፍቶ አንዴ በብሔር፣ ሌላ ጊዜ በቋንቋ እንዲሁም በኃይማኖት እየተባላን እንገኛለን። የአንድ ሀገር ሰዎች “ከየት መጣህ፣ ከዚህ ውጣ፣ ይሄ የኔ ነው፣ ያ የኔ ነው” እየተባባልን እርስ በእርስ እየተባላን፤ እየተጋደልን እንገኛለን።
ሌላው ነጋዴው፣ ሐኪሙ፣ መምህሩ፣ ጋዜጠኛው፣ መሐንዲሱ፣ በአጠቃላይ ሁሉም አገልግሎት ሰጭ ሠራተኛው የበኩሉን ለሀገር እና ወገኑ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ነው? ቢባል የአብዛኛው መልስ ምን እንደሆነ ይታወቃል። ነጋዴው በተንሻፈፈ ነጻ ገበያ ስም ኅብረተሰቡን እርቃኑን እስኪቀር ድረስ ያልባል፤ ሐኪሙ ሳይማር ያስተማረውን ድሃውን ማኅበረሰብ ለማከም ተጠይፎ ከበርቴዎችን ምን ይሻላችሁ በሚልበት፣ ፖለቲከኛው በሕዝብ ሕይወት በሚቆምርበት፤ አስተማሪው እውቀትን ሳይሆን ዘረኝነትን በሚሰብክበት፤ ጋዜጠኛው ለሙያው ሥነምግባር ተገዥ ሆኖ ከወገንተኝነት የጸዳ መረጃ በማያደርስበት፤ በየመንግሥት ተቋማት ያለው አገልግሎት ሰጭ ሠራተኛው “ከየት መጣህ? ብሔርህ ማነው?” ሳይልና የእጅ መንሻ ሳይቀበል ለኅብረተሰቡ አገልግሎት በማይሰጥበት፤ ባለስልጣኑ ሥልጣኑን ተገን አድርጎ የሀገር ሀብት በሚዘርፍበት፤ እንዲሁም ሁሉንም በእኩል አይን ማስተዳደር ሲገባው አንዱን ልጅ፣ ሌላኛውን የእንጀራ ልጅ አድርጎ በሚያስተዳድርበት፤ ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ባሕልና ወጉን ዘንግቶ በምዕራባውያን መጤ ባሕል ተጠልፎ እየዛከረ በሚገኝበት … ወ.ዘ.ተ ሁኔታ ሀገር ውጥንቅጧ ጠፍቶ ይገኛል።
እንዲሁም በቅርቡ በሀገሪቱ የሰሜኑ ክፍል በተካሄደው ጦርነት በሰውና በንብረት ላይ ከደረሰው ጥፋት መማር ተስኖን አንደኛው የጦርነት ምዕራፍ በቅጡ ሳይቋጭ ሌላኛውን የጦርነት ምዕራፍ ለማስጀመር ነጋሪት ሲጎሰም ይደመጣል። ዛሬም ከጦርነት አዙሪት አልወጣንም። ሕዝብ ለሕዝብ ተጨካክኗል። አንዱ ባማረ ሕንጻ ውስጥ እየኖረ ሌላኛው ማደሪያ አጥቶ ከጎዳና ወድቋል፡፡ አንዱ ዳቦ መግዣ ተቸግሮ እጁን ለልመና ይዘረጋል፤ ሌላኛው ገንዘብ መጣያው ጠፍቶበታል። አንዱ አራጅ ሌላኛው ታራጅና ተሳዳጅ ሆኗል፤ . . . ስለዚህ ማንም ከደሙ ንጹሕ የለም።
በመሆኑም ዜጎቿ ዛሬ ምን ይመጣብን? ነገ ደግሞ ምን ይከሰት ይሆን? በሚል የሰቀቀን ኑሮ እንደነፍሰጡር ቀን እየቆጠሩ ይገኛሉ። በስደት በሰው ሃገር ከሚባዝኑና ለስደት ወጥተው የአውሬ እራት ሆነው ከቀሩ ዜጎች ባሻገር በሀገራቸው መኖር ተሳቀው የሚንከራተቱት ብዙዎች ናቸው። በጥቅሉ ሀገራችን ከመከራዋ ክብደት እና ብዛት አንጻር ትክሻዋ ዝሎ፣ ወገቧ ጎብጦ፣ ጉልበቷ ተንቀጥቅጦ የሰው ያለህ እያለች ትገኛለች።
ስለዚህ ሳይረፍድ ሁሉም ዜጋ በተሠማራበት የሙያ መስክ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ሀገራችንን ከተጋረጠባት አደጋ ልንታደግና በጽኑ መሠረት ልናቆም ይገባል። ሁሉም ሀገሩን እንደአይኑ ብሌን መጠበቅ አለበት። ወጣት አዛውንት ሳይባል ሁሉም ማኅበረሰብ የሀገሩን ሰላም በማስጠበቅ ለሀገሩ ዘብ በመቆም የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት። ምክንያቱም ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል! ነው ብሂሉም፣ እውነቱም፡፡ እንዴት ቢሉ፣ ንጉስስ በማን ላይ ነግሶ ይፈርዳል? ነጋዴው ያካበተውን ሀብትና ንብረት የት ተቀምጦ ይበላዋል? የሃይማኖት አባቱስ ለማን ይጸልያል? መምህሩስ ማንን ያስተምራል?…፤ እናም አገራችንን እንደ ብሌናችን፤ ወገናችንን እንደ አካላችን ልንጠብቅና ልንወድ ይገባል፡፡
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም