
የአፍሪካ ሕብረት አኅጉሪቱን በንግድ የማስተሳሰርና ኢኮኖሚያቸውን በጋራ ማሳደግ የረጅም ጊዜ አጀንዳው መሆኑ ይታወቃል። ይህንንም ለማሳካት ሀገራቱ በይፋ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል። ስምምነቱ ከኤርትራ በስተቀር 54 የአፍሪካ ሀገራት የፈረሙት መሆኑ ከዓለም ንግድ ድርጅት ቀጥሎ ግዙፍ የንግድ ስምምነት ስለመሆኑ ይጠቃሳል።
በዋናነትም በገቢ እቃዎች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ 97 በመቶ እና ከዚያ በላይ የማስቀረት ግብ ያለው ሲሆን ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያንን እርስ በርስ የሚያቀራርብና 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን የሚገመት ዶላር አኅጉራዊ የግብይት ሥርዓትን ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ስምምነቱ ተፈርሞ በተጨባጭ ወደ ተግባር ከገባ ከአስር ዓመታት በላይ የዘለቀ ቢሆንም ቅሉ በስምምነቱ መሰረት ለነፃ የንግድ ቀጣናው እውን መሆን በሀገራቱ እየተሠራ ያለው ሥራ እምብዛም ስለመሆኑ ይጠቀሳል። በተለይም ደግሞ ለትስስሩ መሳለጥ ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና ጠንካራ ፖሊሲ አዘጋጅቶ በመንቀሳቀስ ረገድ ብዙ የሚቀራቸው እንደሆነ ነው በዘርፉ ምሁራን የሚነሳሳው።
ኢትዮጵያ ቀድመው ስምምነቱን ተቀብለው ካፀደቁ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን፤ ለተግባራዊነቱም የተሻለ ጥረት በማድረግም ፊት መሪ እንደሆነች ይታመናል። በዚህ ረገድ አጠቃላይ ነፃ የንግድ ቀጣናው እውን መሆን እየተከናወኑ ባሉና ሊከናወኑ በሚገባቸው ሥራዎች ዙሪያ ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያና በጆሆንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ፎር ገቨርናንስ ኤንድ ኢንትራ አፍሪካ ስተዲ ዳይሬክተር ሰይፈ ታደለ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዳይ በሃሳብ ደረጃ ከተፀነሰ ረጅም ዓመታት እንደሆኑት ይታወቃል፤ በእነዚህ ዓመታት የሀገራቱ ጉዞ በእርሶ እይታ ምን ይመስላል?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እንደሚታወሰው የአፍሪካ ነፃ ቀጣና ሃሳብ የመነጨው በእ.ኤ.አ 1991 የአቡጃ ስምምነት በተደረገበት ጊዜ ሲሆን በወቅቱ ቁልፍ ጉዳይ የነበረው አፍሪካን በንግድ ማስተሳሰር ነበር። ለስምምነት የበቃው ግን የአፍሪካ ሕብረት መጋቢት 2010 በሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ ነበር። መጀመሪያ ላይ በከስተምስ ዩኒየን በኩል እንዲመሰረት የታሰበ ሲሆን፤ አምስቱ ቀጣናዎች አንድ ላይ ሰርተው ከስተምስ ዩኒየን ከመሰረቱ በኋላ ነው ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲመሰረት ይደረጋል። ይህ ሂደት በሌሎች ክፍላተ-ዓለማት የተለመደ ሲሆን በአፍሪካ ግን የሆነው ‘’ከፈረሱ ጋሪው’’ እንደሚባለው አይነት ነው። ይህም ሲባል መጀመሪያ ሊመሰረት የሚገባው ምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ምዕራብና ሰሜን እንደየ አደረጃጀታቸው የየራሳቸውን ቀጣናዊ ትስስር ከፈጠሩ በኋላ ትልቁን አሁጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረት ነበረበት።
አሁን ባለው ሁኔታ እንደ አህጉር ቀጣናዊ ትስስር ሊፈጠር የሚችል ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የለንም። ምንአልባት እንደ አብነት መጥቀስ እንኳን የምንችለው የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የንግድ ቀጣናን (ሳውዘርን አፍሪካን ዩኒየን ሪጅናል ኢኮኖሚክ ዩኒየን) ወይም ‘’ሳኩ’’ ነው። እሱም ቢሆን ግን በአፍሪካ ሕብረት ተቀባይነት አላገኘም። በተቃራኒው የተሻለ ደረጃ ላይ ያለው የምስራቅ አፍሪካ ኮሚኒቲ (ኢኤሲ) ነው። እነሱም እንደሚታወቀው ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋናዳ፣ ደቡብ ሱዳንን አሁን ደግሞ በቅርቡ ሱማሊያ ተቀላቅለውታል። አንፃራዊ በሆነ መልኩ ይሄ ነው ጠንከር ያለ ከስተምስ ዩኒየን የሚባለው።
ይሁንና የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ (ኢኮዋስም) ሆነ የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ (ሳዲክም) ቢባል ጠንካራ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መፍጠር አልቻሉም። በመሆኑም ጠንካራ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መፍጠር በቀጣና ደረጃ ሳይኖረን በአህጉር ደረጃ መኖሩ ምንም ፋይዳ የለውም ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ደግሞ የመጨረሻ ግቡ የታሪፍ ክፍተቱን ማስወገድ እና ነፃ የእቃና የሰዎች ዝውውር ማሳለጥ ነው።
ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ ነፃ ቪዛ የፈቀዱት በጣት የሚቆጠሩ ሀገራት ብቻ ናቸው። እነሱም ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና ና ሞሪታኒያ ናቸው፤ ሌሎቹ እስከአሁን ይህንን አልፈቀዱም። ማንኛውም አፍሪካዊ የፈለገበት የአፍሪካ ሀገርና የፈለገበት ቦታ እንዳሻው ተዘዋውሮ ምርቱንም ይዞ መንቀሳቀስ የሚችልበት እድል ካልተፈጠረ ትስስሩ እውን ሊሆን አይችልምና ነው። ይህ በሌለበት ሁኔታ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እውን ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። እንዲያውም የሌላ አኅጉራት ሸቀጥ ማራገፊያ እንዳንሆን እሰጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ ቢያብራሩልን?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- ይህም ሲባል እንደሚታወቀው ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ውጭ የሚልኩት እሴት ያልተጨመረበት የግብርና ምርት ነው። በአንፃሩ ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ አቅማችን በጣም ውስን በመሆኑ አብዛኛውን ከውጭ እያስመጣን ነው ጥቅም ላይ የምናውለው። በተለይ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብና ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ተኪ የኢንዱስትሪ ምርት በማምረት ረገድ ገና በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለችው። አሁን ባለው ሁኔታ የአፍሪካውያንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ኢንዱስትሪም ሆነ አቅም የለንም፡፡
ይህን ስል ግን ጅምሮች ግን የሉም ማለቴ አይደለም፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ በማስፋፋት ረገድ እንደሞዴል እየተጠቀሰች ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም። ስለዚህ ኢንዱስትሪያችን መጠንከር አለበት፤ መሰረተ ልማቶቻችን ማስፋፋት ይገባናል ባይ ነኝ።
ከዚህ ባሻገር ቢዝነስ የምንሰራበትን መንገድ ማሻሻል አለብን የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ ንግድ ፍቃድ ለማውጣትም ሆነ ለሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የምንሰጥበትን የአሠራር ሥርዓት ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ልንቃኘው ይገባል። በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚስተዋለው የተንዛዛ አሠራር፤ አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም ያለው ውጣ ውረድ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችና ንግድ ሥራ ላይ መሰማራት የሚሹ ባለሃብቶችን የሚያሸሽበት ሁኔታ አለ። ይህንን ኋላቀር አሠራር ማስቀረትና ለዘርፉ ተዋናዮች ሊያሠራ የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፤ ምቹ የሕግ ማሕቀፍ ማዘጋጀት፤ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። እነዚህን ነገሮች ማስተካከል ከቻለች በብዙ መልኩ ኢትዮጵያ ተመራጭ ሀገር ናት የምትሆነው። በተለይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ከዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው የሚሠራ ወጣት ኃይል መሆኑ ተፈላጊ ያደርጋታል።
በሌላ በኩል ግን ነፃ የንግድ ቀጣና በአግባቡ ካልመራነው ጥቅም ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ ተግዳሮቶችም እንዳሉት ማወቅ ይገባል። አያያዙን ካላወቅንበት ከእኛ የተሻለ አቅም፣ ገንዘብና እውቀት ያላቸው ሀገራት ደግሞ ከእኛ የበለጠ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማሰቡ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ብንጠቅስ እንኳን የእኛ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን የጠነከሩ አይደሉም፤ የእነ ደቡብ አፍሪካ ወስደን ካየን ድግሞ ለአጠቃላይ ለአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ሽፋን መስጠት የሚችል አቅም ላይ ደርሰዋል። በተመሳሳይ ኬኒያ፣ ግብፅ፣ ናይጂያና ጋና በተወሰነ ደረጃ ጠንካራ የሚባል አቅም ላይ ነው የሚገኙት። ወደ እኛ ተቋማት ስንመጣ ግን ብዙ የሚቀራቸው ናቸው፤ አይደለም ለአፍሪካ ሀገራት ቀርቶ ለሀገር ውስጥም በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆን አልቻሉም፤ ሰፊና የሚታይ ውስንነቶች ያሉባቸው በመሆኑ ስለዚህ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን አቅማቸውን ሊያጠነክሩ ይገባል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።
በተመሳሳይ የባንኩ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በጣም መዘመን አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን በጣም በተደራሽነት ረገድም መስፋፋት ይኖርባቸዋል። እንደሚታወቀው እንደ ሀገር በተደራሽነት ስፋትም ሆነ በአቅም የተሻለ ደረጃ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ባንኩ በሀገር ውስጥ ያለውን አቅም በማሳደግ ግን በቀጣናውም ሆነ በአኅጉር ደረጃ ተደራሽና ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት ይገባል ባይ ነኝ። በአንፃሩ ደግሞ የደቡብ አፍሪካውያኖቹን ባንኮች ስንመለከት ግን በአቅም ሆነ በተደራሽነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በመሰረቱ የሚሰጡት አገልግሎት በቴክኖሎጂም የታገዙ በመሆናቸው የበለጠ ተመራጮች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችና ሥራ ፈጣሪዎች እይታቸውን የማስፋት በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ በመሆን ረገድ ምን ሊሠራ ይገባል ይላሉ?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እንደተባለው አብዛኞቹ የሀገራችን ሥራ ፈጣሪዎች እይታቸው በሀገር ውስጥ ምሕዳር ላይ የተመሰረተ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅኝታቸውም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላትና ትርፍ ማግኘት ላይ ነው። በእኔ እምነት ግን ሀገር የምትገነባው የንግድ እይታቸው በሰፋና ለሀገር ፋይዳ ያለው ሥራ ለመሥራት በሚታትሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ተዋናዮች ነው። አሁን ያሉት ኢንዱስትሪዎቻችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት ለጎረቤት ብሎም ለአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ተደራሽ መሆን መቻል አለባቸው።
በዚህ ረገድ መንግሥት ቁርጠኝነቱን ወስዶ እየሠራ እንደሆነ ባውቅም ጥረቱን ግን ማጠናከር አለበት ብዬ
አምናለሁ። በተለይ ወጣቶችና ሴቶች የተለየ ንቃት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲያመጡ ከኢትዮጵያ ውጭ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን አቅም እንዲያጎለብቱ ማገዝ ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ ወጣቶችን በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው ዘንድ ስናሳትፋቸው ነው እንደ ሀገር ተጠቃሚነታችን የሚጎለብተው። እንደ እኔ እምነት አሁን በጣም ጎበዝና የሥራ ፈጣሪ ሥነ-ልቦና ያላቸው ወጣቶች ነው ያሉን። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የአፍሪካ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የፈጠራ ሥራ በማቅረብ የሀገራቸውንና የአኅጉራቸውን ጭምር ስም እያስጠሩ ነው ያሉት። ስለሆነም ይህንን የወጣቱን ሥራ ፈጣሪ አስተሳብ ወደ ጥቅም ማምጣት መቻል አለብን ብዬ ነው የማስበው። አልያም እሱን ወደ ጥቅም ካልቀየርነው እንደምናየው የተወዳዳሪነት አቅማችን ቀጫጫ ሆኖ ነው የሚቀረው። የንግድ እሳቤያችንም እዚሁ መንደር ላይ ባለ ትንንሽ ንግዶች ላይ ተንጠልጥሎ ነው የሚቀረው።
በመሆኑም ወጣቶቻችን ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንዲያገለብቱ ማድረግ ይገባናል፤ ምክንያቱም ልንነግድ የምናስበው ለ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሕዝብ በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ቻይና በዓመት እስከ 40 የሚደርሱ ቢሊየኖሮችን ትፈጥራለች። ስለዚህ አፍሪካም ያንን ምሳሌ ተከትላ ብዙ ወጣት ቢሊየነሮችን መፍጠር ይገባታል ብዬ አምናለሁ። ቢሊየነሮኖች መፍጠር ማለት ሥራ የሚፈጥሩ ሰዎችን መፍጠር ማለት ነው። ብዙ ሥራ ከተፈጠረ ደግሞ ሥራ አጥነት ይቀንሳል፤ ሥራ አጥነት ሲቀንስ ድህነት ይቀንሳል። ሁሉም ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ናቸው። እነዚህ ነገሮችን ባሰፋን ቁጥር መሰረተ ልማትም ሆነ የሃብት ክፍፍሉ ፍትሓዊ ይሆናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች አኅጉራት ተሞክሮ አንፃር ነፃ የንግድ ቀጣና ሥርዓት መስፋፋቱ ለሀገር እድገት ያለው አበርክቶ ምን ይመስላል?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እንደሚታወቀው አውሮፓ ከ60 በመቶ በላይ ርስበርስ ይነጋገዳሉ። እኛ እንደ አፍሪካ ርስበርስ የምንነጋገደው አሁን 16 በመቶ ብቻ ነው። በእርግጥ አንዳንድ መረጃዎች እስከ 20 ያደርሱታል። እኔ ግን ከ16ም በታች ነው የማስበው። ስለዚህ ከአውሮፓውያን ልንማር የምንችለው ብዙ ነገር አለ። በተለይ እነሱ ያደረጉት የመጀመሪያው መሰረታዊ ነገር በአውሮፓ ሀገራት መካከል ዜጎቻቸውም ሆነ በየሀገራቱ የሚመረቱትን ምርቶች ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላኛው ሀገር በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ሥርዓት መፍጠራቸው ነው። ገደብና የተለየ ታሪፍ ሳያስቀምጡ የሚገበያዩበት እድል በመፈጠራቸው ንግዱም የዚያኑ ያህል መጎልበት ችሏል።
በተመሳሳይ ላቲን አሜሪካም በተወሰነ መልኩ የተሻለ የርስበርስ የንግድ ትስስር የፈጠሩ ሲሆን ፤ ኤዢያ ደግሞ በጣም ጠንክራ የሚባል ሥርዓት ነው ያላቸው። ስለዚህ ዋናው ነገር እኛ አፍሪካውያን መማር አለብን ብዬ የማስበው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ዋናው ግባችን የአኅጉሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ በመሆኑ የንግድ ትስስራችንን እናጠናክር የምንለው ዝም ብሎ ለይስሙላ መሆን የለበትም ባይ ነኝ። የምናገረውም ሆነ የምንሰራው መፈክር አይደለም መሆን ያለበት። ከትስስሩ እኔና አንቺ ተጠቃሚ ነው መሆን ያለብን። የምንገዛው ልብስ ዋጋ ከአውሮፓና ከሌሎች ሀገራት ከምናስመጣው መቀነስ አለበት፤ ጠረጴዛችን ላይ የሚመጣልን ምግብና መጠጥ ሁሉ መርከስ አለበት፤ እኛ ልንገዛው በምንችለው ዋጋ እንደልብም ልናገኘው ይገባል። ይህም ሲባል ከምናገኘው ገቢ ጋር የተመጣጠነ መሆን አለበት ማለት ነው። ስለዚህ ንግድ እንዲስፋፋ ስንል ተጠቃሚነታችን እንዲጎለብት ማለታችን ነው እንጂ ተስፋፍቶ እኔና አንቺን ደሃ የሚያደርገን ከሆነ ጥቅም የለውም። ስለዚህ ከዚህ አኳያ ነው መቃኘት ያለበት። እናም ከዚህ አንፃር ምን አልባት ልናሻሽለው እንችላለን። አለበለዚያ ፋይዳው ብዙ አይታየኝም።
አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ቀጣናውን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ረገድ ያደረጉት ጥረት እንዴት ይታያል?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እውነት ለመናገር አሁንም ቢሆን ለነፃ የንግድ ቀጣናው መሳለጥ የአፍሪካ ሀገራት እያከናወኑት ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ በጣም አነስተኛ የሚባል ነው። በእርግጥ ከኬፕታውን ተነስቶ ካይሮ የሚደርስ መንገድ አለ፤ ይህም በተወሰነ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም ይሁንና ከጅቡቲ ተነስቶ ሴኔጋል ዳካር የሚደርስ መንገድ ግን ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ እሱ ላይ ብዙ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ።
በነገራችን ላይ መሰረተ ልማት ስንል መንገድ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ነገሮች ናቸው ያሉት፤ የአየር ትራንስፖርት ሊሆን ይችላል፤ የመርከብ ሊሆን ይችላል፤ እነዚህ በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያሉት። በአግባቡ ከሠራንበት የመሰረተ ልማት ግንባታው ብቻውን ለወጣቱ ከፍተኛ የሆነ የሥራ እድል ይፈጥራል። በሌላ በኩል በቻይና እና በአሜሪካ ሊሠራ የታሰበው ሪንግ ሮድ (የቀለበት መንገዶች) ገና በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ላይ ነው ያሉት። የአፍሪካ መንግሥታት ተጠናክረው ይህንን ሲያጎለብቱት ትልቅ የሆነ ፋይዳ ያለው ንግድ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ለዚህ አንድ ትልቅ ምሳሌ ልስጥሽ። በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ትልቅ ከተማ የለም። ትስስር ማለት እኮ አንዱ ይሄ ነው። ከጅቡቲ ጋር በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፤ ብዙ ወደ ውጭ የምንልከው አለ፤ እነሱም የወደብ አገልግሎት ይሰጡናል፤ ከሱማሊያ ጋር እንዲዚህ አይነት ቀጣናዊ ትስስር ላይ ያን ያህል ጉልህ የሚባልና እንዳው ሊጨበጥና ሊዳሰስ የሚችል ነገር አላየሁም። ሌሎች አፍሪካ ሀገራት በተለይ ደቡብ አፍሪካ አካባቢ ሌሴቶ ፣ ሲዋዚላንድ ፣ ናቢያና ቦትስዋና የንግድ ትስስራቸው ከሌላ የአፍሪካ ሀገራት በጣም የተሻለ ነው። በጥቅሉ የንግድ ልውውጣቸው ከ22 በመቶ በላይ ነው የሚገመተው። በመሆኑም መሰረተ ልማቶችን ባሰፋንና የጋራ ተቋማትን በገነባን ቁጥር ተጠቃሚነታችን ይጎለብታል ብዬ አስባለሁ፡፡
*አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አብዛኛው ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች እሴት ያልተጨመረባቸው እንደሆኑ ይታወቃል፤ ከዚህስ አኳያ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እንዳነሳሽው አንዲት ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ከተፈለገ በምትልካቸው ምርቶች ላይ እሴት መጨመር ይገባታል። ይህንን ለመሥራት በመጀመሪያ ደረጃ በመንግሥት በኩል ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫና ድጋፍ መኖር አለበት። እንደምረዳውም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአሁኑ ወቅት እየተደረጉ ጥረቶች አሉ። ግን መንግሥት ብቻውን ሊያመጣው የሚችለው ለውጥ ስለሌ የግሉ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ግኑኝነት መጠናከር አለበት።
አሁን ባለሁ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ሊመረት የሚችሉ በርካታ ተኪ ምርቶች እያሉ ከመርፌ ጀምሮ ከውጭ ነው የምናስመጣሁ፤ በተቀራኒው ሰፊ ሃብት ይዘን፤ ምንም እሴት ያልተጨመረበት ምርት ነው የምንልከው። እናም ይሄ ባልተስተካከለበት ሁኔታ ንግድን ማሳለጥ አይቻልም፤ እሴት እየጨመርን የምንልክ ካልሆነ ንግዳችን ቀጫጫ ነው የሚሆነው። ስለዚህ መጎልበት አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እውን መሆን ከመሪዎች ምን ይጠበቃል?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- ትልቁ ተግዳሮት የሚመስለኝ የአፍሪካ መንግሥታት አንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው ያለመሥራታቸው ነው። ለዚህ አብነት መጥቀስ ካስፈለገ እንደምታስታውሺው የአፍሪካ ዋነኛው ችግር ግጭት መሆኑ ታምኖበት ‘’አፈሙዝን ፀጥ የማሰኘት አጀንዳ’’ን በ2020 ነበር እናሳካለን ተብሎ የታቀደው። ነገር ግን አሁንም ድረስ ብዙ ሚሊዮን ወጣቶች አልቀውብናል፤ እያለቁብንም ነው። አሁንም በየቦታው ግጭቶችና አለረመጋጋቶች አሉ። ስለዚህ ትልቁ ጉዳይ ብዬ የማስበው ለአቀድነው ነገር ተፈፃሚነት ትኩረት ሰጥተን አለመሥራት ነው። አንዱ አጀንዳ ሳይቋጭ ሌላ አጀንዳ ለመተግበር ነው የምንሯሯጠው።
የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ በየዓመቱ አዳዲስ አጀንዳ ተይዞ ይቀርባል፤ ሆኖም ያንን ለማስፈፀም የሚታይ ቁርጠኝነት የለም። በተለይ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ፍትሓዊ ተጠቃሚ እንድንሆንና እንደሰው እንድንቆጠር እያልን ነው። እንደ የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ያሉ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እያቆሙ ነው። አፍሪካውያን የዓለም አቀፍ ድጋፎች መቋረጥ ሊያነቃቸው እና እንደበረከት ሊቆጥሩት ይገባል። አልተረዳነውም እንጂ እነሱ እየነገሩን ያለው ነገር ቤታችሁ ያለውን ሥራ ሥሩ የሚል ነው። ይኸውም ለራሳችሁ ሕዝብ ምግብ አቅርቡ፤ የምግብ ዋስትናን አስከብሩ ነው እያሉን ያለው። በጥቅሉ የዓለም አቀፍ ድጋፎች መቋረጥ ወደ ውስጥ የምንመለከትበት እንደወርቃማ እድል ነው።
እስከዛሬ እነሱ በሚሰጡን ሽርፍራፌ ድጋፍ ብንቆይም በመሰረታዊነት ከድህነት ሕዝባችንን ማላቀቅ አልቻልንም። ምክንያቱም ማዳበሪያና መሰል ግብዓቶችን ሰጥተውን ስለምናምርት የምናመርተውን ሲወስኑልን ነው የኖሩት። አሁን ግን ሊወስኑልን ስለማይገባ በራሳችን ሃብት አኅጉራችንን ከድህነት ልናወጣና ከተረጂነት መላቀቅ ይገባናል። ይሄን የመሰለ መሬትና የአየር ንብረት እያለን እኛ ቲማቲምና ሽንኩርት የሚቸግረን ሀገር ሆነናል። እናም ይህንን አስተሳሰባችንን አውጥተን ስንጥለው ነው ከድህነት አረንቋ የምንወጣው። እንደ እኔ እምነት እንዳውም
ዶናልድ ትራንፕ እግዚአብሔር እኛን ሊባርከን ወደ አፍሪካ ያመጣው መሪ ይመስለኛል። ቆመን እንድናስብና በምግብ እህል ራሳችንን እንድንችል የመቀስቀሻ ደውል ነው የላከልን።
በእርግጥ መንግሥት አቅሙ ውስን ነው፤ በመሆኑም የግል ባለሃብቱ፤ ተቋማትና ማኅበረሰቡ በእጁ ላይ ያሉትን ፀጋዎች አውቆ ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ትልቁን ለውጥ የምናመጣው ሁላችንም በጋራ ስንቀሳቀስ እንጂ በመንግሥት ብቻ የትም ልንደርስ አንችልም። ስለዚህ ወደ ውስጣችን ማየት፤ ያለንን አቅም በመጠቀም ምርታማነታችንን ካሳደግንና የርስበርስ ንግዳችንን ማሳለጥ ከቻለን በእርግጠኝነት መለወጥ እንችላለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም አንዳንድ ሀገራት አሜሪካ እየወሰደች ያለችው ርምጃ የአፍሪካ ሀገራትን አዘቅት ውስጥ ይከታል ብለው ይሰጋሉ። የእርሶ እምነት ምንድን ነው?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- በመሰረቱ እርዳታ የለመደ እጅና አፍ ሁልጊዜም ቢሆን ርዳታ ነው የሚጠብቀው። የሚሰጡት እርዳታ እኮ እነሱ ፋብሪካ ውስጥ የታተመ ብር ነው። እኛ ስለብር ያለን ምልከታ ስላለወጥን ነው ርዳታቸው ሲቆም ሰማይ የተደፋብንን የሚመስለን። ይሄንን አይነቱን አስተሳሰብን ነው መለወጥ ያለብን። አፍሪካ ኢኮኖሚዋን ራሷ ከተቆጣጠረች ከአሜሪካ የተሻለ አቅም ይኖራታል። ምክንያቱም ደግሞ አፍሪካ በርካታ ማዕድናት ባለቤት ናት፤ አሜሪካ ያላት ወታደራዊ ኃይል ነው። ያለንን እምቅ አቅም እኛው ነን ዝቅ ያደረግነው። በሕብረት ከሠራን አሁን ያለንበትን ሁኔታ መለወጥ እንችላለን።
አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ አብዛኞቹን የአፍሪካ ሀገራትን ወደ ኋላያስራቸው የቀኝ ግዛት አስተሳሰብ፤ የተረጂነት መንፈስ ነው። በመሰረቱ አሜሪካና አውሮፓ ያለውን የፎቅ ድርድር እኛም እዚሁ መገንባት የምንችለው ነው። እንደሚባለው አንዳንድ ሰዎች ቆንጆ ቦታ ይሄዳሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ቦታቸውን ቆንጆ ያደርጋሉ። ስለዚህ ምቹ የአየር ንብረት፣ መልዓከምድር፣ የተፈጥሮ ሀብትን የሚሠራ የሰው ኃይል እስካለን ድረስ ሀገራችንንም ሆነ አኅጉራችንን መቀየር የማንችልበት ምክንያት የለም። ግን ደግሞ የበታችነት አስተሳሰብ አንገታችንን ሰቅሶ ይዞናል። ለዚህም ነው ለም መሬት እያለን ስደት የምንናፍቀውና የአካል ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ባሪያ የሆንነው።
በነገራችን ላይ እርስ በርስ እንዳንነጋገድ የሚያደርጉን የአውሮፓና የአሜሪካ ኃይሎች ናቸው። በመካከላችን መከፋፈልን ፈጥረው እነሱ እንዳሻቸው ሲመጡ እኛ ግን ለመሄድ ቪዛ ያስፈልገናል። ሌላው ይቀርና በእኛ ሀገር አሁን ባለው ሁኔታ እንደልብሽ መንቀሳቀስ እንኳን አደጋች እየሆነ ነው። ስለዚህ ይህንን ነው መጀመሪያ መለወጥ ያለብን። እዚህ ያላጎለበትነውን ንግድ ከጎረቤት ሀገራት ወይም ከሌሎቹ ጋር እውን ልናደርገው አንችልም። ልጆቻንንም ያንን መልመድ አለባቸው። ለውጥ የምናመጣው እኔና አንቺ ነን።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በተለይ በመሪዎች ረገድ ሊሠራ ይገባል ብለው የሚያስገነዝቡት ጉዳይ ካለ እድሉን ልስጥዎና ውይይታችንን በዚህ እናብቃ?
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- በእኔ እምነት መሪዎች በዋናነት ሊያስተካክሉት ይገባል ብዬ የማስበው በየሀገራቸውን ያለውን የተለጠጠ የሉዓላዊነት አስተሳሰብ ነው። ይህም ሲባል የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር መልካም ሆኖ ሳለ ከሚገባው በላይ አግዝፈነው ከሌላ ሀገራት ጋር የምናደርገውን ግንኙነት በጥርጥሬ ላይ የተመሰረተ ማድረጋችን ነው። ይህ አይነቱ አካሄድ አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ የሚያወጣ ባለመሆኑ በተወሰነ መልኩ በራችንን ክፍት ልናደርግና እርስ በርስ ያለንን ቅርበት ልናጠናክር ይገባል።
ለምሳሌ አንድ ሱዳናዊ ወይም ኬኒያዊ ኢትዮጵያ መጥቶ በነፃነት የሚኖርበትና የሚነግድበት አልያም የሚሸምትበትን እድል መፍጠር ይገባናል። በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካ የተሻለ ተሞክሮ ያላት ሲሆን የየትኛውም ሀገር ዜጋ እንዳሻው መንቀሳቀስና በመገበያያት የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው። እነሱ እኛ ሀገር መጥተው መሥራት አይችሉም፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ግን ከ400 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ይሰራሉ። እኛም ሀገር ይህ አይነቱ መሻሻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ሰይፈ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል