በሀገራችን በተለይም ደግሞ በመዲናችን አዲስ አበባ የኑሮ ውድነቱ ከፍ ብሎ መታየቱ ከማንም የተሰወረ አይደለም::በተለይ ደግሞ ከሰሞኑን የጤፍ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሻቅቧል::የመዲናዋ ነዋሪዎችም በኑሮ ውድነቱ ክፉኛ እየተፈተኑ ነው::ከዚህ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ መንስኤው ምንድን ነው? ችግሩን ለመቅረፍስ ምን እየተሠራ ነው? ስንል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ጃንጥራር አባይ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል። መልካም ንባብ ::
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ ኅብረተሰቡን እያሰቃየ ያለውን የኑሮ ውድነት የከተማ አስተዳደሩ ያውቀዋል? ካወቀው በየቀኑ በፍጥነት ለሚጨምረው የኑሮ ውድነት ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– ችግሩን የከተማ አስተዳደሩ ያውቀዋል። ያለው ኑሮ ውድነት በጣም አስከፊ መሆኑን እንረዳለን:: ከኑሮ ውድነት አኳያ በየጓዳው ገብተን የምናያቸው ችግሮች እጅግ በጣም አሳሳቢ ናቸው:: የኑሮ ውድነትን ለመፍታት ለአለፉት ሁለት ዓመታት የማኅበራትን አቅም ተጠቅመን ምርት ወደ መጋዘን እያስገባን በማኅበራት በኩል ተዘዋዋሪ ፈንድ መድበን ግዥ እንዲፈጽም በማድረግ አንጻራዊ ምርት ለነዋሪው እንዲቀርብ ተደርጓል::
ሲቀርቡ የነበሩ ምርቶቹም በጣም የድሎት ሳይሆን ኅብረተሰቡ የሚፈልገው እና በአቅሙ ልክ ሊገዛው የሚችለው አይነት ምርቶችን ነው:: ከዚህ አንጻር ስንዴ፣ ቀይ እና ሰርገኛ ጤፍ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ለኅብረተሰቡ እንዲቀርቡ ተደርጓል::
ለዳቦ ፋብሪካዎችም በቂ ጥሬ እቃ በማቅረብ ዳቦ በተመጣጠነ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ ሲሠራ ቆይቷል:: ይህንንም ለማሳለጥ ከተማ አስተዳደሩ እየደጎመ በተለይም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ የሸገር ዳቦ ኩባንያም ድጋፍ በማድረግ እና በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል::
ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር ለበዓላት ወቅት እንኳን ሆነ ተብሎ ምርት ሊያዝ ይችላል ብለን ስለምናስብ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር ግብይቱ እንዲሳለጥ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራን ነው የመጣነው:: ለገናም፣ለዘመን መለወጫ ፣ ለመስቀል ፣ ለእሬቻም ለሁሉም በዓላት የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር የሚያስችል አደረጃጀት እንዲሁም ግብረ ኃይል በማደራጀት እየሠራን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችን አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል::
አሁን ላይ ችግሩን ያለማወቅ ወይም ችግሩን ችላ የማለት ጉዳይ አይደለም:: እንደ ከተማ አስተዳደራችን ያለው እና በቅርብ ጊዜ የገጠመን ችግር ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ያለ ነው:: በቅርቡም ይህ ችግር ያጋጥመናል ብለን በመስጋት ምርት በስፋት መግዛት አለብን ብለን ዩንየኖች ገዝተው እንዲያከማቹ ለማድረግ ሙከራዎች አድርገናል::
እንዳጋጣሚ ባለፉት ሁለት ወራት ምርት ወደከተማው በስፋት ያለመግባት ሁኔታዎች አስተውለናል:: ይህም ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ ቀድሞ ለነዋሪው ገዝቶ መጋዘን ላይ የተቀመጠ ምርት ስለነበር ያንን ሙሉ በሙሉ ወደ ግብይት አስገብተነዋል:: የሚሸጥበት ዋጋም አንጻራዊ የሆነ ቅናሽ ያለው ነው ::
ነገር ግን ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ ይህ በቂ አይደለም:: በቂ ባለመሆኑ ምክንያት አሁን ላይ ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ ንሯል:: በተለይ ጤፍ ፣ስንዴ ፣ ዱቄት እና የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ እየተስተዋለው ያለው የዋጋ ንረት ከፍተኛ ነው::
አሁን ላይ ለተከሰተው የዋጋ ንረት በርካታ ምክንያቶች አሉ:: አንዱ ምክንያት ምርት ወደ ከተማው እንዳይገባ በማሰብ በአንዳንድ አካባቢዎች ምርት እንዳይወጣ የመከልከል ሁኔታዎች መፈጠሩ ነው:: በሌላ መንገድ ደግሞ ንግድ ላይ ያሉ፣ ድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ምርት በመጋዘን የማጠራቀም እና ወደ ግብይት እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታዎች አጋጥመዋል:: በወፍጮ ቤቶችም ብዙ ምርቶችን በመያዝ ወደ ግብይት የሚገባውንም ምርት በትንሹ ቀናንሰው ብቻ በማቅረብ ዋጋ ሲወደድ ለመሸጥ የሚታዩ ፍላጎቶች እና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች አሉ:: ሌላው ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ኬላዎችን በመዘርጋት ምርት በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ እና ግብይቱ እንዳይሳለጥ መደረጉ ነው:: አሁን ላይ ለተከሰተው የዋጋ ንረት ምርት እንዳይገባ የሚያደርግ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች የወለዱት ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ::
ከክልሎች ጋር ባለን ግንኙነት ወይም መስተጋብር ያረጋገጥነው በዚህ ዓመት ያለው የምርት መጠን እና የተመረተው ምርት ለፍጆታ በቂ ምርት መኖሩን ነው::
ከዚህ ባሻገር የከተማ አስተዳደሩ ምርት እንዳይደርሰው ለማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ምርቱ እንዲወጣ የማድረግ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ:: በእርግጥ ይህንን እንደ ከተማ አስተዳደር የምንከታተልበትም እና የምንሠራበት ሁኔታ የለም። እኛ አዲስ አበባ ላይ ኬላ የለንም:: ምርት በነጻነት እንዲገባልን ነው የምንፈልገው:: ነገር ግን ይህ እንዳይሆን የሚያደርጉ አካላት አሉ:: እነኝህ አካላት በግለሰብ እና በቡድን ደረጃም ሕገወጥ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ::
አንዳንድ አካባቢ ደግሞ በአንድ ወረዳም ጭምር የመታጠር ሁኔታዎች አሉ:: ምርት ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ እንኳን እንዳይንቀሳቀስ የሚደረግበት ምልክቶች ታይተዋል:: እነኝህ በጣም ትክክል አይደሉም:: በዚህም የክልል ዩንየኖች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው በቂ የሆነ ምርት እንኳን ማከማቸት አልቻሉም ::
ዩንየኖች በበቂ ሁኔታ መግዛት ባለመቻላቸው አዲስ አበባ ያሉት ዩንየኖች ክልል ላይ ከሚገኙ ዩንየኖች ምርት ገዝተው ማምጣት አልቻሉም:: በሕጉ መሠረት የአዲስ አበባ ዩንየን ምርት ከአርሶ አደሮች አይገዛም:: የሚገዛው ከዩንየኖች ነው :: ይሁን እንጂ ከተማ አስተዳደሩ አለፍ ብሎ ወስኖ ከመሠረታዊ ማኅበራትም ጭምር ምርት ተገዝቶ እንዲመጣ አድርጓል:: ከማኅበራቱ ግን መግዛት አይቻልም :: ይህን ያደረግነው ኑሮ ውድነቱን ለማስታገስ በማሰብ ሕግ ጥሰን ነው ::
ሌላው የዋጋ ንረቱን ካባባሱ ምክንያቶች አንዱ ወደ አዲስ አበባ የመጣውን ምርት ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ መጋዘኖችም፣ አዲስ አበባም በማይታዩ አካባቢዎች በመከዘን እና ለወፍጮ ቤት ትንሽ ምርት በማቅረብ ወደፊትም ይጨምራል የሚል የተዛባ አመለካከትን በኅብረተሰቡ ውስጥ የመፍጠር እንቅስቃሴዎች አሉ:: ይህም የዋጋ ንረቱን ከወለዱ ምክንያቶች አንዱ ነው ::
ከዚህ አኳያ በከተማ አስተዳደሩ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት እናውቀዋለን:: የመፍትሔ አቅጣጫዎችም አስቀምጠናል:: ነገር ግን ከጥር ወር አጋማሽ በኋላ ያለው ሁኔታ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካለው ፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር በሕገ ወጥ መንገድ ዋጋ በማናር ሕዝብን ለማነሳሳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም ::
ምክንያቱም ምርት አለ፤ ምርት ካለ ደግሞ ወደ ግብይት መግባት አለበት:: አዲስ አበባ ግን ኬላ ዘርግታ የምትከለክልበት ሁኔታ የለም:: የምንፈልገው ምርቱ እንዲገባ ነው:: ነገር ግን እጥረት እንዲፈጠር እና ብጥብጥ እንዲነሳ የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ምልክቶች አሉ:: በሌላ መንገድ ደግሞ ከገባ በኋላ ትንሸ ትንሽ ብቻ ምርት በማውጣት እና በመሸጥ አብዛኛውን ምርት ደግሞ የመደበቅ ሁኔታዎች ይታያሉ:: እነኝህን እየፈተሽን ማስተካከያ እያደረግን ነው:: ነገር ግን በትልቁ ችግሩን የፈጠረው ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው አቅርቦት አለመኖሩ ነው ::
አዲስ ዘመን ፡- ለዋጋ መናሩ በየቦታው ሕገ ወጥ ኬላዎች መኖራቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል:: ኬላዎቹ የት እና በማን የተዘጉ ናቸው ?
አቶ ጃንጥራር ፡- ኬላዎቹ ያሉት የት ነው የሚለውን ነገር ልዩ ቦታው ይህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም :: ይሁንና ኬላዎቹ እንዲነሱ ተደርጓል:: ትክክል አለመሆኑንም ከፌደራል መንግሥቱ ጭምር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው:: ይህ ችግር በሁሉም አካባቢዎች የተከሰተበት ሁኔታ አለ:: ይሄ ለምን ይፈጠራል? ለሚለው እንደ አዲስ አበባም ንግድ ቢሮ ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ውይይት ተደርጎበታል:: ችግሩ አሳሳቢ ነው:: በተለይ ከክልሎች የሚመጣውን ምርት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ ነጻ መሆን አለበት የሚለውን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ተሞክሯል::
አዲስ ዘመን ፡- በዘይት እና መሰል ሸቀጦች ላይ የዋጋ መሻሻል አይታይም:: ከቀን ወደ ቀን ዋጋቸው የመጨመር ነገር ይስተዋላል:: እዚህ ላይ የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው?
አቶ ጃንጥራር ፡– አንዴ ዋጋቸው ከተሰቀለ በኋላ ዋጋቸው ያልቀነሱ ዘይትን የመሰሉ ምርቶች አሉ:: በነገራችን ላይ የገበያ ንረቱ ዓለማቀፋዊ ገጽታም አለው:: ሀገራዊ ብቻ አይደለም:: ከተማ አቀፍ ገጽታ ብቻ አይደለም:: አንዳንድ ጊዜ የሚካሄዱ ጦርነቶች የምርት ዋጋ ላይ ንረት እንዲኖር አድርጓል:: ይሄ የሚካድ አይደለም:: ዘይት እና ስንዴ ከየት እንደምናመጣ ይታወቃል:: በመሆኑም አሁን ላይ በፊት እንደነበረው ስንዴ እና ዘይት በምቹ ሁኔታ የምናመጣበት ሁኔታ የለም ::
ይህንን ችግር መንግሥት ተረድቶ ገበያውን ለማረጋጋት ምርቶች ከመንግሥት በጀት ድጎማ እየተደረገ እየቀረቡ እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል:: ነገር ግን የዋጋ ንረቱ ከመንግሥት ድጎማም በላይ ነው::
ነጋዴዎች ዘይትን የሚያስገቡብት ዋጋ እየታወቀ ከዚህ በላይ ዋጋ መሸጥ አትችልም ቢባል ምርቱን ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ነጋዴዎች ምርት ማስገባቱን ያቆማሉ:: ስለዚህ የመጀመሪያ አማራጫችን ነጋዴዎች ምርቱን እንዲያስገቡ ማድረግ ነው:: አቅርቦቱን ማስፋት ነው:: አቅርቦቱ በሰፋ ቁጥር የዋጋ መቀነስ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ:: ስለዚህ የመንግሥት ሚና የሚሆነው አቅርቦት እንዲኖር መሥራት ነው::
የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ መንግሥት ሁሉን አቀፍ ሙከራ እያደረገ ነው:: ለምሳሌ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ማስገባት እና የመሳሰሉት እርምጃዎችን እየወሰደ ነው:: ይሁንና የምርቶች ዋጋ መናር ዓለማቀፋዊ አንድምታ ስላላቸው ችግሩ ከፍተኛ ነው:: የእኛ ለየት የሚያደርገው ሸማቹ ከሚያገኘው ገቢ አንጻር ምርቶቹ የሚገዙበት ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆኑ ነው:: ማኅበረሰቡንም ችግር ላይ የጣለው ይኸው ነው:: የመንግሥት ሠራተኛው ለቤት ኪራይ የሚያወጣው ዋጋ ከፍተኛ ነው:: የቤት ኪራይን እኛም ለመቆጣጠር ሕግ አውጥተናል፤ ደንብ አጽድቀናል:: በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳይደረግ እና ከተከራዩት ዋጋ በላይ እንዳይጨምሩ እየተሠራ ነው:: ምክንያቱም የዋጋ ንረት የምንለው የግድ የሰብል ምርቱን ብቻ ስላልሆነ ነው::
አንድ ደመወዝተኛ የሚያገኛትን ገቢ ለቤት ኪራይ ካዋለ ሌሎቹን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በምን ገዝቶ ይጠቀማል? ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ሕዝባችንን እየፈተነ ያለው የሚያገኛው የገቢ አቅም ጭምር ነው:: ከሚያገኛት የገቢ አቅም ለትራንስፖርት፣ለቤት ኪራይ አውጥቶ፣ለመብራት ለውሃ ከፍሎ ከዚያ የምትቀረዋን ደግሞ ጤፍ ለመግዛት የማያስችል ሁኔታ እንዳለ በብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ብሎም በብዙዎቹ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎቻችን ምሬት አለ:: ይህን በደንብ በዝርዝር እናውቀዋለን:: ምን ያህል ከፍተኛ ችግር እንዳለም ይታወቃል::
ይህንን ችግር ለማቃለል ቢያንስ ቢያንስ ትምህርት ቤት የሚውሉ ሕጻናትን በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እያደረግን ነው:: የሴፍትኔት ተጠቃሚዎችንም በስፋት አገልግሎቱን እያገኙ ነው:: ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን አዲስ አበባ ላይ ካለው ችግር አኳያ በቂ አይደለም::
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ላይ ሳይወለድ የመጣ የሕዝብ ቁጥር እድገት አለ:: በአዲስ አበባ ከፍተኛ የውልደት መጠን ስላለ አይደለም:: ሰፊ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍል ወደ አዲስ አበባ ስለሚገባ እንጂ::
በዚህ ምክንያት የቤት ዋጋም ይንራል ፤ የሥራ ዕድል ፈጠራውንም መሻማት ይኖራል ፤ የምታመርተውን ምርት መቀራመት ይኖራል:: ሁሉም ገዥ ይሆናል:: የምርት ዋጋው ይጨምራል:: ይህም ሌላ ምክንያት ነው:: እነኝህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት ኅብረተሰቡ በጣም የሚታገስ እና የሚተሳሰብ ሕዝብ በመሆኑ ብዙዎቹን ችግሮች ከመንግሥት ብቻ ሳይጠብቅ በራሱ ይፈታል::
በንግዱ ማኅበረሰብም በቀናነት ሕዝብን አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች መኖራቸው፤ ምርትንም በማቅረብ የሽያጭን ዋጋ ባለማናር፤ ብዙዎቹ በተለይም ኢንዱስትሪው ላይ የተሰማሩ ወገኖች እየከሰሩም ፤ ሠራተኛን በሥራቸው ላይ የሥራ አጡን ችግር ይቀንሳሉ:: የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንኳን ቢያጋጥማቸው ሠራተኛ አንበትንም ብለው ዋጋ እየከፈሉ የሚያኖሩ እና ጥሩ ሥራ የሚሠሩ ኩባንያዎች አሉ:: የዚህ ሁሉ ድምር ግን ኑሮ ውድነቱን ከመቀነስ አኳያ አሁንም ቢሆን መሠረታዊ ለውጥ ያልመጣበት ሁኔታ እንዳለ እንረዳለን ::
የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የከተማ ግብርና ብለን ጀመርን፤ በዚህም ጥሩ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ብንችልም አሁንም ቢሆን ዳር እስከዳር ሁሉም ሰው የማይተገብረው በመሆኑ በቂ አቅም እና በቂ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ ተፈጥሯል ማለ አይቻልም ::
ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ግን ገቢን ማሳደግ እና ምርትን መጨመር ነው:: ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም:: እኛ የምንኖርበት ከተማ ስለሆነ የግብርና ምርት ማምረት ባይቻል እንኳን ቢያንስ ከኢንዱስትሪዎች እና ከአገልግሎት የሚገኘውን ምርት ማሳደግ ያስፈልጋል::
ሁለተኛ በገጠሩ እና በክልሎች የሚደረገውን የምርት እድገት ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል:: በዚያው ልክ አቅርቦቱ ከፍ ስለሚል ገቢውም እንዲሁ እየሆነ ዋጋውም እየቀነሰ የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል::
ዓለማቀፋዊ ተግዳሮቶች ተጽዕኖ የሚያሳድሩበትን ጉዳይ ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ችግሩ ፈታኝ ነው:: ይህ ምንም የሚያሻማ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ የግብርና አቅም ባለው ሀገር ብዙ ምርት አምርቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለውን መሸፈን የሚያስችል እድል እያለ ይህን አለመጠቀማችን በራሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ምሬት እየፈጠረ ነው ::
ይህንን ከማድረግ አንጻር አሁን የተጀመሩ የምርታማነት ስትራቴጂዎች አሉ:: እነኝህ የበጋ ስንዴ ምርት ፣ የመስኖ ምርት ፣ የከተማ ግብርና ሥራዎች በአጠቃላይ እንደ ሀገር የልማት ትሩፋት ተብሎ ታውጆ እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎች ናቸው። ሁሉንም ተግባራዊ ካደረግናቸው ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል:: ያኔ የምርቶቹን ዋጋ ማረጋጋት ይቻላል::
በዘላቂነት የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ግን መፍትሔው በሁሉም መስክ ምርታማነትን መጨመር ነው:: ይህ ሲባል ምርታማነት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው፣በሆቴል እና ቱሪዝም እንዲሁም በግብርና እና በመሳሰሉት ያለውን ያካትታል::
እንደ አዲስ አበባ ግን ሰፊ የጤፍ ፍጆታ ኅብረተሰቡ ይፈልጋል:: ይህንን ለመፍታት አሁንም ማኅበራቱን በተጠናከረ መንገድ ምርት ወደ ከተማ እንዲያስገቡ ለማድረግ የሚያስችል ትስስር ፈጥረናል:: ይህ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለን እናስባለን ፤ ግብረኃይልም ተደራጅቷል፤ እየሠራ ነው ::
ግብረኃይሉ ያሉት ሥራዎች ሁለት ናቸው:: አንደኛው አገልግሎቱን ማሳለጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሕገወጥነትን መቆጣጠር ነው:: ከዚህ አኳያ ዋና ተቀዳሚው አጀንዳችን ምርት ወደ ገበያ እንዲወጣ ማድረግ ነው :: ዋጋ ይጨምራል በሚል ምርትን ለመያዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢነት የላቸውም:: ሁሉም ሰው በሀገሪቱ በንግድ ሕግ መሠረት መንቀሳቀስ አለበት::
ወደፊት ዋጋ ይጨምራል በማለት ትክክል ባልሆነ አስተሳሰብ ምርትን በመያዝ ሌላ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ:: ይህ ትክክል አይደለም:: ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት ቁጥጥሩን አጠናክሮ ይቀጥላል:: ከምንም በላይ ግን ቀዳሚ የሚሆነው አቅርቦትን ማስፋት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለመላ ሕዝብም ሆነ ለንግዱ ማኅበረሰብም ማሳሰብ የምንፈልገው የሕዝብን እሮሮ ለመጨመር፣ የሕዝብን ብሶት ለማባባስ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው የሚለውን ነው:: ይህ ድርጊታቸው ተገቢ ነው ብለን አናስብም:: በመንግሥት የቁጥጥር እርምጃ መውሰድ ይቻላል:: ነገር ግን ከዚያ በፊት ሰዎች መተሳሰብ አለባቸው:: ያላቸውን ምርት ወደ ግብይት ማውጣት አለባቸው:: መጠነኛ የሆነ ትርፍ እስካለ ድረስ ዘላቂ የሆነውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ማሰብ ያስፈልጋል::
በሰዎች ጉዳት የሚገኝ ሀብት፤ በግጭት የሚያተርፍ ሰው የለም:: ለግጭት የሚዳርጉ አካሄዶች እና የሰዎችን እሮሮ መሣሪያ እናደርጋቸዋለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ይህ ጠቀሜታ ያለው አይመስለኝም:: በእንደዚህ አይነት ድርጊት የሚሳተፉ ኃይሎች ካሉ ይህንን ‹‹ተው›› የሚል ማኅበረሰብ ያስፈልጋል:: ማኅበረሰቡ ችግሩን ተገንዘዝቦ ራሱን ከማይጠቅሙ እንቅስቃሴዎች መውጣት ያስፈልጋል:: ይህን በሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል::
አሁን ኬላዎችም ክፍት ናቸው፤ ምርትም ክልሎች ላይ አለ:: ምርት የሚገባበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው:: ችግሩን ለመፍታት መንግሥት አልተኛም ፤እየሠራ ነው:: ችግሩም በዝርዝር ይታወቃል::
አዲስ ዘመን፡- የጤፍ ዋጋስ ከውጭ እንደሚገባው ዘይት ተሰቅሎ ይቀራል ወይስ ወደነበረበት ይወርዳል? አሁን የናረውን የምርት ዋጋ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ያስተካክለዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ጃንጥራር፡- አሁን ለምሳሌ ማኅበራት ቀደም ብለው ገዝተው የነበሩትን ምርት የሚሸጡበት ዋጋ እንደገባበት ጊዜ ይወሰናል:: ከ4 ሺ 800 እስከ 6 ሺ 500 ድረስም ሲሸጡ ቆይተዋል:: አሁን ያለን ስምምነት የጤፍ ዋጋ በተለይ ከማኅበራት ጋር መጠባበቂያ በመውሰድ የእኛ ማኅበራት ለክልል ማኅበራት ገንዘብ በመስጠት ከየአካባቢው ገዝተው እንዲያመጡ ስምምነት ላይ ደርሰናል:: ስምምነታችን ዋጋውን በሚቀንስበት መንገድ ላይ ያተኩራል:: የትራንስፖርት ዋጋና መሰል ሁኔታዎችን ጨምሮ አዲስ አበባ ላይ የሚገባበትን ዋጋ ገና እያየነው ነው:: ነገር ግን አሁን የሚወራውን አይነት ከፍተኛ የዋጋ መጠን በአንጻራዊነት ይቀንሳል ብለን አቅደን እየሠራን ነው:: ይህም ተከታታይ የሆነውን የምርት ክምችት መፍጠር ከቻልን ቢያንስ ቢያንስ ዝም ብሎ የተሰቀለውን ዋጋ አንጻራዊ የሆነ ቅናሽ እንዲያመጣ ለማድረግ እየተሠራ ነው:: ይህ ማለት ግን ችግር አይኖርም ማለት ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ መዛባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ:: ባለፈው ዓመት 6 ሺ 500 ይሸጥ የነበረው ጤፍ አሁን ከ6 ሺ 500 በታች እናወርደዋለን ማለት አይደለም:: ይህ ሊሆን አይችልም:: ቢያንስ ቢያንስ እንኳን ገበያው የሰቀለውን፤ ድንገት የወጣውን ፤በሕገወጥ መንገድ ከፍ ያለውን ዋጋ በሚፈታ መልኩ እንዲወርድ የሚያስችል እንቅስቃሴ ይደረጋል:: በምን ያህል መሸጥ አለበት የሚለውን መወሰን የሚቻለው ምርቱ በስፋት ቀርቦ ዋጋውን ስናየው ነው ::
አሁን ባለን ግምገማ አዋጭ ነው ብለን የገባንበት ሁኔታ አለ:: ገበያ ላይ ያለው ማለትም እዚህም እዚያም በሚደረገው አሉባልታ ያለው የገበያ ዋጋና እኛ የምንገዛበት ዋጋ በፍጹም ልዩነት አለው:: እርሱን ዝቅ አድርገን የምናቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል:: በልበ ሙሉነት በዚህ ዋጋ የማንልበት ምክንያት ግዢው ላይ የሚሳተፈው ማኅበር ገና ወደ ክልሎች ሄዷል:: ከክልሎች ሰብስቦ ይዞ የሚመጣውን ዋጋ በሚቀጥለው ሳምንት አካባቢ የሚያቀርብ ይሆናል:: እኛም ስለሁኔታው የምንገልጽበት ሁኔታ ይኖራል::
አዲስ ዘመን፡- ኑሮውን ለማረጋጋት በሚል የሰንበት ገበያ ተቋቁሞ ነበር:: በተጨማሪ ማኅበራት ለዳቦ አምራቾች ግብዓት እንዲያቀርቡ ሲደረግ ነበር:: ይህና መሰል ተግባራት የኑሮ ውድነቱን አቅልሎታል ተብሎ ይታሰባል? ካሉ ተጨባጭ መሳያዎችን ቢጠቅሱልን?
አቶ ጃንጥራር፡– እውነት ለመናገር የሰንበት ገበያ በየአካባቢው በመፈጠሩ ምክንያት ዋጋን ከማረጋጋት አኳያ ብዙ አዎንታዊ ሚናዎችን ተጫውቷል:: በአዲስ አበባ መጀመሪያ ላይ 119 የሰንበት ገበያዎች ነበሩ:: በኋላም 126 የሆኑ አካባቢያዊ ገበያዎች ተፈጥረዋል:: በዚህም አንጻራዊ የዋጋ ቅናሽ ባለው ሁኔታ ምርት የሚገዛበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ምርቱን ከተፈለገበት ለማድረስ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል:: በአዲስ አበባ ውስጥ ምርት ጭኖ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ደግሞ የምታወጣው ወጪ በጣም ከባድ ነው:: የታክሲ ዋጋ፤ እኔ እጭናለሁ በሚል የሚደረግ ፍትጊያና የጫኝ አውራጅ ክፍያ ብዙ ነው:: እነኝህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ የሰንበት ገበያዎች የሕዝቡን ችግር በሚፈታ መንገድ አካባቢያዊ ግብይት መፈጠር ችለዋል::
ሁለተኛ ገበያው የተፈጠረላቸው አካላት ቀጥታ አምራቾች በመሆናቸው ምርቱን ይዘው መጥተው እዚያው ቆመው የሚሸጡ ስለሆነ መሐል ላይ ያለውን ደላላ ለማስቀረትም ተችሏል:: መሐል ላይ ያለው የገበያ ሽግግር ቀንሷል:: ይህንና መሰል ነገሮች ደግሞ ዋጋውን እንዲቀንስ እድል ሰጥተውታል:: ይህ ሲባል ግን ሰው ከሚገዛበት አቅም አንጻር አይደለም የሚታየው:: ገበያ ላይ ካለው ዋጋ አኳያና ከሚያወጣው ወጪ አንጻር እንጂ:: ስለዚህም የሰንበት ገበያ ለነዋሪዎቹ ዋጋን ከማረጋጋት አንጻር መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ የቆየ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ይህ አልቆመም፤ ይቀጥላል::
አሁን ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ጾም ላይ ነው:: ስለሆነም በዚህ ሰሞን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ጨመር ያለበት ሁኔታ አለ:: በእስልምናውም የረመዳን ጾም በቅርቡ ይጀምራል:: ኢድ አልፈጥር በዓል እና የትንሳኤ በዓልም በተከታታይ እንደሚመጡ ይታወቃል:: በመሆኑም ከበዓላቱ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የዋጋ ንረቶችን ለመከላከል እየተሠራ ነው::
ይህንን ችግር ለመፍታት የት አካባቢ ላይ ነው ምርት ያለው? ብለን ምርቱ ካለበት አካባቢ ጋር ትስስር ለመፍጠር እየሠራን ነው:: ከዚያ ውጪ እነዚህ አምራቾች በቀጥታ ወደ ገበያው ይዘው እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ እንሠራለን:: እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ አንጻራዊ የሆነ ቅናሽ ይኖራቸዋል:: ምርቱን በሚፈልገው አካባቢ ማግኘት ለኅብረተሰቡ ይጠቅማል የሚል እሳቤ አለን :: ከዚህ ጋር ተያይዞ ሚዲያውም የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ከሕገወጦቹ ጋር በተያያዘ ምን መነሻ ተደርጎ ነው እየተሠራ ያለው? መንግሥት የደረሰበት ግምገማ ካለ ቢጠቀስ ?
አቶ ጃንጥራር፡- ግብረኃይሉ ተደራጅቶ እየሠራ ነው:: በተጨባጭ ምንድነው ምክንያቱ ብለን ብናይ መጀመሪያ ሆኖ ያገኘነው ምርት ወደአዲስ አበባ እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታዎች አሉ:: ኬላዎች ይዘጋሉ፤ ምርት ይጨምራል በሚል ዝቅተኛ ዋጋ ጭምር ተወስኗል የሚል ነገር በአንዳንድ አካባቢዎች ሰማን:: ችግሮች አሉ ብለንም ለንግድና ቀጣናዊ ትስስርም ጉዳዩን አቀረብን:: በዚህም ኬላዎች እንዲከፈቱና መሰል ችግሮች እንዲታረሙ በሚልም አቀረብን:: በዚህም ጥሩ ምላሽ ተገኝቷል::
ሌሎች ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት ደግሞ በየክልሎች ላይ ገዝተው እዚያው በአካባቢያቸው
እያከማቹ ያሉ ነጋዴዎች እና ደላሎች መኖራቸውን ሰማን:: እኛ በዓይናችን ሄደን የት አካባቢ ምን ያህል ምርት፤ የትኞቹ ወፍጮ ቤቶች የሚለውን አላየንም:: ይህ ነገር እንደሚኖር ግን መገመት የሚያዳግት አይደለም:: ምክንያቱም ዋጋ ሲተመን ፤ ኬላ ሲዘጋ ምርቶችን ሰብስቦ ማከማቸቱ የሚቀር አይደለምና:: ከዚህ አንጻር ከክልሎች ጋር ተግባብተን እየሠራን ነው::
ከዚህ አለፍ ባለ መንገድ ደግሞ ፖለቲካ ችግር እንፈጥራለን የሚሉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ:: እነማን ናቸው የሚል ጥያቄ ቢነሳ ልንመልስ አንችልም:: ምክንያቱም መልሱ ሊመለስ የሚችለው በምርመራ ስለሆነ:: ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስተካከል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሠራን ነው::
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ምርት ተከማችቷል የሚሉ ሀሳቦች ይሰማሉ:: የት ላይ ነው ያለው የሚለውን ገና እየፈተሽን ነው:: ማነው በዚያ መንገድ እየተሳተፈ ያለው የሚሉትን እያየን ነው። አስቀድመን ግን በሕገወጥ መልኩ ምርት ለአከማቹ አካላት እጃችሁ ላይ ያከማቻችሁት ምርት ካለ ወደገበያ አውጡ ስንል ጥሪ እያስተላለፍን ነው:: የንግድ ሕጉ በሚፈቅድላችሁ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆናችሁ ተንቀሳቀሱ፤ ይህ አይጠቅምም:: ሁላችንም ለሕዝባችን ማሰብ ያስፈልገናል:: ልናስብ ይገባልም የሚል ነው:: ‹‹አይ ይህንን አላደርግም፣ በሕገወጥ በመደበቅ ጊዜውን አልፌው እንዲህ አደርጋለሁ›› የሚል ሰው ካለ ከሕግና ከሰው እይታ ውጪ ስላልሆነ መረጃዎች መስጠት ያስፈልጋል፤ እርምጃ እንወስዳለን::
ይህ ደግሞ ሕግ በሚፈቅደው መንገድ የሚወሰድ እርምጃ ነው የሚሆነው፤ያ ደግሞ አደገኛ ነው፤ አያስተምርም:: የሚያስተምረው መተሳሰብ ሲኖር ብቻ ነው:: የተወሰነ ጥቅም የሚያገኝ ሰው ለሌላው ሕዝብም ማሰብ አለበት :: የኢትዮጵያውያን ባሕላችንም ይህ ነው::
የዳቦ ገበያውንም ለማረጋጋት በየቦታው በርካታ ቁጥር ያላቸው የዳቦ ፋብሪካዎች አቋቋምን:: አሁንም እያቋቋምን ያለነው:: ለእነዚህ ስንዴ ዱቄት ያስፈልጋቸዋል:: ማኅበራት ደግሞ ይህንን እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋን ነው :: ከክልል እንዲመጣ ኬላዎች መከፈትና ነጻ መሆን አለባቸው እያልን ነው:: ይህም ሆኖ ደግሞ አንዳንዶቹ ቀና ሆነው ለሕዝባችን መድረስ አለብን ብለው ከሚያመርቱት ምርት ደጉመው እያቀረቡ ባሉበት እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ይህንን አጋጣሚ ለሌላ ዓላማ መጠቀም ተገቢ አይደለም:: ወይም ለሕዝብ አመጽ ማነሳሻነት ለመጠቀም የሚያስቡ ኃይሎች ካሉ አይጠቅማቸውም:: በሕዝብ ግጭት የሚያተርፍ የለም:: ዝም ብሎ መቆጣጠር፤ እርምጃ መውሰድ፤ የት ገባህ የት ወጣህ በማለት ማሳደድ ሳይሆን መተሳሰብ ነው መቅደም ያለበት፡፡
ምርት የያዘ ሰው ወደ ገበያው ያውጣ፤ ሕዝብ መቸገር የለበትም ነው እያልን ያለነው:: ይህ እስኪሆን ድረስ እኛ አንቆምም:: በየትኛውም አካባቢ ያለው ምርት ወደ ከተማ እንዲገባ የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተናል፤ ደግሞም ይሳካልናል ብለን ነው የምናስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብረኃይሉ ከምን ከምን የተውጣጣ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– የግብረኃይሉ አደረጃጀት በምክትል ከንቲባ የሚመራ ሲሆን፤ የንግድ፣ የገቢዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ ደንብ ማስከበርና ማኅበራትን ያቀፈ ነው:: ይህ አደረጃጀት ክፍለ ከተማ ላይ አለ:: ወረዳ ላይም እንዲሁ ተፈጥሯል:: ስለዚህም በየወረዳዎች ላይ ያለው ሁኔታ ሁሉ ይታወቃል ::
ከማኅበራት ጋር ተያይዞ በእቅድ መመራት እንዳለባቸው ይታወቃል:: ከዚህ አንጻር ማኅበራት መቼ ምርት ማቅረብ እንዳለባቸው፤ የት መግዛት እንዳለባቸው አቅደን አሁን ወደ ሥራ ገብተናል፤ ከሳምንት በኋላም ውጤቱን መለካት እንጀምራለን ::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊትም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ያውቃል:: ያላቸው ውጤታማነት ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: አሁን የተቋቋመው ከዚህ አኳያ ውጤታማነቱ እንዴት ይታያል?
አቶ ጃንጥራር፡- በነገራችን ላይ ይህ ድንገተኛ አጋጣሚ ሆነብን እንጂ ግብረ ኃይሉ በመሥራቱ ብዙ ነገሮችን ፈትቷል:: ቀደም ብዬ ገልጫለሁ:: ምርት ባለበት አካባቢ እየሄደ ምርት ያመጣል:: ማኅበራት ቅርብ ጊዜም ተነቃቅተው ምርት እንዲያስገቡ በማድረግ ሽያጭ እንዲያከናውኑ እየተደረገ ነው:: ለበዓላት የእንስሳት ውጤቶችም፤ የግብርና ምርቶችም በስፋት እንዲቀርቡ የተደረገው ክፍተት ያለበትን እየገመገምን በመሙላት ነው::
አሁን ቅርብ ጊዜ የተፈጠረው ጉዳይ ግን ቅድም እንደገለጽኩት ከሕገወጥነት ጋር በተያያዘ ችግር የተከሰተ ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተማ አስተዳደሩ እንደውም ከከተማው ውጪ አቅዶ እየሠራ ነበር:: ምርትም ለማስገባት ሞክሯል:: ሰው እየተቸገረ ምርትን ይዘን መቆየት ስለሌለብን ለመጠባበቂያ በመጋዘን ይገኝ የነበሩ ምርቶችን አውጥተን ሽጠናል::
የግብረ ኃይሉ ዋነኛ ሥራው ነገሮችን ማስተባበር ላይ እንጂ ጤፍ ኖሮት ጤፍ የሚያቀርብ ፤ ስንዴ ኖሮት ስንዴ የሚያቀርብ አይደለም:: ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ገበያውን ለመቆጣጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማሳለጥ ነው:: ለምሳሌ የእሁድ ገበያን ጸጥታ፣ የሚቀርቡ ምርቶች ችግር እንዳይገጥማቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ አርሶ አደሮች ግብይት እንዲፈጠርላቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ወደ ግብይት እንዲገባ በማድረግ፤ ክፍለ ከተማና ወረዳ ላይ ያለው ጥምረትን በሚመለከት ሲሠራ ነው የቆየው::
ግብረኃይሉ ዝም ብሎ የሚቋቋምና የሚፈርስ አይነትም አይደለም:: ይህንን እንደገና የከለስንበት ብሎም አደረጃጀቱም በአግባቡ ሲመራ ነው የቆየው። ነገር ግን ከዚህ ወጣ ባለ መንገድ ለየት ያለ ባህሪ ያለው መሆኑ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል የማጠናከር ነው። አዲስ የማፍረስ አዲስ የመገንባት አይነት አይደለም። ዋናው የግብረኃይሉ ሥራ ማመቻቸት ወይም ማደራጀት እና ቁጥጥር ሥራዎችን ማከናወን ነው። ለአቅርቦቱም እንዲሁም የግብይት ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያስችል አደረጃጀት ነው እንደከተማ ወስነን እየገባንበት ያለው።
አዲስ ዘመን:- ሕገወጦች ትልቅ ሚና አላቸው ከሚባሉት ደላሎች ተጠቃሾች ናቸው። የደላላን ጣልቃ ገብነት ከማስቆም አንጻር የተሠራው ሠራ ምንድን ነው ?
አቶ ጃንጥራር:- ደላላ ይኖራል። አይኖርም ማለት አይደለም። ለአብነት በመንግሥት በኩል በዓላት ሲቃረቡ የማዋከብና በገበያ ቦታዎች ላይ ችግሮችን የመፍጠር ሁኔታዎች እንደነበሩ ይታወሳል። ይህ እንዳይኖር የሚያስችል እንቅስቃሴ ባለፉት በዓላት አድርገናል። ለገና በዓልም ለዘመን መለወጫም ለአረፋ በዓልም ወዘተ በሁሉም በዓላት ላይ ማለት ይቻላል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ደላላውና ነጋዴው የመቀላቀል ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ነጋዴ በተፈቀደለት የንግድ ፍቃድ መሠረት ምርት ወይም አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ነው። ስለዚህ ምርትና አገልግሎትን ገዝቶ ወደ ውጭ ይልካል፤ ወይም ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባል::
በአንጻሩ ደላላው ወይም ሕገወጡ አካል ደግሞ በተጠቃሚውና በአቅራቢው መካከል ያለውን የፍላጎትና የአቅርቦት መጣጣምን ሚዛን በማሳጣት በዚህ መካከል የሚገኘውን ትርፍ በራሱ ያደርጋል:: በዚህም የከፋ ጉዳት ያደርሳል:: ይህ አካሄድ በሕዝብ ላይ ጫና ከመፍጠር በቀር ሌላ የሚያስገኘው ጥቅም የለም ። ስለሆነም ሕገወጦች ከዚህ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል::
ሽንኩርትን ከሸዋ ሮቢት ጭነን ካመጣን እና ሸዋ ሮቢት ያለው አርሶ አደር በቀጥታ አዲስ አበባ አምጥቶ የሚሸጥበትን እድል እስከፈጠርን ድረስ ሸዋ ሮቢት ያለው አርሶ አደር ተጠቃሚ ይሆናል:: አዲስ አበባ ያለው ሕዝብም እንዲሁ ተጠቃሚ ይሆናል::
ነገር ግን ሸዋ ሮቢት ያለው አርሶ አደር የደብረ ሲና ደላላ ከተቀበለው ፤ የደብረሲናውን ደግሞ የደብረ ብርሃን ደላላ ከተቀበለው በዚህ ላይ የሚኖረው የምርት ዋጋ ጭማሪ እዚህ ላይ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ትከሻ ላይ ይወድቃል::
ይህንን ሰንሰለት ለማሳጠር አምራቹን በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚደርስበት ሥርዓት በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል አምራቹ ለማኅበራቱ በቀጥታ አምጥቶ የሚሸጥበትን እድል ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::
ከዚህ በተጨማሪ ለአንዳንዶቹ ደግሞ በተደራጀ መልኩ የሚያመጡትን ምርት በቀጥታ የሚያከማቹበት እድል ተፈጥሯል ፤ የገበያ ማዕከላት በማስፋፋት በርካታ ሥራዎችን ሥንሰራ ቆይተናል:: በዚህ በኩል ባለፉት ጊዜያት ብዙ ነገሮችን አሳክተናል።
አሁን የተፈጠረው ጉድለት ግን አስቀድሜ በጠቀስኩት ምክንያት በመሆኑ የደላላን ጣልቃ ገብነት መበጣጠስ ይጠይቃል። ህገወጥ ኬላዎችን ማጥፋት ይጠይቃል። አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በነጻ የሚሸጥበት እድል ሊፈጠር ይገባል። ይህንን ለማድረግ በአንድ ከተማ ብቻ የሚታጠር አይደለም። ከክልሎች ጋር መቀናጀት የግድ ነው።
በከተማችንም ያሉትን ማኅበራት በማጠናከር በገንዘብ አቅም ውስንነት ምክንያት ምርት ለመግዛት ችግር እንዳይገጥማቸው አድርገናል። ነገር ግን ያላቸው የገንዘብ አቅም ብቻ መፍትሔ ሊሆን አልቻለም። በተለያዩ አካባቢዎች የገበያ ልውውጡን የሚያውኩ ነገሮች አሉ:: አምራቹ ወደገበያ እንዳይመጣ ያደርጋሉ:: ይህ ደግሞ ዩንየኖችን በነጻነት ተንቀሳቅሰው መግዛት እንዳይችሉ እክል ይፈጥርባቸዋል::
እንደዚህ አይነት ተግባር ላይ በስፋት የሚገኙት ደግሞ ደላላዎች እና በመንግሥት አሻጥር የሚሠሩ የራሳቸው ተልዕኮ ያላቸው ኃይሎች ናቸው:: ስለዚህ ገንዘብ መኖሩ ብቻ በቂ ስላልሆነ በሀገሪቱ የሚካሄዱ ግብይቶችን ለማሳለጥ በየአካባቢው ግብይት ላይ እክል ሚፈጥሩ አካላትን ሕዝብ እና መንግሥት ተባብረው ማረም ይኖርባቸዋል::
ገበያውን እየዘወረው ያለው ደላላው ነው የሚለው የአዲስ አበባን ብቻ ነጥሎ አይሠራም። እንደዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ አልደረስንም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አዲስ አበባ ላይ ደላላ አለ። በዚህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን እንደሚያበላሽ ይታወቃል። በሁሉም መስኮች ላይ የደላላ ጣልቃ ገብነት አለ። ግልጽ ነው። ከግብርና ምርት ጋር ተያይዞ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለአብነት ማኅበራት ደላላ ጣልቃ አይገባባቸውም። ክልል ማኅበራት ላይ ምርት ማምጣት አለባቸው። የክልል ማኅበራት ግን በቂ ምርት አልያዙም። ምርቱንም ይዘው ለመሸጥ እና እኛ ጋር ትስስር ለመፍጠር ባለፉት ጊዜያት የተወሰኑ እንቅፋቶች ገጥመው ነበር። አሁን ያ ችግር እንዲፈታ ነው እየተነጋገርን ያለነው። ይሄን ደላላው ፈጥሮታል ማለት አይቻልም።
ማኅበራት የሚያመጡትን ምርት ሲያከፋፍሉ ወይም ሲሸጡ ደላላው ሊገባበት አይችልም። በንግዱ ውስጥ ግን ደላላው አይኖርም ማለት አይደለም። በከፍተኛ ሁኔታ አለ። ይሄ ችግር በአዲስ አበባ ብቻ የሚታጠር አይደለም። በክልሎችም ምርት እያከማቹ ለረጅም ጊዜ ምርት የሚይዙበት እንቅስቃሴዎች የደላላው እጅ የለበትም እያልኩ አይደለም። የደላላው እጅ እንዳለበት አሻሚ አይደለም። በአጠቃላይ ግን በአዲስ አበባ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ደላላው በበላይነት እየዘወረው ነው፤ አሁን ላይ ቁጥጥር እያደረግን ስለሆነ የምንደርስበት ይሆናል። ምን ያህል ነው ስፋቱ የሚለውን እናውቃለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን:- በተለያየ ጊዜ የቤት ኪራይን በተመለከተ በአስተዳደሩ መመሪያዎች ይወርዳሉ። በትክክል ወደ ኅብረተሰቡ ከማድረስ አኳያ ምን ሥራዎች ተከናውነዋል? ተመን አበጅቶ ወይም በሌላ መንገድ ከመቆጣጠር አንጻር ምንድን ነው በተጨባጭ እየተሠራ ያለው?
አቶ ጃንጥራር:- በመሠረታዊነት የቤት ኪራይ በዚህ አከራይ ተብሎ ተመን መተመን ተገቢ ነው ብለን አናስብም:: ነጻ ገበያን የምታራምድ ሀገር ላይ በሁሉም ነገር ላይ መንግሥት ዋጋ እየተመነ መቀጠል አይችልም::
ነገር ግን አንድ ሰው ቤት ሲከራይ ከአከራዩ ጋር የኮንትራት ውል ሲዋዋል አከራዩ በፈለገው ጊዜ ሁኔታዎችን እየጠበቀ የቤት ኪራይ ሊጨምር አይገባም ወይም ኅብረተሰቡ ያለበትን የኑሮ ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት መጀመሪያ ተከራይ ቤቱን ሲከራይ ከተጠየቀው ገንዘብ በላይ እንዳይጨመር ነው የእኛ አቋም:: ባለፈው ዓመት ከተማ አስተዳደሩ አንድ ደንብ አውጥቷል:: ያ ደንብ በየስድስት ወሩ እየቀጠለ ነው ያለው:: አሁንም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በቤት ኪራይ ላይ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ወስኗል::
መንግሥት ይህን የመሰለ ውሳኔ ወስኖ እያለ አከራይ ቢጨምር ተከራይ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት:: መክፈልም የለበትም:: ነገር ግን መንግሥትን ተወው አንተና እኔ እንስማማ የሚል ተከራይ ካለ ችግሩ የተከራዩ ነው::
ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ቢኖር ከቤት ኪራይ ተመን ጋር ተያይዞ መንግስት በካሬ ሜትር ለክቶ የቤት ኪራይን ዋጋ አልወሰንም ::
በከተማ አስተዳደሩ የቤት ኪራይን ዋጋ መናርን ለመቀነስ አከራዮች ባከራዩበት ዋጋ እንዲጸኑ ማድረጉ ችግሩን በዘላቂነት አይፈታውም:: ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት በግላቸው ለሚሠሩ ሰዎች በግላቸው እንዲገነቡ መፍቀድ ፤ መንግስትም ያለውን አቅም ተጠቅሞ ተጨማሪ ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን ፡- የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አንጻር ሕዝብ ምን ይጠብቅ?
አቶ ጃንጥራር ፡– በነገራችን ላይ መንግሥት ቁጥር አንድ አጀንዳ አድርጎ በትኩረት እየሠራ ያለው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ነው:: እንደአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህንን ችግር እንዴት እንፍታ ብለን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገን እየሰራን ነው ያለነው::
እንደ አዲስ አበባ ከተማ ገበያውን ምቹ ማድረግ አንዱ ሥራችን ነው:: አቅርቦት እንዲኖር መሥራት ሁለተኛው ሥራችን ነው:: ሕገወጥነትን መቆጣጠር ሌላቸው ተግባራችን ነው::
የግብይት ሥርዓቱ እንዲፋጠን የሰንበት ገበያ ብቻ አይደለም ፤ተጨማሪ የገበያ ማዕከሎችን እየገነባን ነው:: ከዚህ አንጻር በመንቀሳቀስ ከተማ አስተዳደሩ የተሻለ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር እየሠራነው ::
አዲስ ዘመን:- ለኑሮ ውድነቱ መባባስ በተለያዩ አካባቢዎች ኬላዎች መጣላቸው ፣ ሕገወጦች መበራከታቸውን መሆኑን ነግረውናል:: ከዚህ አንጻር የከተማ አስተዳደሩ ብሎም መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል በእርግጥስ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ያስችላል?
አቶ ጃንጥራር ፡– እኔ የማወራው ስለ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው:: ችግሩን ከመፍታት አይን ካየነው ችግሩ ብዙ ስለሆነ ችግሩን አልፈታነውም:: መንግሥት ግን እንደ መንግሥት ከመንግሥት የሚጠበቅበትን ሥራ ለመሥራት ችግር የለበትም ::
አዲስ ዘመን ፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ጃንጥራር ፡– እኔም አመሰግናለሁ::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም