- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ተመረቀ
አዲስ አበባ፡- የመደመር ትውልድ የኢትዮጵያን ብልጽግና ያረጋግጣል ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት “የመደመር ትውልድ መጽሐፍ” ተመርቋል።
በሦስት ቋንቋዎች የተጻፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ትናንት በአንድነት ፓርክ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት፤ የመደመር ትውልድ በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙትም እነዚህን ፈተናዎች ተሻግሮ የሚያልፍና ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚያሻግር ነው።
የመደመር ትውልድ ብዙ ተስፋ ያለው ትውልድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ትውልድ ለመጪው ትውልድ አሻራውን የሚያስቀምጥና ከተናጠል እውነት ወደ ወል እውነት የሚሸጋገርና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
አሻግሮ የሚያይና ፈተናዎችን የሚቋቋም ትውልድ ወደ ብልጽግና መሄዱ እንደማይቀር ገልጸው፤ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ የተገለጸው የመደመር ትውልድ ትናንትን በማስተካከል ዛሬን በመገንባትና አሻራ በማስቀመጥ ለሚቀጥለው ትውልድ ዕዳ ሳይሆን ትርፍ የሚተው መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ትውልዱ ሰፈርተኝነትን የሚጸየፍና የወደፊት ዕድሎቹን አሻግሮ በማየት በአብሮነት ወደ ሀብት መለወጥ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል። ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታ፣በሥራ፣በምክንያትና በሳይንስ የሚያምን ይሆናል ብለዋል።
የመደመር መጽሐፍ ሀሳቡ ለትውልድ፤ገቢው ደግሞ ለልማት የሚውል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የመደመር ትውልድ መጽሐፍ 274 ገፆች ያሉት ሲሆን በሦሥት ክፍሎችና በ10 ምዕራፎች የተዋቀረ መሆኑን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል። መጽሐፉ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው።
አዲሱን የመደመር መጽሐፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለታዳጊዎች ያበረከቱ ሲሆን፤ ይህ መጽሐፍ ስምንተኛ መጽሐፋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ትውልዱን በአምስት የሚከፋልና ጥንካሬያቸውንና ድክመቶቻቸውን የሚያትትና ከእነዚህ ትውልዶች ትምህርት በመወሰድ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምድ ሀገር በቀል ሀሳቦችን የያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመትም ሌላ የመደመር መጽሐፍ እንደሚያስመርቁ ነው የጠቆሙት።
የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ከያዛቸው አንኳር ነጥቦች መካከልም በአርቲስት ደበበ እሸቱ፥ ደራሲ ሕይወት ተፈራና ሌሎች ምሑራን አማካኝነት በንባብ ለታዳሚው አሰምተዋል።
ሀገራችን ሙሉ አቅምና ብልጽግናዋ ሊረጋገጥ የሚችለው ዘመን ተሻጋሪ ውበትና ሀብትን መፍጠር የሚችል ትውልድ ሲፈጠር ብቻ እንደሆነ በመጽሐፉ ላይ ሰፍሯል።
“ሌላውን እንደራሱ የሚመለከት፤ ብሔሩንና ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ያስታረቀ፤ የትናንቱን በጎ ነገር ይዞ የትናንቱን ስህተት የሚያርም፤ ትናንትን ከዛሬና ከነገ ያስማማ፤ በእነዚህ ጉዳዮች የልሂቃንን ስምምነት በማምጣት ሀገራዊ መግባባትና እርቅን የሚያሰፍን ትውልድ ይፈጠርበታል” የሚሉ ጉዳዮች በመጽሐፉ ተቀምጧል።
በአማራ ክልል የሚሸጠው ገቢ በሙሉ ለአጼ ፋሲል ግንብ እድሳት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚሸጠው ገቢ ደግሞ ለሶፍ ዑመር ዋሻ ዕድሳት፣ በአፋር ክልል የሚሸጠው ገቢው አይሳኢታ ለሚገኘው የሱልጣን ቤተ መንግሥት ዕድሳትና በሌሎች ክልሎች ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢም በየክልላቸው ቤተ መጽሐፍት፣ስፖርት ማዘውተሪያና ለሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የሚገነቡበት እንደሆነ ለክልል ፕሬዚዳንቶች ኃላፊነቱን ሰጥተዋል።
መጽሐፉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፥ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ታዳጊዎች በተገኙበት በአንድነት ፓርክ ተመርቋል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም