34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ በኮትዲቯር አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። 24 ሀገራት ለሚካፈሉበት ለዚህ ውድድርም የማጣሪያ ጨዋታዎች ካለፈው አመት ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በዚህ ማጣሪያ የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታ ከጊኒ ጋር መጋቢት 15 እና 18/2015 ዓ.ም በሞሮኮ ያከናውናሉ።
በተያዘው መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም አጋማሽ ለሚከናወኑት ጨዋታዎችም በምድብ 4 የተደለደሉት ሁለቱ ሀገራት በዚህ ጨዋታ ላይ የሚካፈሉ ተጫዋቾቻቸውን አሳውቀዋል። የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የ23 ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ባለፈው ዓርብ አመሻሽ ይፋ አድርገዋል። በዝርዝሩ ውስጥም ከሀገር ውጭ የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር እንዲሁም ኡመድ ኡክሪም ተካተዋል። በዚህም መሰረት ግብ ጠባቂዎች የባህር ዳር ከተማው ፋሲል ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ መድኑ አቡበከር ኑራ እና የአዳማ ከተማው ሰኢድ ሃብታሙ ጥሪ ደርሷቸዋል። በተከላካይ በኩልም የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ረመዳን የሱፍ፣ ሱለይማን ሃሚድ፣ ምኞት ደበበ፣ የሃዲያ ሆሳዕናው ብርሃኑ በቀለ፣ የአዳማ ከተማው ሚሊዮን ሰለሞን፣ የሲዳማ ቡናው ጊት ጋትኩት፣ የባህርዳር ከተማው ያሬድ ባዬ እና የፋሲል ከተማው አስቻለው ታመነ ተካተዋል፡፡
ይገዙ ቦጋለ ከሲዳማ ቡና፣ አቤል ያለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ ከአዳማ ከተማ፣ አቡበከር ናስር ከማሜሎዲ ሰንዳውስ እንዲሁም ከረጅም ጊዜ በኋላ ኡመድ ኡክሪ ከአል ሱዋይቅ ለቡድኑ በአጥቂ ስፍራ እንዲጫወቱ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። አማካዮችም ጋቶች ፓኖም እና ቢኒያም በላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ይሁን እንዳሻው፣ ታፈሰ ሰለሞን ከፋሲል ከተማ፣ አማኑኤል ዮሃንስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከነዓን ማርክነህ ከመቻል እንዲሁም ሽመልስ በቀለ ከግብፁ ኤንፒ ክለብ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲወክሉ ጥሪ የቀረበላቸው ተጫዋቾች ሆነዋል።
በምድቡ ኢትዮጵያ ከማላዊ፣ ጊኒ እና ግብጽ ጋር የተደለደለች ሲሆን፤ ሁሉም ቡድኖች ሁለት ሁለት ጨዋታዎችንን ከወራት በፊት ማከናወናቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የምድቡን ጨዋታ ከማላዊ ጋር ያደረገች ሲሆን፤ በቤንጉ ስታዲየም በተካሄደው ግጥሚያ 2ለ1 በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር የተሸነፈችው። ከቀናት በኋላ በዚያው ስታዲየም ግብጽን በማስተናገድም አስደማሚ የሆነ የ2ለ0 ውጤት ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ በግብጽ የአንድ ለምንም ሽንፈት የደረሰባት ጊኒ በበኩሏ፤ በቀጣዩ ጨዋታ ማላዊን በሜዳዋ አስተናግዳ 1ለባዶ መርታት ችላለች። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይም ሁሉም ቡድኖች በመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸው አንድ አንድ ጨዋታ ተሸንፈው ሁለተኛ ጨዋታቸውን በማሸነፋቸው በእኩል ሶስት ሶስት ነጥቦችን ማስመዝገብ ችለዋል።
ይህም የምድቡ ቀሪ ጨዋታዎች ለውጥ ያመጡ ይሆናል በሚል በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ከቀናት በኋላ ቡድኖቹ የምድባቸውን ሶስተኛ ጨዋታ የሚያከናውኑም ይሆናል። የራሷ ሜዳ የሌላት ኢትዮጵያ ሞሮኮ ላይ የጊኒ ብሔራዊ ቡድንን ትገጥማለች። በዚያው ዕለት ካይሮ ላይ ደግሞ ማላዊ እና ግብጽ ሌላኛውን የምድቡን ጨዋታ የሚያከናውኑ መሆኑን የተያዘው መርሃ ግብር ያሳያል። በቀጣይም በምድቡ የተደለደሉ አራቱ ሀገራት በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በማከናወን ከምድቡ በማለፍ የአፍሪካ ዋንጫው ላይ የሚሳተፉት ሁለቱ ቡድኖች የሚለዩ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም