ዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ የግብርናውን ስራ ማሳለጥ በጭራሽ አይታሰብም። በኢትዮጵያ ምድር ግን ያለው አስተሳሰብ የሚያመላክተው ዘርቶ መቃም የሚቻለው የግድ በዝናብ ላይ በመንጠላጠል ብቻ እንደሆነ ነው። ሀገሪቱ ያላት የመሬትም ሆነ የውሃ ሀብት ከበቂም በላይ ሆኖ ሳለ በተፈለገው ልክ መጠቀም አልተቻለም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ዝናብ በወቅቱ ካልዘነበ ዙሪያው ገደል መሆኑ ነው። ለአብነት ያህል መውሰድ ከተቻለ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች ባሉ አንዳንድ ዞኖች ውስጥ ዝናብ ካለመዝነቡ የተነሳ የተፈጠረውን ድርቅ በማየት መረዳት ይቻላል። ፈተናው ከድርቅም በላይ የከፋ እንዳይሆን ዘላቂ መፍትሔዎች ከወዲሁ ማስቀመጡ አጠያያቂ አይደለም። በኦሮሚያ ቦረና አካባቢ የተፈጠረውን ድርቅ አይነት ጅማሬ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞንም በመታየት ላይ ነው። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞኑ ስላለው ሁኔታ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ከሆኑት ከአቶ ንጋቱ ዳንሳ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል። ይህም እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።
አዲስ ዘመን፡- በደቡብ ኦሞ ዞን የተፈጠረው ድርቅ ምክንያቱ ምንድን ነው? አሳሳቢነቱ በምን ያህል ደረጃ ይገለጻል?
አቶ ንጋቱ፡- በዞናችን ለተከሰተው የድርቅ ችግር ምንጩ የተፈጥሮ አየር ጸባይ መዛባት ነው። በዞኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት በትክክል የመኸርና የበልግ ዝናብ መዝነብ አልቻለም። ዝናቡ በተጠበቀው ልክ ካለመዝነቡ የተነሳ የፈጠረው ችግር ነው። እንደሚታወቀው አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የሕይወቱ መሰረት ውሃ ነው። አርብቶ አደሩ ደግሞ እንስሳውን ሊያጠጣ የሚችል ውሃ መኖር የግድ ነው። ይሁንና ዝናብ ባለመዝነቡና ውሃ ባለመኖሩ ምክንያት አርሶ አደሩ ለእንስሳቱ በቂ የግጦሽ ሳር እንዳያገኝ አድርጎታል። ይህንንም ያደረገው የዝናቡ መዛባት ሲሆን፣ ይህም በሰውም ሆነ በእንስሳቱ ላይ ጫና አሳድሯል።
በዚህም ምክንያት በዚህ ዓመት ለኅብረተሰቡ የሚያስፈልግ ምግብ የለም። የምግብ እጥረቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ባደረግነውም ፍተሻ ከ337 ሺ በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል። የምግብ እጥረቱ በህጻናትም አካባቢ ጎልቶ የታየ ነው። ህጻናቱ የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት የሚከሰቱ አይነት በሽታዎች በየጤና ተቋማቱ ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ከዚህ ቀደም በዞኑ ይታይ ከነበረው የወባ በሽታ ሰፋ ባለ መልኩ በጤና ተቋማት ታይቷል። በተመሳሳይ የኩፍኝ ወረርሽም እንዲሁ በመታየት ላይ ነው። በተጨማሪም ‹‹ሸማኒያ›› በመባል የሚታወቀው የበሽታ አይነት የሚከሰተው በተለይ ከሰውነት መጎዳት ጋር ተያይዞ ነው። ይህ የበሽታ አይነት እስከ ሕይወት ማሳጣት አድርሷል። በአጠቃላይ ከምግብ እጥረቱ ጋር ተያይዞ በሰው ጤና እና ኑሮ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ ይገኛል።
የውሃ እጥረቱ ድርቁን በከፍተኛ ሁኔታ አስከትሏል። በአካባቢው የሚገኝ ወይጦ በመባል የሚታወቅ ወንዝ ሰፋ ያለ ቦታን ይሸፍን የነበረ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን አዋሳኝ አካባቢም በመገኘት በርካታ የዞኑን በተለይ ደግሞ በያቤሎ ዋዩ የሚባል አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በስፋት የሚጠቀሙበት ወንዝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኮንሶ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮችም የሚጠቀሙበት ወንዝ ነው። በእኛ ዞን ደግሞ የሐመርና የአርቦሬ አርብቶ አደሮች እንስሳቱን ውሃ የሚያጠጡበት ወንዝ ነው። ሌሎችም በአካባቢው ያሉ ሁሉ ከብቶቻቸውን ውሃ የሚያጠጡት ከዚሁ ወንዝ ነው። አሁንም ይህ ወንዝ ወደመድረቁ ሲሄድ የአካባቢው ሰው ሁሉ ለችግር ተጋልጧል። የዝናቡ በተሟላ መልኩ አለመዝነብ ለሰው ልጅ የምግብ እህል መጥፋት ብቻ ሳይሆን እንስሳ የሚመገቡትንም የግጦሽ ሳር ማጣት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል። ከዚህም የተነሳ የተፈጠረው የውሃ እጥረት ለሰውም ለእንስሳቱም መቸገር ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል።
የውሃው አለመኖር ለእንስሳቱ ከፍ ያለ አደጋ ጋርጦበታል። በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንስሳት የመኖ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ቀደም እንደ ዞናችን የበልግ ጊዜ የሚባለው ከጥር ወር ጀምሮ ያለውን ነው። በልግ ከጥር ወር ጀምሮ መግባት ሲገባው እሱ ግን አልሆነም። አሁን ያለንበት ወር መጋቢት ቢሆንም እስካሁን የዝናብ ነገር አልተከሰተም። እንደ ወትሮው ቢሆን ጥር በገባው የበልግ ዝናብ በመታገዝ የካቲት ላይ የዘር ጊዜ ይሆንና መጋቢት ላይ ደግሞ ቡቃያው የሚያብብና ግንቦት ላይ የሚያፈራበት ወቅት ነበር። ነገር ግን አሁንም ድረስ በልጉ የለም፤ ከዚህ የተነሳ አርሶ አደሩ መዝራት አልቻለም። የዝናቡ መዘግየት የመጠጥ ውሃም ለማግኘት ችግር እንዲሆን አድርጓል። ከዚህ የተነሳ ፈተናው ከፍ እያለ መምጣቱን ማየት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ምን ይመስላል? ችግሩ እየባሰ እንዳይመጣስ ምን መፍትሔ እየተቀመጠ ነው?
አቶ ንጋቱ፡- በእስካሁኑ የተደረገው ነገር በተለይ ሰውን ያጋጠመውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ የተወሰዱ እርምጃዎች አሉ፤ በመጀመሪያ ደረጃ በዞኑ በኩል የተፈጠረውን ችግር ለክልሉ መንግስት የማሳወቁ ተግባር ቀዳሚው ነበርና ይህን አድርገናል። ይህ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ችግሩ አለበት ብለን የለየናቸው ወረዳዎች ላይ ተጨማሪ ማጣራት አድርጎ ችግሩ ስለመፈጠሩ ማረጋገጥ ችሏል። ይህ በመሆኑም ክልሉ ችግሩን ለፌዴራል ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳውቋል። ኮሚሽኑ ደግሞ በበኩሉ ለተለያዩ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት የየበኩላቸውን እርዳታ እንዲያደርጉልን ጥያቄ አቅርቦ ዎርልድ ቪዥን በመባል የሚታወቀው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ለ337 ሺ ለሚሆኑ ሰዎች የእርዳታ እህል ላለፉት ሁለት ወራት ማቅረብ ችሏል።
በአሁኑ ወቅትም ችግሩ በስፋት ያለበት ቦታ ተጠንቶ ስላልተጠቃለለ ነው እንጂ ቁጥር ከአሁን ቀደም ከነበረው ይልቅ በጣም በመጨመር ላይ ነው። በልጉ ባለመኖሩ ምክንያት ችግሩ የበለጠ እየከፋ መጥቷል። ደጋማ እና ወይና ደጋ የሆኑ አካባቢዎችም ላይ ችግሩ በመግባት ላይ ይገኛል። እንደ ዞናችን፣ በአሁኑ ወቅት ችግሩ ጎልቶ የታየው አርብቶ አደሮች የሚገኙባቸው ስድስት ወረዳዎች ላይ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ በዞናችን አርሶ አደር ወረዳዎች አሉ፤ አርሶ አደር ወረዳዎች፣ ደጋማ ቦታዎች እና ከፍተኛ ቦታዎች ስላሉ ዝናቡ ባለፈው ጊዜ የከፋ ባለመሆኑ ቢያንስ እነርሱም ሆኑ ከብቶቻቸውን የሚመግቡት ነገር አግኝተው ቆይተዋል።
ነገር ግን ቆላማ ያልኳቸው ስድስቱ የአርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ ድርቁ አይሎ ታይቷል። እንዲያም ሆኖ የበልጉ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት ደጋማ የሆኑ አካባቢዎች ላይ አደጋው እንደተጋረጠ ማስተዋል ይቻላል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የምግብ ድጋፉን ዎርልድ ቪዥን አቅርቧል። በማቅረብ ላይም ይገኛል፤ ይህ ደግሞ መልካም ነገር ነው። ዎርልድ ቪዥንን በዞኑና በአርሶና በአርብቶ አደሩ ስም ላመሰግን እወዳለሁ። በእነርሱ በኩልም የተናገሩት ነገር ቢኖር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቁርጠኞች መሆናቸውን ነው።
ነገር ግን የእነርሱ ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ ድጋፉ በአንድ ድርጅት ላይ ብቻ የሚተው አይደለም። እንደዚያ ከሆነ ውጤታማ ለመሆን ያስቸግራል፤ ምክንያቱም ደግሞ በምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዱ ህጻናትም ሆኑ አረጋውያን አልሚ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ድርጅት ብቻውን ይህን ሊያደርግ አይችልም። በእስካሁንም የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያደረግነው ችግሩ የባሰባቸውን ነው። በጣም ተቸግረዋል፤ ምንም የላቸውም ያልናቸውን ሰዎች ብቻ በማቅረብ ነው እንዲረዱ ያደረግናቸው እንጂ የምግብ ችግር ተጋርጦባቸዋል ብለን ያልናቸውን ሁሉ ብናቀርብ ቁጥሩ በጣም ላቅ ያለ ነው። እንዲያም ሆኖ ችግሩን በማየት ድጋፍ ለማድረግ በወርልድ ቪዥን በኩል የተወሰደው እርምጃ በእጅጉ የሚያስመሰግን ሆኖ በቀጣይ ግን በግብረ ሰናይ ድርጅቱ ብቻ የሚደረገው ድጋፍ በቂ አይደለምና ሌሎች የሚመለከታቸውም የየበኩላቸውን ሊያደርጉ የሚገባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በውሃ በኩልስ ያለው እጥረት ምን ያህል መፍትሔ አግኝቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ንጋቱ፡- ከዚህ ውጭ የውሃ እጥረቱን ለመቅረፍ የደቡብ ክልል መንግስት የውሃ ቦቴዎችን ለመከራየት በማስታወቂያ ጨረታ አውጥቶ ለውሃ የሚያገለግሉ የውሃ ቦቴዎችን በእስካሁኑ ሒደት እየተከራየ ነው። በዚህም ወደ ሶስት ያህል ቦቴዎች ስራ በመስራት ላይ ሲሆኑ፣ ይህ ግን በቂ አይደለም። ለጊዜው የሚያስፈልጉት ወደ አስራ አምስት የውሃ ቦቴዎች ናቸው። እነዚህ 15 ያህል ቦቴዎች ውሃ ካለበት ቦታ በማጓጓዝ ወደ የትምህርት ቤቱና ወደ የሰፈሩ ለማድረስ የሚረዱ ናቸው። ይሁንና እነዚህ ቦቴዎች ገና ባለመገዛታቸው አገልግሎት ለመስጠት አልደረሱም፤ ገና በግዥ ሒደት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለእንስሳት የመኖ ችግር እንዳለም ተነግሯል፤ ይህስ ችግር በምን አግባብ በመፈታት ላይ ይገኛል?
አቶ ንጋቱ፡- የእንስሳት መኖን በተመለከተ ችግር ያለ ሲሆን፣ እስካሁን ያለው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ወደ 14 ሺ ከብቶች ከድርቁ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች በመጎዳታቸው በሕይወት መቆየት አልቻሉም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል። እኛ እንደ መፍትሔ የወሰድነው ነገር ቢኖር በእርግጥ አደጋው በአንድ ጊዜ እንደ ዱብ እዳ የተከሰተ ጉዳይ ሳይሆን በሒደት የመጣ እንደመሆኑ አዝማሚያውን አስቀድመን በመረዳት ከብቶቻችን ከእኛ ድርቅ ካጠቃቸው አካባቢዎች ወጣ ብለው አዋሳኝ ወደሆነው ወደ ማዶ ማለትም ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ የተሻለ በመሆኑ በርከት ያሉ ከብቶች እንዲጓዙ አድርገናል። በተመሳሳይ በጎረቤት ሀገር ኬንያም ስለምናዋስን በቱርካና ሐይቅ አካባቢ የተወሰነ ሳር ስላለ በተለይ የዳሰነች ከብቶች ወደስፍራው እንዲያቀኑ ለማድረግ ሞክረናል።
ሌሎች ደግሞ ለድርቁ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ወረዳዎች አሉ፤ እነዚህም እንደ እነ ሐመር፣ በና ጸማይ ሲሆኑ፣ ብዙ አማራጭ የሌላቸው ናቸው። ነገር ግን እንደሚታወቀው በእኛ ዞን ፓርኮች አሉ፤ ወደእዛ አካባቢ ተጠግተው ሳሩንም የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአካባቢውም ወንዝ ስላለ ያንን ለጊዜውም ቢሆን እንዲያቆያቸው በማሰብ እንደ አንድ መፍትሔነት ልንጠቀም ተገደናል። በእርግጥ ደግሞ እሱ በመሆኑ ነው በተወሰነ ያህልም ቢሆን ችግሩን ለማቃለል የተቻለው። ለአደጋ የተጋለጠው ከብት ቁጥር ግን እሱ ብቻ አይደለም። ካሉት ከብቶች ውስጥ መኖ ማግኘት የማይችሉ፣ ሳርም ማግኘት ያልሆነላቸው፤ እንደሌሎቹ ከብቶች ደግሞ ራቅ ያለ ቦታ ተጉዘው መኖ ለማግኘት ካሉበት ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ በመሆናቸው በጉዳት ውስጥ ያሉ ከብቶች አሁንም አሉ። እነዚህ ከብቶች ከምግብ እጥረት የተነሳ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ባሉበት ቦታ አፋጣኝ የሆነ መኖ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህም ሕይወታቸውን ማቆያ መኖ
ካለበት ተገዝቶ ሊመገቡ ይገባል ተብሎ እየተሰራበት ነው ያለው፤ በዚህ ጉዳይ የክልሉ መንግስት ሀብት የማፈላለግ ተግባርም እያከናወነ ይገኛል። እንዲያም ሆኖ ከከብቶች ቁጥር መብዛት የተነሳ በክልሉ መንግስት ብቻ ፍላጎትን ማርካት አይቻልም። ስለዚህም የፌዴራል መንግስት የተለያዩ ተቋማት ልክ በሚዲያ እያየን እንዳለነው ሁሉ የቦረና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የደረሰውን ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተኬደበትን ርቀት እና የተፈጠረው ችግር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተረድተናል፤ ይህ ችግር ደግሞ ወደእኛ መምጣት እንዳይችል የሚያደርግ ምንም አይነት ዋስትና የለንም። እንደሚታወቀውም የእኛ አካባቢና የቦረና አካባቢ ስለሚዋሰን የአየር ንብረቱ አንድ አይነት ነው ማለት ያስችላል። ከዚህም የተነሳ በእኛም ዘንድ እየተስተዋለ ያለው ፈተና ልክ እንደ ቦረና አካባቢ እንደታየው አይነት ነው። በእርግጥ ለቦረና የተደረገው ድጋፍ ከብዙ ጉዳት በኋላ ቢሆንም አሁን እየተደረገ ያለው ርብርብ በጣም ጥሩና የሚያስመሰግን ነው። በተመሳሳይ እንዲህ አይነቱ ድጋፍ ከወዲሁ ለእኛም ሊደረግ ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ። የፌዴራል ተቋማት የአርሶ አደር እና የቆላማ አካባቢዎችን እንደ ቦረናው ሁሉ ሊደርሱለት ይገባል እላለሁ። አደጋው የከፋ ቢሆንም ሁላችንም የምንረባረብ ከሆነ ችግሩን መቋቋም እንችላለን።
በእርግጥ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት በምን አይነት መከራ ውስጥ እንዳለፈች አሳምረን እናውቃለን። አሁንም ደግሞ ከጦርነቱ እፎይ ስንል የኢኮኖሚው ሁኔታ ችግር ውስጥ መሆኑን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ከዚህ የተነሳ ችግሩን መንግስት ብቻ እንዲፈታው መጠበቅ የለብንም። ሌሎች ተቋማትም የየበኩላቸውን ሊያደርጉ ይገባል። በእርግጥ ከቀናት በፊት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ችግሩ መኖሩን ይፋ አድርጓል። ይህንን ተከትለው ዓለም አቀፍ ተቋማትም በደቡብ ኦሞና አካባቢው ላይ ያጋጠመውን የድርቅ አደጋ ምላሽ በመስጠት ሰብዓዊ ድጋፋቸውን ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የቤት እንስሳት ለአርብቶ አደሩ የሕልውና መሰረት ነው። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ የሀገር ሀብት ነው። በተለይ ከብቶች ደልበው በርካታ ሀብት ለሀገር ማስገኘት የሚያስችሉ ናቸው። ይህ ሀብት ደግሞ ለከባድ ችግር ተጋርጧልና ዝናቡ እስከሚመጣና አንዳች መላ እስኪፈጠር ሁላችንም ተረባርበን መፍትሔ ልናመጣ ይገባል ባይ ነኝ። በተለይ የተጋረጠብንን አደጋ ማለፍ እንድንችል ጊዜያዊ መፍትሔ በሆኑት በእንስሳት መኖ ላይ፣ እንዲሁም በእንስሳት ክትባት ላይ ድጋፍ የሚያደርግልንን አካል እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ዞኑ የከፋ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት ምን የጀመረው መፍትሔ አለ?
አቶ ንጋቱ፡- እኛ በራሳችን መኖ እናለማለን ብለን የጀመርነው ስራ አለ። ይሁንና መስኖ ለማልማት በራሱ ውሃ ይፈልጋል። ውሃ ለማግኘት ደግሞ ችግር ነው፤ ምክንያቱም በርካታ ቦታዎች ላይ ውሃ በመድረቅ ላይ ነው። ስለዚህ ለወደፊቱ በዘላቂነት የሚሆን መፍትሔ የምናስብ ካልሆነ በስተቀር ችግሩ ስር የሰደደ እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለተራቡ ከብት የመድረስ አቅማችን ዝቅተኛ ነው፡፡
ለቀጣይ ግን ትልልቅ ፓምፖችን ወንዞች አካባቢ ማድረግ ከቻልን ሰፋ ባለ መልኩ መኖ ማልማት እንችላለን። ይህን በማድረጉ በኩል የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያስፈልገናል። እናም በዚህ ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አሉ። ለአብነትም ግብርና ሚኒስቴር፣ ቆላማ እና መስኖ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለምሳሌ ግቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ በየጊዜው የሚለቀው ውሃ ወደ 98 ሺ ሔክታር መሬት ሊያለማ ይችላል። የዳሰነች አርሶ አደሮች የሚኖሩበትን መሬት ሐይቁ ተኝቶበታል። በዚህ ምክንያት ወደ 62 ሺ የዳሰነች አርሶ አደሮች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ይገኛሉ። እነሱን መልሶ ለማደራጀት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድርሻ መውሰድ እንዳለበት ከእነርሱ ጋር ተወያይተናል። ሰፋ አድርጎ ገብቶ ማቋቋም በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ብቻ በሚደረገው የመፍትሔ አቅጣጫ ያን ያህል ውጤት ማምጣት ይቻላል? በዞኑ ችግር የተፈጠረባቸው ስድስት ወረዳ ላይ ያሉ አርብቶ አደሮች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ?
አቶ ንጋቱ፡- አሁን ያለው በዞኑ ብቻ መፍትሔ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። የፌዴራል መንግስትን ጣልቃ መግባት ይፈልጋል። የራሳችን ሚና የአርሶ አደሩ ንቃተ ሕሊና በማሳደግ በኩል፣ ስልተ ምርቱንም በማሻሻል በኩል ሰፊ ስራ በመስራት ላይ ነን። በተጨማሪም ምርታችን ገበያ ተኮር እንዲሁም ምርት ተኮር እንዲሆን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን። የእንስሳቱ ዝሪያ የተሻሻለና እና ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ ምርታማ የሚሆኑበትንም መንገድ ከግምት ውስጥ በማስገባት የጀመርናቸው ስራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ስራዎች ብቻ የሚጠበቀውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም። እንደሚታወቀው በአካባቢው ሰፊ የሆነ የውሃ ሀብት አለ። ለምሳሌ የኦሞ ወንዝ ከ175 ሺ ሔክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን፣ ለዚህም ምቹ የሆነ ሰፊ መሬት ደግሞ አለ። ይሁንና ውሃውን በምን አግባብ መጠቀም ይቻላል የሚለው ጉዳይ አቅምን ከግምት ውስጥ ያስገባ ጉዳይ ነው። ነገር ግን እሱን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ እና የወይጦን ወንዝ መገደብ ከተቻለ በብዙ ማትረፍ ይቻላል።
ወይጦ ወንዝ ቢገደብ ከ29 ሺ በላይ ሔክታር ማልማት የሚያስችል አቅም ያለው ወንዝ ነው። በአሁኑ ወቅት እስከ ሰባት ሺ ሔክታር መሬት በመስኖ እያለመ ቢሆንም ይህም እርሻ ወንዙ በመድረቁ አደጋ ውስጥ ነው ያለው። በመሆኑም እነዚህን መሰል ወንዞችን በማልማት፣ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ደግሞ ምንም የውሃ አማራጭ የሌላቸው በመሆኑ በእነዚህ ወረዳዎች ላይ የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት በመጠጥ ውሃ ብሎም በመስኖም ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በብዙ መጠን ኢንቨስት መደረግ መቻል አለበት። ይህ ካልተደረገ ግን በአካባቢው ላይ ለውጥ ማምጣት የሚታሰብ አይሆንም። በእርግጥ ንግግር መናገር ይቻል ይሆናል፤ ቀደም ባሉት ዓመታትም እኔን ጨምሮ ሌሎች በየደረጃው ያሉ መሪዎች ብዙ ነገር ተናግረዋል። ይሁንና በተጨባጭ መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር አልታየም። በአሁኑ ወቅት ያሉ ጅማሬዎች ግን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው። ሰፊ ስራ ከተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመላካችም ናቸው፤ ነገር ግን ቀጣይነት ያላቸው እንዲሁኑ የተደገፉ አይደሉም፤ ከዚህም የተነሳ አርብቶ አደሩ እንዲሁም የሚያረባው ከብት አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡
በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጡን አርብቶ አደሩ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የፈጠረው አይደለም። ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ነው። ይህን ተጽዕኖ ሊቋቋም የሚችል አርሶ አደር ማብቃት የግድ ነው። ይህን ለማድረግ በዞኑም ሆነ በክልሉ አቅም ብቻ ማሳካት አይቻልም። ስለዚህም የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ተካቶበት፣ የክልሉ ትኩረት ታክሎበት፣ እንደ ዞን ደግሞ የእኛም ጥረት ተጨምሮ ድርቅን መቋቋም የሚያስችለንን አቅም መፍጠር እንችላለን ማለት እወዳለሁ። ይህ ለቀጣይ ዓመታት በእቅድ ተይዞ በዘላቂነት ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በድርቁ ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ንጋቱ፡- በአሁኑ ሰዓት የሉም፤ ባሉበት አካባቢ የሚያስፈልገውን ምግብ በማቅረብ ላይ ስለሆንን ቀዬቸውን ወደመልቀቁ አልገቡም። አርብቶ አደሩ ግን እንደሚታወቀው ለከብቱ የተሻለ ውሃና የግጦሽ ሳር ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራል። ይህ ባህሪው ነው። ከዚህም የተነሳ አሁንም በድርቁ ምክንያት ውሃ ፍለጋ ከብቱን ይዞ ወደተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ላይ ነው። በእርግጥ ያንን ተከትለው ከድርቁ የተነሳ ከብቶቹን ተከትሎ የሚንቀሳቀስ የኅብረተሰብ ክፍል አለ፤ ምክንያቱም ከከብቱ የሚገኘውን ተዋጽኦ ለመቃመስ የሚደረግ ጉዞ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን በድርቅ ምክንያት ነው በሚል አካባቢውን ለቆ የተሰደደ ሰው የለም።
አዲስ ዘመን፡- አስቀድመው በውሃ መጥፋትም ሆነ በምግብ እጥረት የተነሳ ወባም እንዲሁም የኩፍኝም ወረርሽ እየተቀሰቀሰ እንዳለ ጠቅሰዋል፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ ጤና ቢሮ አሊያም የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እያደረገ ያለ ድጋፍ አለ?
አቶ ንጋቱ፡- በእርግጥ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም ተጨማሪ ድጋፎች ግን አስፈላጊዎች ናቸው። የህጻናት አልሚ ምግብ እንዲደርስ ለማድረግ በተለየ መልኩ ተጠንቶ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ እንዲደርስ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም የሕክምና ቁሳቁስን በተመለከተ እንዲሁ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ለምሳሌ የሽማኒያ የተባለው በሽታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንም ጭምር በመጠቀም በዘመቻ መልክ ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የሕክምና ቡድን በክልሉ ጤና ቢሮ አማካይነት የጤና ሚኒስቴር እገዛ ታክሎበት በመጋበዛቸው በስፍራው ተገኝተው ሕዝቡን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የክትባት አገልግሎት ለመስጠት እየተሞከረ ነው። ይሁንና ችግሩ ሰፋ እያለ የመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒቶች ያንሳሉ። ይህን ጉድለት በማሟላት አደጋው እንዲቀንስ ማድረግ ተገቢ ነው። የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም እየደረሰ ካለው አደጋ ጋር የሚመጣጠን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ዝናብ አለመዝነቡ ይታወቃል፤ ይህ ደግሞ ከቀጠለ በሌሎች ዞኖች የደረሰው አይነት ችግር ይፈጠራልና ችግሩ ከፍቶ ከመምጣቱ በፊት ምን አማራጭ መውሰድ አለበት ይላሉ?
አቶ ንጋቱ፡- ዘላቂ አማራጭ ያለው ከሰማይ ከፈጣሪ ዘንድ ነው። ዝናብ መዝነብ አለበት። ይህን ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ የሃይማኖት አባቶችም የሀገር ሽማግሌዎችም እንደ የእምነታቸው መጸለይ አለባቸው፤ መንግስት ደግሞ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። እኛም የበኩላችንን እናደርጋለን። ነገር ግን ዋናው መፍትሔ እንዳልኩሽ ዝናብ ነው። ዝናብ ካለ ብዙ የከፋ ነገር ወደመልካም ለመለወጥ የሚወስድበት ጊዜ አጭር ነው። ዝናብ ካለ አርሶ አደሩ ያርሳል፤ አርብቶ አደሩም ለከብቱ ሳር ያገኛል፡፡
ነገር ግን ይህ እስከሚሆን ድረስ አሁን ባለው ሁኔታ የኦሞ ወንዝን በመጠቀም መኖ የማልማቱን ስራ መስራት እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ለሰው የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ነው፤ ለቀጣዮቹ አምስትና ስድስት ወራት በአሁኑ ወቅት ለአደጋ የተጋለጠው ሕዝብ ቁጥር ከጨመረ ያለው አማራጭ ምግብ ማቅረብ ነው። ለእንስሳቱ ደግሞ ሕክምናም መኖም ማቅረብ ነው። በእኛ በኩል እንዲያውም የእንስሳቱን ቁጥር በመቀነስ ጥራት እንዲኖራቸው በማድረጉ በኩል እየሰራን ነው፤ አሁን ለተፈጠረው ችግር ልክ እንደሌላው አካባቢ እንስሳቱ በጣም ከመጎዳታቸው በፊት መሸጥም አንድ አማራጭ ነው ወደሚለው መጥተናል። ምክንያቱም ችግሩ ካለፈ በኋላ አርብቶ አደሩ ጥጃም ገዝቶ ወደማርባቱ የሚመጣበትን ሁኔታ እንደ አማራጭ አስቀምጠናል። በዞኑ ለተከሰተው ድርቅ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ግን ዘላቂ ልማት ማምጣት ሲቻል ነው።
ዘላቂ ልማት ከተሰራ ድርቅ ቢመጣም ባይመጣም ችግሩን መቋቋም የሚችል የኅብረተሰብ ክፍል ይኖራል ማለት እወዳለሁ። ለዚህ ደግሞ ትኩረት የሚፈልግ ስራ መስራት ነው እንጂ በየዓመቱ ይህንኑ እያወራን መኖር አንችልም ። የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው የሚባለው ግን በአሁኑ ሰዓት ድጋፎችን ማድረግ ነው። አርብቶ አደሩ ሕልውናውን እያጣ ስለመሆኑ በቀላሉ ከቦረና እያየን እንገኛለን። በእኛ አካባቢ ለምሳሌ በ2009 ዓ.ም ከፍተኛ ድርቅ ነበር፤ ከ590 ሺ በላይ የሚሆኑ ከብቶችም ደቡብ ኦሞ ላይ ሞተው ነበር። ዘንድሮም ገና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ድርቁን ተከትሎ ከ14 ሺ በላይ ከብቶች ሞተዋል። ይህ ደግሞ ወዴት እያመራ እንደሆነ በግልጽ የሚያመላክት ነው። ስለሆነም ይህንን አደጋ መከላከል የሚያስችል እንደ ሀገር ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል። ተደጋግፈን ሕዝቡን አሁን እየደረሰበት ካለው ድርቅ መታደግ አለብን እላለሁ፤ በዚህ አጋጣሚም ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ንጋቱ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም