በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ ተብለው ከተመረጡ አምስት ዘርፎች መካከል ማዕድን አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴርም በማዕድን ጥናት፣ ልማትና ግብይት ላይ የሚካሄዱ ተግባሮችን በመምራትና በመከታተል የሚጠበቅበትን ለመወጣት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ሚኒስቴሩ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለውን አደረጃጀት በመከተል (ሪፎርም በማድረግ) በሥሩ ተጠሪ የሆነ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን አቋቋሟል። የዚህ ኢንስቲትዩት ዋና ተልዕኮና ተግባር ማዕድን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ነው። ድጋፉም ከጥሬ እቃ ግብዓት ፍለጋ ጀምሮ ጥራትን እስከ ማረጋገጥ ፣ የሀብት መጠንን እስከ መለየት፣ በአጠቃላይ ከግብዓት እስከ ምርት ሂደት ድረስ የሚዘልቅ ይሆናል። በተጨማሪም በቴክኖሎጂና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ሙያዊ እገዛ በማድረግ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለዘርፉ የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀትም ድጋፍ ያደርጋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሠ እንደሚናገሩት፤ኢንስቲትዩቱ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት አቅርቦት ችግር ሲያጋጥማቸው ችግሮቹ የሚፈቱባቸውን አማራጮችንም በጥናት ያመቻቻል። ለአብነትም እንደ ሀገር የብረት ግብዓት ችግር በማጋጠሙ ለተለያየ ጥቅም ውለው ከአገልግሎት ውጪ የተደረጉ የብረታብረት ቁርጥራጮች ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት እንዲውሉ በማመቻቸት ኢንስቲትዩቱ ተልዕኮውን ተወጥቷል። በሌሎችም ዘርፎች ክፍተቶች ሲፈጠሩ በጥናት የታገዘ የመፍትሔ አቅጣጫ በማዘጋጀት ለውሳኔ ያቀርባል። ሚኒስቴሩ የቴክኒክ ክንፍ በመሆን የማዕድን ዘርፍን እያገዘ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ በዚህ ወቅትም በማዳበሪያ፣ በብረትና ማርብል ፕሮጀክት ቀርጾ በትኩረት እየሠራ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በጌጣጌጥ ማዕድናት (ጄም ስቶን) ላይም ለውጦች እንዲመጡ ግፊት እያደረገ ይገኛል። የጌጣጌጥ ማዕድናት እሴት ተጨምሮባቸውና ሳይጨመርባቸው ለገበያ ቢቀርቡ የትኛው አዋጭ እንደሆነ ጥናት ተደርጓል።
የጥናት ግኝቱም እሴት ያልተጨመረበት ምርት ለገበያ ማቅረብ ዝቅተኛ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ማመልከቱንና እሴት ያልተጨመረበት ሽያጭ መቆም እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ የተቀመጠበት ጥናት እንደሆነ አስረድተዋል። ማዕድን ሚኒስቴርም ጥናቱን መሠረት አድርጎ የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ በኢንስቲትዩቱ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማዕድንን ተጠቅመው የሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች ሥልጠና እንዲያገኙም እየተሠራ መሆኑንም ዶክተር ጉታ አመልክተዋል። ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለማዕድን ሚኒስቴር፣ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለክልሎች፣ በማኅበር ተደራጅተው በማዕድን ዘርፉ ላይ ለሚሠሩ አካላት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት መቋቋሙን የጠቆሙት ዶክተር ጉታ፤ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ የገባው ግን በተያዘው 2015 በጀት መሆኑን ተናግረዋል። በማዕድን ዘርፉ የተሻለ ውጤት ተመዝግቦ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍ ያለ አስተዋፅዖ እንዲኖረው የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርስቲዎች) ጋርም በአጋርነት ይሠራል። ሰሞኑንም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራር ሟል።
በኢንስቲትዩቱና በዩኒቨርሲቲው መካከል ስለተደረገው ስምምነትና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ስላለው አጋርነት ዶክተር ጉታ እንዳብራሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በተወሰኑት ላይ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሚና አለው። ዩኒቨርስቲው ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የአምራቾችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚረዱ ሥራዎች ዙሪያ አደረጃጀት አለው። በዚህ ረገድ ጥሩ ድጋፍ ማድረግ ይችላል። ለመደገፍም ፍላጎት አለው። ለአብነትም በብረታብረት እንዲሁም በሀገር ውስጥ መለዋወጫ በማምረት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የተደራጀ ቤተሙከራ (ላቦራቶሪ) ባለቤት ነው። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ያለውን የተደራጀ ቴክኖሎጂ ለማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ያጋራል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሥልጠናዎችንና የጥናት ሥራዎች በጋራና በተናጠል በመሥራት ሁለቱ አካላት ይደጋገፋሉ። ዩኒቨርሰቲው ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ እንዲወጡ ሲያደርግም ኢንስቲትዩቱ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ ያደርጋል።
ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወጭ ቆጣቢ ምርት በማምረት ላይም በጋራ ይሠራሉ። ኢንስቲትዩቱ ካደረገው የቴክኖሎጂ ሙከራ መካከል አንዱ ከአፈር ያመረተው ለግንባታ የሚውል ብሎኬት ነው። ብሎኬቱ ኢንስቲትዩቱ ጥናት ካደረገ በኋላ የሠራው ሲሆን፣ የጥራት ደረጃውም በሚመለከተው የመንግሥት አካል ማረጋገጫ አግኝቷል። እንዲህ ያሉ የቴክኖሎጂ ሙከራ ምርቶች ወደ ተግባር ተለውጠው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በኢንስቲትዩቱ በኩል ጥረት እየተደረገ ነው።
ከአፈር የሚሠራውን ብሎኬት ለመጭመቅ የሚያግዘውን ማሽን በሀገር ውስጥ መሥራት የሚቻልበት እድል መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር ጉታ፤ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማሽኑን በመሥራት፣ በተለይ ደግሞ የተሻለ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ሊያግዝ እንደሚችል አመልክተዋል።
በፖሊሲና ስትራቴጂ ዝግጅት ዙሪያም ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ሥራዎችን መሥራቱን አስታውሰው፣ በፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ የሚስተዋል ክፍተት ካለ እንደገና በመፈተሽ በቀጣይ 10 ዓመት ምን አይነት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ አብሮ ለመሥራት መግባባት ላይ መድረሳቸውንና የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈራረማቸውንም አስረድተዋል። የመግባቢያ ሰነዱ በአጠቃላይ ቴክኖሎጂን በማላመድ፣ ለተለያየ ኢንዱስትሪ ግብዓት መሥሪያ ማሽኖች መለዋወጫ በሀገር ውስጥ መሥራት፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በመጨመርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል። ሴሚናሮችና ወርክሾፖችን በጋራ ማዘጋጀትም ተጨማሪ የጋራ ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተቋማት መካከል ስለሚደረጉ ስምምነቶች ቀጣይነትና ውጤታማነት ዶክተር ጉታ ሲገልጹ ‹‹በኢንስቲትዩቱ የኃላፊ መቀያየር ቢያጋጥም ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው በሚያደርግ አደረጃጀት እንዲዋቀር ተደርጓል። አሁን እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ቀጣይ እንዲሆኑ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ አምስት የሥራ ክፍሎች ተዋቅረዋል። እነዚህ ተናብበው እንዲሠሩ በመደረጉ ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል›› ይላሉ።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለሙ ዲሣሣ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራ ተልዕኮዎች ያላቸው እንደመሆኑ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተቀመጠውን ተልዕኮውን ለመወጣት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ይጠበቅበታል።
‹‹ከዩኒቨርስቲው ጋር የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢንስቲትዩት ተግባር ተኮር ሥራዎችን ነው የሚያከናውኑት። ስለዚህ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ወይንም ምሑራን በተቋሙ ተገኝተው የሚያደርጉት ሙያዊ እገዛ እንዲሁም ተቋሙ ወደ ዩኒቨርስቲው በመሄድ የሚወስዳቸው አጫጭር ሥልጠናዎችም ሆኑ በሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ የሚሰጠው ትምህርት የተቋማቱንና የዩኒቨርስቲውን ጥረት ፍሬያማ ያደርጉታል። ሀገራዊ ለውጥም ያመጣል የሚል እምነት አለኝ›› ሲሉ ዶክተር ዓለሙ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚውል የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሰፊ የማዕድን ሀብት መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል ሙከራዎች ቢደረጉም የሚፈለገው ስኬት ላይ መድረስ ግን እንዳልተቻለ ይነገራል። በዚህ ረገድ በአንድ በኩል በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አለመሆኑና የትኩረት ማነስና የመሳሰሉት ጉዳዮች ይጠቀሳሉ።
ዶክተር ዓለሙ እንደሚያስረዱት፤ ለማዕድን ልማቱ ትልቁ ማነቆ የሆነው የቴክኖሎጂ እጥረት ነው። ቴክኖሎጂና የሰው ሀብት ልማቱ የተነጣጠለ አይደለም። በማዕድን ሀብት ፍለጋ ላይ በቂ የሆነ የሰው ኃይል ካለ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ቀላል እንደሆነ፣ ሁለቱ ከተሟላ በኋላ ደግሞ ቀጣይ የሚሆነው ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ነው።
በቴክኖሎጂና በሰው ሀብት ልማት ላይ ቁልፍ የሆነ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ፣ዶክተር ዓለሙ ተናግረው፣ ይህም ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት፣ እንደ ሀገር የተያዘው አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈሩ ቢሆኑም ተማሪዎቻቸውን በተግባር በተደገፈ ትምህርት ባለማነጻቸው ከየትምህርት ተቋማቱ ተመርቀው የሚወጡ ምሉዕ እንዳልሆኑና ቀጣሪ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እንደገና ሥልጠና ለመሥጠት የሚገደዱበት ሁኔታ ስለመኖሩም ይነገራል።
ዶክተር ዓለሙ ስለጉዳዩ ሲገልጹ ‹‹በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የሚያገኙት እውቀት በተግባር እንዲደገፍ ዩኒቨርሲቲው በጋራ ከሚሠራቸው ተቋማት ጋር ባለው ስምምነት የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ያመቻቻል። ከማዕድን ልማት ጋር የተያያዘውንም በተመሳሳይ ከተቋማት ጋር በመሥራት በዘርፉ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ሙሉ ሆነው እንዲወጡ ይደረጋል›› ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዓለሙ ገለጻ፤ ከተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት በዘርፉ ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኩል ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ፣ ዩኒቨርሲቲውም በተቻለ አቅሙ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል።
የዩኒቨርሰቲው ቤተ-ሙከራ በተሻለ ሁኔታ የተደራጀና የተሟላ መሠረተ ልማት አለው። በቅርቡም ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ዘመናዊ መሠረተ ልማት ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ‹‹እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ወደፊት ብዙ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል። እንዲህ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ሲቀጥሉ ኢንዱስትሪዎች ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል›› ብለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲውም በዋናነት ተልዕኮ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማዘመንና፣ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ብቃት ያለው የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ክፍተት ለመሙላት ነው። ቅድሚያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ቢሰጥም በግብርናው ዘርፍ ላይም ተዛማጅ የሆነ የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ ያግዛል።
ከመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስምምነቱ መረዳት እንደሚቻለው፣ አምራች ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አጋሮች ያስፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት የሚገኝበትን ሥፍራ በማመላከት፤ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ኤጀንሲ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማቅረብ፤ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ደግሞ ከግብዓት እስከ ምርት ያለውን ሂደት በመደገፍ በጋራ ይሠራሉ። አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በምርምር፣ በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች መስኮች ድጋፍ ያደርጋል። እነዚህ አካላት በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን ማዕድን ሚኒስቴር ዋና ተልዕኮ አስፈጻሚ ሆኖ ይሠራል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም