ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው አዲስ አበባ ልዩ መጠሪያ ሰፈሩ ኮልፌ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በሁለት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ነው፤ አንደኛው በቀድሞ አጠራሩ ‹‹እውቀት ወገኔ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቀድሞው አጠራሩ ‹‹ሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት›› ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ ምህንድስና ትምህርት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በ1987 ዓ.ም ተመርቀዋል፤ የእርሻ ምህንድስና ትምህርት ሰፋ ያለ ዘርፍ ያለው ሲሆን፣ አንዱ ዘርፍ ውሃን ከመስኖ ጋር በተያያዘ ማልማት ላይ የሚያተኩር ነው። በመሆኑም እርሳቸው ከተመረቁ በኋላ አነስተኛ ግድቦችን ሰርቶ ለመስኖ ልማት ማዋል ላይ ሰርተዋል። ዲግሪያቸውን እንደያዙም በአማራ ክልል በዘርፉ የጥናትና ዲዛይን ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል። በስምንት አነስተኛ ግድቦች ጥናት ላይ ተሳትፈዋል። በዛው በአማራ ክልል በወሎ የሲሪንቃ ምርምር ማዕከል በውሃ መስኖ ልማት ምርምር ላይ ለሶስት ዓመት ያህል ሰርተዋል። ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ ወደ ሕንድ አቅንተው ከውሃ ጋር በተያያዘ ሩርኪ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ፍሰት ምህንድስና (በ ሃይድሮሎጂካል ኢንጂነሪንግ) ተምረዋል። ከሕንድ ከተመለሱ በኋላ በወቅቱ በውሃ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ገብተው ለሁለት ዓመት ያህል አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የመስኖ ጥናቶችና የልማት ስራዎች ላይ ከሰሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የማስተማር ስራን ተቀላቅለው እስካሁንም በማስተማር ላይ ናቸው። ዩኒቨርሲቲ የመምጣታቸው ምስጢር ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ጭምር በመሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ኢንጂነሪንግ ምህንድስና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር በለጠ ብርሃኑ።
ዶክተር በለጠ፣ በተለይ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ገለልተኛ የሆነ የሳይንሳዊ ቡድን በየሀገራቱ ሲቋቋም የዚያ ቡድን መሪ ሆነው ስራ የጀመሩ ናቸው። እኤአ ከ2017 ጀምሮ እስካሁን ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ የድርድሩም አባል ሆነው ቀጥለዋል። የግድቡ የቴክኒክ ቡድን አባልም ከሆኑት እንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቂ የዝናብ ውሃ መጠን ያላት ሀገር እንደመሆኗ ውሃ ማጠራቀም የሚያስችላት እስከ ምን ያህል ሜትር ኪዩብ ነው?
ዶክተር በለጠ፡- ይሄ ጥያቄ ወደ ውሃ ፍሰት ጥናት ይወስደናል። በአሁኑ ወቅት በዝናብ የምናገኘው አማካይ የውሃ መጠን በዓመት ወደ አንድ ሺ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው። ይህ በገጸ ምድር ዝናብ በምናገኝባቸው ቦታዎች የሚዘንበው የውሃ መጠን ስንገምተው ማለት ነው። ይህንን ሁሉ በቀጥታ ወደማጠራቀሚያ መቀየር አይቻልም። ሳይንሱ አብዛኛውን ጊዜ የሚያየው ከዚህ ውስጥ ከ60 እስከ 70 በመቶ አካባቢ የትነት አካል ነው። ከዚህ በኋላ ነው ወደገጸ ምድር ወይም ደግሞ ወደከርሰ ምድር ውሃ የሚቀየረው። በዚህ መነሻነት ስናየው 30 በመቶውን ወደታች እናገኛለን ብለን ብናስብ እስከ 300 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የማጠራቀም አቅም አለን ማለት ነው። ጥሩ ጂኦጆሎጂ ያለው የመሬት ቦታ ካገኘን በከርሰ ምድርም ማጠራቀም ይቻላል።
ትልቁ ችግር የሆነው የገጸ ምድር ማጠራቀሚያ ከውሃ ትነት ውጭ ያለውን መቆጣጠር ይቻላል፤ የከርሰ ምድር ማጠራቀሚያውን ግን መቆጣጠር አይቻልም። መሬት ለመሬት ሰርጎ ሊባክን ይችላል። ስለዚህም ነው ብዙ ጊዜ የገጸ ምድር ማጠራቀሚያን የምንመርጠው። ይህ እንዳለ ሆኖ እኛ በገጸ ምድር ላይ ያለንን አቅም አሳድገን በትንሹ ወደ 300 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ብናጠራቅም አሁን ላለን የሕዝብ ብዛት እና ወደፊትም እያደገ ለሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ብናካፍለው በትንሹ በአንድ ሰው ከአንድ ሺ በላይ ሜትር ኪዩብ ውሃ በዓመት እናገኛለን። ስለዚህ የማጠራቀም አቅማችን ከአንድ ሺ ፐር ካፒታል ከሆነ ከውሃ እጥረት እንወጣለን። ነገር ግን እዛ ላይ አልደረስንም።
አዲስ ዘመን፡- የሚገኘውን የውሃ ሀብት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በቀጣይ ከሁሉም በላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ የሚገባው ምን ላይ ነው?
ዶክተር በለጠ፡- ውሃን በአግባቡ ይዞ ለመጠቀም ሰላሙም ሆነ የፖለቲካ መረጋጋቱ ፋይዳቸው ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ በዋናነት ውሃ ተኮር ስትራቴጂ ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያ በትክክል ማመን ያለባት ነገር ያልተጠቀመችው ሀብት የት ዘንድ ነው ያለው የሚለው ሲታይ ውሃዋን መሆኑን ማወቅ ነው። በእርግጥ በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ሀገር ናት። ነገር ግን በቀላሉ የሚገኝ በተለይ በዝናብ ሀብቷ የምትታወቅ መሆኗን ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ውሃን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ያስፈልጋታል። ውሃን ማዕከል ስናደርግ ሁሉ ነገር ይነሳል። ከተሞቻችን፣ ኢንዱስትሪዎቻችን ሁሉ እዛ ማዕከል ላይ ሆነው ማደግ ይችላሉ።
ለአብነት የሕዳሴ ግድባችንን ወስደን ብንመለከት በሕዳሴ ግድብ ሐይቅ ዙሪያ የሚመጡት ብዙ የልማት አይነቶች ናቸው። ለምሳሌ ግብጽን ለንጽጽር ብንወስድ የግብጽ ልማትና እድገት፣ የከተሞቿ አሰፋፈር ሁሉ ያለው የናይልን ወንዝ ተከትሎ ነው። ማስፋት ሲፈልጉ ደግሞ ውሃ ማከፋፈያ ይፈጥሩና በሰው ሰራሽ ቦይ ውሃውን ወደሚፈልጉበት ቦታ ያደርሱታል። ስለዚህ የመጀመሪያው የእድገት ስትራቴጂ መሆን የሚገባው ውሃን ማዕከል ያደረገ ልማት ላይ ነው።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነው ሕንድ ናት፤ ሕንድ ቀደም ሲል በችግር ውስጥ የነበረች ሀገር ናት። በወቅቱ ኢትዮጵያ ለዚህች ሀገር እርዳታ አድርሳለች። ከዚህም የተነሳ በሀገራቸው በአጼ ኃይለስላሴ የተሰየመ አንድ ቤተ ክርስትያንና አንድ አዳራሽ አላቸው። በዚህ ሁኔታ ያለፈችው ሕንድ ዛሬ ላይ ተቀይራለች። ለመቀየሯ ትልቁ ምክንያት ደግሞ በልማት ስትራቴጂያቸው ላይ አንድ ባህል ያደረጉት ነገር በመኖሩ ነው። እርሱም ቀደም ብዬ የጠቀስኩልሽ አረንጓዴው አብዮት ነው። የዚህ መሪ ሃሳብ ትልቁ ማዕከሉ ደግሞ ውሃቸውን ሁሉ በቻሉት መጠን መገደብና ማጠራቀም ነው። ያጠራቀሙትን ውሃ ወደመስኖና ወደ ኃይል በመቀየር ምግብና ኢነርጂ ማምረት ነው። እኤአ ከ2000 ጀምሮ በአብዛኛው የቴክኖሎጂ ልማታቸው ያመጡበት የአይቲ ሪቮሉሽን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ነገር አሳሳቢ ነው፤ በተለይም ከድርቅ ጋር በተያያዘ እያጋጠመን ያለውን ችግር በዘለቄታ ለመፍታት የውሃ ሀብታችን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፤ በዚህ ዙሪያ ያለው እውነታስ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር በለጠ፡-በእርግጥ ዝናብ ትልቁ ችግሩ ተለዋዋጭ መሆኑ ነው። ደግሞም በእኛ እጅ ላይ ያለ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ የእኛ አቅም እንደ ሰው የሚሆነው ዛሬ የመጣውን ውሃ እንደ ችግር አለማየት ነው። ልክ ዝናቡ ሲመጣ እንደ ችግር እያየነው ቶሎ በወጣልን ማለቱ ተገቢ አይደለም። ጎርፍን እንደ ችግር ማየት ሳይሆን ተቆጣጥሮ ለቁም ነገር ማዋል ነው።
አሁን የምናያቸው የድርቅ ችግሮቻችን መነሻው ልማቶቻችን፣ ኑሯችንና ሁለመናችን ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ ነው። ከዚህ የተነሳ ሁሌም ወደሰማይ እናንጋጥጣለን። እኛ አለን የምንለው ሀብት ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ አንዳንዴም በድርቅ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጎርፍ እንጎዳበታለን። በሁለቱም የጥፋት በትሮች እንመታለን። መቀየር ያለብን ይህንን ነው። ይህንን ለመቀየር በዋናነት የውሃ መሰብሰብን እድገትን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ መከተል አለብን። እሱን ይዘን ከተነሳን ሌሎቹን ሁሉ ልማቶች ማምጣት እንችላለን። ይህን ስናደርግ የምናተርፈው በርካታ ነገር አለ። ግድቡ ሲገደብ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ሁሉ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ የሚይዘው ሰራተኛ ብዙ ነው። ከዚህ የተነሳ የእድገት ማነቆዎች ሁሉ ይፈታሉ። ውሃን ማዕከል ያደረገ እድገት ሀገርን መለወጥ የሚያስችል ነው።
ድርቅ የሚመጣው ዝናብ ጠባቂ በመሆናችን ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ እርዳታ ጠያቂዎች እንሆናለን። እርዳታ ደግሞ የሚመጣው ዝም ብሎ አይደለም። ሌላ የፖለቲካ ጥያቄ ይዞ ነው። እስካሁን ያለው ግብርናችን የተመሰረተው በዝናብ ላይ ነው። ይህ ካልተለወጠ አሁንም ቢሆን ከድርቅ አንወጣም። ከድርቅ የምንወጣው በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርናችንን ወደ መስኖ ግብርና ማምጣት ስንችል ነው።
በቅርቡ በበጋ መስኖ ማልማት ጀምረናል። በዚህ በሁለትና ሶስት ዓመት ሒደታችን እንኳ የስንዴ ፍላጎታችንን ማሟላት እንችላለን ወደሚል ቁርጠኝነት ነው የተመጣው፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ወደ ውጭ ገበያ ልንመጣ እንችላለን በሚል ርምጃው ተጀምሯል፤ ስለዚህ በቁርጠኝነት ከሰራን ውጤቱን ማየት ቀላል ነገር ነው። ትልቁ ነገር ውሃን ሰብስበን ይዘን ወደመስኖ ማምጣት ላይ ማተኮር ነው።
አዲስ ዘመን፡- መስኖዎችን በማስፋፋት የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ እንደ ሀገር ለጀመርነው በምግብ እህል እራስን የመቻል ስትራቴጂ አቅም እንደሆነ ይነገራል፤ ይህን ማድረግ አለመቻልም ድርቅና ድርቅ ከሚፈጥረው ፈተና ጋር አብሮ መኖርን እንደመፍቀድ ይቆጠራል የሚሉ አሉ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር በለጠ፡-ይህ በጣም ትክክል ነው። የግብርና ሥርዓታችንን ወደመስኖ ልማት መቀየር እስካልቻልን ድረስ ሁሌ እየተጓዝን ያለነው ከድርቅ ጋር ስምምነት ፈጥረን ወስነን ነው። የዝናብ ግብርናን መሰረት አድርገን በተለይ አሁን እያደገ የሚሄደውን ሕዝባችንን መግበን እንኖራለን ማለት አይቻልም። ይህን መቀየር የምንችለው የግብርና ስልታችንን ከዝናብ መንጠልጠል አውጥተን ወደመስኖ ስንቀይር ነው። ወደ መስኖ ካልቀየርንና አሁንም በዝናብ ግብርና ላይ የምንቆይ ከሆነ ሁሌም የድርቅ ደንበኞች እንሆናለን።
ምክንያቱም የዝናብ ትልቁ ችግር ማጠሩ ብቻ ሳይሆን የበዛ ጊዜም የሚሄደው እርሻችንን አበላሽቶት መሆኑ ነው። ዝናብ በበዛ ዓመት ጎርፉ ስለሚበዛ የእርሻ መሬታችን ይበላሻል። በበዛ ጊዜ ውሃውን መቆጣጠር ካልቻልን የሚያጠፋ ጭምር ነው። ከዛሬ 40 እና 50 ዓመት በፊት አምራች የነበሩ ቦታዎች ዛሬ በጎርፍ ተጠርገዋል። ከዚህም የተነሳ አካባቢዎቹ የሴፍትኔት ማዕከል ሆነዋል። ስለዚህ ግብርናችንን በዝናብ ላይ እንደተንተራሰ እንተወው የምንል ከሆነ የሚቆጠረው ከድርቅ ጋር ተስማምተን እንደመኖር ነው። ከድርቅ ጋር ብቻ አይደለም፤ ድርቅ እየሰፋ ሲሄድ ወደረሃብ ይቀየርና የከፋ ችግር ይፈጠራል። ከድርቅ ጋር ተስማምተን ስንኖር የሚወለደውም ትውልድ እየቀነጨረ ይመጣል። የቀነጨረ ትውልድ ደግሞ በተገቢው ልክ ማሰብ ይሳነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የድርቁ እየሰፋ መምጣት ከሚያስከትለው የከፋ ረሃብ ጎን ለጎን እርዳታ ሰጪዎች እጅ የሚጥል ይሆናል፤ ይህ እንደ ሀገር ነጻነትን አያሳጣም?
ዶክተር በለጠ፡-በሚገባ ያሳጣል። ራሳችንን በምግብና በኢነርጂ ካለመቻላችን የተነሳ ልንሆን የምንችለው ነገር ቢኖር በሁሉ ነገር ተመሪዎች መሆን ነው። ረጂ አካላት እንደፈለጉ የሚቆጣጠሩንና እንድንከተላቸው የሚያስገድዱን ይሆናሉ። ስለዚህ በተፈጥሮ የተቸርነው ሀብት ብሎም እውቀት እያለ የሚስተዋለው ግን ያለመስራት ክፍተት ነው። ስለዚህ ስትራቴጂያችንም ሆነ አመለካከታችን ጭምር መቀየር አለበት ባይ ነኝ። በቂ ዝናብ ስላለኝ እያመረትኩ እኖራለሁ ማለት ከድርቅ ጋር እኖራለሁ እንደማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውሃ ሀብታችንን ለመጠቀም በምናደርገው ጥረት በግብጽ በኩል የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ቀን ከለሌት ግብጽ አየሰራች ነው፤ ይህ በሀገራቱ መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሀዊ አሰራር እንዳይሰፍን እያደረገ አይደለም ?
ዶክተር በለጠ፡-በግልጽ በሀገራቱ መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሀዊ አሰራር እንዳይሰፍን እያደረገ ነው። ፍትሃዊ አጠቃቀም ብቻ ሳይሆን እኛ ላለመልማታችን እንደ አመክንዮ የምንወስደው ሁሌም ግብጽን ነው። ሁሌም መሰናክል የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። በተለይ ውሃን ለመስኖ እየተጠቀምን በሄድን ቁጥር ትልቁን ውሃ የሚያገኙት ከእኛ ነው።
የአባይ ውሃ የተፋሰሱ ሀገራት ቢሆኑም ትልቁ አስተዋጽኦ ያለው ኢትዮጵያ ዘንድ ነው። ኢትዮጵያ በሁሉም ተፋሰሶቿ እስከ 86 በመቶ ድርሻ ያላት ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህን ውሃ ልጠቀም ብላ ከተነሳች ግብጽ ትጎዳለች። ስለዚህ በእነርሱ አተያይ ኢትዮጵያ መጠቀም የለባትም።
በእርግጥ ትክክለኛ የሚሆነው አመለካከት እንደማንኛውም የታችኛው ሀገር እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለውን ግብጽ ትታ ፍትሃዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ላይ ማተኮር ይገባታል። እንደታችኛው ሀገር ፍትሃዊ አጠቃቀም ይኑረኝ ብላ ብትነሳና ኢትዮጵያን በዚህ አግባብ ብትጠይቅ ጥሩ ነበር። እኛ እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ግብጽ ያለውም ማኅብረሰብ የዚህ ምድር ሰው ነው። ስለሆነም ውሃ ያስፈልገዋል። የእነርሱ ከእኛ የሚለየው እነርሱ ከዝናብ የሚያገኙት ነገር አለመኖሩ ነው። ስለዚህ እኛ ውሃውን ባላለማን ቁጥር ከዝናብ የምናገኘው ውሃ ሁሉ የሚሄደው ወደእነርሱ ነው። እነርሱ ወደለውጥ የመጡት የአስዋንን ግድብ በመስራታቸው ነው። ግድቡ ባይኖራቸው ኖሮ በጣም ችግር ውስጥ ይወድቁ ነበር። ግብጽ ለረጅም ጊዜ በጎርፍ የምትጠቃ፣ ሰው ለመኖር የሚቸገርባት ምድር ነበረች። ይህን ሁሉ ቀይሮ የግብጽን የእድገት መርህ የፈጠረው የአስዋን ግድብ ነው። ስለዚህ የአስዋን ግድብ መጀመሪያ የታችኛው አስዋን የምንለው የድሮው ግድብ በ1904 አካባቢ የሰሩት ነው፤ የግድቡን ጥቅም ሲያዩ ደግሞ ከፍ አደረጉና መጠኑን አሳድገው ትልቁን አስዋን ግድብ ገነቡት። ቀጥለውም ውሃ ወደተለያየ ቦታ የሚያሰራጩበት፣ የሚያከፋፍሉበት እና እየቀነሱ የሚያደርሱበትንም ሰሩ። ከዚህም የተነሳ ሙሉ የእድገታቸው መሰረት አስዋን ሆነ። እስከቅርብ ጊዜ ድረስም የምግብም የኢነርጂም ምንጭ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።
ከዚያ በኋላ ግን አማራጮች እየፈለጉ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ኢነርጂውን ወደሌላ ብዙ ነገር ቀይረውታል። አሁን ውሃው ላይ የኢነርጂ ጥገኝነታቸው በጣም ቀንሷል። ውሃውን ሙሉ ለሙሉ የምግብ አቅም መፍጠሪያ እንዲሆን ለመስኖ አውለውታል። ኢነርጃቸውን በሁለት የተለያዩ ዘርፎች ላይ አተኩረው ሄደዋል። ለምሳሌ፣ በሶላር ኃይል ማመንጨት አንዱ ትኩረታቸው ሲሆን፤ ሶላር ላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየገነቡ ነው። የባዮ ጋዝ ልማትም ሌላው የኃይል አማራጭ የትኩረት መስካቸው ነው። የአቶሚክ ኢነርጂም አላቸው። ጂኦ ተርማል እና ሌሎችም የኢነርጂው አማራጮቻቸው ሆነዋል።
በከፍተኛ መጠን ውሃውን ለመስኖ ከማዋላቸው የተነሳም፣ አሁን እያሉ ያሉት ‹‹መልሰን እየተጠቀምንም አልቻልንም›› የሚል ነው። ውሃውን እየተጠቀሙ ያለው ለመስኖ፣ ለመጠጥ እና ለኢንዱስትሪ ነው። እናም ኢነርጂውን በተወሰነ መልኩ እየተኩት መጥተዋል። መነሻቸው ግን በሱ ነበር።
ለምንድን ነው ኢነርጂውን የሚለውጡት ሲባል የመሬት አቀማመጣቸው አድካሚ ስለሆነ ነው። ይሄን ያህል ውሃ ይዘው እና ትንሽ ውሃ ይዘን የምናመነጨውን/የምናመርተውን ያህል ኢነርጂ አያመርቱም። ብዙ ጊዜ አስዋን ግድብ እና የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሰዎች ዘንድ የአገላለጽ ስህተት ይስተዋላል። ህዳሴ ግድብ በስትራክቸሩ/በቁመቱ ትልቅ ነው። በሚይዘው አቅም ግን ከአስዋን አይደርስበትም። ይህ ማለት ውሃን በማጠራቀም አቅም አስዋን ግድብ ይበልጠናል። የአስዋን ግድብ ውሃ የሚያጠራቅመው ከእጥፍ በላይ ነው። እስከ 160 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ያጠራቅማል። ህዳሴን ትልቅ የሚያደርገው ግን ከአስዋን ያነሰ ውሃም ይዞ ከፍ ያለ ሃይል ማምረት መቻሉ ነው። ስለዚህ የተለወጡት ይህንን ውሃ በማጠራቀማቸው ነው።
ሁሌም እንደምንለው የአስዋን ግድብ ባይኖር ኖሮ እና ቀድሞ የተሰራው የህዳሴ ግድብ ቢሆን የህዳሴን ግድብ በጣም ወድደውት ነበር የሚኖሩት። ምክንያቱም ግድቡ ለሃይድሮ ፓወር የምናውለው እንደመሆኑ ውሃው ተጠብቆ የሚለቀቅላቸውና የሚደርሳቸው በመሆኑ ነው። ለዚህ ነው ሱዳን መሃል ላይ ያለች አገር ትልቅ አቅም የተፈጠረላት፤ በህዳሴው ግድብ የተጠበቀ ውሃ እየደረሳት ሜዳ የሆነ መሬቷን በሙሉ አቅም ወደ ማልማት የሚያስገባት ነው። ይህ ትልቅ እምርታ ነው።
ስለዚህ ግብጾች አስቀድመው የአስዋን ግድብ አጠቃላይ የውሃውን ፍሰት መጠቀም የሚያስችል አቅም ስለፈጠሩ ይህ አቅም እንዳይስተጓጎልባቸው ይፈልጋሉ። እንዳይስተጓጎልባቸው ምንድን ነው ፍላጎታቸው ቢባል ደግሞ ኢትዮጵያን ከውሃ ልማት ውጪ ማድረግ ነው። በየትኛውም መንገድ፣ በየትኛውም ፖለቲካ ጫና ውስጥም መክተት ነው። ስለዚህ ዓለምአቀፍ ጫናዎችን ይፈጥራሉ፤ ዓለምአቀፍ ተቋሞችን ይጠቀማሉ፤ ጉዳዩን የፖለቲካ ጨዋታ ያደርጋሉ። ሚዲያዎቻቸው ላይ አጠንክረው ይሰራሉ። ሕዝባቸው ላይ ከፍ ያለ የሥነ ልቦና ጫና በመፍጠር አመለካከታቸው እንዲቀየር ያደርጋሉ። በተለይም ‹‹ኢትዮጵያ የምትባል አገር የእኛ ትልቅ እንቅፋት ናት፤ የውሃችን ማነቆ ናት፣ ውሃችንን ልታስቀርብን ነው፤ እኛ ደግሞ ለዚህ ለናይል ውሃ ነው የተፈጠርነው፤ ያለ ናይል እኛ የለንም፤ ይህንን እየቀማችን ያለችው ኢትዮጵያ ናት።›› በሚል ለሕዝባቸው ያልተገባ ትርክት ይናገራሉ። ከዚህም የተነሳ ዝመት ቢባል የግብጽ ሕዝብ በሙሉ አቅሙ ይዘምታል። ዘምቶ ያዋጣዋል አያዋጣውም የሚለው ሌላ ችግር ይሆናል እንጂ። ምክንያቱም የግብጽ ልሂቃኑ አዕምሮው ላይ ሁሉን ነገር ፈጥረውበታል።
ወደዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ስንሄድ ግብጻውያኑ የሚያደርጉት እንደዛው ነው። ከሌሎቹ ሃያላን ሀገራት ጋር ያላቸውን ፖለቲካ የሚሰሩት በናይል ውሃ ላይ ነው። እናንተ ናይል ውሃ ላይ እንደዚህ አግዙን እኛ ለእናንተ እንደዚህ እናደርግላችኋለን የሚል ነው። የሁሌም የዲፕሎማሲያቸው ምንጭ ይህ ነው። ባላቸው እና በገቡበት ቦታ ሁሉ የሚጠይቁት ያ ተቋም የናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እንዲፈጥርላቸው ነው። ጥማታቸው ኢትዮጵያ በተለይ የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀም ማድረግ ላይ ነው።
አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ውሃ ወደ ናይል ከሚገብሩ ወንዞች መካከል ትልቁ የዓባይ ውሃ ነው። እዛ ዓባይ ላይ የሚሰራ ነገር በእነሱ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። አሁን በታሪክ የሚታወቅ ነገር አለ። የአስዋንን ግድብ ሲሰሩ የረዳቻቸው ራሽያ ነበረች። ልክ ያንን ርዳታ ሲያዩ ነው አሜሪካኖቹ መጥተው ኢትዮጵያን እነዚህ ትንንሽ ግድቦች የምንላቸውን ጥናቶች የመጀመሪያውን ጥናት ያጠኑት። አሜሪካ ያንን ያደረገችው ግብጽ የፖለቲካ ለውጥ አደረገችብን በሚል እሳቤ ሲሆን፣ ግብጾችን ለመቆጣጠር ፈልጋ ነው። ልክ አሜሪካኖቹ ይህን ጥናት ማጥናታቸውን ሲያዩ ግብጾቹ ቶሎ ነው አቅጣጫቸውን የቀየሩት። ያን ያህል ግድብ እንኳን እየገደበችላቸው ከራሺያ ጋር ለመቆየት አልወሰኑም። ምክንያቱም አሜሪካ ጥናቱን ጀምራ ጥናቱን ወደ ግድብነት የምትለውጠው ከሆነ ፖለቲካው ከባድ ይሆናል። እናም የተውት ጥናቱን ካጠኑ በኋላ ነው።
ጥናቱን አፄ ኃይለስላሴ የጠየቁት ገና እንግሊዞቹ ሙሉ ለሙሉ ከግብጽ እና ከሱዳን ለቅቀው ሳይወጡ በነበረ ጊዜ ሁሉ ነው። የዚያን ጊዜ በፖለቲካው ዙሪያ ጤናማ ስለነበሩ ግን አልመጡላቸውም ነበር። ልክ ግብጽ የፖለቲካ አቅጣጫዋ ወደ ሶሻሊስቱ ካምፕ ተቀየረብን ብለው ሲያስቡ ግን ቶሎ መጥተው ለኢትዮጵያ ጥናት ማጥናት ጀመሩ። ልክ ይህን ጥናት ማጥናታቸውን ሲጀምሩ ግብጾቹ ደግሞ ተሰበሰቡና ‹‹አደጋ ውስጥ ነን፤ ስለዚህ እንመለስ›› ብለው እንደገና የፖለቲካ አቅጣጫቸውን ማስተካከል ጀመሩ።
አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ አሁንም ትልቁን የዓለምን ፖለቲካ የሚዘውሩበት ነው። ከአረብ ሊግ ጋርም አረቦች ከኢትዮጵያ ጋር ህብረት እንዳይኖራቸው ለማድረግ የሚሰሩት ለዚሁ ለናይል ውሃ ሲሉ ነው። ስለዚህ የትኛውም የውሃ ልማት ተግዳሮታችን የሚነሳው ከግብጽ ጋር ነው። ግብጽም ይህን ስላሰበች ፍትሃዊ እና ርትዕ የሆነው አጠቃቀም እኔን ይጎዳኛል፤ እኔ አስቀድሜ ስለለማሁ፣ አብዛኛውንም ውሃ እኔ ስለተቆጣጠርኩት እንደተቆጣጠርኩት ልኑር ብላ ስለምታስብ ነው እንጂ እንዲያውም በመሰረተ ሃሳቡ ቢታይ አሁን ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለችው መሰረታዊው ሐሳብ ይህ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም የሚጠቅመው የታችኞቹን ሀገሮች ነው። የላይኞቹን ሀገሮች ማሰሪያ ነው።
ስለዚህ እኛንም የተሻለ የሚያደርገው ግብጾች አመለካከታቸውን አስተካክለው ቢጠይቁ ነበር ። ከዚህ ውጭ መንገዳቸው ፍትሃዊና ርትእ አካሄድን አይፈጥርም። ምክንያቱም አስዋን ግድብ አላቸው፤ እስካሁን ባለው ፍሰት አብዛኛውን (ሙሉውን ማለትም ይቻላል፣ የተወሰነ ያህል መቶኛ በሱዳን ጥቅም ላይ ከመዋሉ ውጪ) የውሃውን ፍሰት እነሱ መጠቀም የሚችሉበት እድል ነው የፈጠሩት።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ግብጽ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ጥሪ አቅርባለች፤ ይህ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አይሆንም?
ዶክተር በለጠ፡- የአረብ ሊግ ጉዳይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ነው። ምክንያቱም ጣልቃ እየገቡ ያሉት ባልተገባቸው ጉዳይ ላይ ነውና። የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብን አጀንዳ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ምክንያት የለውም። ራሳቸው ሱዳኖች ጉዳዩ የአረብ ሊግ አጀንዳ እንዲሆን አይፈልጉትም። ግብጾች ግን የትኛውም ዓለም አቀፍ ተቋም ሕዳሴን አጀንዳው እንዲያደርግላቸው ይሻሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እንደሚታወቀው የአረብ ሊግ በግብጾች ተጽዕኖ ውስጥ ያለ ነው። ወደኋላ መልስ ብለን ከታሪክ ማህደር ማየት ብንችል አብዛኛዎቹ የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ ጸሐፊዎች ዋና ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ግብጻውያን ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች የሕዳሴ ግድቡን በአረብ ሊግ ቋሚ አጀንዳ ማድረጋቸው በሕዳሴ ግድቡ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል?
ዶክተር በለጠ፡- የተለየ ተጽዕኖ አያመጣም። የእነርሱ ፍላጎት የፖለቲካ መልክ እንዲይዝ ነው። የውሃ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ ይሆናል። እሱ ሲሆን ደግሞ ለሌላ መጠቀሚያ ለማዋል ይረዳቸዋል። እኛ ደግሞ ከአረብ ሀገራት ጋር በብዙ መልኩ ትብብር አለን። አብረን የምናከናውናቸው የልማት አጀንዳዎች አሉ። ብዙዎቹ ዜጎቻችን አረብ ሀገራት ሔደው ስራ ይሰራሉ። ይህ ስለሆነ ግብጾች ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ማድረጋቸው አረብ ሀገራት የኢትዮጵያ ጉዳይን ሲመለከቱ በአንዳንድ ትብብሮቻችን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ያስችላቸው ዘንድ እንደመነሻ ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል።
በነገራችን ላይ ግብጾች የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ቢሮ ድረስ ወስደው ነበር፣ ኢትዮጵያ በሰጠችው ተገቢ መልስ ግን ወደአፍሪካ ይመለስ በሚል መወሰኑ የሚታወስ ነው። ይሁንና ግብጾች ድሉ የእኛ ነው ሲሉ ነበር። ምክንያት ሲባሉ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የሕዳሴን ጉዳይ አጀንዳ እንዲያደርገው ችለናል ሲሉ ይመልሳሉ። ግብጾች ቢችሉ በሁሉም ቦታ ጉዳዩ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ነው። የትኛውም ዲፕሎማት ይሁን በማንኛውም ደረጃ ያለ ባለሥልጣን ሀገራቸው ሲመጣ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ ላይ እያደረገች ያለው ሁኔታ ሳይነገረው አይወጣም። ይህን የሚያደርጉበት ዋናው ነገር በፖለቲካ አጀንዳ ካልሆነ በስተቀር በሕግና በሥርዓት ውሃውን መቆጣጠር ስለማይችሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግብጾች አካሄድ ቀደም ብሎ የተቀመጠውን ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ›› የሚለውን መርህ የሚጻረር አይሆንም?
ዶክተር በለጠ፡- ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ላይ ፍትሃዊ የሆነ አጠቃቀም እስከተጠቀምን ድረስ ሌላ ነገር አያስፈልግም ስትል ነበር። ግብጻውያኑ ግን አይሆንም በሚል ነው እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድረስ ጉዳዩን የወሰዱት። ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ ህብረት ‹‹የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት›› የሚል መርህ ስላለው በእዛ መሰረት እንፍታ ስትል ነው የተናገረችው። ግብጾች በአረብ ሊግ ቋሚ አጀንዳ ይሁን ብለው እንዳስደረጉት አይነት የተባበሩት መንግሥታትን እንደፈለጉት መቆጣጠር ግን አልቻሉም፤ የአፍሪካ ህብረትም የሆነባቸው እንደዚያ ነው። ስለዚህ የአፍሪካ ህብረቱን መርህ ለማክበር ፍላጎታቸው የቀነሰ ነው።
በነገራችን ላይ ግብጻውያን በናይል ጉዳይ መርህም ሕግም የሚሉት ነገር የላቸውም። የትኛውንም ሕግም ሆነ መርህ ተከትለው መኖር አይፈልጉም። አንድ እና አንድ የሆነ ፍላጎታቸው ውሃውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ መኖር ነው። መርህ ብቻ ሳይሆን ሳይንስን ራሱ መቀየር የሚፈልጉ ናቸው። በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ የሚታተም ጽሑፍን ለማስቀየር ድረስ የሚሄዱ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ግድቡ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስጋዋል የሚል ከእውነት የራቀ ሐሳብ እስከመሰንዘር የደረሱ ናቸው። ይህ እንዳልሆነ ደግሞ ራሳቸው የፈረሙት ሰነድ ተሰንዶ ተቀምጧል።
እንዲያውም የአስዋን ግድብ ካለው ጤናማ ኢንቫይሮንመንት በላይ የሕዳሴ ግድብ የተሰራበትም ቴክኖሎጂ ሆነ ያለበት ሁኔታ ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ነጻ መሆኑ በተጠናው የጥናት ውጤት ላይ ራሳቸው ግብጻውያኑ ፈርመዋል። ይህን መፈረማቸውን እያወቁ በግድቡ ላይ ችግር ለማስመዝገብ ሲሉ የተጣመመ ትንታኔ ሁሉ ሲጽፉ ይታያሉ።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራቱ መካከል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለው አማራጭ ምንድን ነው?
ዶክተር በለጠ፡- ሁሌም የሚባለው ነው። ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚሆነው ሀገራቱ በአንድነት ተቀምጠው ፍትሃዊና ምክንያታዊ የሆነ የመሬት ውሃ አጠቃቀም ሥርዓት ምን ይሁን ብለው መወሰን ነው። ቢቻላቸው ከዚያም በላይ ይህን የውሃ መከፋፈል ትተው በጋራ ውሃውን እንዴት እናልማው ብሎ መሥራት አዋጭ ነው። በተፈጥሮ እየመጣ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት መከላት እና የተፋሰሱ አለመልማት እየፈጠረ ያለው ተጽዕኖ በጋራ መቀየር የምንችለው እንዴት ነው ብለው መምከር አለባቸው፤ ይህን ማድረግ ከቻሉ መፍትሄ ይመጣል።
ኢትዮጵያ ደጋግማ የምታነሳው ቢቻል የጋራ ኮሚሽን ኖሮን የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ስትራቴጂ እና ዓላማ ቀርፀን ውሃውን በጋራ እናልማ የሚል ነው። ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ጋር በመሆን የጋራ ዘርፈ ብዙ ተግባር የሚል ቀርጸው ብዙ ታግላለች። የትብብር ማዕቀፉ እንዲፈረም ብዙ ዓመታት ተደራድራለች። ይህ ሁሉ ጥረት አጠቃላይ የተፋሰሱን ውሃ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል ነው። ውሃ ደግሞ ለሰው ልጅ ኑሮ አስፈላጊ ነው። ሁሉም ሀገር ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ውሃውን መጠቀም አለበት። ትልቁ ችግር ግብጻውያን በዋናነት እዚህ ሐሳብ ላይ መድረስ አልቻሉም። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ መግፋት ያለባት። ኢትዮጵያ አብዝታ ማልማት ስትጀምር ሁሉም ወዲህ ይመጣሉ። ከአስር ዓመታት በላይ በህዳሴው ግድብ ላይ ድርድር የተካሄደው ልማቱ ስለተጀመረ ነው። ልማቱ ባይጀመር ኖሮ እዚህ ሁሉ ድርድር እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ውስጥ አይገቡም ነበር። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እስካልለማች ድረስ ውሃው ፈስሶ እነርሱ ዘንድ ይደርሳል። እንደ መርህ ውጤታማ የሚሆነው ፍትሃዊና ምክንያታዊ የአጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህን በድርድርና በሕግ ማምጣት ከተቻለ እሰየው ነው። ወደዚህ የማይመጡ ከሆነና ኢትዮጵያንም ውጤታማ የሚያደርገው እነርሱንም ወደ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የአጠቃቀም አጀንዳ ውስጥ እንዲገቡ የሚደርጋቸው የኢትዮጵያ ጠንካራ ልማት ነው። አሁን ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ ባሻገር ሌሎች ልማቶቿን ማከናወን አለባት። የተጠኑ ጥናቶች አሉ። እነርሱን መተግበር አለባት። ለምሳሌ ባሮ አኮቦ ላይ የተጠና ጥናት አለ። ዓባይ ላይም ከላይ የተጠኑ ጥናቶች አሉ። ከዚህም ከፍ ያለና ሎሉችም አማራጮች እየታዩ ወደ ሌሎች ጠንካራ ልማት ውስጥ መግባት ይገባል። ግብጽን ወደ ሥርዓቱ ለማምጣት ከህዳሴ ግድብ በሻገር ማየት መጀመር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ተርባይኖች በመሥራታቸው ብንጠቀምም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል። መነሻው በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ነበር። በእርስዎ እይታ ይህን እንዴት ይረዱታል?
ዶክተር በለጠ፡- እውነት ለመናገር ጊዜው አልበዛም። በመጀመሪያም እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ልማት ሲጀመር የሚያነሳሳ ሃሳብ ይፈልጋል። ትልቅ ልማት ነውና 20 እና 30 ዓመት ይወስዳል ብለን ብንነሳ የመነሳሳት አቅማችን ደካማ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በአጭር ጊዜ ታጥቀን በዘመቻ በአምስት ዓመት እንጨርሰዋለን ብሎ መነሳት የጋራ መነሳሻ አጀንዳ ይሆናል እንጂ እንደ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት በአምስት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እናጠናቅቀዋለን ብሎ መነሳት ከባድ ነው። በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ተሞክሮውም የለም።
በዓለማችን አሉ የምንላቸው ትልልቅ ግድቦች ስንወስድ እንዲያውም አሁን የህዳሴ ግድብ 90 ነጥብ 7 በመቶ መድረስ ዓመቱ በዛ የሚያስብል አይደለም። በዓለም የተገነቡ ትልልቅ ግድቦችም ስንመለከት ከ15 ዓመት ቀድሞ የተጠናቀቀ የለም። ስለዚህ እኛ ጥሩ እምርታ ላይ ነን። በፕሮግራማችን መሰረት በፈረንጆች አቆጣጠር 2024 ላይ ሙሉ ለሙሉ ግድቡን እናጠናቅቃለን። በእርግጥ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ብዙ ነገር የሚፈልግ ነው። አንድ ተርባይን ከማኑፋክቸሪንግ ወጥቶ፣ ሳይት ደርሶ ገጥሞና ሞክሮ ለመጨረስ ጥናቶች የሚያሳዩትና እኛም እያየን ያለነው ከ8 እስከ 9 ወር ይፈጃል። ስለዚህ 11 ስናደርጋቸው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ህዳሴውን በተመለከተም አንዱ ከሌላው የመቅደም ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የሁለተኛው ተርባይን ስንገጥም የመጀመሪውን ከገጠምነው ጊዜ ያነሰ ነው። ሦስተኛው ሲገጠም ደግሞ የተሻለ ይሆናል። እንዲህ እያለ የሚፈጥንበት ሁኔታ አለ። በእርግጠኝነት ግን ሲቪል ሥራው በተባለው ጊዜ ይጠናቀቃል። ከአንድ አመት በኋላም ሙሌቱ ይጠናቀቃል። በሚቀጥለው ሃምሌ ወርም የተወሰነ እንሞላለን፤ እየሄድንም ያለነው በመርህም ነው። እዚህ ላይ ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ በየትኛው ዓለም አቀፍ ተቋም አቤቱታ ቢቀርብባትም አቤቱታውን ያለፈችው መርህን ተከትላ በመሄዷ ነው። የሙሌት መርህ አስቀምጣለች፤ ለእነርሱም በሥምምነት አቅርባለች። በግልጽ ባይስማሙበትም ውስጣቸው ተስማምተውበት ተቀብለዋል፤ ኢትዮጵያ የምትሄደው ይህን ተከትላ ነው። ዓረብ ሊግ ላይ ራሱ ኢትዮጵያ ብቻዋን ተነጥላ ውሃው ሞላች የሚለው በራሱ አግባብ አይደለም።
ሁለተኛው ስለዚህ ግድብ ለየት ባለ መንገድ መረዳት የሚገባን በትይዩ እያለማ ነው። ለምሳሌ ወደኋላ ተመልሰን የሌሎች ሀገራትን ስንመለከት በዓለማችን ውስጥ እያስገባ ያለው አዲስ ልምድ ነው። አዲሱ ልምድ መሰል ግድቦች ወደ ምርት የሚሄዱት ሙሉ ግንባታቸውና የውሃ ሙሌታቸውን ጨርሰው ነው። ስለዚህ 10ም ሆነ 20 ዓመት የወሰዱት ያለምርት ነው። ህዳሴ ግድብ ግን ይህን እሳቤ ቀይሮታል። በመሆኑም የታቀደበት መንገድ ለዓለማችን ትልቅ ትምህርት ነው። ሦስተኛው ሁሌም የምናነሳው ለእኛ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው። ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መነሳሻ የሆነው በራስ አቅም መልማት ይቻላል የሚለው ነው። ካሰብንበትና ከተስማማንበት እርዳታ ላይ ያልተመሰረተና ትልልቅ ልማቶችን መሥራት ይቻላል። በመሆኑም ህዝብም መንግስትም ቁርጠኛ መሆን አለብን። በራስ አቅም ለመልማት ይህ ግድብ ማሳያ ነው።
በተፋሰሱ ሀገራት ስብሰባ ላይ ስንመለከት ሀገራት እየጠየቁ ነው። እኛም ልክ እንደ ኢትዮጵያ በራሳችን በጀት ማልማት አለብን እያሉ ነው። ትልቁ እዚህ ውስጥ ያስገባን የግብፆቹ አካሄድ ነው። የትኛውንም ፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርገውን አካል ልትጎዱን ነው ወይ በሚል ስለሚከላከሉ ነው። አብዛኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ልማታቸው የተገደበበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው። ስለዚህ የህዳሴ ግድብ በዚህ ደረጃ መሠራት ለእኛም ለሌሎችም በራስ አቅም ተነሳስቶ በየደረጃው አቅምን ሳይገዳደር መስራት ያስችላል። እኛ 750 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨን ግድብ መስራት ቀላል ነገር አይደለም። አሁን ካሉን ሁሉም ግድቦች ከጊቤ ሦስት በስተቀር በሁለቱ ተርባይኖች የሚመረተው ከሁሉም ይበልጣል። ስለዚህ እነዚህ እመርታዎች አሉን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ።
ዶክተር በለጠ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም